>
5:13 pm - Saturday April 20, 9709

ከጣፋጩና አማልዩ የህልም ዓለም፣ "ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣... ኢትዮጵያዊነት ሱሴ፣" በጊዜ መባነን ይበጃል!!! (አብርሀም አለሙ)

ከጣፋጩና አማልዩ የህልም ዓለም፣ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣… ኢትዮጵያዊነት ሱሴ፣” በጊዜ መባነን ይበጃል!!!
አብርሀም አለሙ
አዲስ አበባን በባለቤትነት መያዝ ማለት፣ የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ብሔራዊ አንድነትና ነጻነት ለአንዴና መጨረሻ ጊዜ ሰብሮ፣ የኦህዴድን/ኦነግን የሃምሳ ወይም “150” ዓመታት “ህልም” እውን የማድረግ የመጀመሪያው ወሳኝ እርምጃ ነው!!
ዊልያም ሼክስፒር እንዳለው፣ “አምባገነኖች የሚስሙህ ሲመስሉ፣ ያኔ ነው መፍራት፤” (It’s time to fear when tyrants seem to kiss).
በጠሚው የሚመራው የኦህዴድ/ኦነግ “መንግስት” ላለፉት 11 ወራት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የቆመ ለማስመሰል የሚጠቀምባቸው “ጣፋጭ መግለጫዎች/ንግግሮች” ያለቁበት ይመስላል። ዛሬ እስክንድር ነጋ በራስ ሆቴል ስለ አዲስ አበባ የባልደራስ ምክር ቤት ሊሰጥ የነበረውን ጋዜጣዊ መግለጫ አግዷል። ይህም አልፎ አልፎ እውነተኛውን ኦነጋዊ መልኩን የሸፈነበትን ጭምብሉን ካስወለቁ፣ ለማንና ለምን እንደቆመ ለማየት እድል ከሰጡን አጋጣሚዎች አንዱ ነው።
የዐቢይ መንግስት ዛሬ ያስቆመው/ያገደው የአዲስ አበባን ህዝብ ህጋዊ መብት ለማስከበር በሰላማዊ መንገድ የሚታገለውን የእስክንድር ነጋን የባልደራስ ምክር ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ አይደለም። መግለጫው ምንም ያህል ለውጥ እንደማያመጣ ያውቁታል። ለማስቆም የሞከሩት ለመላው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ አንድነትና ነጻነት የሚደረግን ትግል ነው፤ የብሔር/ጎሳ ፖለቲካን አስወግዶ፣ በዜጎች ነጻ ፈቃድና መብት ላይ የተመሰረተ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መንግስት እንዲመሰረት የሚደረግን ትግል የማፈን የአደባባይ ሙከራ ነው። አዲስ አበባ ጠ.ሚ.ሩ እንደሚለው፣ “እንደ ጂማ፣ ባህር ዳር፣ ነቀምት፣ አምቦ፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ አዋሳ…ማንም ሰው እንደፈለገ ሊኖርባት የሚችል፣ የሁላችንም ከተማ” አይደለችም። ከነዚህ ሁሉ ከተሞች የተለየች ናት አዲስ አበባ፤ ቢያንስ በአንድ ዋና ምክንያት።
እነዚህ “የሁላችንም ናቸው” የተባሉት ከተሞች፣ የወያኔ “ህገ-መንግስት” በፈጠራቸው ልዩ ልዩ የክልል/ብሄር “መንግስታት” (የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የትግራይ፣ የደቡብ) “ባለቤትነት” የተያዙ፣ የአንድ ወይም ከዚያም በላይ (ደቡብን ይመለከቷል) ብሄር/ጎሳ ከተሞች ናቸው። ባንጻሩ አዲስ አበባ ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት ብቸኛዋ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ማእከል፣ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ አንድነት ተምሳሌት መገለጫ ነች።
 አዲስ አበባን በባለቤትነት መያዝ ማለት፣ የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ብሔራዊ አንድነትና ነጻነት ለአንዴና መጨረሻ ጊዜ ሰብሮ፣ የኦህዴድን/ኦነግን የሃምሳ ወይም “150” ዓመታት “ህልም” እውን የማድረግ የመጀመሪያው ወሳኝ እርምጃ ነው። “ባለቤቱን ካልናቁ፣ አጥሩን አይነቀንቁ፤” እንዲሉ አበው፣ አስከፊውን የጎሳ ፖለቲካ የመጨረሻ ግብ (የአንድ ብሄር ነጻ ሀገረ-መንግስት ማቋቋም) ለማሳካት፣ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን ጥንካሬ፣ ቁርጠኝነት፣ የታቀደውን የጎሳ ፖለቲካ “ስትራቴጂዎች” የመቋቋም አቅም መለኪያ ፈተና ነው፤ አማሪካኖች “testing the waters” የሚሉት ዓይነት ነው። እና ከጣፋጩና አማልዩ የህልም ዓለም፣ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣… ኢትዮጵያዊነት ሱሴ፣” በጊዜ መባነን ይበጃል።
እግዝአብሔር ኢትዮጵያን ከክፉ ሁሉ ይጠብቃት።
Filed in: Amharic