>

"ከዘር ፌደራሊዝም አላቀህ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ላይ የተመሰረተ አድርገህ ገላግለን!!" (አርቲስት አስቴር በዳኔ)

“ከዘር ፌደራሊዝም አላቀህ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ላይ የተመሰረተ አድርገህ ገላግለን!!”
ግልጽ ደብዳቤ ለጠ/ሚኒስትሩ
ከአርቲስት አስቴር በዳኔ
ጎርፉ ውስጥ ቆመን ስለጎርፉ ከማውራት ጨከን ብሎ ድልድይ መስራትና ከፍ ማለት ይሻላል፡፡ ያኔ የጎርፉ ቆሻሻ አይነካንም፤ ያኔ ጎርፉ ጠርጎ ይወስደን ይሆን ብለን አንሰጋም፡፡ ከላይ ቆመን ከሥር ሲያልፍ እናየው ይሆናል እንጂ፡፡
የማይወለድ ልጅ ሆና ያረገዝናት ኢትዮጵያችን ጉዳይ ነው ዛሬም እንቀልፍ አሣጥቶ ክፉ ደግ የሚያነጋግረን፡፡
በአንድ አመት የስልጣን ቆይታህ እጅግ በጣም ብዙ ድንቅ ድንቅ ስራዎችን ሰርተሀል፡፡ ይህን መልካም ስራህን እየሸፈነ እጀ ሰባራ የሚያደርግህም ጉዳይ የዛኑ ያህል በዝቷል፡፡ በአጠቃላይ ስንዴውና እንክርዳዱ እኩል በቅሏል፡፡ ትልቁ ችግር የምትመራው ድርጅት ኢህአዴግ የተጠመቀበት ጥንስስ ነው፡፡ እሱ ከመሰረቱ ካልተቀየረ ልፋትህ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ ቆሻሻ ትሪ ላይ በጣም የሚጣፍጥ ምግብ በየዓይነቱ ብታቀርብ የሚበላው ዓይኑን የጨፈነ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የምግቡን ጣፋጭነት የሚመጥን ንጹህ ማቅረቢያ ያስፈልጋል፡፡
የኢህአዴግ ኢትዮጵያ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬና ደቡብ ህዝቦች ናቸው፡፡ ችግሩ ከዚህ ይጀምራል፡፡ በዚህ አካሔድ 83ቱንም ብሔሮች በስም ካልጠራህ ስለ እኩልነት ማውራት አትችልም፡፡ ሀገር የምትወከለው በብሔረሰብ ማንነት ከሆነ ማን ከማን ያንሳል፡፡ ይሄን ሀገርን በአንድነት ከማቆም ይልቅ ሀገርን  ለማፍረስ የሚመች ህገመንግስት መሠረታዊ ችግሩን ካልቀየርከው በስተቀር እዚህ ጋር ስትገነባ አዚያ ጋር እየተናደ፤ አዛጋ ስትደፍን እዚህጋ እየተሸነቆረ አሮጌ ጠጋኝ ሆነህ መሞትህ ነው፡፡ ችግሮች አፍጥጠው እዚህ ከደረሱ ከምርጫው በፊት ይሄ ቢሰራ ይሻላል፡፡ ንግግርህ ውስጥም ለተለያዩ ብሔሮችን ስም እየጠራህ ሁሉን ለማስደሰት ብትሞክር ያልጠራኸው አኩራፊ ይበዛል፡፡ ኢትዮጵያን ከዘር ፌደራሊዝም አላቀህ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ላይ የተመሰረተ አድርገህ ገላግለን፡፡ ያኔ እውነተኛ ለውጥ መጣ እንላለን፡፡ እባክህ በዘር መተላለቅ ይብቃን፤ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከድህነት እንወጣ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፤ በነጻነት ተንቀሳቅሶ ይስራ፡፡ ያለዛ ይሄ ሁሉ ወርቅ ሀሳብህና ስራህ የእምቧይ ካብ ይሆናል… አትልፋ!!!
ታናሽና ደፋር መካሪ አስቴር በዳኔ 
መጋቢት 19/2011
Filed in: Amharic