>
5:13 pm - Tuesday April 20, 2179

አብይነትዎ!!! (ደረጄ ደስታ)

አብይነትዎ!!!
ደረጄ ደስታ
አብይ ሆይ! ባነጋገረው የሰሞኑ ንግግርዎ፣ አስረውና ገድለው ያውቁ ይመስል፣ ማሰርና መግደል እንደሰለችዎት መናገርዎን ሰማሁ። እርስዎ ባይገድሉ እኛ እንገድልልዎታለን እሚሉትንስ ምን አሏቸው? እኛ ስንሞት ስንገደል ኖረናል፣ አሁን ደግሞ በተራችን ስለ በደል በቀላችን መግደል እንፈልጋለን፣ እሚሉትንስ ምን ብለዋቸዋል? እንኳን የሰለቻቸው፣ ገና ያልጀመሩ ወደ ጦርሜዳቸው እየዘመሩ እሚተሙትን ገዳዮችንስ እንዴት አይዋቸው? ከበትር እስከ ጠመንጃ ይዘው ስለ ወጡትስ ብሔርተኞች ምን ብለዋል? ተደራጅተው እሚያስፈራሩትን ትተው፣ ገና ያልተደራጁትንስ ስለምን ፈሯቸው?
እኔ ስለ ኢትዮጵያዊነትዎ የመጠርጠርና ያለመጠርጠር ከንቱ ጨዋታ ውስጥ አልገባም። ኢትዮጵያዊነት የግድ እሚበላለጥ ከሆነ ከኔ ቢበልጡ እንጂ ያነሱ ኢትዮጵያዊ ነዎት የሚል እምነት የለኝም። እንኳን አገሬን ከፍ አድርገው እሚጠሩልኝን እርስዎን ቀርቶ አገሬን ከዚህ ችግር የጣሉብኝና ያጣጣሉብኝን አቶ መለስ ዜናዊን እንኳ በኢትዮጵያዊነታቸው አልጠረጥራቸውም። ለነገሩ ኢትዮጵያዊነት “ነኝ” ብለው በኩራት እሚናገሩት እንጂ “ነህ አይደለህም” እየተባለ እሚሰጥ እሚነሳ ነገር አለመሆኑ ይገባኛል።
ኢትዮጵያዊነት ግን ብቻውን በቂ አይደለም። ድሮውንም የተቃውሞዬና የድጋፌ መሠረቱ ዜግነትዎ አይደለም። ከርስዎ እምፈልገውና እምጠብቀው፣ ቃል እንደገቡልኝ፣ ኢትዮጵያዊያንን በእኩል ዓይን ተመልከተው፣ አገራዊ ተቋምና መሠረት ገንብተው፣ ኢትዮጵያን በመልካም አስተዳደርዎ እንዲያሸጋግሩ ነው። ውግዘትና ጦርነትን ለያይተው እንዲሰፍሩ አንዱን ቆንጠጥ አንዱን ደፍጠጥ እንዲያደርጉ አይደለም። በዚያ ላይ ደግሞ መግደልን እሚያቆሙት ስለሰለቸዎ ሳይሆን ስለማያስፈልግና ስለማይገባ እንደሆነ ያዉቁልኛል ብዬ ነው። ቀድሞ ነገር “መግደል” እሚባል ነገር፣ ጦርነት እሚባል አነጋገር ከአፍዎ ምን ሲያደርግ ገባ? ይገባኛል ተበሳጭተውም ተስፋም ቆርጠው ሊሆን ይችላል። ምነው ገና ዓመት ሳይሞላዎ፣ እንዲህ መሆንዎ ስለምን ነው? ለመሆኑ “አንተ ትፈራርሳታለህ እንጂ ኢትዮጵያ አትፈራርሳትም” ብለው ያሉት ማንን ወይም እነማንን ነበር? ዝርዝር ኪስ ቢቀድም እንዲህ ያለው ዝርዝር ግን አገር እንጂ ኪስ አይቀድምና ዘርዝረው ቢነግሩን ጥሩ ነበር። ግን እነሱ እነሱን ሲሆን እንደ ክርስቶስ በምሳሌ ይናገራሉ። ኢትዮጵያ አትፍረስም ብሎ የደግፈዎትን ወገን ግን የጨከኑበት መሰሉ። ወይም አነጋገርዎ እንደዚያ አስመስልዎቦታል።
ሌላውና ዋናው ነገር ደግሞ የዘመኑ ፖለቲካ የተናገሩትን ብቻ ሳይሆን ሳይናገሩ ያስቀሩትንም እሚሰማ ስለሆነ መናገር ብቻ ሳይሆን አለመናገርም የሚያስቆጣም የሚያስቀጣም መሆኑን ቢያስተውሉ ደህና ይመስለኛል። ግድ የልዎትም ግልጽ ያድርጉት አይስጉ። እርስዎ አልናገር አሉ እርስዎ ከትዝብት ወደቁ፣ ለተቃዋሚዎችዎም ተመቹ እንጂ ሳናውቀው ከኛ የተሰወረ ምግባር የለም። በዚያ ላይ ደግሞ ብናውቀው እርስዎ አንድ ነገር ይሆኑ እንደሁ እንጂ እኛ ምንም አንሆንም። እንተዋወቃለን። ሁሉም ገመናችን ሁሉም ልጃችን ሁሉም ወንድማችን ነው። አይዝዎት ስጋት አይግባዎት፣ በዘንድሮ ፖለቲካ ብዙዎቻችን አዲስ አበባም ነቀምትም መቀሌም አዋሳም ሆነ ባህርዳር ላይ ተያይዘን እየዘቀጥን ነውና አይስጉ። ቆጥሬ ባልደርስበትም አብዛኛው ሰው ግራ የገባው፣ ሆድ የባሰው፣ የፈራ፣ የተቆጣ፣ የተቀየመ፣ ጥላቻና በቀልንም የተቀመመ ይመስለኛል። ለዚህ መፍትሔው እርስዎ እንደተናገሩት ኤርትራን እሚያህል ባላንጣ መንግሥት ወደ እርቅ ማዕድ እንዳመጡት ሁሉ ሌላውንም እንዲሁ ማድረግ ይመስለኛል። እስክንድርንም ሆነ የባልደራስን ወጣቶች ጸልየውበትም ሆነ ተኝተውበት አነጋግረው ቢያደምጧቸው፣ የታወጀብዎትን የመልስ ጦርነት የጠራውን የርስዎን ጦርነት እስከመናገር ባልሄዱ ነበር። ቢያንስ ቢያንስ አቅርቦና አቀራርቦ የማነጋገር ሙከራዎን በዚህም በኩል ብንሰማ ደህና ነበር። ይህን ስል ነገሩና አገሩ ውስብስብ አለመሆኑን ዘንግቼ በማየት አይደለም። በፍጹም። ግን ከጦርነትም ሆነ ከእስርና ዛቻ ይህኛው መንገድ ይሻላል ብዬ ነው።
 “ደሀ ተበድሎ ማሩኝ ይላል ቶሎ!” 
ግን ደግሞ ልብ ያድርጉ፣ እችላለሁ፣ ይህን ችግር ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ እፈታዋለሁ! ብለው የገቡበት እርስዎ እንጂ አገር አልመረጥዎትም። በዚያ ላይ ይቅርታውንም ማሰሩንም መፍታቱንም መግደሉንም መሰልቸቱንም ያወሩት እርስዎ ነዎት። አጥብቄ አደራ እምልዎት ግን አቅም የላቸውም ደካማ ናቸው እያሉ እሚያጣጥሉዎትን አይስሟቸው። አቅም በጠመንጃ ብቻ አይገለጽም። የርስዎ ተልዕኮ፣ ካሁን በኋላ በርስዎ ቦታ እሚቀመጥ ሰው የተለጠጠና ያልተገደበ አቅም እንዳይኖረው ማድረግ ነው።  እኔ በበኩሌ መንግሥት የማስተዳደር እንጂ የማስገበር አቅም እንዲኖረው አልመኝም። አቅምና ሥልጣን ማበጀት ያለበት ህዝቡ ነው። ትልቁና ተፈላጊው አቅም ህዝብን የሥልጣን ባለቤት ማድረግ መቻል ነው። ከዚያ ውጭ ያለው አቅም ማንም እሚታደለው ነው። እንኳን የአገሬ ጠቅላይ ምኒስትር፣ የቀበሌም ሆነ የጎጥ ሹም አቅም ኖሮት በየመንደርና በየከተማው ሲያውክና ሲያግድ እያየን ነው። እኔ እንደ ተቃዋሚዎ ሳይሆን እንደ አንድ ጽኑ ደጋፊዎ ይህን አሰተያየት ጽፌያለሁ። ስለዚህ አብይነትዎ እርስዎ እንደተቆጡት እኔም ተቆጥቻለሁና እላፊ ተናገሬ እንደሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ። አብዝቼውም ከሆነ “ደሀ ተበድሎ ማሩኝ ይላል ቶሎ” እሚለውን አነጋገር ብቻ ለመናገር ይፈቀድልኝ! የኔ ነው ያልኩትን የገዛ ጠቅላይ ምኒስትሬን በገዛ ጠቅላይ ምኒስትሬ ስነጠቅ ተያይዞ እሚመጣው ጣጣና ፈንጣጣ ታይቶኝ ነው። ወይ መከራዬ! እከተለው መሪ ፍለጋ ደግሞ እንደገና ሀ ብዬ ገበያ ልወጣ ነው ማለት ነው።  እንደ አዝማሪ ቤት ግጥም በየጊዜውና በየሜዳው “ተቀበል!” እምባለው መሪ ግን እየበዛ ሰልችቶኛል። ከዚህ በላይ በደል ምን አለ?
Filed in: Amharic