>

ዶ/ር አብይ ሆይ፥ ምንን እንደምር? (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)


ዶ/ር አብይ ሆይ፥ ምንን እንደምር?

 

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

ዛሬ ይቅርታ መጠየቅዎ የልቤን ቀልብ ሳበው። ትልቅ ሰው እንዲህ ነው። በዚህ ደብዳቤዬ ባለፈው ዓመት በደከሙበት ፈንታ በሚቀጥለው አዲስ ዓመት የሚልቁበት ይሆን ዘንድ ልሞግትዎ ነው። ይህ ሕዝብ አሁንም ዕድል እየሰጠዎት እንደሆነ በማወቅ በቃልዎ እንደሚተጉ አምናለሁ። ባለፈው ዓመት ብዙ ግሩምና ድንቅ ሥራ አደረጉ። በተጨማሪም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ደግሞ ግሩምና ድንቅ የተስፋ ቃል ሰጡን። በፊታችን ያለው አዲሱ ዓመት ደግሞ ከዚህ በፊት የተናገሩትን መልካም የፈውስና የአንድነት ተስፋ ቃል ወደ መሬት አውርደው በተግባር በመግለጥ ታሪክ የሚሰሩበት ይሆን ዘንድ ነው።

እንግዲህ መደመርን የምናቀነቅነው ዜሮን እያዋጣን አይሁን። ሁሉንም በእኔነት እና በየኔነት አጥር እያጠርን፥ ለጋራዊ ኢትዮጵያዊነት ዜሮ መዋጮ ማዋጣት ይቅር። ከራሳችን ብሔር እንውጣ ሲባል በቃል ብቻ ሳይሆን በምግባር ይሁን። አዲስ አበባ ከእኛ አልፎ የአፍሪካ ናት ማለት ያልቻልን፥ በዚያ ፈንታ አዲስ አበባን በየኔነት አጥረን ስለ ኢትዮጵያ አንድነት መዘከር ከንቱ ነው። አንድነት ከእኔነት ወደ እኛነት የማያሻግረን ከሆነ ትርጉሙ ምንድነው? በመደመር ዘመነ መንግስት እስክንድር ነጋ በምደረበዳ የሚጮህ የመደመር ድምፅ ሆኖ ሲገኝ እርስዎ ግራ መጋባትዎ ግራ ያጋባልና አንድ ይበሉ።

ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኦ ብሎ በፍፁም ፍቅር እርስዎን ማወደሱና መደገፉ፥ የእርስዎን ታላቅነት ከማሳየቱ በላይ፥ የዚህን ሕዝብ የልብ ንፅህና እና ቅንነት የሚያሳይ ነው። ይህን የፍቅር ሕዝብ ከዘረኛ ፌዴራሊዝም ቀንበር አርነት አውጥተው፥ ወደ ቤተሰባዊ ፌዴራላዊ አስተዳደር ያሻግሩት ዘንድ ምድርና ሰማይ ይጮሃል። እባክዎን ጆሮ ይስጡ።

እርስዎን የኢትዮጵያ ሙሴ ብሎ ሕዝብ ተስፋ አድርጎ ነበር። እናስተውልና ትምህርት ከጥንቱ ታሪክ እንውሰድ። እስራኤል ከግብፅ ባርነት ነፃ ሲወጣ በደስታ ነበር። ጥቂት ሳይቆይ የግብፅ ሰራዊት የእስራኤል ሕዝብን ሊገድል ከበስተዋላቸው ሲያሳድዳቸው አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ተጨነቁ። በመጨረሻም አምላክ ጣልቃ ገባና እስራኤል የኤርትራን ባህር ተሻገሩ፥ አሳዳጁም ሰጥሞ ቀረ።

አሁንስ ተስፋችን ማነው? እግዚአብሔር አይደለምን?

ኢሜል፥ Z@myEthiopia.com

Filed in: Amharic