>

የጉዞ ማስታወሻ ከአሜሪካ እስከ አሜሪካ (መሳይ መኮንን )

 

የጉዞ ማስታወሻ

ከአሜሪካ እስከ አሜሪካ
መሳይ መኮንን
(በተለይ ለጊዮን መጽሄት የተጻፈ)
የካቲት 7 2011 ዓም ጠዋት ነው፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ የሰዓት አቆጣጠር 8ሰዓት፡፡ ለታሪካዊው የኢሳት ጉዞ የዋሽንግተን የኢሳት ባልደረቦች የልዑካን ቡድን አባላት ከደለስ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሰዋል፡፡ እኔን ጨምሮ አምስት አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ፊት ላይ የሚነበበው ምን እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ይከብዳል፡፡ ለእኔ ነገሮች ሁሉ ህልም ይመስሉኝ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ ከሀገር ስወጣ እንዲህ በቀላሉ እመለሳለሁ የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ ምንም እንኳን ከሀገር የወጣሁት በቦሌ ቢሆንም ተመልሼ በቦሌ በክብር እገባለሁ ብዬ ለአፍታም እስቤው አላውቅም፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በኤርትራ በነበረኝ ጉዞ ውዲቷን ሀገሬን በቅርብ ርቀት ለማየት የቻልኩበት አጋጣሚ ውስጤን ረብሾት ነበር፡፡ በሁመራ በኩል ከ1ኪሎሜትር ባነሰ ርቀት የኢትዮጵያን አየር የማግኩበት እድል በውስጤ ናፍቆትንና የሀገር ፍቅር ስሜትን ቀሰቀሰብኝ እንጂ ሰላም አልሰጠኝም፡፡ አሳይቶ የነሳኝ እስኪመስል ፈጣሪን መርገሜን አስታውሳለሁ፡፡ ጥሩ ስሜት አልነበረም፡፡
በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ በተከማቹትና አፋቸውን ከፍተው ቅንቡላ እሳት ለመትፋት በተዘጋጁት የቢኤም መሳሪያዎች ባሻገር፤ ከግዙፉ ኮንክሪት ምሽግ ማዶ፤ የሁለቱ ሀገራት ወታደሮች አድፍጠው ከሚገኙባቸው የቀበሮ ጉድጓዶች በቅርበት የምትገኘውን የሁመራን ከተማ ከኤርትራዋ ኡምናህጅር መንደር ሆኖ መመልከት ከደስታ ይልቅ አጥንት ድረስ ዘልቆ በሚሰማ ሀዘን የሚያሰቃይ ሆኖነብኝ፡፡ ክፉ የታሪክ አጋጣሚ፡፡
ከዋሽንግተኑ ደለስ አውሮፕላን ማረፊያ ሆኜ የሁመራው አጋጣሚ ትውስ አለኝ፡፡ አሁን እነዚያ የጥላቻ ምሽጎች ተነደዋል፡፡ አፋቸውን ከፍተውን እሳት ሊተፉ አሰፍስፈው የነበሩት የቢኤም መሳሪያዎች ተዘግተው ከቦታው ተነስተዋል፡፡ ወንድሙን ለመግደል ከቀበሮ ጉድጓድ ቀንና ሌሊቱን የሚያሳልፈው ወታደርም የለም፡፡ መቼም ተአምር ነው፡፡ ለሽምግልና እድል ሳይሰጥ፤ ከመገዳደል ውጪ አማራጭ እንዳይኖረው ሆኖ ለ20 ዓመታት ለያዥ ለገናዥ አስቸግሮ የዘለቀው፤ የሁለቱንም ሀገራት ሰብዓዊ ፍጡርና ኢኮኖሚያቸውን የበላው ጥይት አልባው ጦርነት በአጭር ጊዜ መፍትሄ አግኝቶ የጥላቻው ግምብ ፈርሶ ታሪካዊ በሆነ ስምምነት ድንበሮች ተከፍተው ሰላም መፈጠሩ አስገራሚ ነው፡፡ የሆነው በቅርብ ጊዜ ይሆናሉ ተብለው ከማይታሰቡ ክስተቶች አንዱ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ደለስ አውሮፕላን ማረፊያ ሆኜ አሰብኩት፡፡ በሰሜን በአናት በኩል ለመግባት ያሰብኩት አልሆነምና በክብር በቦሌ በኩል የሀገሬን ምድር ልረግጣት ሰዓታት ቀርተዋል፡፡ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ውስጤን ተቆጣጥሮታል፡፡
በእርግጥ የመጣው ለውጥ ለመደፍረስ ዳር ዳር እያለ በነበረበት ጊዜ ላይ ነው የኢሳት የልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ የሚያመራው፡፡ በኢትዮጵያ ወጣቶች የህይወት መስዋእትነትና በእነ ዶ/ር አብይ የአጨራረስ ብስለት የህወሀትን ዘረኛ ስርዓት ወደ መቀሌ የሸኘው ታሪካዊ ለውጥ መዋቅራዊ በሆነ ስርነቀል ድል ከመታጀቡ በፊት ፈተናዎች ገጥመውታል፡፡ ተረኛ ነን በሚል ስሜት የተሸነፉ፤ በሌላው ኪሳራ የዘር ቡድንን የበላይነት ለማስጠበቅ ያሰፈሰፉ፤ በመንደርና ጎጥ የተሰባሰቡ በጎበዝ አለቆች የሚመሩ ቡድኖች ለአያሌ ኢትዮጵያውያን የብርሃን መጋረጃ የገለጠውን ለውጥ ለመቀልበስ በተነሱበት ወቅት ላይ ነው ኢሳት የኢትዮጵያውን ጉዞ ለማድረግ የተዘጋጀው፡፡ ከዳር እስከዳር፤ በውጭም በሀገር ውስጥም ኢትዮጵያውያን በደስታና በተስፋ በተሞሉበት በዚህን ታሪካዊ የሽግግር ጊዜ ላይ ቁስል ነካክተው፤ በደልን እየዘመሩ ‘’ጊዜው የእኛ ነው” በሚል ቅኝት ተውጠው ሌላ ዙር መከራና ስቃይ ኢትዮጵያ ላይ ለማምጣት የጥፋት በትር ያነሱት የመንደር አበጋዞች እዚህም እዚያም ድምጻቸውና የጭካኔ ተግባራቸው በገነነበት ወቅት ላይ የኢሳት ባልደረቦች ወደ ሀገር ቤት ለማቅናት መዘጋጀታቸው በብዙዎች ዘንድ መልካም ምላሽ አልነበረውም፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ መላው የኢሳት ደጋፊና ኢትዮጵያዊ ወገናችን ወቅቱ ጥሩ እይደለም በሚል የተቆርቋሪነት ስሜት ጉዞአችንን እንድናዘገየው መክረውናል፡፡
ግን ረፍዷል፡፡ የሚቀለበስ ውሳኔ አይደለም፡፡ ኢሳት ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርገው ጉዞ እንደውም ዘግይቷል የሚል ስሜት ውስጣችን ነበር፡፡ የሚደርስብንን ለመቀበል ተዘጋጅተናል፡፡ በሀገር የመጣን እኛ የምንሸሽበት ምክንያት ሊኖር አይገባም፡፡ ለውጡ ላይ አሻራችን በደማቁ ይታያል፡፡ ኢትዮጵያ ብለን ስንጮህ ቆየን፡፡ ከህዝቡ ትግል ጎን ሆነን በመረጃ ሃይል የህወሀት አገዛዝ ውስጡ ተቦርቡሮ፤ ምስጥ እንደበላው ኩይሳ በቁሞ ተዳክሞ እንዲቀር የሚቻለንን አድርገናል፡፡ ኢትዮጵያን የሚወድ፤ ለህዝቡ ክብር የሚሰጥ መሪ ቤተመንግስት መግባቱ ለኢሳት ባልደረቦች ትልቅ ድል ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህ ለውጥ የእኛም ልፋት የታከለበት ነው፡፡ የደከምንለት ነው፡፡ ምቾት በሞላው የሰለጠነው ዓለም እየኖርን ነገር ግን ለዚያ ብልጭልጭ ደስታ ሳንሸነፍ መስዋዕት የከፍልንበት ለውጥ ነው፡፡ ምንም እንኳን ለውጡ ስርነቀል ባይሆንም፤ በጊዚያዊ ፈተናዎች ቢታጀብም በሚታዩት መልካም ነገሮች ለውጡን ማመስገን ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በሽብር ክስ ፋይል የተከፈተበት ኢሳትና ከመሀላችንም በሽብርተኝነት የተከሰሱ ባልደረቦቻችን በክብር ወደ ሀገራቸው መሄዳቸው በራሱ የለውጡ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ይህንን ለውጥ ከህዝባችን ጋር ማክበር አለብን፡፡ ሀገራቸውን እንዳያዩ የተፈረደባቸው የኢሳት ጋዜጠኞች በድል ስሜት ወደ እናት ምድራቸው ከመሄዳቸው በላይ ምን የሚያስደስት ነገር ይኖር ይሆን?
ከዋሽንገተን ዲሲ ደለስ አውሮፕላን ማረፊያ ሆኜ ጉዞአችንን ከለውጡና ከተደቀኑበት ፈተናዎች ጋር እያሰላሰልኩ የመነሻችንን ሰዓት የበሙሉ በልዩ ስሜት አድናቆታቸውን ሲገልጹልን ይበልጥ ድፍረት ይሰማን ጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቲኬት ክፍል ሰራተኞች በተለየ አክብሮት ሲያስተናግዱን፤ አብረውን በአንድ አውሮፕላን ሊጓዙ የተዘጋጁትም በልዩ የአድናቆት ስሜት ሲቀበሉን የነበረው ሁኔታ ለማመን የሚያስቸግር ነበር፡፡ ከተርሚናሉ ውስጥ ሆኜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንን ተመለክትኳት፡፡ እኛን አሳፍራ፤ ሰማዩን ቀዝፋ፤ ከእናት ምድራችን የምትወስደንን ጢያራ እያየኋት ውስጤ በእንዳች ስሜት ይናጥ ያዘ፡፡ ሰንደቃችንን በጭራዋ ላይ ከትባ በግርማ ሞገስ የምትታየኝ አውሮፕላናችን እኛን ልታሳፍር ቅድመዝግጅቷን እያጠናቀቀች ነው፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳፈርኩት ከ16 ዓመታት በፊት ከቡሩንዲ ቡጁምቡራ ወደ አዲስ አበባ በነበረን ጉዞ ነው፡፡ በሰላም አስከባሪ ሰራዊት ውስጥ በአስተርጓሚነት በነበረን ዘመቻ የመልስ ጉዞ ላይ የተሳፈርንባት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከስቃይ ወደ እፎይታ፤ ከሀዘን ወደ ደስታ ያሻገረችን አድርገን ስለወሰድናት በልዩ ትዝታ በልቤ ማህደር ውስጥ ተቀምጣለች፡፡ በቡሩንዲ የህወሀት አገዛዝ ያደረሰብን ስቃይና መከራ ተዘርዝሮ የሚያልቅ ባለመሆኑ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡
ግዞት ላይ ለነበርነው አስተርጓሚዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀገራችን መመለሳችን ከሲዖል ቆይታ ወደ ገነት የማምራት ያህል የሚያስደስት ነበር፡፡ የኢትዮጵያን የሀገር ባህል በለበሱ ቆነጃጅት የአየር መንገዱ አስተናጋጆች ትህትና የተሞላበት አቀባበል ስናይ ፊታችን በእንባ ዘለላዎች ተሞሉ፡፡ አለቀስን፡፡ የኢትዮጵያን ምድር የረገጥን ያህል የአውሮፕላኑን ወለል ተደፍተን ሳምነው፡፡  ከዚያን ወዲህ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የተሳፈርኩበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡ የዛሬ 10ዓመት ከሀገር የወጣሁትም በጀርመኑ ሉፍታንዛ አውሮፕላን ነበር፡፡
እንግዲህ በመልካም አጋጣሚ በልቤ ማህደር የተከተበችዋ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በሌላ የታሪክ ክስተት ዳግም ወደ ሀገሬ ልትወስደኝ ሞተሯን እያሞቀች ነው፡፡ ይህ አጋጣሚ በእርግጥ ከበፊቱ የተለየ ነው፡፡ ይህኛው በተለየ ሀገራዊ ተግባር በድል አድራጊነት ስሜት የሚደረግ ጉዞ ነው፡፡ በሰራናት ቅንጣቢ ስራ የተደሰተውን ህዝባችንን ለማመስገን ነው፡፡ ክብር ለሰጠንንና የማይነጥፍ አድናቆቱን ሳይሰስት ለቸረን ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋናችንን አቅርበን ደስታውን ለመጋራት ነው፡፡ በርቀት በመከራና ስቃዩ የምናቀውን ወገናችንን አጠገቡ ተጠግተን፤ ትንፋሹን እየማግን የተጀመረውን ለውጥ በጋራ ልናከብረው ነው፡፡ ከወገን ፍቅር በላይ ምን አለ? ትንፋሹም እኮ ቀለብ ነው ሲባል ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ይህ ጉዞ በታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው፡፡
ሰዓቱ ደርሷል፡፡ የልቤ ምት ሲጨምር ይሰማኛል፡፡ ባለቤቴንና ልጆቼን ከቤት ተሰናብቼእለሁ፡፡ ለታላቁ የኢሳት ጉዞ የተሰናዳው የዋሽንገተኑ ልዑክ ቡድን አባላት የመጨረሻውን ስንብት አድርጎ ወደ አውሮፕላኑ ውስጥ ገብቷል፡፡ የአውሮፓው ኢሳት የልዑካን ቡድን አባላት ደግም ማምሻውን ሊነሱ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ በወጣው መረሀ ግብር መሰረት ከአውሮፓና አሜሪካ የሚጓዙት የኢሳት ባልደረቦች በተመሳሳይ ሰዓት አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡ አንድ ላይ ሆነው ህዝባቸውን ያገኛሉ፡፡ መቼም ድንቅ ነው፡፡ ያልታሰበ የታሪክ ክስተት፡፡ አውሮፕላናችን ተነስታለች፡፡ ከ13ሰዓታት ያለማቋረጥ የሰማዩ ላይ ጉዞ በኋላ ከሀገራችን መዲና አዲስ አበባ ትደርሳለች፡፡
አዲስ አበባ
የካቲት 8 2011 ዓም በኢትዮጵያ አቆጣጠት ከጠዋቱ 1 ሰዓት
የአውሮፕላን ጉዞ አልወድም፡፡ ፎቢያ የሚሉት ጥልቅ ፍርሃት አለብኝ፡፡ ከመነሻው እስከመድረሻው በፍርሃት እንደተናጥኩ የእየር ላይ ጉዞው ያስጨንቀኛል፡፡ 13 ሰዓአታት ሙሉ በፍርሃት ውስጥ መቆየት ደግሞ ከባድ ነው፡፡ በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ረጅም የአውሮፕላን ጉዞ የመጀመሪያዬ አይደለም፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ወደኤርትራ ያደረግነው ጉዞ በድምሩ 16 ሰዓታትን የወሰደ ነበረ፡፡ በኳታር ዶሀ ትራንዚት ያደረግንበት ቆይታ ትንሽ ፋታ ሰጠን እንጂ ያን ያህል ከምድር ርቆ መቆየት ይረብሻል፡፡ በተለይ እንደኔ የእውሮፕላን ጉዞ ፍርሃት ላለበት ሰው ምጡ ረጅም ይሆንበታል፡፡ ኮሜዲያን ክበበው ገዳ ወደ አውስትራሊያ ያደረገውን ረጅም የአየር ላይ ጉዞ አስመልክቶ ፈገግ ያሰኘኝ ቀልድ አስታወስኩት፡፡ ጉዞው ረጅም ከመሆኑ የተነሳ አጠገብህ የተቀመጠው ሰው ወንድምህ አልያም አጎትህ ሊመስልህ ይችላል ሲል የኮመካት ሁሌም ታስቀኛለች፡፡
የሆኖ ሆኖ ታሪካዊው የኢሳት የሀገር ቤት ጉዞ አዲስ አበባ ተቃርቧል፡፡ ፍርሃቴን ያስረሳኝ የነበረው በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበረው የተሳፋሪው አቀባበል ነበር፡፡ ከበረራ አስተናጋጆች ጀምሮ የተደረገለን ልዩ አቀባበል ፍርሃቴን አስወግዶልኛል፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት በትግሉ አንጻር ላደረግነው አስተዋጽኦ በየቦታው የምናገኘው ክብርና አድናቆት ከአእምሮ በላይ ሆኖብኛል፡፡ ይህቺን ታህል ላደረኘው እስተዋጽኦ የሚሰጠን ቦታ የበለጠ እንድንሰራ ሃላፊነትና አደራ የሚያሸክመን እንጂ በትዕቢትና ጉራ የሚያስኮፍሰን እንዳልሆነ ይሰማኛል፡፡ አድናቆት ሽልማት ነው፡፡ ክብር ለተሰራ ስራ የሚሰጥ ውጤት ነው፡፡ በአግባቡ ካልያዙት ኪሳራው የትየለሌ ነው፡፡ ዝና በአግባቡ ካልተያዘ የአረቄ ስካር ማለት ነው፡፡ ትንሽ ስም ይዘው ሀገር ምድሩ አይበቃንም የሚሉ ሰዎች እንደ ጉም በነው ሲጠፉ ላየ ሰው የዝናን መልካምነት ብቻ ሳይሆን መጥፎ ውጤቱንም በቅጡ ይገነዘባል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከደረሰበት መከራና ግፍ፤ ከኖረበት ጨለማ ህይወት አንጻር ትንሽ ውለታ የዋለለትን በሰፊው ያከብራል፡፡ ደግሞም ቅጣቱንም ይችልበታል፡፡ ላይ ሰቅሎ ማውረድን ያውቅበታል፡፡ ማንዴላ ብሎ አክብሮ ሲበላሽበት ከሰቀለበት ፈጥፍጦ ሲጥል ያየንበትን የቅርብ ጊዜ ታሪክ እናስታውሳለን፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ የሰጠንን ክብር መመንዘር ያለብን ሌላ የቤት ስራ ከመረከብ አንጻር ነው፡፡ ትልቅ ተራራ ከፊት ተደቅኗል፡፡ ከተሰራው ይልቅ የሚቀረው በብዙ እጥፍ ይበልጣል፡፡ ከኢትዮጵያ ህዝብ በየቦታው የምናገኘው እድናቆትና ክብር ቀብድ ነው፡፡ ለዋናው የቤት ስራ የተከፈለ መነሻ ዋጋ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ከዋሽንግተን ዲሲ ወደ አዲስ አበባ በምትበረው አውሮፕላን ውስጥ የተሳፈረውና ለኢሳት ባልደረቦች ፍቅርና አቅብሮቱን ሳይሰስት እየሰጠ ያለው ወገናችንም የበለጠ ሃላፊነት ከፊታችን መኖሩን በጎን እየነገረን እንደሆነ አድርጌ ወስጄዋለሁ፡፡
በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ከዋሽንግተን ዲሲ የተነሳችው አውሮፕላን የኢትዮጵያን ሰማይ ሰንጥቃ ገብታለች፡፡ ከወንበራችን ላይ የተገጠመው ስክሪን ላይ በሚታየውና የጉዞአችንን ሂደት በሚያመላክተው መረጃ መሰረት ጎንደርን አልፈናል፡፡ የአውሮፕላኑ ምክትል አብራሪም ማብራሪያ ወደ ኢትዮጵያ የአየር ክልል መግባታችንን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነው፡፡ እኔ ከ10ዓመት፤ ሲሳይ አጌና ከ8 ዓመት፤ አበበ ገላው ከ20 ዓመት፤ እንግዱ ወልዴ ከ16 ዓመታት በኋላ የሀገራችንን ምድር ለመርገጥ ተቃርበናል፡፡ በመርሃ ግብሩ መሰረት ከአምስተርዳም አፈወርቅ አግደውና ደረጀ ሀብተወልድ፤ ከለንደን ወንድማገኝ ጋሹ ከደቂቃዎች በፊት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ የዲሲና የአውሮፓ የኢሳት ባልደረቦችም ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል የሚገናኙበትም አጋጣሚ መሆኑ ደግሞ ሌላው አስገራሚ ነገር ነው፡:
ከአውሮፕላኗ አብራሪዎች እንደምንሰማው አዲስ አበባ ደርሰናል፡፡ በውጭ በአውሮፕላኑ መስኮት በኩል አሻግሬ ተመለከትኩ፡፡ እንደችቦ ቀጥ ብለው የቆሙ ፎቆች ከርቀት ይታዩኛል፡፡ ተመሳሳይ የሆኑና እጅብ ብለው የሚታዩ መኖሪያ ቤቶችን በብዛት ተሰርተዋል፡፡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች እንደሆኑ በቀላሉ መለየት ይቻላል፡፡ ከሰማይ ወደታች የምናያት አዲስ አበባ ከምናቃት የበለጠ ሰፍታለች፡፡ የቻልኩትን ያህል በቪዲዮ ለመያዝ ሞከርኩኝ፡፡ ድብልቅልቅ ባለ ስሜት ውስጥ ሆኜ አዲስ አበባን እያየኋት ነው፡፡ ከወራት በፊት ‘’ሀገራችሁ አትገቡም” ተብለን ከተከለከልናት ምድር በነጻነትና በክብር ልናርፍ መሆኑ የሚሰጠውን ልዩ ስሜት ያየ ያውቀዋል፡፡ ማንን ማመስገን እንዳለብኝ አላውቅም፡፡ በጥቅሉ ይህ ይሆን ዘንድ ላደረገው ላሃያሉ ፈጣሪ እግዚያብሄር ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ሰው ያደረገው አይደለም፡፡ የእግዚያብሄር ፍቃድ ሆነና እኛም ለሀገራችን ከወገናችን በቅተናል፡፡ አዲስ አበባ፡፡ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት፡፡ ከተርሚናሉ ማዶ ከእንግዶች መቀበያ የሚጠብቀንን በትክክል አላወቅንም፡፡ ከአውሮፕላኑ እንደወረድን ግን የተሰማኝ ስሜት አሁን ላይ አላስታውሰውም፡፡ ሀገሬ ገባሁ፡፡ ተመስገን አምላኬ!!!
ከተሳፋሪዎች ተለይተናል፡፡ የመንግስት ደህንነት ሰራተኞች ባዘጋጁት ተሽከርካሪ ወደ ተርሚናሉ የክብር እንግዶች መቀበያ ቦታ ተወሰድን፡፡ ቀይ ስጋጃ በተነጠፈበት ክፍል አልፈን ወደ ልዩ እንግዳ መቀበያ ሳሎን ገባን፡፡ የፕሬዝዳንት ሳህለወርቅና የጠ/ሚር አብይ አህመድ ፎግራፎች በትልቁ የተሰቀለበት ሳሎን በጋዜጠኞች ተሞልቷል፡፡ ቀድመው የደረሱት የአምስተርዳምና የለንደን ባልደረቦቻችንንም ከልዩ የእንግዳ መቀበያ ሳሎን አገኘናቸው፡፡ ሳሎኗ ከአቅሟ በላይ በሰዎች ተሞልታለች፡፡ ቤተሰብ እየገባ ነው፡፡ ከ10 ዓመታት በኋላ እኔም ወላጆቼን አገኘኋቸው፡፡ በሳሎኗ በደስታ ሲቃ የተዋጡ ሰዎች ድምጽ ጎልቶን ይሰማል፡፡ ደስታና ለቅሶ! እናትና አባቴን በህይወት አገኛቸዋለሁ ብዬ አላሰብኩም፡፡ እንደኔ ሀሳብ ሳይሆን እንደፈጣሪ ፈቃድ ሆነና ከቤተሰቦቼ አንድም ከቁጥር ሳይጎድል በጥሩ ሁኔታ ሳገኛቸው ደስታዬ እጥፍ ድርብ ሆነብኝ፡፡ ግን ያ ደስታ ወዲያውኑ እንደጉም ከውስጤ ሲጠፋ ታወቀኝ፡፡ ለካንስ ይህ ቀን እውን እንዲሆን የብዙዎች ህይወት ዋጋ ተከፍሎበታል?! አያሌ ቤተሰብ ተበታትኗል፡፡ ሺዎች ተሰውተዋል፡፡ ሀገር ጥለው ተሰደዋል፡፡ እኔ ቤተሰቤን በሀገሬ ምድር በሰላም አገኛቸው ዘንድ የስንቱ ቤተሰብ ህይወት ተመሰቃቅሏል?! ለደቂቃዎች አሰብኳቸው፡፡ ይህ ቀን ያለናንተ አልመጣምና ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለመስዋዕትነታቸው ይሆን ዘንድ ተመኘሁ፡፡
የክብር እንግዳ መቀበያ ሳሎኗ በሰዎች እንደተጨናነቀች የመንግስት ሃላፊዎች መግባታቸው ተነገረን፡፡ የባህል ሚኒስትሯ እንዲሁም የአዲስ አበባ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ሃላፊ እኛን ለመቀቀበል መምጣታቸውን አወቅን፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተወካይ ተገኝተዋል፡፡ ረ/ፕ ነብዩ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባውን ወክለው ንግግር ጀመሩ፡፡ መምጣታችን የለውጡ አካል መሆኑን ከነገሩን በኋላ በቆይታችን ስለሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በአካል በመገኘት ግ ንዛቤ የምንወስድበት አጋጣሚ እንደሚሆን ነገሩን፡፡ የባህል ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት መልካም አቀባበል ካደረጉልን በኋላ የሰራነውን በአወንታዊ መልኩ አንስተው ወደፊት በስፊው ሃላፊነት እንደሚጠበቅብን ገለጹልን፡፡ መንግስትም ከጎናችን መሆኑንን ነገሩን፡፡ እኛን ወክለው ሲሳይ አጌናና አበበ ገላው ንግግር አደረጉ፡፡ ‘’በአርበኝነት የሚታወቀው ኢሳት ለውጡን ተከትሎ አወንታዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ ተዘጋጅቷል” አሉ ባለድረቦቻችን፡፡ የፎትግራፍ ፕሮግራም ተደረገ፡፡ የአቀባበሎ ስነስርዓቱም አበቃ፡፡ ከተርሚናሉ ውጭ ዘመድ አዝማድ፤ ጓደኛ እንደሚጠብቀን ተነገረን፡፡
ለደህንነት ሲባል የተለጠጠ አቀባበል እንደማይኖር ቀድመን አውቀናል፡፡ ከእኛ ቀድመው ሀገር ቤት የገቡ ታዋቂ ሰዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመቀበል በነበረው ፉክክር አላስፈላጊ ነገሮች በመከተላቸው የእኛ እቀባበል እንዲደምቅ አልተፈለገም፡፡ ጥሩ ያልሆኑ አዝማማያዎችን ለማስቀረት ሲባል አቀባበሉ ድምጽ አልባ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ለእኛ ኝ ከበቂም በላይ ሆኖ ተሰምቶናል፡፡
በደህንነት ሰራተኞች የተከበበው የኢሳት የልዑካን ቡድን በቀጥታ ያመራው ወደ ተያዘለት ሆቴል ነበር፡፡ ሆቴሉ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ብዙም አይርቅም፡፡ ጥርስ ያለው ከሚመስለው የአሜሪካን ቅዝቃዜ ለመጣው የኢሳት ቡድን የአዲስ አበባው አየር እፎይታን የሚሰጥ ነው፡፡ አዲስ አበባ ተለውጣለች፡፡ የፎቁ ብዛት ትንፋሽ ያሳጣት ይመስላል፡፡ ትርምሱ አይጣል ነው፡፡ ሰው በዝቷል፡፡ መንገድ ላይ ሰውና ተሽከርካሪ እየተጋፉና እየተሻሹ ሲያልፉ ማየት በፊት ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ አሁን ያስደነግጣል፡፡ አዲሱን የአየር መንገዱን ስካይላይት ዘመናዊ ሆቴል በስተግራ እያየን በርቀት እንደችቦ የተገተሩትን የፎቅ ጫካ እየታዘብን ወደ ሆቴላችንአመራን፡፡ አዲስ አበባ ወደላይም ወደጎንም ሰፍታለች፡፡ በስተቀኝ በኩል የሚሌኒየሙን አዳራሽ እያለፍን ነበር፡፡ የኢሳት ጋዜጠኞች ፎቶግራፎች ያለበት ባነር በአዳራሹ በር ላይ በትልቁ ተሰቅሎ አየን፡፡ ለየካቲት 9 የኢሳት ቀን ተፍ ተፍ እየተባለ ለመሆኑ አንድ ማሳያ ነበር፡፡ ድብልቅልቅ ባለ ስሜት ተውጬ ከሆቴል ደረስን፡፡ በዕለቱ ከተያዘው መርሃ ግብር አንዱ ከምክትል ጠ/ሚር ደመቀ መኮንን ጋር መገናኘት ነበር፡፡ ትንሽ እረፍት አድርገን ወደዚያው ልናመራ ተዘጋጅተናል፡፡
 
(ይቀጥላል)
Filed in: Amharic