>

" በወገኖቹ" የተካደው አብይ አህመድ ! (ሳምሶን ሚካኤል)

” በወገኖቹ” የተካደው አብይ አህመድ !
ሳምሶን ሚካኤል
አቢይ አህመድ አሁንም ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሬ ነው። ሰውየው ተካደ እንጂ ህዝብን ከዳ ወይም ቃሉን አጠፈ የሚል እምነት የለኝም። አቢይ አህመድ እንደ እነ ጃጋማ ኬሎ ፣ ጎበና ዳጬ ፣ አብዲሳ አጋ ፣ አበበ በቂላ ያሉ ምርጥ ኢትዮጵያውያን ከብሄሩ በላይ ሀገሩን አሻግሮ ማየት የቻለ ፣ ከተሜ ፣ የሀሳብ አጥርን ለመዝለል ዘወትር የሚተጋ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኛ ነው። ከስሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ፣ ከአረብ ሀገራት እስከ አሜሪካ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ድረስ በአጭር ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ማንም ያላገኘውን ተቀባይነት አግኝቶ የነበረው አቢይ ዛሬ ቢናገር የሚደመጥ ለመሆንም እየከበደው ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ ዋንኛውን ሚና የተጫወቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእኔ ሲል የሚጠራቸው የራሱ ፓርቲ ካድሬዎችና በቀል የሚነዳቸው የኦሮሞ ልሂቃን ነቸው።
 
፩ አብይ አህመድና ኦህዴድ 
ኦህዴድ የጎሳ ፓርቲ ነው። ለማ መገርሳና አብይ አህመድ እስኪመጡለት ድረስ የፓለቲካ ርዕዮትን አንዴ ከወያኔ ፣ ሌላ ጊዜ ከኦነግ እየቀዳ በተጣጣፈና እርስ በእርሱ የማይግባባ ህሳቤ ይዞ የኖረ ድርጅት። የኦህዴድ ጉልበት የተገነባውም ወያኔ ባዋሰው ነፍጥ ማስተማር የደበራቸውን የአንደኛ ደረጃ መምህራን በሶስት ወር የካድሬ ኮርስ ከፊት አድርጎ እውር ድንብሩን ሲዳክር የነበረ ድርጅት ነው።
የእነ አቢይ አህመድ ትልቁ ክፍተት የለውጥ ሂደቱ ሲጀመር እላይ ካለው የኦህዴድ ጎጠኛ እስከታች ድረስ የኢትዮጵያን ህብረ ብሄራዊ ፓለቲካ አስትምህሮት ሳይሰብኩት ወንበር መያዛቸው ነው።( ለዚያ ደግሞ ጊዜ አልነበረም ) ይህ ደግሞ ድርጅቱን የርዕዮት ጎዶሎ ውስጥ ከቶት አብዛኛው የድርጅቱ አባል ጽንፈኞች በሚሰጡት አጀንዳ የሚነዳ እንዲሆን አድርጎታል። እነ አብይም በማስፈጸም ደረጃ ከቤተመንግስቱ የሚርቅ አቅም እንዳይኖራቸው አድርጓል።
ኦህዴድ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ቁምነገር አስመዘገብኩ ካለ የእነ ኦነግን የመገንጠል ትርክት ባዶ ማስቀረቱ እና ኦሮሞ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት መኖር ይችላል የሚለውን ህሳቤ ህዝብ ዘንድ ማስረጹ ብቻ ነው።
ጃዋራውያንና አቢይ አህመድ 
ከአቢይ እህመድ እግር ስር ሰውየው ሀገር ሲያግባባ ምንጣፉን ያነሳው ዋንኛው ቡድን ጃዋር የሚመራው ቅድሚያ ለኦሮሞ OromoFirst ጥምረት ነው። ይህ ቡድን በጃዋር አህመድ የርዕዮት መሪነት በአቶ በቀለ ገርባ የፓርቲ አደራጅነት የሚዘወር ነው። ቡድኑ ኦነግም ኦህዴድም እንዲዳከሙለት የሚፈልግ ዋና ትኩረቱን መጪውን ሀገራዊ ምርጫ ላይ ያደረገ ነው። ውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት አዲስ ጽንፈኛ የኦሮሞ ፓርቲ የማቋቋም ትልሙ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀድሞ ቄሮ የተባለውን አደረጃጀት ወደ ፓርቲ ቅርጽ የመሰብሰብ ስራው መንገድ ከያዘ ቆይቷል።
ጃዋራውያን ድህረ ለውጥ መጀመሪያ ያደረጉት ነገር ቢኖር አቢይ አህመድ ይዞት የመጣው አጀንዳ ” የሚኒሊክን ኢትዮጵያ ” መልሶ የሚያመጣ ነው በሚል ሰውየው በመላው ኦሮሚያ ተቀባይነት እንዲያጣ መስራት ነበር። የአዲስአበባ ጉዳይ ያለጊዜው እንዲነሳ የተፈለገው ” የኦሮሞ ህዝብ ትግል እምብርት ነው” የሚል አዲስ ትርክትም የመጣው አቢይን ቅርቃር ውስጥ ለመክተት እነ ጃዋርን ደግሞ የትግል መሪ አድርጎ ለማስቀመጥ ነው።
ያ አሁን የተሳካ ይመስላል። እንኳን ህዝቡ የኦህዴድ ካድሬም አቢይን ከሳሽ ጃዋርን አንጋሽ ከሆነ ቆይቷል። ይህ ትርክት ግን ከህዝብ አልፎ የአስተዳደር እና ጸጥታ አካላትም ውስጥ ከገባ ሰንብቷል። ከፌዴራል ፓሊስ ጀምሮ እስከ ክልል ያሉ ሹመኞች ዛሬ ዛሬ እነ ጃዋር የሚጠሯቸውን ሰልፎች ከፊት የሚመሩት ነገ በመንግስትህ አስበኝ በሚል ምኞት ነው። ለገጣፎ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን በግፍ ሲፈናቀሉ አንድም የኦህዴድ ባለስልጣን ይህ ድርጊት ኢሰብአዊነት ነው ያላለው ክፋቱ ሳይታየው ቀርቶ አይደለም ከእነ ጃዋር ወገን የሚመጣውን ቁጣ ትከሻው መሸከም እንደማይችል ስለሚያውቅ እንጂ።
ለማጠቃለል በግሌ አቢይ አህመድ ኦሮሞን ብቻ ወደፊት የሚያመጣ የፓለቲካ ውጥን ከቀን አንድ ጀምሮ ነበረው የሚለው ክርክር ብዙ አይዋጥልኝም። ሰውየው የኢትዮጵያን ታሪክ ጠንቅቆ የተረዳ የብሄር ፓለቲካ ሀገሪቷ ላይ ያደረሰውን አደጋ በቅጡ ያወቀ ሰው ነው። ሰውየው የህዝብና የልሂቃኑን ጥሪ ሊሰማ ሞክሯል ሁሉንም የሚያሳትፍ የፓለቲካ ሂደትም እየፈጠረ ነበር። ይህ ግን የተሳካለት አይመስልም በዋንኛነት አጋር ይሆኑኛል ያላቸው ” የራሱ ወገኖች ” ገሚሶቹ ውስጣቸው ያለውን የበቀል ስሜት ሊያዳፍኑት ባለመቻላቸው ሌሎቹ ደግሞ የእርሱኑ ወንበር ገና ድሮ ከሚኖሶታ ሲነሱ ጀምሮ ይፈልጉት ስለነበር !
Filed in: Amharic