>

ዱላችን በጃችን - በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ዐድማ ስለመጥራት (ይነጋል በላቸው)

ዱላችን በጃችን – በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ዐድማ ስለመጥራት

ይነጋል በላቸው

ውድ ኢትዮጵያውያን በያላችሁበት ሰላምታየ ይድረሳችሁ፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ በምሕረት ዐይኖቹ እንዲያየን እንጸልይ፤ በጸሎትና በንስሃ የማይፈታ ችግር የለምና ፊታችንን ወደርሱ እናዙር፡፡ ብዙዎቻችን ጆሮ ዳባ ያልነው የምንመስለው የሀገራችን ወቅታዊ ችግር እጅግ ከባድና ፈታኝ ነውና በየሃይማኖታችን ሱባኤ ገብተን እንጸልይ፡፡ ከፈሰሰ አይታፈስም፡፡ አደጋ ውስጥ ነን!!

አንድ የዐድማ ጥሪና ጥቂት ማሳሰቢያዎች አሉኝ፡፡

• የሁላችን ሊሆን የሚገባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልክ እንደወያኔዎች ጊዜ ሁሉ በጎሠኝነት ባህር ተዘፍቆ ከአወቃቀሩና ከቅጥር አፈጻጸሙ ጀምሮ እየሠራው ያለውን የዘረኝነት ዕኩይ ድርጊት በአግራሞት እየተከታተልን ነው፡፡ በእግረ መንገድም ዐይን አውጣነትና ይሉኝታ-ቢስነት ወይም ሀፍረተ-ቢስነት በነገድ የማይከለሉ የሰው ልጆች የወል እርጉም ሀብቶች መሆናቸውን እየተገነዘብን ነው፡፡ ከወያኔ በላይ ይሉኝታቢስ የለም ብለን በድፍረት የተከራከርን እኔን መሰል ሰዎች በጊዜው ኦህዲዳዊ ተግባር ክፉኛ በሀፍረት ልንሸማቀቀቅና አቋማችንን ልናስተካክል ተገደናል፡፡ ከ58 የኢ. ን. ባንክ የሥራ ኃላፊዎች በጥቂት ወራት የሹመት አሰጣጥ ጊዜ ውስጥ 31ዱ ኦሮሞዎች ሆነው ከተገኙ አሠራሩ የልምድና ችሎታ ሳይሆን የዘረኝነት መሆኑ ሊካድ አይገባም፡፡ በሌሎች የመንግሥት የሥራ ዘርፎችም ሁኔታው ከዚህ ቢከፋ እንጂ እንደማይሻል እየሰማን ነው – በብዙ ቦታዎች በሚከናወኑ የውስጥና የውጭ ውድድሮች አማራና ሌሎች ዜጎች ውድድሩን ካለፉ ኦሮሞ እስኪገኝ መዝገቡ ይያዛል ወይም በዝውውርና በዕድገት ስም ከሌሎች የኦሮሞ ክልል በመጡ የጎሣው አባላት እንዲያዝ ይደረጋል – ያለ በቂ ችሎታና ልምድ እንዲሁም የትምህርት ደረጃ ( አለቃ ገ/ሃና በቤታቸው ሰልችቷቸው እጓደኛቸው ቤት የተሻለ ምግብ የሚያገኙ መስሏቸው ቢሄዱ ያቺው በቤታቸው የጠሏት ሽሮ ትሁን ጎመን በጓደኛቸውም ቤት ስትቀርብላቸው “በየት ዞረሽ ቀደምሽኝ” እንዳሉት የኛም እንደዚያው ሆኖኣል)፡፡ ይባስ ብለው እነዚሁ ዘረኛ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች እነሱ የማፈናቀል አበጋዞች ሆነው ለሚተውኑት አሳዛኝ ትያትር 36 ሚሊዮን ብር አካባቢ ለክልላቸው ያላንዳች ሀፍረት ሲመድቡ ለእውነተኞቹ የአማራ ተፈናቃዮች ግን 4 ሚሊዮን ብር ብቻ መድበው “እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው” የሚለውን ልጨኛ ብሂል እያስታወሱን ነው፡፡ ይህ ነገር አንድም በማንአለብኝት ላይ የተመሠረተ ድንቁርናና ንቀት ነው አለዚያም ዘመኑን ያልዋጀ የሞኞች ቁጭበሉ አጉል ሙከራ ነው፡፡ “በቅሎ ገመዷን በጠሰች…” ቢሉ….፡፡ ፉከራና ማስፈራሪያ እንዳይመስላችሁ – ዕጥፍ ድርብ ይከፍሏታል፡፡

ስለዚህ ይህ ሸውራራ የዘረኝነት አካሄድ እስኪስተካከል ጤነኛ ዜጎች ነን የምንል ሁሉ በዚህ ባንክ እንዳንጠቀም ግፈኞችና ዐረመኔዎች በሚመጠምጡት የኢትዮጵያችን ዕድለቢስ ጡቶች እማጸናችኋለሁ፡፡ በዚህ ባንክ የምንጠቀም ዜጎች ዛሬ ነገና ትንሽ ነው ብዙ ነው ሳንል ያለንን ገንዘብ በማውጣት በኢትዮጵያዊነታቸው በማይታሙ ባንኮች እናስገባ፤ በነሱም እንገልገል፡፡ ዘረኛ ባንኮችን በዚህ መልክ አደብ ማስገዛት ይቻላል፡፡ ይህ ትግል አንዱ የሰላማዊ ትግል ገጽታ ነውና አንቦዝን፡፡
የኢትየጵያ ንግድ ባንክ ዱሮውንም የሚገለገሉበት ኢትዮጵያውያን በተለይም አማሮች እንጂ ሌላውና በዘረኝነት መርዝ የተለከፈው ሀብታምና ተራ ዜጋ ዘሩን እያነፈነፈ ነው “የኔ ናቸው “ በሚላቸው ባንኮች ገንዘቡን ያስገባና ያወጣ የነበረው፡፡ ለምሣሌ አዋሽ ባንክ እያለለት ዘረኛ ኦሮሞ በሌላ ባንክ አይጠቀምም፡፡ ወጋገንና አንበሣ ባንኮች እያሉለት ዘረኛ ትግሬ በሌላ ባንክ አይጠቀምም፡፡ኅያዋን ሰዎች ብቻ ሳንሆን ባንኮችም በዘረኝነት የሚሰቃዩ ግዑዝ ነገሮች ናቸው፡፡ ኦህዲድ የቀማን ብቸኛ መጠቀሚያችንን ነው፡፡ እነሱ ዱሮውንም የማይጠቀሙበትን ባንክ ነው ያሳጡን፡፡ የግፍ ግፍ ነው፡፡ ስለዚህ ንጹሕ ኢትዮጵያውያን ይህን ባንክ መጠቀም ቢያቆሙ ንግድ ባንክ በቂጡ እንዘጭ እንደሚል ግልጽ ነው፡፡

• ለፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች የምለው አለኝ፡፡

ፌስቡክ ጥሩ ነው፡፡ ጥሩም አይደለም፡፡ በዚህ ማኅበራዊ ሚዲያ የሚባለውን ሁሉ እንደ እውነት ከተቀበልን እናብዳለን ወይም እንታመማለን፡፡ ለምሣሌ ከደቂቃዎች በፊት ከፍቼ ስመለከት “ኦሮሞና ትግሬ ወደው አይደለም አማራ ከብት ነው የሚሉት ከከብትም ከብት ነው፡፡ እንኩዋን አዲስ አበባ ተወለድኩ፡፡” የሚል አነበብኩ፡፡ “ከሰደበኝ ስድቤን አምጥቶ የነገረኝ” ለሚለው ወቀሳ እንኳን የማይበቃ እጅግ የወረደ “ስድብ” ስለሆነ ነው እንዳለ ያስቀመጥኩት፡፡ እናም እንዲህ ያለ አርቲ ቡርቲ የሚጽፉ “ሰዎች” ወያኔም ይመድባቸው፣ ኦነግና ኦህዲድም ድርጎ እየከፈሉ ያሰማሯቸው፣ በአእምሮ የማሰብ ችሎታ ማነስም ተገደው ከራሳቸው ያፍልቁት … በንቀት ስቀንባቸው መተው እንጂ ከነሱ ጋር መመላለስና መናደድ ዓላማቸውን እንደማሳካት ነው – ከነሱ ጋር መናቆር ሥራ ፈትነት እንጂ ገምቢ አይደለም፡፡ ማንም ይሁኑ ማን፣ ምድርም ይላካቸው ሰማይ – እነዚህን ዓይነት ወራዳ ሰዎች መከተል አውቆ ገደል እንደመግባት ነው፡፡ በሚባለው ሁሉ እየተወሰድን ወርቃማ ጊዜያችንን በከንቱ ማባከን የለብንም፡፡ ብዙ ባለጌና ዋልጌ በሞላባት ምድር ሁሉም ጻዲቅ እንዲሆን መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡
ይህን እውነት ደግሞ እንረዳ፡- በአማራ ስም ኦሮሞንና ትግሬን ከአማራ ለማጣላት፣ በትግሬ ስም ትግሬንና አማራን ከኦሮሞ ለማጣላት፣ በኦሮሞ ስም ኦሮሞንና አማራን ለማጣላት የዱሮ ተረቶችንና አባባሎችን ሳይቀር በመጥቀስ ሰይጣናዊ ዘር የሚዘሩና ዕልቂት ለማፈስ የሚቋምጡ የሳይበር ጦርነት ፊታውራሪዎች ሞልተዋል – አስፈላጊው ሥልጠና ተሰጥቷቸውና ወፋፍራም ደሞዝ ተቆርጦላቸው፡፡ ስለዚህ አማራም ሆነ ትግሬ፣ ኦሮሞም ሆነ ጉራጌ፣ ሶማሌም ሆነ ከምባታ ይህን ዓይነቱን የተንኮለኞችና የሸረኞች መቀስ ንቆ በመተው አንድነቱን ማጽናት ይገባዋል፡፡ የተባለውን ነገር ሁሉ እንደወረደ መቀበል ወደ ጥፋት ይወስደናል እንጂ የምንፈልገውን የጋራ ልማትና ሰላም አያመጣልንም – ጎሣዊ መበሻሸቅ ደግሞ በየትም ሀገር ያለና የነበረ ነውና ባለፈ የሞተ ታሪክ አንነታረክ፡፡

ለክፉዎች በር አንክፈት፡፡ አንዱ ነገድ ተበድሎና ተጠቅቶ ሌላው ሰላምና መረጋጋት አይኖረውም፡፡ የሰላም አለመኖር ደግሞ ሁላችንንም በእኩል ይጎዳልና በጠላቶቻችን መረብ እየገባን ከመተላለቅ መቆጠብ አለብን፡፡ የፌስ ቡክ የስድብና የዘለፋ ዘመቻቸውን የምናከሽፈው ንቀን በመተው እንጂ በመናደድና እርስ በርስ በመነቋቆር አይደለም – ይሄ እነሱን የልብ ልብ እየሰጠ ይበልጥ ያጠናክራቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ፣ የአማራና የትግሬ አክቲቪስቶች ልትጫወቱት የምትችሉት አወንታዊ ሚና ከፍተኛ ነውና እየተከታተላችሁ ወጥመዶችን በጣጥሱ፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ውኃ የማያነሣ አክሳሪ አካሄድ እናንተ ራሳችሁም ተጠበቁ፡፡ሁሉን ነገር ሁለቴ በማሰብ እናከናውን፡፡

በመጨረሻም ማለት የምፈልገው በሃሳብ የበላይነት እንጂ በዱላና በቡጢ አንመን፡፡ ለምሣሌ አንድ የፖለቲካ ቡድን ስብሰባ ቢጠራ ስብሰባው እንዳይካሄድ ሁከት መፍጠር ሳይሆን በስብሰባው ተገኝቶ ስህተቱን በመረጃና በማስረጃ አስደግፎ በመናገር ወይም ሌላ ስብሰባ በመጥራት ራቁቱን ማስቀረት ሲገባ ነገ ዕድሉን ብናገኝ የምናደርገውን ነገር ከአሁኑ ማሳየት ትልቅ የሀገር ሸክምና የትግልም እንቅፋት ነው፡፡ በዛቻና በማስፈራሪያ ለማስቆም መሞከር የያዝነው እውነት እንደሌለ ያሳብቃልና በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ ሃሳብ ከጠበንጃ ይበልጣል፡፡ ሃሳብን ወደ መፍራትና በሃሳብም ወደመሸናነፍ ደረጃ ካልወጣን፤ ወደ ኃይልና ጉልበት አሸናፊነት ከወረድን ታጥቦ ጭቃ ነው፡፡ በኃይልና በጉልበት አንድን ዓላማ ለማሳካት መሞከር የስንኩል ወይም የደካማ አስተሳሰብ መግለጫ እንጂ የምጡቅ አእምሮ ባለቤትነትን አያሳይም፡፡ በዚህ መልክ ከተጓዝን ቅኔው ቢጎድልበት ቀረርቶ ጨመረበት እንደተባለው የየጁ ደብተራ መሆናችን ነው፡፡ በራስ የሚተማመንና አመክንዮ ያለው ወገን በኃይልና በቡጢ አያምንም፡፡ ዱላን ለማስወገድ አእምሮ እንጂ ዱላ አይጠቅምም፡፡ መጽሐፉ “ብዔል ዘቡል በብዔል ዘቡል አይወጣም” እንዲል፡፡ በአስተሳሰብ እንደግ፤ እንመንደግ፡፡ በከንቱም አንጠላለፍ፡፡

በተጨማሪም በስሜት እየተነዳን የዘረኝነት ስድቦችን ከማስወንጨፍ እንቆጠብ፡፡ ስንናደድ አንደበታችንንና ብዕራችንን መቆጣጠር ያቅተናልና ያኔ ቢቻለን ዝም እንበል፡፡ መጠጥና ንዴት ተመሳሳይነት አላቸውና ከነዚህ የውስጥ ድብቅ ገመናን አውጭዎች እንጠበቅ፡፡ ራሳችንን በጤናማ አስተሳሰብ እንገንባ፡፡ መርዘኛውንና አብሮ የማያኗኑረውን አስተሳሰብና ፍልስፍና በአንዴም ባይቻለን ቀስ በቀስ ከሰውነታችን እያወጣን በዘመናዊ አስተሳሰብ እንተካ፡፡ መሰዳደብና መጎነታተል ቂምን እየፈጠረ፣ የቆዬ ጥላቻን እያመረቀዘ ለበለጠ የጋራ መጠፋፋት ይዳርገናል እንጂ አንድም ጠቀሜታ የለውም፡፡ እንደኛ በነገርና በዱላ አቅን ሳይፈታተሸ ወደ ከፍተኛው የዓለማችን ሥልጣኔ ያመራ አንድም ሀገር እንደሌለ ደግሞ እንረዳ፡፡ የኛ ከሌሎቹ የሚለየው ባለንበት እየረገጥን ብቻ ሣይሆን ቁልቁል እየሸመጠጥን ሌላው ዓለም ካለፈው ብዙ ዘመናት ያስቆጠሩትን በምግብ እንኳን ራስን ወዳለመቻል እንስሳዊ ደረጃ መድረሳችን ነው፡፡ እናሳዝናለን፡፡ ወደፊት መራመድ ባይቻለን የነበረንን አንጻራዊ የአብሮነት ዘመን መልሰን በፍቅርና በመተሳሰብ ለመኖር እንጣር፡፡ በጎደለ ሙሉበት፤ ባጠፋሁ ይቅርታችሁን አትንፈጉኝ፡፡

 

Email: yinegal3@gmail.com

Filed in: Amharic