>

የጠቅላይ ምኒስትሩ ቪዲዮ (ደረጄ ደስታ)


የጠቅላይ ምኒስትሩ ቪዲዮ

ደረጄ ደስታ

 

* ከዚህ በፊት የሠሩትን ሳይሆን ገና ወደፊት እሚሰሩትን ቪዲዮ “አይቼ” ነው የደገፍኩዎት፡፡ ቅስቀሳ ነው እንዳይባል ጊዜው የምርጫ ሳይሆን የርግጫ ጊዜ መስሏል!!!

ሰሞኑን እርስዎን አስመልክቶ የተለቀቀውን ምናልባትም እርስዎ ፈቅደው የለቀቁትን ቪዲዮ ወድጄ አይቸዋለሁ። የጨመረው የቀነሰው ነገር ባይኖርም አልተቸገርኩበትም። ከርስዎ እምደብቀው የለምና ግን መጠየቄ አልቀረም። ከዚህ በፊት የሠሩትን ሳይሆን ገና ወደፊት እሚሰሩትን ቪዲዮ “አይቼ” ነው የደገፍክዎት፡፡ ቅስቀሳ ነው እንዳይባል ጊዜው የምርጫ ሳይሆን የርግጫ ጊዜ መስሏል። ወስላታው በየቦታው እየተራገጠ ሊፋጅ እየተፋጠጠ ነው። ተገንጥለውም ሆነ ተጠልለው በተቀመጡ ክልሎች ጉዳይ ላይ፣ በፈረሱ ቤቶች ጉዳይ፣ በሚፋናቀሉ ሰዎች ጉዳይ ላይ፣ ከሁሉም በላይ በአዲስ አበባ እና በኦሮምያ መካከል ስላለው ችግር፣ ስለታወከው አገር፣ በአክራሪ ብሔርተኝነቱ ተሰናክልሏል ስለተባለው ድርጅትዎ ቅልብጭ ክሽን ያለች ቪዲዮ ይለቃሉ ብዬ ጠብቄ ነበር። መሆኑ ካልቀረ የናፈቅኩት ቪዲዮ እሱን ነበር። ባይሆንስ እንኳ አንዲት ቃል ማንን ገደለች! እኔ አምኜዎት ጨርሻለሁ። እምነቴን አይጨምርልኝልም። ያላመኑትንም እርስዎን ከመጠርጠር አልፈው ለመመንጠር ለተነሱትም ወገኖች እሚጨምረው እሚለውጠው ነገር ያለ አልመሰለኝም። አንድ ቪዲዮ ከመልቀቅ አንዲት ቃል መልቀቅ አገር ታረጋጋለች። መቸም የተባሉትን እየሰሙ ነው።
ለርስዎ የቆሙት እየደሙ እየታመሙ ነው። ስለርስዎ ሆነው ምላሽ እየሰጡ በማያውቁት ነገር የማያውቁትና ያልገባቸውን ነገር ለማስረዳት እያማጡ ነው። ይህን ማድረጋቸው መጪው ታይቷቸው ሁኔታዎች አስገተዋቸው እንጂ ሌላ አይምሰልዎ። እርስዎ ግን ጭራሽ ነገርዎ ግራ እየሆነ የተጠየቁት አራምባ የሚመልሱት ቆቦ እየሆነ ነው። የጨረፍታ ንግግርና የሾላ በደፈናው ዲስኩር ሳይሆን ነገሮችን አብራርተውና አፍታተው ይንግሩን። እባክዎን እሚያምኑበትም ከሆነ ፍርጥም አድርገው ይከራከሩበትና እንረፈው። የአንድነትም ሆነ ብሔርተኝነት፣ የሰው ልጅነትም ሆነ ከዚያ ያነሰው ጎጠኝነት ሰበር ዜና አይደለምና አንደነግጥበትም። ወይም ደግሞ ሰግተውና ፈርተውም ከሆነ ፍርሃትዎን ይንገሩና፣ ነቅለን ወጥተን አደባባዩን እንሙላው። እንዳለፈ ጊዜ ጉልበትዎ ሆነን ጉልበታችንን እናሳያቸው። እንሮጥበት እንደበቅበት ዘንድ ሌላ አገር የለንም። ያለችን ያቺው አንድ ኢትዮጵያ ናት። ያውም ብልጥ ልጅ አዲስ አባባን ይዞ ስለኢትዮጵያ ያለቅሳል እምንባባልባት ኢትዮጵያ!
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1495710430564646&id=682829441852753

Filed in: Amharic