>
5:13 pm - Monday April 18, 2072

ቋንቋ ሲያገል ሳይሆን - ሲያማልል ነው የሚያድገው!!!  (አበበ ቶላ ፈይሳ)

ቋንቋ ሲያገል ሳይሆን ሲያማልል ነው የሚያድገው!!!
አበበ ቶላ ፈይሳ
አቶ በቀለ ገርባ ኦሮምኛ ቋንቋን ለማሳደግ ንግድ ቦታ ስትሄዱ “ሜቃ” ብላችሁ ጠይቁ እና አላውቅም ካለህ “ነጋቲ” ብላችሁ ሂዱ… ሲል ኦሮምኛ የማይችሉ ሰዎችን በማግለል ኦሮምኛን ማሳደግ እንደሚቻል ሲሰብክ ተሰምቷል። ተሳስቷል።
ኦሮምኛም ሆነ ሌላ ቋንቋ ለማደግ ሌላውን ቋንቋ መግፋትም ማግለልም አይጠበቅበትም። በተለያየ መልኩ ራሱን እያሰማመረ ማማለል ነው የበለጠ የሚያሳድገው።
የመጀመሪያው ነገር በዚህ በግሎባላይዜሽን ዘመን ሃገርንም ሆነ ቋንቋን እንኳን ሌላው ቀርቶ ግለሰብን፤ የኮስታራ እና ቆፍጣና አፕሮች አያሳድጋቸውም። “ሜቃ” ብለህ ካላወቀ “ነጋቲ” ብለህ ሂድ ማለት በጣም አግላይ የሆነ ኮስትር ያለ ማንንም የማይስብ አቀራረብ ነው። “ሜቃ” ብለህ ጠይቀው እና ካላወቀ “ሜቃ ማለት በኦሮምኛ ስንት ነው? ማለት ነው… ብላችሁ ነጋዴው ቋንቋችንን እንዲለምድ አግዙት…” ማለት ካልተጀመረ… በግድ እና በጉልበት በማግለል እና በመግፋት ቋንቋም ሰውም አያድግም።
ማማለል ይገባል ያልኩት ቋንቋ በገዛ ብሄረሰቡ ብቻ ተወስኖ ቢነገር አደገ አይባልም ቋንቋ በደንብ እንዲያድግ ከብሄረሰቡ ውጪ የሆኑ ሰዎችም እንዲናገሩት ማበረታት ያስፈልጋል። እንደዛ ለማድረግ ቋንቋው ሳቢ ወይም አማላይ እንዲሆን መጣር ጥሩ ብልሃት ነው… ቋንቋ አማላይ እንዲሆን ሙዚቃ፣ ፊልም፣ መፅሃፍት ያላቸው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም… ከተማችንን ዞር ዞር ብለን ሪሰርች ብንሰራ ድሮ ህንድኛ ዛሬ ደግሞ ቱርክ የሚሞካክር አበሻ ብዙ ነው… ይሄ ከፊልማቸው አማላይነት የተነሳ ነው እንጂ “ሜቃ” ብሎ አልችል ሲሉ “ነጋቲ” በማለት የመጣ አይደለም።
ከአቶ በቀለ ገርባ ገለፃ እንደተረዳሁት አሁንም ገና ከቁጣ የፖለቲካ ደረጃ እንዳላለፉ ነው። ኦሮሞም ሆነ ሌሎች ብሄርተኞች ከቁጣ ፖለቲካ ወጥተው በፈገግታ እና ማራኪ አቀራረብ ሌሎች በጥርጣሬ እና በስጋት የማያይዋቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ በጣም ጠቃሚ ነው።
በተለይ ቋንቋ በቁጣ እና በግዳጅ አያድግም!
ቅድም YonatanTR ሲያነሳ እንዳየሁት ኦሮምኛ የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን መታገል እና ሃሳቡን ሌሎች ሰዎችም እንዲደግፉት ማግባባትም ተገቢ እና ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ከሚታወቁ ሰዎች አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ኦሮምኛ ቋንቋ ከአማርኛ ጎን ለጎን የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን ብዙ ግዜ ሃሳብ ሲያነሱ ሰምተናቸዋል። ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም ይሄንን ሃሳብ ሲያራምድ ቆይቷል… እንዲህ እንዲህ እያሉ እርስ በርሱ እና “ወደድክም ጠላህም” ከሚለው ግዜው ያለፈበት አሮጌ አመለካከት በመውጣት ሌሎችም ኬዙን እንዲደግፉት በማድረግ ኦሮምኛ ሌላ የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን ከተረገ ቋንቋው የማደግ እድሉ ይሰፋል።
“ሜቃ” ብለህ አላውቅም ካለ ላጥ በል አይነት ኮስታራ እና ቆምጣጣ አካሄድ ግን ቋንቋን አያሳድገውም!
ነጋቲ ቡላ (ደህና እደሩ) እንዲህ ነው ቋንቋ የሚያድገው። አይደል እንዴ
Filed in: Amharic