>

የአብይ አህመድን ንግግር ልብ ብሎ ላዳመጠው ብዙ ነገር ይነግራል!!! (መስከረም አበራ)

የአብይ አህመድን ንግግር ልብ ብሎ ላዳመጠው ብዙ ነገር ይነግራል!!!
መስከረም አበራ 
ከንግግራቸው መረዳት የሚቻለው ትችት እና ጥያቄን በገንቢነት ለመረዳት የሚቸገሩ ሰው መሆናቸውን ነው፡፡መንግስታቸውም የሚፀናውም በሙገሳ ብቻ ሳይመስላቸውም አልቀረም፡፡ዕለት ዕለት ሳናቋርጥ እንድናሞሳቸው ከመፈጋቸው የተነሳ የሚያስሞግሳቸውን ስራ በሰሩባቸው ወራት ብዙ እንደተመሰገኑም ረስተውታል፤ በምስጋና ቢስነት ሊወቅሱንም ሞክሯቸዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ እርሳቸውን እና ቡድናቸውን በተመለከተ ከጠዋቱ የወረደላቸው መወድስ የምስጋና ግሽበት አምጥቶ ህዝብ እንዳይፈሩ እንዳደረጋቸው የሚገምትም አይጠፋም፡፡በዚህ እሳቤ እና በአብይ አልተመሰገንኩም የሚል ምሬት መሃል ያለውን ልዩነት ያመጣው የአብይ መንግስት ህዝብን የግንዛቤ ደረጃ ዝቅ አድርጎ ማየት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አብይ ወደ ታላቁ የኢትዮያዊነት ሰገነት ተተኮስኩ ያለበት የ”simulation” ፕሮግራም በተግባር ሲቀየር ቢያይም ባያይም ዝም ብሎ ሊደሰት አይችልም፡፡ምስጋና እንዲቀጥል ከተፈለገ ቃልን እና ተግባርን ማመሳሰል ነው፡፡ማመሳሰል ካልተቻለ ደግሞ ያመኑበትን እየሰሩ እንደ መለስ ዜናዊ የሚመጣውን ለመቀበል ፈርጠም ብሎ መጠበቅ ነው፡፡እንጅ ምን ቆርጧችሁ ቃል እና ተግባር ምዘና ውስጥ ገባችሁ ማለት አይቻልም- አነሰም አደገ ሰው የሚመዝንበት የየራሱ ልቦና አለውና!
በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ያወረዱት ምሬት፣እርግማን እና ማጣጣልም ልቦናችሁ ምን ሲል አገናዘበ አይነት ኢህአዴጋዊ ልክፍት እንጅ ማህበራዊ ሚዲያው እሳቸው በሚሉት መጠን ሃገር የሚያፈርስ የሃሰት ወሬ አናፍሶ አይደለም፡፡ የማህበራዊ ሚዲያውን የሚወቅሱት ለምን በር ዘግቼ ምስኪኖችን አላስራብኩም፣ለምን አዲስ አበባ ላይ የሚፈልገውን ነቅየ የምፈልገውን ስተክል ታወቀብኝ ተብሎ ካልሆነ ሌላ ምክንያት የለም!
በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ወደ ጦርነት እንገባለን ያሉበት መንገድ የዘር ፖለቲካ መስህብ ሃያል ብርታቱን ያየሁበት መንገድ ነው፡፡ትዝብት ላይም የሚጥል ነው፡፡ በአንድ ወቅት በወሬ መሃል “Dont trust politicians” ያለ አንድ ዩጋንዳዊ ሰው እንዳስታውስም አድርጎኛል፡፡በጣም የገረመኝ ንግግራቸው ግን “ሁሉም ብሄርተኛ ነው; የዜግነት ፖለቲከኛ ነኝ ቢልም” ሲሉ ጀምረው ይህን ያጠናክርልኛል ብለው ያመጡት ነገር ደግሞ “ማን የዜግነት ፖለቲከኛ ነው ትግራይ ሄዶ ለምን እንዳኮረፉ የጠየቀው?” ያሉት ነገር ነው፡፡የዜግነት ፖለቲከኛ ሚዛኑ የእርሳቸውን የድሮ ጌቶች ሄዶ በማባበል የሆነው እንዴት እንደሆነ ግራ ነው፡፡
ደግሞስ ትግራይ ያሉ ሰዎች የዘረፉት አስደንብሯቸው፤ያፈሰሱት ደም አብርሯቸው ነው ወይስ ተበድለው አኩርፈው እዛ የተቀመጡት? የተዘረፍነው አንሶን ደግሞ ሌባ እና ነፍሰገዳይ አባብሉ የምንባለው በምን ፍርድ ነው? እነዛ ሰዎች ትግራይ የከተሙት አኩረርፈው ከሆነ ለምን ራሳቸው ተጉዘው አምጥተው እንደለመዱት አያብሏቸውም-ሃያ ሰባት አመት ሲያደገድግ ለኖረ ማባበሉ ቀላል ስራ ነው፡፡ትግራይ ያሉ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው ማባበል ከሆነ አብይ ራሳቸው የፍርድቤት መጥሪያ የቆረጡባቸው ለምንድን ነው?
የኢህአዴግ ካድሬዎች ራሳቸው አጥንት የሚባል ነገር የሌላቸው ልምጥምጦች ስለሆኑ ሌላውም ሰው እንደነሱው እንዲልመጠመጥ እና እንዲያስመስል ይፈልጋሉ፡፡ከኢህአዴግ የተላቀቀች ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች፤ ግን በየት በኩል?
Filed in: Amharic