>
5:13 pm - Tuesday April 19, 4687

 ዛሬም ቢሆን ዱላ ጨብጠው መግለጫ የሚከለክሉት ጀብደኞች ሳይሆኑ ብዕሩን የያዘው እስክንድር አሸንፏል!!! (ሳምሶም ሚሀይሎቪች)

የባለ አደራ ምክር ቤቱ መግለጫ “ከበላይ አካል በመጣ”  ቀጥተኛ ትዕዛዝ ክልከላ ተደርጎበታል!!!
ሳምሶም ሚሀይሎቪች
ዛሬም ቢሆን ዱላ ጨብጠው መግለጫ የሚከለክሉት ጀብደኞች ሳይሆኑ ብዕሩን የያዘው እስክንድር አሸንፏል!!!
ሰላማዊ በሮች ሲዘጉ የዓመፃ በሮች ይከፈታሉ!!!
* ዶክተር አቢይ የዛተበትን «ግልፅ ጦርነት» ጀምሮታል!!!
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ፖሊስ በጉልበት እንደበተነው ተሰምቷል።  እስክንድር መግለጫውን በቦታው ለተገኙት ጋዜጠኞች ከራስ ሆቴል ውጭ ለመስጠት ሙከራ አድርጎ ነበረ። ሆኖም ፖሊሶች ሐይል አጠናክረው በመጨመር ቦታውን ወርረው መግለጫው እንዲቋረጥ አድርገው ሕዝቡን በትነውታል።
~ የክልከላው ምክንያት አስመልክቶ በቦታው ላይ በዋነኛነት መመሪያ ሲሰጥ የነበረው አዛዥ ፖሊስ “ክልከላው ከበላይ አካል የተሰጠ ትዕዛዝ ነው”ከማለት ውጪ ለጋዜጠኞችም ሆነ ጋዜጣዊ መግለጫ ላዘጋጅቱ አካላት ምንም ዓይነት ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ አልነበረም ለውጥ መጥቷል ብሎ ለሚያስበው አፍቃሬ ዲሞክራሲ ወገን ይሄ የፓሊስ ድርጊት አሳፋሪም አስደንጋጭም ነው። በአንድ በኩል ለውጥ አለ እያልክ በሌላ በኩል ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የምትገድብ ከሆነ የለውጥን ምንነት በቅጡ አልገባህም አልያም ከቃላት ማሰማመር ጀርባ አምባገነንት አሁንም አድፍጣለች ማለት ነው።
እስክንድር ባለፈው እሁድ ህዝባዊ ስብሰባ ጠርቶ ይህ ህዝብን ጉዳት ላይ የሚዳርግ መሆኑ ሲሰማው በሀላፊነት መንፈስ ስብሰባውን የሰረዘ ሰው ነው። የዛሬውን መግለጫ የከለከሉት ባለስልጣናት የእስክንድርን ድምጽ ያፈኑ መስሎ ተሰምቷቸው ይህንንም እንደ ድል ቆጥረውት ይሆናል። ከእስክንድር ሀሳብ ጀርባ ሚሊዮኖች እንዳሉ ፣ ለውጥ የተባለው ሂደት ለአንዱ በማንኪያ ለሌላው በአካፋ የሚታደል ወገንተኛ ድጎማ እንደሆነ እየተረዱ እንዲሄድ ያደርጋል። ይህ ስሜት ህዝብ የበለጠ እንዲጠራጠር ከእለት እለት ወዳልተፈለገ መንገድ እየተገፋ እንዲሄድ ያደርገዋል።
ስናጠቃልለው ዛሬም ቢሆን ዱላ ጨብጠው መግለጫ የሚከለክሉት ጀብደኞች ሳይሆኑ ብዕሩን የያዘው እስክንድር አሸንፏል። እኛም ፓሊስ ተብዬው ተቋም ጥቂት ፊቶች ቀየረ እንጂ ውስጡ ያው የድሮው ከህግ ይልቅ በባለስልጣናት ትዕዛዝ የሚመራ ተቋም እንደሆነ ታዝበናል።
በዛሬው እለት መግለጫ እንዳይሰጥ ክልከላ የተደረገበት ባለአደራ ምክር ቤት /ባልደራስ/ በመጪው አጭር ቀናት ውስጥ ጉዳዩን አስመልክቶ እንዲሁም ተያያዥ በሆነ ነገሮች ቦታው እና ሰዓቱ ኮሚቴው ግልጽ በሚያደርገው ቀን ለህዝብ መግለጫ እንደሚሰጥ ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድ ነጋ መልዕክቱን አስተላልፏል።
እስክንድር አሸንፏል !
ድል ለእዉነተኛ ዴሞክራሲ !!!
Filed in: Amharic