>

የልባችንን ጫና አስተንፈሰን ተለያየን! በለንደን እንደራሴ ጽህፈት ቤት የተደረገው ቀዳሚና ህዝባዊ ጉባኤ (ናፍቆት በዛብህ)

የልባችንን ጫና አስተንፈሰን ተለያየን!

በለንደን እንደራሴ ጽህፈት ቤት የተደረገው ቀዳሚና ህዝባዊ ጉባኤ – መጋቢት ፯፡ ፪ሺ፲፩ ዓ.ም.

 

ናፍቆት በዛብህ

ጉባኤው ሊጀመር ዐሥራ አምሥት ደቂቃ ሲቀረው፤ ለንደን ከሚገኘው የኢትዮጵያ እንደራሴ (Embassy) ደጃፍ ላይ ተገናኘን። በቀጠሯችን መሠረት ቃላችንን አክብረን በሰዓቱ መገናኘት በመቻላችን፤ በየበኩላችን ሳንደሰት አልቀረንም። ጉባኤው ይጀመራል ተብሎ የተነገረን ከቀኑ ኹለት ሰዓት ነው። ወንበር ለማግኘት ተስፋ ይኖረናል ተባባልን። ኩራት ብጤም ተሰምቶናል።

ኃይለኛ ነፋስ ይነፍሳል። ውርጩ አንገት ያስደፋል። የስደት ዓመታት ሲጨምር፤ ከቅዝቃዜው መላመዱ እንዲሁ በተጓዳኝ የሚሄድ ይመስለኝ ነበር። ዛሬ ላይ በተቃራኒ መኾኑን ሳልረዳ። ይኽም ኹኖ ከወዳጄ የሞቀ ሰላምታ ከመለዋወጥ አልገተንም።

‘ሽቅርቅር ብለህ የይሖዋ ምስክር መስለሀል።’ አልኩት በተለይ ያጠለቀውን ነጭ ጫማ እየተመለከትኩ።

ኹኔታችንን በጥንቃቄ ሲመለከቱ ለነበሩት የህንጻ ጠባቂዎች፤ በያዙት መሣሪያ ይዳብሱን ዘንድ እጆቻችንን እንደምርኮኛ ወደላይ ሰቀለን። ግራና ቀኝ ጎናችንን ደባብሰው ከሚጠበቀው ነፃ መሆናችንን ካረጋገጡ በኋላ ወደውስጥ እንድንገባ ፈቀዱልን።

የእንደራሴው ጽህፈት ቤት እደሳ የተጠናቀቀው በቅርቡ (ባለፉት ወራት) ውስጥ እንደነበረ ተመልክቻለሁ። መቼም ጥሩ ባለሞያ የሰራው ማንኛውንም የሥራ ፍጻሜ መመልከት ደስ ያሰኛል። የተደረገለት እድሳት ከቀድሞው በበለጠ ንጽሁ አድርጎታል። እንደወዳጄ ጫማ ተመልካችን ይስባል። በወቅቱ አፄ ኃይለስላሴ ፳ሺ የእንግሊዝ ፓውንድ እንደገዘቱ አንብቢያለሁ። ዛሬ ቢተመን ዋጋው ጣራ ይነካል። ሥፍራው አስፈላጊና አመቺነቱ ከሚወሳላቸው የለንደን አካባቢዎች አንዱ ነው። የማወቅ ጉጉት ውስጤ አደረበት። አንድ ሰሞን ወያኔዎች ሊሸጡት እንደሆነ ተናፍሶ ቆሽቴ አርሮ ነበር። እንዴት ሰው የሀገር ቅርስ ሊሸጥ ይደራደራል? ይሁዳ! በገንኩኝ። ለነገሩ ንብረት ከሰው ልጅ እልቂት አይበልጥ። ይመስለናል እንጂ። በኋላ ሳጣራ ሀሰት ነው ተባለ። መጠራጠሬን ግን አላቆምኩም። አትፍረዱብኝ! ኢትዮጵያዊ አይደለሁ? ያልጠረጠረ ተመነጠረ እንዲሉ መጠራጠር ልዩ መብታችን ኹኗል። ተሞክሮ ሳይሰምር ቀርቶላቸው ይሆናል በማለት ደመደምኩኝ።

ከዚኽ ቀደም የይለፍ ፈቃድ ለመጠየቅ ካለሆነ፤ እዚህ ሥፍራ ደርሼ አላውቅም። ለዘመናት ሰፍፎ የቆየው የፍረሀት ድባብ ኢትዮጵያዊን የሚያስጠጋ አልነበረም። ወላፈኑ ከርቀት ይጋረፋል። ይገለማል። ይቅርታ ስለቋንቋዬ። እናም የመቃብር ያህል ስሸሸው ቆይቻለሁ። ስመለከተው እንኳ ውስጤን ምቾት እየነሳ፤ ኮሶ እንዳጋቱት ህጻን ሰውነቴን ይሰብቀዋል። ዛሬ ላይ ነገሮች በተቃራኒ መቆም የጀመሩ እየመሰለኝ መጠነኛ እፎይታ ይሰማኛል። ምናልባት ውስጤን እየደለልኩት ይሆናል። መቼም ለዚህ ትውልድ ከመጠራጠር አዙሪት ለመውጣት ቀላል አይደለም። ሌላ ትውልድ መፈጠር ይኖርበታል። ታምኖ የሚታመን። ለማንኛውም፤ ሙሹሮቹን ለመቀበል እንደተዘጋጀ ሠርግ ቤት፤ በሮች በኹለት ወገን ወለል ተደርጎ ተከፍተው ስለነበረ፤ እኔና ወዳጄ ዘው ብለን ገባን።

በሕይወት መገኘት ጥሩ ነው በማለት ለራሴው አጉተመተምኩ። እውነቴን እላችሁለሁ! ኑረን ለዚህ መብቃታችን ተመስገን ነው። በሕይወት ያለ፤ ደረጃው ምን ዝቅ ቢል፤ በመጨረሻውም ሰዓት ቢኾን ለውጥ መመልከቱ አይቀርም። እይታና አመለካከት ከጊዜ ጋር አብሮ ሲለወጥ ያያል። ላይ የነበረው መቀመቅ ሲወርድ፤ ሥልጣን አሳብዶት ናላው የዞረበት ለስደት ሲዳረግ ለመመልከት ዕድሉን ያገኛል። አዎን! የሞተ ብቻ ነው የሚጎዳው። ሞት ጉዳት ከሆነ።

የጽህፈት ቤት ሠራተኛ ነው መሰለኝ፤ በዙሪያው ለተሰበሰቡት በዋናው እልፍኝ ውስጥ ስለሚገኙት ጥንታዊ ቅርሳ ቅርስ ገለጻ ያደርጋል። ገለጻውን እየቋጨ ስለነበረ መደባለቅ ሳይሆንልን ቀረ። ቀደም ብለን ቢሆን ኑሮ ተባባልን። በቃላት ሳይሆን በመተያየት።

ለጥቂት ደቂቃዎች ተዟሩረን በየግላችን ስንመለከት ቆየን። በተለያየ ዘመነ-መንግሥት፤ ለአግልጋሎት ውለው የነበሩትን የኢትዮጵያ ኬላ ወረቀት (passport) ድንገት ተመልክቼ ትኩረቴን ሳበው። ቀለማቸው የተለያየ ነው። ልክ እንደኢትዮጵያዊ። ስድስት ናቸው። ብዛታቸው ደነቀኝ። ያለንንና የነበረንን ለመቀየር`ኮ ተወዳዳሪ አይገኝልንም። አንደኛው የኬላ ወረቀት የፊት ሽፋን ላይ የተጻፈውን ተጠግቼ ተመለከትኩ። እንዲህ ይነበባል።

‘ኢትዮጵያ፡ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር” ማለትም፡-

”ኢትዮጵያ፡ እጆቿን ወደእግዚአብሔር ትዘረጋለች”

ነፍሳቸውን በገነት ያቆየውና፤ የተከበሩት ኒክሰን ማንዴላ በትግላቸው ዘመን፤ ይለፍ ፈቃድ ሳያስፈልጋቸው፤ በቀላሉ ከአገር ወደአገር ለመዘዋወር ያስችላቸውና ይጠቀሙበት እንደነበረ የተነገረለት ኬላ ወረቀት ይህ ሊሆን ይገባል የሚል ጥርጥር አደረብኝ። በወቅቱ ዋጋችን ምን ያህል እንደማማ ተሰቅሎ እንደነበረ ለአፍታ ሳስብ ምራቄ በአፌ ሞላ። ይለፍ ፈቃድ ሳያስፈልግህ፤ ልብህ ወዳሻህ አገር ደርሰህ የመመለስህን ጉዳይ እስቲ አስበው? ሊቢያ ውስጥ በወገን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ እልቂት ደግሞ ገምተው። መገመት ከተቻለ? የዛን ዘመን (የጥንቱን) ተካፋይ የነበርኩ ቢሆን በማለት ተመኘሁ።

ስሜቴ እንደዕለቱ አየር ይቀያየራል። ባለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት የፈጸምነው የኋልዮሽ ጉዞ በሀሳቤ ተደቅኖ ውስጤ ተላወሰ። የወያኔ መንግሥት በነሰነሰብን የጥላቻ መርዝ የተነሳ፤ በመኻከላችን እንዲሰፍን የፈቀድንለት የዘረኝነት ደዌ፤ በቀላሉ መወጣት ከማንችልበት ደረጃ ስለመድረሱ፤ እንደማንኛውም እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንዳብከነከነኝ እኖራለሁ። ሰው በተፈጥሮ ያገኘውን እግዚአብሔራዊ ማንነት በፍላጎትና በምርጫው ሲለውጥ ውጤቱ እጅግ አደገኛ ይሆናል። ወደማይገባው ሰንካላ መንገድ ማሽቆልቆል ይጀምራል። ያበቀለው አዲስ ማንነት እስከምን ደረጃ ሊያደርሰው እንደሚችል ለማረጋገጥ፤ ከኢትዮጵያዊ የተሻለ መስካሪ ይገኝ ይሆን? እጠራጠራለሁ።

ለማንኛውም ጉባኤው ላይ የሚሆነውን እናያለን በማለት ህንጻውን በጓሮ በር ለቅቀን፤ ስብሰባው ወደሚስተናገድበት አቅጣጫ አመራን። ደረጃው ላይ ተቁሞ፤ ረዥሙን ነጭ የድንኳን አዳራሽ መመልከት ይቻላል። ባለሞያ የሰራው ዘመናዊ የመጓጓዣ መርከብ ይመስላል። በድንኳኑ መግቢያ አካባቢ የነበሩት አስተናባሪዎች፤ የታሸገ ወኃ አቀበሉን። በድምጽ ባንነጋገርም በዓይኖቻቸው ‘እንኳን በደህና መጣችሁ!’ ተባባልን። ገጽታቸው ላይ የሚንጸባረቀው ፈገግታ እኛ ዘንድ ደርሶ እንደሸማ አለበሰን።

ወኃችንን ይዘን ድንኳን ውስጥ ገባን። ዮናስን እንደዋጠው አሳ ነበሪ የአዳራሹ ሆድ ሰፊ ነው። አንድ እግር ኳስ ሜዳ ይተካከላል። በአድንቆት ዙሪያውን ቃኘሁት። ጥቂት የማይባሉ ሠራተኞች፤ በሰገነቱ ዙሪያ ከወዲያ ወዲህ ይሯሯጣሉ። የደምጽ ማጉያ መቆጣጠሪያውን ይገጥማሉ። መስራት አለመስራቱን ደጋግመው ይፈትሻሉ። ለጉባኤው መሪዎች የሚመጥናቸውን መቀመጫዎችና ጠረጴዛዎች ያስተካክላሉ። ረዥም ዘንግ ላይ ለተሰቀለው ኤሌትሪክ ማሞቂያ ሥፍራ ይመርጣሉ።

ፈቅቅ ብሎ ደግሞ ለየት ያለ እንቅስቃሴ ይታያል። ከዚህ ቀደም ተመልክቼ የማላውቀው የሀገር ልብስ የለበሱ ኢትዮጵያውያን የማይመስሉ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፤ እንደ ሸማኔ መደወሪያ ከወዲያ ወዲህ ይሯሯጣሉ። ከአንደኛው መዓዘን፤ በሥረዓት ከተደረደሩት የድፎ ዳቦ ቁርጥራጭ በማንሳት ወደ ትሪ ያሸጋግራሉ። የረባ ምሳ ባለመመገቤ ነው መሰለኝ ሆዴ መንጫጫት ጀመረ። ወንበር እንደያዝን፤ አንድኛዋ ወጣት የተቆላ ቡና አምጥታ አሸተተችን። ኹለታችንም እንደማረገቢያ እጆቻችንን አረገበገብን። የቡናውን ጢስ ተከትዬ ጉዞ ጀመርሁ።

ሰው ሲተባበር መግባባት ይፈጠርና ጉዳዩን ከፍ በማድረግ ወደፍቅር ያሸጋግረዋል። በዚህ ደረጃ ላይ ስትገኝ`ኮ ሕይወትህንም አሳልፈህ ለመስጠት ዝግጁ ትሆናለህ። ከዚኽ ቀደምም ቢኾን ተመሳሳዩን ነገር መፈጸም ይቻላቸው ነበር። አጋጣሚው ነበራቸው። ክፋት ካለሆነ በቀር ምን ገታቸው? ለአንድ ስደተኛ ሰው፤ የእንደራሴው ጽህፈት ቤት ማለት`ኮ መጠለያው ዳስ ነው። ሲቸግረው ወገኑን ማግኛው ሥፍራ፤ ማኩረፊያውና ማረፊያው። ችግሩ ለጸናበት ደግሞ ጠቅልሎ እስኪገባ ማገገሚያው።

‘ይገርምሀል! ስምንት ሰዓት አለፈ። ሥራው ገና አልተጠናቀቀም’

አለኝ ወዳጄ ሀዘን በቀላቀለው ድምጸት። ትዝብቱን ያልተጋራሁት ቢመስለው ነው መሰለኝ፤ ቀኝ እጁን ዘርግቶ ሰገነቱ ላይ የሚታየውን እንቅስቃሴ አመለከተኝ።

‘ሰዓትና ኢትዮጵያዊ ትይዩ መሥመሮች ናቸው። ዙረው ላይገናኙ ተማምለዋል።’

አልኩት ደጅ ደጁን እየተመለከትኩ። ማካፋት ጀምሯል። ንፋሱ እንደጉድ ይነፍሳል። ረዥሙን ድንኳን ገንጥሎ ለመንቀል ትንቅንቅ የያዘ ይመስላል። የተለያየ መልክና ቅርጽ የለው ኢትዮጵያዊ (እድምተኛ) እየተንጠባጠበ ወደውስጥ ይገባል። የሚያውቁት ሰው ድንገት ቢኖር ብለው ነው መሰለኝ ዓይኖቻቸው ከወዲህ ወዲያ ይማትራል።

‘ይገርምሀል አንተዬ! ኦክስፎርድ መንገድ ላይ ስንደርስ፤ አውቶቡሱ ተገትሮ ቀረ። ወርጄ መግፋት ዳድቶኝ ነበር። አማራጭ በማጣቴ ባቡር መያዝ ነበረብኝ። ለምን ብትለኝ በሰዓቱ መድረስ ፈልጌ። ሀበሻ ሰዓት ማክበር ለምን ይሳነዋል? ግድ የለውም። ይኽን መጥፎ ዝንባሌ የገዛ ሥራው ላይ አትመለከትበትም። ማልዶ ነው የሚነሳው።’

አለኝ ከቀድሞው ባልተናነስ የሀዝና የቁጭት ድምጽ።

አመልካችና አውራ ጣቶቼን በማቀናጀት፤ ገንዘብ እንደሚቆጥር ሰው አፋተኩት። የእንጀራ ጉዳይ ስለመኾኑ መጠቆሜ ነበር። ጥሎብኝ ‘ሀበሻ’ የሚለውን ቃል አልወደውም። ይቀነቅነኛል። አንዳንዶች እርዳታ ይፈልጉና `ይቅርታ ሀበሻ ነህ?` ሲሉኝ፤ ‘የለም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ!` እላቸዋለሁ። `አንድ ነው` በማለት አተካራ ሊገጥሙኝ ይፈልጋሉ። ታሪክ የመመርመር አቅማቸው ደካማ ስለመኾኑ ተመልክቼ ‘እናንተ ማለት ገደል ማሚቶዎች ሁናችኋል።’ እላለሁ። ጥቂቶች መጠየቅ የፈለጉትን በመተው ሌላ ሰው ፍለጋ ይሄዳሉ።

“ኢትዮጵያ” ወይም “ኢትዮጽያዊ” ላለማለት፤ ወይንም ለማለት ፈልገው የሚጠቀሙበት፡ “ኻበሽ” ወይም “አበሽ” የሚለው የዓረብኛ መጠሪያ ቃል እንደቀልድ ተቀብለን ማጽደቃችን ያሳምመኛል። ባዕድ ባወጣልን ስያሜ፤ እርስ በእርሳችን ለመጠራራት ስምምነት የፈጸምን ብቸኛው የዓለም ዜጋ እኛው ሳንሆን አንቀርም። ‘ጉደኞች ናቸው` የሚያሰኙን ነገሮች እየበዙ ሳይሆን አይቀርም። ‘ኢትዮጵያዊ’ ማለት ለምን እንዲገባ፤ ከዚህ ቀደም አጫውቼው ነበረ። ላስታውሰው ብፈልግም ኹኔታውን ማባባስ ይሆናል በሚል አለፍኩት።

ሰዓትን ስለማክበር ወዳጄ የተናገረው እውነት ነበረ። ለሰዓት ያለን አክብሮት አናሳ የመሆኑ ምሥጢር ምንጊዜም ይደንቀኛል። ነገሮችን በሰዓቱ ተገኝቶ የማከናወን አስፈላጊነት ገና አልተረዳንም። ግንዛቢያችን ከእውነታው የራቀ ይመስለኛል። በተለይ፤ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የምናሳየው የግዴለሽነት ዝንባሌ በእጅጉ አሳዛኝ ነው።

‘ግን ምን ነክቶን ነው?’
በማለት አጉነፈነፍኩ። ድምጼ ከእኔ አልፎ መሻገሩን አላስተውልኩም ነበር።

‘ምን አልክ?’
አለኝ አጠገቤ የተቀመጠው ወዳጄ ሲቁነጠነጥ።

‘መቼም ቢሆን ሙሉ ሰው እንሆናለን የሚል እምነት የለኝም። ይኽ በእኛ ዕድሜ ሊሆን አይችልም። ምናልባት በቀጣዩ ትውልድ ይሳካልን ይሆናል። አዎን! ይህም ቢሆን፤ መጪው ትውልድ እንደኛ ያልነቀዘና ሀሰትን የሚያወግዝ ከሆነ ብቻ ነው። ትውልድ’ኮ የየራሱ እይታና ምርጫ ይኖረዋል። አይመስልህም?`

የተናገርኩት አልጣመውም። መልስ አልሰጠኝም። የድንኳኑን ደጃፍ በዝምታ ይመለከታል።

ሰዓቱ ስምንት ሰዓት ተኩል አልፏል። የእድምተኞቹ ቁጥር ከሰዓቱ መግፋት ጋር ጨምሯል። ከፊትና ከበስተኋላችን ይታዩ የነበሩት ሰው አልባ ወንበሮች ተይዘዋል። ድንገት ስዞር ከ፲፭ ዓመታት በኋላ አንድ ወዳጄን ተመልክቼ ከተቀመጥኩበት ተነሳሁ። ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈን ሰላምታ ተለዋወጥን። ቁመን ሳለን፤ ‘በሕይወት አለህ አለህ፤ መቆየት ደግ ነው’ ተባባልን። አፍታም ሳልቆይ ኹለት አብሮ አደጎቼን ተመለከትሁ። አንዱ ታላቄ ሌላኛው ታናሼ። ልጆች ሳለን አንድ ሠፈር ነበርን። ገና ተማሪ ሳለሁ እንተዋወቅ የነበረችውን እጮኛዬን ከርቀት ተመልክቼ ኹለታችንም እጆቻችንን ለሰላምታ አውለበለብን። ሀር የመሰለውን ጸጉራን ተተኩሷ ቁልቁል ለቅቃዋለች። ሳቀች። ሳቅና ፈገግታ ተለይቷት አያውቅም። የኑሮውን ውጣ ውረድ ተቋቁማ፤ በአንድ ቤተ ህሙማን ውስጥ አስታማሚ ሁናለች። አንድ ቀን ተገናኝተን ሻሂ ስንጠጣ፤

‘ህመምተኞቼን አክሜ የማድነው በመሳቅ ነው’

አለችኝ። በጥድፊያ ተራምዶ ያለፈ አንድ ወጥመሻ ጠብደል፤ ወዳጄ ያጠለቀውን አዲስ ነጭ ጫማ ረግጦ ተራመደ።

‘ድልድይ መሰልኩት እንዴ!` ወዳጄ ተቆጣ።
‘ይኽን ጫማ ማድረግ አልነበረብህም። የበጋው ወራት እሲኪቃረብ መታገስ ነበረብህ’

አልኩት። እርሱ ግን በዝምታ ተጎንብሶ ጫማውን ሲጠራርግ ቆየ። በቀስታ እና በትንሽ በትንሹ ቆሻሻው ከጫማው ላይ ሲለቅቅ፤ ጫማውም ወደቀድሞው ይዘቱ ሲመለስ በአድናቆት እመለከታለሁ። ጫማውን ለማጽዳት የወሰደበት ጊዜ አስደመመኝ።

‘የለበስነውን የቆሸሸ ኩታ፤ እንደጫማህ ጠርገን ከላያችን ማራገፍ አለብን። የሰው ልጅ የመንፈስ ተሀድሶ ያስፈልገዋል መባሉ እውነት ነው። ያኔ ብቻ ነው ከተጠበቅንበት ሥፍራ በሰዓቱ መገኘት የሚሆንልን።’

አልኩት።

‘አዲስ ትውልድ ማብቀል ማብቀል ትላለህ። አዲሱ ትውልድ አዲስ ነገር ከወዴት ያገኛል? አሸጋጋሪዎቹ እኛ መኾን ነበረብን። ከምንሰጠው የተለይ ከየት ሊያመጣ ይችለዋል?’

ምን መመለስ እንዳለብኝ ሳስብ፤ ከፊተኛው ረድፍ የተቀመጡት እድምተኞች እንዲለቅቁ ትእዛዝ ተላልፎላቸው መጠነኛ ግርግር ተፈጠረ።

‘መቀመጫዎቹ ለሌሎች ተይዘዋልና ልቀቁ’

ተባሉ። መቀመጫዎቹ ስለመያዛቸው ጠቋሚ የሆነ ምልክት አልነበረም። በሰዓቱ ደርሶና ወንበር መርጦ የተቀመጠን ሰው፤ ተንስቶ ሌላ ወንበር ፍለጋ እንዲሄድ እንዴት ጥያቄ ይቀርብለታል? `አቤት ሰው ማፈናቀል ስንወድ! በተፈናቃዩ ቦታ የሚተካውን ሰው ስትመለከት ነው ጨጓራህ የሚላጠው። እዚህ ግባ የማይባል ወሮበላ ሰው ሆኖ ታገኘዋለህ። ወይም ይመስልሀል።’ እይታችን ኹሉ ሳይንሸዋረር አልቀረም። ይቅር ይበለን። መሳቅ ከጀለኝ። ተበሳጭተው ወንበር ፍለጋ ላይ የሚገኙትን ተፈናቃዮች ማባባስ እንዳይሆን ፈርቼ አንደበቴ ልጓም አበጀሁለት።

ቆየት ብሏል። ዛሬ ድንኳን ውስጥ በእርቀት ላይ ሰላምታ ከተለዋወጥነው እጮኛዬ ጋር ሠርግ ተጠርተን በሰዓቱ ደረሰን። ለእይታ እንዲመቸን ከኹለተኛው ረድፍ ወንበር መርጠን ተቀመጠን። የፈለገ ረዥም ሰው ከፊተኛው ወንበር ቢደነቀር ሰገነቱን ለመመልከት አያግደንም በማለት ስንፎክር ቆየን። ከኹለተኛው ረድፍ ላይ ነበርን። ከብዙ ጥበቃና መጉላላት በኋላ፤ ሙሹሮቹ መግባት ሲጀምሩ ወንበራችንን እንድንለቅቅ ተጠየቅን። ችግሩ መፈናቀላችን አልነበረም። ትርፍ ወንበር አለመገኘቱ ነበር። ከዛን ምሽት ጀምሮ ከፊተኛ ወንበር ላለመቀመጥ ለራሴ ቃል ገባሁ። እርግፍ አድርጌ ተውኩ። ለቅዳሴ እንኳ ስሄድ ፊት መቀመጥ ተውኩ።

አጠገቢ ከተቀመጠው ወዳጄ ጋር ብዙ ተወያየን። በቂ መወያያ ጊዜ ነበረን። ጥናካሬና ጉድለታችንን አጉልቶና ለይቶ የሚያመለክተን መስታውት ያስፈልገናል ተባባልን። ከምንኖርበት ህብረተሰብ ጥሩውን መርጠን መውሰድ ነበረብን ስንል በቁጭት ተናገርን። የእኛ ነገር አድሮ ጭቃ ነው መባባላችንም አልቀረም። አጀንዳውን እንኳ ሳናውቅ ስብሰባ ለመምጣት መወሰናችን አስደነቀን። ምናልባት መስማት የፈለግነው አንድ ድብቅ የሆነ የጋራ መሰብሰቢያ ርእስ ኑሮ ይሆናል።

ዳቦ ሲታደል ለኹለተኛ ጊዜ አነሳን። ዳቦው እጅ ያስቆረጥማል። ልምድ ባለው ዳቦ ጋጋሪ የተዘጋጀ መኾን አለበት። የተፈለ የጀበና ቡና መግዛት እንደሚቻል በድምጽ ማጉያ ተነገረ። ገቢው ለበጎ አድራጎት ነው ተባለ። ጥቂት የማይባሉ እጆች እንደ ሸንበቆ ወደ ሰማይ ተመዘዙ። ለየት ያለ ሀገር ልብስ የለበሱት እነዛ ኢትዮጵያውያን የማይመስሉት ኢትዮጵያውያን ሴቶች፤ እንድንብ ክንፍ አውጥተው በረሩ። ረዥም የሆነውን ቀሚሳቸውን ሽቅብ ሰብስበው፤ አዳራሹ ውስጥ ተምነሸነሹ። ዓውዳ ዓመት ለማክበር የተሰባሰብን መሰለኝ። ለምን አይመስለኝም? ድንኳን ውስጥ፤ ይባሱኑ

የኢትዮጵያ እንደራሴ ግቢ። ድፎ ዳቦ ተቆርሷል። ቡና ተፈልቷል። እጣን ይጨሳል። የቀድሞዋ እጮኛዬን በተገኘሁበት ታዛ ተገኝታለች። አብሮ አደጎቼን ሳይቀሩ አግኝቻለሁ። እናም የዝግጅቱን መጀመር ለመመልከት ጓጓሁ። ሰዓቱ ደግሞ ክንፍ አውጥቶ ይበርራል።

እንደቀልድ ዘጠኝ ሰዓት ሞላ። አስተናጋጁ ወደ ድምጽ ማጉያው ቀርቦ ጉሮሮውን መጠራረግ ጀመረ። ሊጀመር መስሎኝ ተመስገን አልኩ። በሰላሳዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ገደማ የሚገኝ ወጣት ነው። ድምጹ ጎላ ያለ በራሱ መተማመን የሚታይበት።

‘ዋናው መንገድ ላይ የተሽከርካሪ ፍሰት በምብዛቱና በደረሰው የመኪና መጨናነቅ፤ ጥቂት እንግዶች በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን። ትንሽ እንድትታገሱን በትህትና እንጠይቃችኋለን።’

አለ። ወዳጄ ፊቱን ወደ እኔ መልሶ እንዲህ አለኝ።

‘ታውቃለህ! የሚጠበቁትን ሰዎች መመልከት እፈልጋለሁ። ሰዉ`ኮ ገብቶ ተጠናቅቋል። ለምን አይጀምሩም? ምን ያህል ዘመን ነው የምንጠብቀው? ሌላ ፳፯ ዓመት?’

በእጁ ጎነተለኝ።
‘ይኽ ኹሉ ሰው ተሰብሶ ጥቂት ተጨማሪ እንግዳ መጠበቅ ለምን አስፈለገ?’
‘ምናልባትም`ኮ ርእሰ ብሔሩ ይሆናሉ የሚጠበቁት። ሳይታሰብ ብቅ ማለት ጀምረዋል ይባላል’

አልኩት እያቅማማሁ።

የወዳጄን ብስጭት ያደመጡ ይመስል፤ ሰዉ እንደ ጎርፍ መትመም ጀመረ። ከሰዉ ብዛት የተነሳ ድንኳኑ እንደፊኛ አብጦ ሊፈነዳ ደረሰ። ‘እንግዶቹ’ የተባሉትም ተከታትለው ገቡ። ቀሳውስት ነበሩ። አንድ ሰው፤ ከአስተናጋጆቹ መኻከል ሳይሆን አይቀርም፤ የተፈናቀሉትን ሰዎች ቀድመው ወደተቀመጡበት ወንበራቸው እንዲመለሱ ትእዛዝ መሰል ተደጋጋሚ ጥሪ አቀረበ።

‘በእውነት አቅላችንን ስተናል። የምንሰራውን አናውቅም’

አልኩት ለወዳጄ። ለመመለስ ከወንበሩ የተነሳ ሰው አልነበረም። ወንበራቸውን ለተነጠቁት ባዝንም ላለመመለስ በመወሰናቸው አንጀቴ ቅቤ ጠጣ። ኢትዮጵያዊ ማለት እንዲህ ነው! ጅንን! ኩሩ!

ከቀኑ ዘጠኛ ሰዓት ተኩል ሆነ። አስተናጋጁ ዝግጅቱ መጀመሩን ተናግሮ ለመግቢያ የሚኾን አጠር ያለ ንግግር አደረገ። ከዛም የብሔራዊ መዝሙር እንድንዘምር ጠየቀ። ኹላችንም ፈጥነን ተነሳን። በእንዲህ አይነት ፍጥነት ህዝብ ተምሞ ሲነሳ የተመለከትኩት ቤተመቅደስ ውስጥ ነው። ለመጨረሻ ጊዜ የብሔራዊ መዝሙር የዘመርኩበትን ጊዜ ለማስታወስ ሞክሬ አልተሳካልኝም። የሌላውን ባላውቅም፤ አንዳች ልገልጸው የማይቻለኝ፤ ልዩ የኾነ ስሜት ሰውነቴን ወረረው። ላለቅስ ምንም አልቀረኝም። ግጥሙን ባለማወቄም ተቆጨሁ። እኔ የማውቀው፤ መስታወት ሳጥን ውስጥ ተቀምጦ እንደተቆለፈበት የኬላ ወረቀት፤ አገልግሎቱ ያከተመውን ነው። ማን ነበር፤

‘የነበረንን አጥፍቶ አዲስ ከማዘጋጀት ይልቅ፤ እንዳስፈላጊነቱ እያደስን ብንገለገልበት የተሻለ ይኾን ነበር’

ያለው? ብሔራዊ መዝሙር እንደተጠናቀቀ አዳራሹ ውስጥ ከፍተኛ ጭብጨባ ተስተጋባ።

ወጣቱ አስተዋዋቂ በዚህ ብቻ አላበቃም። ደብረዘየት ቢሾፍቱ ላይ፤ በወገን ለደረሰው አሰቃቂ የጥያራ (Aeroplane crash) አደጋ፤ የህሊና ጸሎት እንድናደርስ ጠየቀ። ወዲያውኑ ጸጥታ ሰፈነ። ጎልቶ ይደመጥ የነበረው ከድንኳኑ ጋር ትንቅንቅ የገጠመውና የማይታየው ነፋስ ነበረ። ምድጃ ላይ እንደተጣደ የሻይ በራድ ያፏጫል። የጋራ መሰባሰቢያ የኾነውን ድንኳናችንን ገንጥሎ እንዳይወስደው በልቤ ጸሎት አደረስሁ። ትኩረቴን ወደተወሳው ርእስ ለመመለስ ሞከርሁ። ጥያራው አፍንጫውን አስቀድሞ ቁልቁል ሲምዘገዘግ በሀሳቤ ተመልክቼ ሰውነቴን ሰቀጠጠው። በሕይወተ ሥጋ ላረፉት ለገነት እንዲበቁ፤ ቤተሰቦቻቸው ደግሞ አንዳች መጽናኛ ያገኙ ዘንድ በልቤ ፈጣሪዬን ተማጸንሁ። የጸሎቱ ዝምታ ሲጠናቀቅ ቀድሞ ከነበረው የጋለ ጭበጨባ በነጩ ድንኳን ውስጥ ተስተጋባ። ቅልል ብሎኛ ዐይኖቼን ከፈትሁ።

በተጋበዙት መሠረት፤ በእንግሊዝ አገር የኢትዮጵያ እንደራሴ የሆኑት አቶ ፍሰሀ ሻወል ጉሮሯቸውን ጠራርገው መናገር ጀመሩ። ከሰላምታ በመቀጠል ንግግራቸውን ያነጣጠሩት ሹመቱን የተቀበሉት ከኹለት ሳምንት አስቀድሞ ስለመኾኑ ግልጽ በማድረግ ነበረ። የትኛውም የፖለቲካ አባል አለመኾናቸውን፤ ባላቸው ሙያ አገራቸውንና ህዝባቸውን ሲረዱ የኖሩ ስለመኾናቸው ተናገሩ። መልእክቱ ግልጽ ነበር። ያለፈውን ወደኋላ ትተን የወደፊቱን በጋራ እንስራ ነው። እውነታቸውን ነው። መወቃቀስ ምን ሊፈይድ? የፈሰሰ ወኃ አይታፈስር። ነገሩ ግን ቀላል አይመስለኝም። ልቡ በሀዘን ቁርሾ የመከነ ስንት ኢትዮጵያዊ አለ? ቤቱ ይቁጠረው። ሀዘንን ከልብ ፈንቅሎ ማውጣት፤ እንደሚታሰበው ቀላል ላይሆን ይችላል። እንደራሴው ሌላም ነገር ተማጸኑ።

‘ሀሳባችሁንና ጥያቂያችሁን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተመላበት ማቅረብ ትችላላችሁ። የመገናኘታችን ተቀዳሚ ዓላማ ይኸው ነው። እኔ እናንተን፤ እናንተ ደግሞ እኔን እንድታውቁ፤ ዘላቂ ለኾነው ተግባር በህብረት እንድንሰራ። ከእንግዲህ ጽህፈት ቤታችን ለማንም ኢትዮጵያዊ ክፍት ነው። ለወደፊቱ ከዚህ በተሻለ ለመወያየት የሚያስችለንን አመቺ ኹኔታ እንፈጥራለን።’

ከፍተኛ ጭብጨባ ተስተጋባ።

የሥራ ባልደረቦቻቸውን ስም በመጥራት ማስተዋወቅ ጀመሩ። ተጠሪዎቹ ስማቸው ሲጠራ ከየተቀመጡበት በመነሳት አንገታቸውን ዝቅ ያደርጋሉ። ሳላደምጠው ያመለጠኝ አንድ ስም ሲጠራ ይሁን ወይንም ሳይጠራ ተመሳሳይ ስም ተደምጦ እንደሆን አላውቅም፤ ከፊተኛው ረድፍ ረብሻ ተነሳ። አንደኛው የጀመረውን ንግግር ሌላኛው ተቀብሎ እንደገደል ማሚቶ ያስተጋበ ጀመር። አዳራሹ በግራና በቀኝ በተፈጠረው ኹከታ መታመሰ ጀመረ። የጥበቃ ሠራተኞች እውነታቸውን እንደሆነ ባላውቅም፤ ዦሯቸው ላይ በሰኩት የሥልክ መገናኛ መነጋገርና ቦታቸውን መያዝ ጀመሩ። ዓይኖቻቸውን በማጉረጥረጥ ግዙፍ ሰውነታቸውን እድምተኛው ላይ አርገፈገፉት። እንደራሴው ረብሻው ቁሞ መረጋጋት እንዲፈጠር በትህትና ያሳስቡ ጀመር። በመጨረሻ ድምጻቸው ተሰምቶ ቁመው የነበሩት ተቀመጡ። መንጫጫቱም ቀነስ። ቅጽበት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ሰፍኖ የነበረው ጸጥታ ሊደፈርስ መቻሉ አስደነቀኝ።

እንደራሴው መደመጣቸውን ካረጋገጡ በኋላ፤

‘ግድየለም! ትውውቁን ለሌላ ጊዜ እንዳርገዋለን። ሥራችንን ገና መጀመራችን ነው። ተከታታይ ዝግጅት ይኖራናል። በሀሳብ ላንስማማ እንችል ይሆናል። ቢሆንም ግን መደማመጥ መቻል አለብን። የትኛው የአሰራር መሥመር የተሻለ እንደሚሆን በጋራ እንመለከታለን። ዲያስፖራን እንደአጋዣችን እንጂ እንደስጋት ምንጭ አንመለከተውም። በልማት ጎዳናችን ላይ ትብብር በመፍጠር የተሻለ ነገር በህብረት መሥራት ይቻለናል።’

ፈንጂ በተቀበረበት ሥፍራ እንደሚረማመድ ወታደር፤ ጉዳዩን በትእግስት ተቆጣጠሩት። ይኽ ሊሆን እንደሚችል አስቀድመው ሳያጤኑ አልቀሩም መሰለኝ። ከርሮ ሊበጠስ የነበረውን የጭቅጭቅ መረብ፤ በዓይን መታየት በማይችል መቀስ ቆራርጠው ከመሬት ላይ ጣሉት። እንደራሴውን አደነቅኋቸው። እና አበረታታች የሆነውንና በተስፋ የተመላ ንግግራቸውን ቋጩ። ወጣቱ አስተናጋጅ፤ የእርሳቸውን ንግግር ተመርኩዞ ጥቂት ነገሮችን ለመናገር ሞሞከሩ አልቀረም። ንግግሩ ውስጥ መመጻን ይደመጣል።

‘አሀዱና አልፋ’ ተወካይ ነበር ቀጣዩ ተናጋሪ። ተናጋሪው ሰው፤ እርዳታን አስመልክቶ ወቀሰ አዘል ንግግራቸውን ፈጸሙ። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለተጎዱ ወገኖቻችን መዋጮ ለማድረግ ከልቤ እፈልጋለሁ። እውነቴን ነው። ሰው ባላጠፋው ጥፋት፤ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማው ተደርጎ፤ ተያይዞ የሚመጣውን ሀዘኔታና ፍርሀት አስታክኮ፤ ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚደረገውን ጥረት እጸየፈዋለሁ። በዚህ መንገድ እጄ ለእርዳታ ሲዘረጋ ተመልክቼው አላውቀውም። ከሰባዊነት ይልቅ ስሜታዊነት አይሎ እርዳታ ማሰባሰብ ተገቢ አይመስለኝም። ይህን መሰል ድርጊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ሳይቀር ተለምዷል። ኪስህ ውስጥ ያኖርከውን ዘርግፈህ ካላዋጣህ ትቀሰፋለህ አይነት ማስጠንቀቂያ ይደረጋል። በቀላል አማርኛ ችግሩን ማሳወቅ ሲቻል፤ ይኽን ኹሉ መቀባጠር ለምን አስፈለገ? ለማንኛውም የተወካዩን ሰው ንግግር ልመዘግበው አልፈለግሁም።

መድረኩ ለአስተያየትና ለጥያቄ ተከፈተ። ይመስለኛል አብዛኛው ተሳታፊ በጉጉት ይጠባበቅ የነበረው ሰዓት መኾኑ ነው። ከመቅጽበት በርካታ እጆች እንደጃንጥላ ተዘረጉ። የመጀመሪያው ተናጋሪ ወጣት፤ ቀደም ሲል ረብሻ ተነስቶበት ከነበረበት ሥፍራ የተቀመጠ ሆነ።

‘በትግሉ ዘመን መስዋእትነት የከፈሉት ሳይሆን፤ በኹለት ቢላዋ ሲበሉ የኖሩት፤ ዛሬም የልብሳቸውን ገበር ቀይረው ስለመኖራቸው’

እልህ በተናነቀው ድምጽ ሲይስረዳ ቆይቶ፤ የተዘጋጀ ጽሁፍ ለማንበብ ፈቃድ ጠየቀ። አጠያየቁ እንደራሴውን ሳይሆን ታዳሚውን ነበር። ብዙ ሰዎች እንዲያነብብ ድምጻቸውን አስሙ። መንግሥት ሊፈጽመው ይገባል በማለት የታሰበበትን፤ የመጀመሪያዎቹን ስምንት ነጥቦች አንብቦ ሲያጠናቅቅ፤ ወረቀቱን ማደል ጀመረ። እንደገና መናገሩን ቀጠለ። እንደራሴው በታላቅ ትእግስትና ማግባባት፤ ድምጽ ማጉያውን ለቀጣዩ ተናጋሪ ሰው እንዲሰጥ አስደረጉ። ከዛ በኋላ በቀጣይነት የታየው ድራማ ይመስል ነበር። አዳራሹ የገበያ ማእከል እስኪመስል ሰዎች መነጋገሪያውን ለመጨበጥ ተሻሙ።

ኹሉም በየፊናው መተንፈስን ፈልጓል። ትእግስታቸው የተሟጠጠው አዳራሹን ለቅቀው ወጡ። የኦሮሚያ ሰንደቅ ዓላማ አንግበው የነበሩት ጥቂት ወጣቶች፤ አዳልጦኝ ወረበሎች ልል ነበር፤ ከኹሉ ቀድመው ወጥተዋል። ጉባኤውን ረግጠው መውጣታቸው ነው መሰለኝ። የአንዳንድ ሰው ተቋውሞ ይህን ይመስላል። ማፈሪያዎች በማለት በዓይኖቼ ዳርቻ ገረመምኳቸው። ሌሎች ደግሞ የደረሰባቸውን በደልና ብሶት ተናገሩ። አንዳንዶቹም፤ ተገኘ ለሚባለው ለውጥ የፈጸሙትን ድርሻ አጉልተው ለማሳየት ተጣጣሩ።

ከተለቀቁት ወንበሮች ላይ፤ አጠገቤ መጥተው ከተቀመጡት ኹለት ሴቶች አንደኛዋ፤
`So what? ‘ታድያ ምን ይሁን? ምን ይደረግ?’ በማለት በግርምት ጥያቄ አቀረበች።

ፊቷን ወደእኔ መልሳ፤
‘ለመሆኑ፤ ከዚህ ጉባኤ የምናተርፈው ምንድን ነው?’ አለችኝ።

‘መተንፈስ ካለሆነ በቀረ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም’ በማለት መልስ ከመፈለግ ገላገለችኝ።

`ጥሩ ርእስ ይወጣዋል። የልብ የልባችንን ተንፍሰን ተለያየን። ከዛሬው መማር ከተቻለን፤ ምናልባት ቀጣዩ ጉባኤ የተዋጣለት ይሆናል።’

አልኳት። አልቆየችም። ጎኗ ተቀምጣ ከነበረችው ወጣት ተያይዘው አዳራሹን ለቅቀው ወጡ። አንዲት ጃማይካዊት ኾኖም ኢትዮጵያዊት፤ ከኹሉ የተሻለ ተናገረች። እራሷን ካስተዋወቀች በኋላ፤

‘እኛ ስለብሔር በማንሳት ተበጣብጠን ችግር ስንፈጥር፤ ሌሎች በመኻከላችን ሾልከው እንዲገቡ ስለመፍቀዳችን ያጤንነው አልመስለኝም። እነርሱ (ነጮችን ይሁን ባንዳዎችን፤ ወይንም ኹለቱንም፤ እግዚአብሔርና እርሷ ብቻ ናቸው የሚውቁት) እኮ ሲመጡ፤ እንደ መንፈስ አይታዩም። እንደጥንቱ የጦር መሳራያም አያነግቡም። ቦዳ እጃቸውን ይደርሳሉ። አስታራቂ ይመስላሉ። ውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኳላ ናቸው። አገራችን ቀኝ ግዛት አልተያዘችም በማለት ስንፎክር፤ በሙሉ ፈቃዳችን አሳልፈን ልንሰጣት ጠርዝ ላይ ደርሰናል። ወንድሞቼና እኀቶቼ፤ እባካችሁ! ዓይኖቻችሁን ክፈቱ! እናም ለይታችሁ ተመልከቱ። ህብረት ካልፈጠርን የያዝነው አቅጣጫ መቀመቅ ይከተናል።’

አለች። የሴትየዋን መልእክት የተረዳን ስለመሆናችን እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ብቻ ብዙ ሰው አጨበጨበ።

የሰዎች ንግግርና አስተያየት ቀጠለ። ያአንዳንዱ ሰው ትንታግ መላስ እንደ እሳት ረመጥ ይፋጃል። ይኽም ኾኖ፤ በየንግግራቸው ማብቂያ፤ አንዳንዴም የተጀመረ አረፍተ ነገር ገና ሳይቋጭ፤ አዳራሹ በጭብጨባ ይደምቃል። ታሪክ እራሱን ይደግማል እንዲሉ፤ ታላቁና የተከበረው ደራሲ አቶ በዓሉ ግርማ፤ ኦሮማይ ላይ እንደጻፉት፤ ዛሬም ተመሳሳይ ሆነ።

‘…በተገቢ ቦታ፤ ለተገቢ ጉዳይ ከልብ ማጨብጨብም እኮ፤ ብስለትና ንቃት ይጠይቃል…’ ወዳጄ እንድንሄድ ጠየቀኝ። አቋርጦ መውጣቱን አልፈለግሁም። አግባባው ጀመር።

‘ከቆየንበት የሚቀረን ሰዓት ትንሽ ነው። እባክህን ታገስ። ባይሆን፤ ያንን ጣፋጭ ዳቦ እንድታመጣለን ያችን ውብ ኢትዮጵያዊት እንለምናት’

አልኩት። ከዚህ በላይ መቆየቱ ደስ አላሳኘውም። ማንም ትእግስተኛ ሰው ከዚህ ሥፍራ ላይ ቢበሳጭ፤ ተገቢ ይሆናል። ሊፈረድበት አይገባም። ወዳጄም በበኩሉ መተንፈስ ነበረበት። ለጊዜው መልስ የማይገኝላቸውን ጥያቄዎች ያዥጎደጉድ ጀመር።

“በጥያቄና በአስተያየት መኻከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት እንዴት ይሳነናል? ለጋራ ህልውናችን ጠቃሚ የሆነውን ርእስ መርጠን በማንሳት ብንወያይ ብልህነት አልነበረም? ለታይታና ለእይታ የሚመስሉ ጥያቆዎችን መጠየቅ የምንታቀበው መቼ ይሆን? ወገናዊነትን ትተን፤ ትልቁን ሥዕል (ኢትዮጵያን) በመመልከት ለጋራ የሚበጀን ጉዳይ ላይ ብናተኩር ምን ነበረበት። በኪሳራ ተወልደን፤ በኪሳራ አድገን፤ በኪሳራ ውስጥ ልናልፍ ተዳርሰናል። አለመታደል ነው…”

የመጨረሻው ተናጋሪ ቄሱ ነበሩ። መጽናኛ ሊሆን ይችላል በማለት ያሰቡትን ተናገሩ። ብዙ ሰው ያዳመጣቸው ይመስለኛል። በተናገሩት ተማርከን ግን አይመስለኝም። መንፈሳዊ ነገር ተነስቶ ሲወሳ ፍረሀት ሳያድርብን አይቀርም። ሰው ይፈራል። በተለይ ተናጋሪው ካባ የለበሰ ሲኾን ለጊዜውም ቢሆን ዦሮውን ይጥላል። ምናልባት ተሳስቼ ይሆናል። ለማንኛውም ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁ መዝሙር መዘመር ጀመሩ። ኹላችንም ከየመቀመጫችን ተነስተን አጀብናቸው። ማስተባበር በመቻላቸው ነው መሰለኝ ገጽታቸው በደስታ እየፈካ ሲሄድ ከርቀት እመለከታለሁ።

‘…ሰላም ለኢትዮጵያ ሰላም ለአገራችን፤

ይባርክልን ኢትዮጵያን ቸሩ አምላካችን…’
የእኔም ገጽታ መፍካት ጀመረ። ለመቆየት መወሰናችንም አስደሰተኝ።

ስለኢትዮጵያ አንድነት መፈራረስ ወይንም እንዲያ ሊሆን እንደሚችል ብዙ እንደሚባል አውቃለሁኝ። ተጽፎም አንብቢያለሁ። እውነት እላችኋላሁ ይህ ኹሉ እኔን አሳስቦኝ አያውቅም። የማያሳስበኝ ወገናዊነቴን ሽሬ አይደለም። ነብይም ኹኜ አይደለም። አንድ ቁም-ነገር ግን ጠንቅቄ አውቃለሁ። ‘አምናለሁ’ ማለቱ ተገቢ ይሆናል። የሰው ልጅ ደረጃውን ምን ከፍ ቢያደርግ፤ የፈጣሪን ሚና መጫወት አይችልም። በፍጹም ድንበሩን አልፎ ሊሄድ አይቻለውም። በእግዚአብሔር መሪነትና ተራዳኢነት ኢትዮጵያ እንደሰዋዊ አሰራር፤ ሀሳብ ወይም ዕቅድ ልትጠፋ አትችልም። በዘመናት ውስጥ፤ በውጪና በውስጥ ወራሪዎች ያ! ይሆን ዘንድ ብዙ ተሞክሯል። በጣም ብዙ ተሞክሯል። ግን አልተሳካም። ወደፊትም አይሳካም። እርግጥ ነው፤ ለኃጢያተኛ የወረደ እንደሚባለው ጉዳት መድረሱ አይቀርም። ይደርሳልም። የንጹሀን ደም በከንቱ ይፈስሳል። እናቶች ያነባሉ። ወጣቱም ለጦርነት ይማገዳል። የእግዚአብሔር ቃል ግን ጸንቶ ይኖራልና የኢትዮጵያ ህልውና ለዘላለም ጸንቶ ይቆያል። እስከወዲያኛው።

ትንቢቱ ይደርሳል!

Filed in: Amharic