>

የ”ኬኛ” ፖለቲካ እንዴት ያሰልፋል? (መስከረም አበራ)

የ”ኬኛ” ፖለቲካ እንዴት ያሰልፋል?

መስከረም አበራ

 

ኦህዴድ ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት የሚያደርጋቸው ድርጊቶች “ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው” ያስባለው የስልጣን ጥም አላማው የኦሮሞ የበላይነትን ማስፈን እንደሆነ የሚያስረዱ ናቸው፡፡የኦሮሞ የበላይነት ፖለቲካ ደግሞ ሊያሳካቸው ከሚፈልጋቸው ዋና ነገሮች አንዱ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ግዛት እና የጨፌ ኦሮሚያ ግዛት ማድረግ ነው፡፡ በህገ-መንግስቱ የኦሮሚያ ግዛት አካልም ሆነ የጨፌ ኦሮሚያ ተዳዳሪ ያልሆነችውን አዲስ አበባን የኦሮሚያ ግዛት የማድረጉ የኦነግ/ኦዴፓ ህልም የሚታለመው ህገ-መንግስቱ አንድም ዓረፍ-ተነገሩ እንዳይነካ በሜንጫ በሚያስፈራሩ ወገኖች መሆኑ ነገሩን ግራ ያደርገዋል፡፡

የህገ-መንግስቱ አንድም መስመር ሳይነካ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ግዛት፣ የጨፌ ኦሮሚያ ተገዥ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ ኦዴፓ/ኦህዴድ አስቻይ አድርጎ የያዘው መንገድ የፌደራል ስልጣን የመጨበጡን መልካም እድል፣ የቆየውን የተበድየ ተረክ ፣የኢህአዴግን የፓርቲ አወቃቀር እና አሰራር (የአጋር/አባል ፓርቲ ነገር) ሊሆን ይችላል፡፡ ህወሃት ሊወድቅ ሲንገዳገድ ኦህዴድን አባይ ማዶ ድረስ ያበረረው የስልጣን አምሮት ምንጩ ስልጣን መያዝ የልብን ለመስራት ቁልፍ ነገር እንደሆነ በአቶ መለስ ህወሃት ስለተማረ ሳይሆን አልቀረም፡፡

አቶ መለስ ስልጣን ላይ መቀመጣቸው በዘረፋ ሳይቀር የወገንን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዳስቻላቸው ኦህዴድ በደንብ ተገንዝቧል፡፡ ስለዚህ አይገቡ ገብቶ፣ አያወሩ አውርቶ፣ የማይከበር ቃል ገብቶ ስልጣን ላይ ተሰየመ፡፡ ከዛ በኋላ ኦነግ ሲያምረው የቀረውን ነገር ሁሉ በአንድ ጀምበር ለማከወን በከፍተኛ መራወጥ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ነገር ይሰምራል ወይ? የዛሬዋ ኢትዮጵያም ሆነች የዛሬው ኢህአዴግ አቶ መለስ እንደነበሩባቸው ዘመናት ያሉ ናቸው ወይ? የሚለውን ነገር ኦህዴድ በቅጡ የመረመረ አልመሰለኝም፡፡ የሆነ ሆኖ ኦዴፓ/ኦህዴድ የኬኛ ፖለቲካውን ለማሳካት ሲንቀሳቀስ የሚያግዙትም ሆኑ የሚያደናቅፉት እውነታዎች አይጠፉም፡፡ አነዚህን እውነታዎች መመርመሩ አስፈላጊ ነውና ለለኬኛ ፖለቲካ አስቻይ መሰረቶችን በማየቱ እንጀምር፡፡

የተበድየ ተረክ

በሃገራችን የተንሰራፋው የዘውግ ፖለቲካ የትግሉ መነሻ በደልን መተረክ ሲሆን መዳረሻው ደግሞ አይኑ የወደደውን ሁሉ “የእኔ ነው” የማለት አካሄድ ነው፡፡አይን የወደደውን የራስ ለማድረግ ደግሞ የተበድየ ፖለቲካን መተረክ ዋነኛው የስኬት መንገድ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ እያጋነኑም እየፈጠሩም በደልን ማውራት ሁለት ጥቅም አለው፡፡ አንደኛ የዘውግ መሰሎችን በቁጭት ለማነሳሳት ይረዳል፡፡ በዘውጉ ምክንያት ብቻ እንደተጨቆነ የሚተርክ የበደል ተረክ የተጋተ ወጣት ቀረቶ ማንኛውም ሰው ግራቀኝ ሳያይ በቀላሉ ወደመሩት ይሄዳል፡፡ ሁለተኛው ጥቅም በበዳይነት የሚከሰሰው አካል አንገቱን እንዲደፋ እና ነገሮች ሁሉ ተበዳይ ነን ባዮች እንደፈለጉ እንዲሆን ይረዳል፡፡

በእኛ ሃገር ሁኔታ የተበድየ ፖለቲካን በማቀንቀን የኦሮሞ እና የትግሬ ልሂቃንን የሚወዳደር የለም፡፡እነዚህ ልሂቃን በደለን የሚሉት ደግሞ የአማራ ብሄርን ነው፡፡ ይህ ምስስሎሽ የትግሬን እና የኦሮሞ ልሂቃንን ከልብ የሚያስተሳስር እውነተኛ እምነታቸው ነው፡፡ የኦሮሞ ልሂቃን የራባቸውን ስልጣን ለማግኘት በለማ ቡድን በኩል ከአማራው ብአዴን ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ብቻ ይህን ተረክ ቀየር አድርገውት የነበረ ቢሆንም ነገሩ ከልብ እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡አማራን በዳይ አድርጎ የሚያቀርቡ የሁለቱ ብሄሮች ልሂቃን አማራ ወደ ስልጣን እንዳይመጣ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ይጠብቃሉ፡፡ አማራው ተጠናክሮ ወደ ስልጣን የመጣ ከመሰላቸው የተጣሉ የሚመስሉት የትግሬ እና የኦሮሞ ልሂቃን ተመልሰው ግንባር ፈጠረው አማራውን ወደ ከረመበት ድብታ ለመክተት እንደሚተባበሩ ጥርጥር የሌለው ነገር ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የአማራን ጭራቅነት ሲሰብኳቸው የኖሩትን የሌሎችን ብሄረሰቦች ካድሬዎች በተከታይነት መጥራታቸው የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡

ህወሃት ሲመራው በኖረው የሃያ ሰባት አመት አስተዳደር አማራው አንገቱን ደፍቶ የኖረው ሲተረክ በኖረው የተበድየ ተረክ ነው፡፡ ይህን ተረክ የበአዴን አመራሮችም ተቀብለውት ኖረዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ አማራው ጊዜው ያለፈበት በዳይ ተደርጎ ይቆጠር ስለነበረ የብአዴን መኳንንትም ሆኑ ተራው አማራ በበዳይነት ሃፍረት ተሸማቀው ኖረዋል፡፡ ይህ ተረክ አማራውን ወክለናል የሚሉት የብአዴን ባለስልጣናት የህዝባቸውን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሙግት አንስተው እንዳይከራከሩ ከልክሏል፡፡

በሃሰት የበዳይነት ተረክ ጨቋኝ ተደርጎ ፕሮፖጋንዳ ሲደለቅበት የኖረው የአማራ ህዝብን በህይወት የመኖር መብትን ጨምሮ ሌሎች መብትን የማስከበር ጥያቄ ሲያነሳ ድሮ በለመደው ጨቋኝነት፣ ጨፍላቂነት፣ አሃዳዊነት ለመግዛት ፈልጎ የሚንቀሳቀስ እንጅ የእውነት ተቸግሮ መብቱን/ህልውናውን ለማስከበር ያነሳው ጥያቄ ተደርጎ አይወሰድም፡፡ ይህ ነገር አሁንም እንዳልቀረ ሰሞኑን ኦዴፓ/ኦህዴድ የአዲስ አበባ ባለቤትነቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ “ድሮ በለመዱት አካሄድ ….” በሚለው ሃረግ ላይ በግልፅ ይታያል፡፡

ይህ መግለጫ የተፃፈው አዴፓ/ብአዴን ትቂት ቀናት ቀደም ብሎ አዲስ አበባን አስመልክቶ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች ሲል ላወጣው መግለጫ መልስ እንደሆነ ከመንፈሱ መረዳት ይቻላል፡፡ ሁለቱም ፓርተዎች ያወጡት መግለጫ በፓርቲዎቹ መሃከል ያለው መደማመጥ ነፋስ እየገባው እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ እነዚህ ፓርቲዎች ህወሃትን ለመጣል ዳርዳር ሲሉ ለሁሉም ዜጋ የምትበቃ፣ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደቆረጡ ሲቀላምዱ የነበረው ቅጥፈት እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ ለቃኪዳኑ መፍረስ ሰበቡ ደግሞ ገበያ እንደወጣ ህፃን ሁሉን ለእኔ የሚለው ኦዴፓ/ኦህዴድ ነው፡፡

በኦነግ አስተምሮ ተፀንሶ ያደገው ኦዴፓ ስለኢትዮጵያ ሃገር ሆኖ መቆም እና በዲሞክራሲ መራመድ ግድ ይለኛል ሲል የባጀው ክፉኛ የተጠማውን ስልጣን በእጁ አድርጎ በአቶ መለስ በክርን ሲደሰቅ የኖረውን ገደብ አልባ ኦነጋዊ አምሮቱን ለማርካት ነበር፡፡ ይህን በወቅቱ መጠርጠሩ አስቸጋሪ ስላልነበረ ብዙዎች በዚህ ዙሪያ ጥንቃቄ እንዲደረግ ያስጠነቅቁ ነበር፡፡ሆኖም የለማ ቡድን “ጤፍ የሚቆላ” ምላስ አዋቂ፣ ጠርጣራውን ሁሉ አደንዝዞት ከረመ፡፡ ይህ አፈ ቂቤ ቡድን በመረጃ ዘመን ህዝቡን በምላሱ አደንዝዞ በሆዱ የያዘውን ጬቤ አውጥቶ የፈለገውን ማድረግ እንደሚችል ማሰቡ ትልቁ ሞኝነቱ ነው፡፡ ሆኖም የለማ ቡድን ይህን ያሳሰበው ሌሎችን ጅል አድርጎ የማሰቡ ኢህአዴጋዊ ዝንባሌ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ ይህን ለማድረግ ያስችለኛል ብሎ እንዲያስብ ያደረገው እና ያስተማመነው አንደኛው ምክንያት የበኦነግ እና ህወሃት ተደርሶ በሁሉም የዘውግ ፖለቲከኛ ሲቀነቀን የኖረው የተበድየ ተረክ ነው፡፡

የተበድየው ተረክ አማራ ያልሆነውን የኢህአዴግ ካድሬ አማራውን ሊፈራ እንደሚገባው ጭራቅ እንዲያይ አድርጎታል፡፡ ዛሬ ግንባር ፈጥረው ሃገር እንምራ ሊሉ የሞከራቸው ብአዴን እና ኦህዴድም በአንድ ፓርቲ ጥላ ስር ነን እያሉም ለዘመናት የጎሪጥ ሲተያዩ የኖሩ አንደሆኑ በውስጣቸው የኖሩ ሰዎች የሚናገሩት ነው፡፡ የኢህአዴግ ፓርቲዎች አማራውን እንዲጠሉ በመለስ ዜናዊ ሲጋቱ የኖሩት የጥላቻ መጠጥ በአማራው ላይ ብቻ አይወሰንም፡፡ ተረኩ የኢትዮጵያን አመሰራረት ጭምር ከፈጠራው የአማራ ጨቋኘነት ጋር የሚፈተል ነው፡፡ ስለሆነ እነዚህ ካድሬዎች የአማራ ጥላቻ ኢትዮጵያን ጭምር ወደ ማፍረስ ጥፋት ለመንጎድ እንዳያመነቱ አድርጓቸዋል፡፡ ህወሃት ከስልጣን ሲነሳ የአዴፓ/ብአዴን ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ ስልጣን ለመምጣት የአቶ ለማን ያህል ጉብ ቂጥ ያላሉት አማራው ወደ ስልጣን ከመጣ ቀሪው የኢህአዴግ ካድሬ ሀገር እስከማፍረስ የሚደርስ መሆኑን ከኖሩበት ሃቅ ስለተረዱ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ኦህዴድ ወደስልጣን መጥቶ ሃገር ብትተርፍ የተሻለ እንደሆነ ብአዴን ራቅ አድርጎ በማሰቡ የሆነው ሆነ፡፡

ነባሩ የኢህአዴግ የሃይል አሰላለፍ

እንደዚህ ባለ መንገድ በብዙ እልልታ ወደስልጣን የመጣው ኦዴፓ/ኦህዴድ በተግባር ሲፈተሽ የሆነው ሌላ ነው፡፡ ኦዴፓ/ኦህዴድ ስላወራው ቃል ግድ ሳይለው ካወራው በተቃራኒ የኦሮሙማን አላማ ይዞ የነጎደበት ሁለተኛው ምክንያት በኢህአዴግ ውስጥ በአቶ መለስ የተበጃጀው የፖለቲካ አሰላለፍ ስልጣን ለያዘ አካል የፈለገውን ለማድረግ የሚመች መሆኑን ስለሚረዳ ነው፡፡ ይህ የሃይል አሰላለፍ በሃገሪቱ ያሉ ዜጎችን እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ “አባል” እና “አጋር” በሚል፣ መስፈሪያው በማይታወቅ አካሄድ የአንድ ሃገር ሰዎችን አንደኛ እና ሁለተኛ ዜጋ የሚደርግ አካሄድ ነው፡፡ አባል የተባሉት አራቱ ፓርቲዎች በህወሃት አዛዥነት የሃገሪቱን ፖለቲካ ሲያሾሩ ሌሎቹ አጋር ተብለው ከዋና የስልጣን ቦታዎችም ሆነ የሃገራቸውን ህልውና ከሚወስኑ ፖለቲካዊ ምክክሮች ተገልለው ኖረዋል፡፡

በእኛ ሃገር ፓርቲ መንግስትን ይመራል፡፡ፓርቲ ደግሞ በአራት አባል ፓርቲ ካድሬዎች ስራ አስፈፃሚ ውሳኔ ይዘወራል፡፡ የአራቱ ፓርቲ ካድሬዎች ደግሞ ለወትሮው በአቶ መለስ ቀጭን ትዕዛዝ ያድራሉ፡፡በዚህ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ አጋር ፓርቲ ተብለው በየክልላቸው የኢህአዴግን ፍላጎት የሚያስፈፅሙ ሶማሌን፣ የጋምቤላን፣ የቤኒሻንልን፣ የሃራሪን፣ አፋርን የሚመሩ ፓርቲዎች አይሳተፉም፡፡ይህን ድልድል ያመጣው “ብሄረሰቦችን ከአማራ እስርቤት ፈትቼ ለቀቅኩ” የሚለው የአቶ መለስ ህወሃት መራሽ አስተዳደር ነው፡፡ ይህ አካሄድ ለውጥ መጣ በተባለ ማግስት የሚቀየር ነገር መስሎኝ ነበር፤ ተቀጥሎበታል፡፡

የለውጥ መሪነኝ ባዩ ብልጣብልጥነት እየሞከራቸው ያለው ጠ/ሚ አብይ ያደረጉት ነገር ቢኖር በቅርቡ በተደረገ አንድ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ የአጋር ፓርቲዎች ሊቀመናብርት ብቻ እንዲገኙ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ትርጉሙ ምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ የተገኙት ሊቀመናብርትም በገዛ ሃገራቸው ጉዳይ ላይ ታዛቢ ብቻ ሆነው እንዲቀመጡ ለብቻቸው ወደተጠሩበት ስብሰባ ምን ሊሆኑ እንደሄዱ አይገባኝም፡፡ እስከዛሬ ድረስ ሁለተኝነታቸውን ተቀብለው፣ በሃገራቸው አንኳር የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ሳይሳተፉ ሰው በወሰነላቸው የኖሩ የአጋር ድርጅቶች ካድሬዎችም ሁሌ የሚደንቁኝ ጉዶች ናቸው፡፡

ጠ/ሚ አብይ እነዚህን የአጋር ፓርቲዎች ሊቀመናብርተ ብቻ ወደ ስራ አስፈፃሚ የጋበዙበት ምክንያት “ይህንንም ያደረግኩላችሁ እኔ ነኝ” የሚል ውለታ ለማስቆጠር ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃው ጠ/ሚው በቅርቡ ወደ አፋር እና ሶማሌ ክልል ባመሩበት ወቅት ስንት ሚኒስትር ከአፋር እና ሱማሌ እንደሾሙ እየቆጠሩ “ተመስገን በሉ” አይነት ነገር ማውራታቸው ነው፡፡ ይህስ ለምን አስገለገ ከተባለ አጭሩ መልስ በውለታ ተይዘው ለኦዴፓ/ኦነግ የኬኛ ፖለቲካ ስምረት የሚሰሩ አዳዲስ ሰራዊቶች ለመሰብሰብ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በኬኛ ፖለቲካ ሳቢያ ኦዴፓ/ኦህዴድ ከአዴፓ/ብአዴን ጋር የገባበት ፍጥጫ የሚካረር ከሆነ እነዚህን አጋር ድርጅቶች ለኦሮሙማ ጥቅም በኦዴፓ/ኦህዴድ ሰልፍ ለማሰለፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ወደ አጋር ድርጅቶች መሄድ ለምን አስፈለገ የሚለውን ተገቢ ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ አጋር ድርጅቶች ያስፈለጉበት ምክንያት ለወትሮው ግንባር ፈጥረው አጋር ድርጅቶችን እንምራ ሲሉ የኖሩት አራቱ አባል ድርጅቶች ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ የተወናከረ፣ የድሮው አዛዥ ታዛዥ ድራማ የጠፋበት እና ግንባሩ ራሱ አለወይ በሚያስብል ሁኔታ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡

ኢህአዴግ የወትሮው ነው?

የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ህወሃት፣ ደኢህዴን፣ አዴፓ እና ኦዴፓ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ህወሃት በስልጣን መነጠቁ ሳቢያ ያኮረፈ እና ከሚወደው ስልጣኑ የመገፍተሩ ዋነኛ ምክንያት ወትሮም የማይወደው የአማራ ልሂቃን መራሹ ብአዴን እንደሆነ ያስባል፡፡ በዚህ ምክንያት ከአዴፓ/ኦዴፓ ጋር ለተቃረነ ሁሉ አላማውን ሳይጠይቅ ጭምር መወገኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ አሁን ከአዴፓ ጋር ሽርክናውን ጨርሶ ወደ መሸካከር የሄደው ኦዴፓ/ኦህዴድ ያየውን ሁሉ የእኔ ለሚለው የልጅ አካሄዱ ጭምር ከህወሃት ጊዜያዊም ቢሆን ድጋፍ ማግኘቱ አይቀርም፡፡ ሆኖም ከህወሃት ጋር አጋርነት መፍጠር በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ በህወሃት ዓይን የመታየት አደገኛ ውጤት ይዞ የሚመጣ መሆኑ ለኦዴፓ አይጠፋውም፡፡ በዚህ ላይ የበላይ ካልሆነ የኖረ ከማይመስለው ህወሃት ጋር የሚደረግ ህብረት መጨረሻው ለኦሮሙማ የሚበጅ ይሁን አይሁን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ከዚህ በፊት በኦሮሙማ ጉዳይ ላይ የነበረው የህወሃት እና የኦህዴድ ግንኙነት የሚያሳየው ነገሩ እንደማይበጅ ነው፡፡

በመቀጠል የሚመጣው የደኢህዴን ጉዳይ ነው፡፡ኦዴፓ ለሚያሳየው የኬኛ ፖለቲካ ደኢህዴን ሊመልሰው የሚችለውን መልስ መገመት አስቸጋሪ የሚያደርገው ደኢህዴን የሚመራው የደቡብ ክልል በአሁን ወቅት ያለበት ቀውስ ነው፡፡ ደኢህዴን የኦዴፓን የኬኛ ፖለቲካ ደግፎ አዲስ አበባን በጨፌ ኦሮሚያ ስር ለማድረግ ለሚያደርገው ሩጫ አጋርነቱን ካሳየ በክልሉ አዋሳ የእኔ ናት ለሚሉት የሲዳማ ፖለቲከኞች ተመሳሳዩን ማድረግ አለበት፡፡በተመሳሳይ አዲስ አበባ የእኔ ነች እያሉ መግለጫ የሚያግተለትሉት ባለጊዜ ነን ባዮቹ ኦዴፓዎች የሲዳማ ፖለቲከኞች የሚያነሱትን የአዋሳ ባለቤትነት ጥያቄ መግፋት አይችሉም፡፡ አዲስ አበባ የኦሮሞ ነች የሚለው ልክ ነው ብሎ መግለጫ የሚያወጣ አካል አዋሳም የሲዳማ ነች የሚለውን የሲዳማ ልሂቃ ጥያቄ የሚገፋበት አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ አይችልም፡፡ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች የሲዳማ ልሂቃንን የአዋሳ ባለቤትነት ጥያቄ አምርረው የሚደግፉት በዚሁ ተመሳሳይነት ሳቢያ ነው፡፡

አዋሳን የራሳቸው ለማድረግ አጥብቀው የሚሹት አቶ ሚሊዮን ማቲወስን እና አቶ ደሴ ዳልኬን የመሰሉ የሲዳማ ልሂቃ የአድራጊ ፈጠሪው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ስራ አስፈፃሚ አባላት ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደኢህዴንን በሊቀመንበርነት የሚመሩት ወ/ሮ ሙፈሪያት በጠ/ሚው ዘንድ ሞገስ ከማግኘታቸው የተነሳ የዶ/ር አብይን መንግስት 2/3ኛ ስልጣን እና ሃላፊነት የተሸከሙ ሴት ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት የኦዴፓ/ኦህዴድ የኬኛ ፖለቲካ ከወደ ደቡብ በሶስቱ ሰዎች ሊደገፍ ይችላል፡፡ ሌሎቹ የደኢህዴን ካድሬዎች በጉዳዩ ላይ ሊኖራቸው የሚችለው አቋም እምብዛም ወደ ኦዴፓ ያጋደለ ላይሆን ይችላል፡፡

ቀጥሎ የሚመጣው በኦዴፓ የኬኛ ፖለቲካ ላይ ጋሬጣ መሆኑን በግልፅ መግለጫ አቋሙን የገለፀው አዴፓ/ብአዴን ነው፡፡ አዴፓ/ብአዴን ከሌሎች አባልም ሆነ አጋር ፓርቲዎች በተለየ የአዲስ አበባን ጉዳይ አስመልክቶ መግለጫ ያወጣውም ሆነ የኦዴፓን የኬኛ ፖለቲካ በአንክሮ የሚከታተለው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ ዋነኛው ምክንያት ኦዴፓ መራሹ የለውጥ መንገድ ሲጀመር ከኦዴፓ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያዊን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የማድረጉን ሃላፊነት ወስዶ እንደሚሰራ ቃል መግባቱ ነው፡፡በዚህ ቃል ሳቢያ የህዝብ ተስፋ አብቦ ነበር፡፡ ይህን ያበበ ተስፋ ኦዴፓ የፈለገው ፈልጎ፣ የበለጠው በልጦበት ገደል ስለከተተው አዴፓም ተከትሎ የህዝብን ተስፋ ማጨለም የለበትም፡፡ ኦዴፓን እና አዴፓን ሁለት እግር አድርጎ የቆመው ኢትየጵያዊያን በእኩል የመኖር ተስፋ በኦዴፓ መንሸራተት ምክንያት አንድ እግሩ ተሰብሮ ያነክስ ይዟል፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት አዴፓ/ብአዴን ቃሉን ጠብቆ የህዝብን ተስፋ ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን የተሰበረውን አንድ እግር በበርካታ ጠንካራ እግሮች ተክቶ የኢትዮጵያንን ተስፋ የማደስ ታሪካዊ ሃላፊነት አለበት፡፡

ይህን ከባድ ሃላፊነት እንዳለበት ኦዴፓም እንደተረዳ አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያዊ እርስት እና የፌደራሉ መንግስት መዲና እንጅ የአንድ ወገን ንብረት እንዳልሆነች ከገለፀበት መግለጫው ያስታውቃል፡፡ ይህ አባባል ደግሞ ከህገ-መንግስቱ ድንጋጌም፣ ከአዲስ አበባ ህዝብፍላጎት ጋርም፣ ከኦህዴድ/አነግ በቀር ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ጋርም አዴፓን የሚያስማማው አቋም ነው፡፡የኬኛ ፖለቲካ በአሁኗ ቅፅበት እንኳ በጌዲኦ፣ ወለጋ፣ በለገጣፎ፣ በሱሉልታ እና ሰበታ እያመረተ ያለውን የህዝብ ሰቆቃ እና እንግልት ያየ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አዲስ አበባን ለኦዴፓ አስረክቦ የኢትዮጵያዊነቱን ምልክት ማጣትን የሚፈቅድ አይመስለኝም፡፡

የኬኛ ፖለቲካ ወዳጅ አለው?

አቶ መለስ በስልጣናቸው ላይ ዘመናቸው የፈቀደላቸውን የመርገጥ እድል ተጠቅመው የዘውጋቸውን ልሂቃ ሁለንተናዊ የበላይነት እውን አድርገው ኖረዋል፡፡ ይህን እያየ ተመሳሳዩን ለመድገም ሲጎመዥ የኖረው አዴፓ የአሳዳጊውን አካሄድ እየተከተለ ነው፡፡ ይህን ሲያደርግ የረሳው ነገር ግን ትናንት ዛሬ እንዳልሆነ ነው፡፡ ትናንት ዛሬ አለመሆኑ ኢህአዴግን ጭምር ቀይሮታል፡፡ ትናንት ለአቶ መለስ ሲያደገድግ የኖረው የአባል ፓርቲ ካድሬ ዛሬ አለቃ ላወጣው መግለጫ ሌላ መግለጫ በሚሰጡ ሰዎች ተቀይሯል፡፡ የአማራን ጭራቅነት አንስቶ ማስፈራራቱም ቢሆን ብዙም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ የኦሮሞ ስልጣን መያዝም ለሌላው ኢትዮጵያዊ ምን እንዳመጣ በአጭር ጊዜ ብዙ ትምህርት እየተገኘ ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው ጭራቅ ስልጣን ላይ ተቀምጦ ስለአሮጌው ጭራቅ ማውራቱ ሞኝ ሊያስመስል ይችላል፡፡

ኦዴፓ በፍጥነት እውነተኛ ምግባሩን መግለፁ በኢትዮጵያዊነቱ በኢትዮጵያ ምድር እኩል ሆኖ የመኖር አምሮት ያለው ዜጋ ሁሉ ፊቱን እንዲያዞርበት አድርጓል፡፡ ይህ ከኦዴፓ በቀር በሃገሪቱ ብቅ እያሉ ያሉ አዳዲስ አመራሮችን ሁሉ የሚጨምር ይመስላል፡፡ ኦዴፓ በኬኛ ፖለቲካ በኩል የኦነግ አምሮት ወደሆነው ኦሮሙማ በፍጥነት በሚምዘገዘግበት ወቅት በሃገሪቱ አዲስ የሆነ የዲሞክራሲ እና የእኩልነት ፖለቲካን የመሻቱ ነገር እያየለ መጥቷል፡፡ የህወሃትን የበላይነት አዝሎ ጀርባው የዛለው የኢትዮጵያ ህዝብ የማንንም የበላይነት የሚያስተናግድበት የጠጠር መጣያ ቦታ አልቀረለትም፡፡ ይህ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ከኦህዴድ የኬኛ ፖለቲካ በተቃራኒው ያቆመዋል፣ ኦህዴድን ጠላተ ብዙ አድርጎ መሞቻውን ጊዜ ያፋጥናል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሚናውን ያልለየው፣ ድምፁን ያጠፋው የተቃውሞ ጎራ አሰላለፉ ከወዴት እንደሆነ ማወቅ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ የተቃውሞ ጎራው ሃገሪቱ እንዲህ አቅጣጫ በጠፋት ጊዜ ብቅ ብሎ ህዝቡን ካላረጋጋ ህልውናው ለመቼ እንደሚያስፈልግ ግልፅ አይደለም፡፡

ኦህዴድ አሁን የያዘው መንገድ በሃገርቤት ብቅ ካሉ አዲስ የለወጥ አመራሮች እስከ አለም ዓቀፉ ማህበረሰብ፣ ከተራው ዜጋ እስከ ሲቪክ ማህበራት ድረስ ወዳጅ የሚያሳጣው ነው፡፡ የምዕራቡ ሚዲያ የሚቀባበለው የጌድኦ ስደተኞች ጉዳይ ጠ/ሚውንም ሆነ እናት ፓርቲያቸውን አይንህ ላፈር የሚስብል እንጅ አበጀህ የሚያስብላቸው ነገር አይደለም፡፡ትናንት በወለጋ ነጆ አካባቢ ሰብዓዊ ፍጡራንን መግደሉ አንሶ በላያቸው ላይ እሳት መልቀቁ የኬኛ ፖለቲካ ቱርፋት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ጠ/ሚ አብይን በሁለት እጃቸው የጨበጧቸው የምዕራብ ሃገራት ባለስልጣናት ፊታቸውን እንዲያዞሩባቸው የሚያደርግ ነው፡፡ የምዕራቡ ሃገራት የወደዷቸውም የኢትዮጵያን ህዝብ ተከትለው ነውና ህዝቡ ፊቱን ሲያዞርባቸው እነሱም ሙገሳውን እንደሚተው ግልፅ ነገር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኦህዴድ መራሹን መንግስት ክፉኛ ማዳከሙ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ኦህዴድ አዝማሚውን ተረድቶ የኬኛ ፖለቲካውን ልጓም ሊያበጅለት ይገባል፡፡ የኬኛ ፖለቲካ ልጓማ ካልገባለት ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት እና ጉዳቱን ለመቀነስ ሌላው ኢትየጵያዊ ምን ማድረግ አለበት የሚለውን ለማየት ለሳምንት ላሳድረው፡፡

Filed in: Amharic