>

"ልዩ ጥቅም" ! (አሰፋ ሃይሉ)

“ልዩ ጥቅም” !
አሰፋ ሃይሉ
“Favoritism” (“አድሏዊነት”) በማንኛውም ስም ቢጠራ ሊወገዝ የሚገባው የሚዛናዊ ህሊና ፀር ነው። በአዲስ አበባ ላይ ለሆነ ዲ ኤን ኤ እየተለየ ልዩ ጥቅም እሰጣለሁ፣ ለሆነ ዲ ኤን ኤ ደግሞ እከለክላለሁ ብሎ የተነሣ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት፣ መንግስትም ሆነ ቡድን – በቀላል ቋንቋ – ከፋሺስታዊ አመለካከት ያልተላቀቀ አድሏዊ ነው።
አፓርታይድ ምንድነው? ለነጮች ብቻ በዘር በቀለም ለይቼ ልዩ ጥቅምን እሰጣለሁ ያለ የበሰበሰ ሥርዓት ነው። በነጩም በጥቁሩም በሁሉም ተጠልቶ በስብሶ ከሥሩ ተመንግሎ የወደቀውም ለዚያ ነው።
ናዚዝም ምንድነው? ናዚዝም ሥርነቀል ብሔራዊ ሶሻሊዝም ነው። በታሪክ በሌሎች ለተጨቆኑ በዲ ኤን ኤ ተለይተው ለታወቁ ደች ቋንቋ ተናጋሪ የጀርመን አርያን ዘሮች ልዩ ጥቅምን እሰጣለሁ ብሎ ዓይን ያወጣ ጥፋትን አንግቦ ዓይን ሊያወጣ የተነሳ የዘረኞች ስብስብ ነው።
ዛሬ በቋንቋ ወይም በደምና አሠፋፈር ከሌላው ሁሉ ነዋሪ ለይቼ የኦሮሞዎችን ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ከተማ ማስጠበቅ ዓላማዬ ነው ብሎ የተነሳ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን የሰው ልጆችን እኩልነት ክዶ የተነሳ ብቻ ነው። የዜጎችን እኩልነት ክዶ ፋሺስታዊ መፈክርን ሊያነግብ የወደደ ብቻ ነው ከእነ እገሌ አብልጬ ለእነ እገሌ ዘሮች ልዩ ጥቅምን ልስጥ ብሎ የሚነሳ። ልዩ ጥቅም ከዜጎች እኩልነትና እኩል ተጠቃሚነት መብት ጋር አብሮ አይሄድም። በመሠረቱ የእኩልነት ፀር ነው።
አንዱን ልጅ፣ ሌላውን የእንጀራ ልጅ ለማድረግ ምሎ የተነሳን ማናቸውንም ዘረኛ ግለሰብም ሆነ ፓርቲ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሁሉ – ኦሮሞውም ሆነ ሌላው – ነጩም ሆነ ጥቁሩ – ሁሉም ፊቱን ሊያዞርበትና – ፋሺስታዊ ዓላማው እስኪላሽቅ ድረስ – አምርሮና አክርሮ ሊታገለው ይገባል። የሀገርልጅ ሚዛኑ ዜጋነት ነው። የእኩልነት ሚዛኑ ሰው-ነት ነው።
ፈጣሪ ለሁሉም ሰው እኩል አየር፣ እኩል ዝናብ፣ እኩል ሰማይ፣ እኩል ምድር፣ እኩል አፈር፣ እኩል ህሊና ሰጥቶን እያለ ስለምን እኛ አንዱን ረግጠን፣ ሌላውን አጉርሰን ነግሠን ልንኖር እንሻለን?? ውጉዝ ከመ አርዮስ!!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ – አንዱንም ሳይለይ – አብዝቶ ይባርክ።
ብዙሃን እናት – የሁሉም ወላጅ እናት – የማንም እንጀራ እናት – እምዬ ኢትዮጵያ – እምዬ ኢትዮጵያ – በፍቅር – ለዘለዓለም ትኑር!!!!!!
Filed in: Amharic