>

ለጠ/ሚ አብይ የምክር ደብዳቤ:- መርፌ ጨርቅ እንጂ አለት አይበሳም!!!  (ያሬድ ሀይለማርያም)

ለጠ/ሚ አብይ የምክር ደብዳቤ
መርፌ ጨርቅ እንጂ አለት አይበሳም!!! 
ያሬድ ሀይለማርያም
ጠ/ሚ አብይ በትላንትናው እለት የማህበራዊ ሚዲያዎችን አጠቃቀም በተመለከተ ምክር አዘል ተግሳጽ የያዘ ደብዳቤ ትላንት ከጽ/ቤታቸው ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል። እርግጥ ነው ጠቅላዩ እንዳሉት ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚተላለፉ ጽንፍ የያዙ እሰጣ ገባዎች፣ በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጸያፍ ንግግሮች፣ ሕዝብን ለግጭት የሚቀሰቅሱ ጥሪዎች፣ የሃሰት መረጃዎች እና ውንጀላዎች ከመቼው ጊዜ በስፋት እየተስተዋለ መጥቷል። ይህ አይነቱ ችግሩ በጊዜ ካልታረመ የእርስ በርስ ንቁሪያው ከማህበራዊ ሚዲያ ወደ መሬት ወርዶ በግልም ሆነ በአገር ደረጃ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ደብዳቤያቸው በግልጽ አስቀምጦታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ሚዲያዎች ጽንፍ ይዘው እና የተሳሳቱ መረጃዎችን እያሰራጩ ሕዝብን የሚያደናግሩ እና ለግጭት የሚያነሳሱ ሰዎችን በመርፌ መስለው አስቀምጠዋል። እንዲህም ይላሉ “መርፌ አይናማ ናት ባለ ስለት፤ ችግሩ የፊቷን እንጂ የሚከተላትን አታይም። እናም ጨርቅ ላይ እሷ አለፍኩ ብላ የክር እና የገመድ መአት ታስገባበታለች። የእኛ አገር አንዳንድ የማህበራዊ ድህረ ገጽ ጦማሪዎች ልክ እንደ መርፌ ናቸው። እነሱ አገር በሚወጋ መርፌያቸው እየወጉን ሲጓዙ እንደ ክር አያሌዎች መድረሻቸውን ሳይጠይቁ ይከተሏቸዋል። …”። አገላለጻቸው ግሩም ነው። ወድጄዋለሁም። ነገር ግን እውነቶች ይጎድሉታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁኔታውን አንድ ገጽታ ብቻ ነው እንደ ዋነኛ ምክንያት ወስደው እና አትኩሮት ሰጥተው ስጋታቸውን እና ማሳሰቢያቸውን የሰጡት። እኔ ያላዩት ወይም ችላ ብለው ያለፉት ገጽታ አለ እላለሁ። መርፌ መርቅ እንጂ አለት አሰፋም ወይም አይበሳም።
አዎ አገር እንደ እንደ አለት ካልጠነከረች በመርቤ ስለት በቻ ሳይሆን በዶለዶመ ብረትም ትበሳለች። የመርፌ አቅሙ ጨርቅ ወይም እንደ ጨርቅ በሳሳ ነገር ላይ ነው። አገራችን ደግሞ ከመቼውም በከፋ ሁኔታ ሳስታለች።
አገር እንደ አለት የሚጸናው በጥሩ ሕግ፣ የሕግ የበላይነትን በሚያረጋግጡ ጠንካራ ተቋማት፣ ሕግን በሚያከብሩ እና በሚያስከብሩ የመንግስት ተቋማት እና ሕግ አክባሪ በሆነ ማህበረሰብ ነው።
በሁሉም አለም ማህበራዊ ሚዲያዎች ጥሩም፤ መጥፎም ገጽታ አላቸው። የሕግ የበላይነት በሳሳበት እና መንግስት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ባልቻለበት ስፍራ አሉታዊ ጎኑ ይበረታና አገር እሰከ ማተራመስ አልፎም እስከ ማፍረስ ይደርሳል። በሕግ የጸና ጠንካራ አገር እና ሕግ አክባሪ ማብሀረሰብ ባለበት አገር ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያዎች ጩኸት ሰሚ አልባ ነው። እዛው አየር ላይ ተንሳፎ ይቀራል።
ክቡርነትዎ የእኛ አገር የማህበራዊ ድህረገጾች መረን የለቀቀ የእርስ በርስ ንቁሪያ እኮ መሬት ላይ ያለው እውነታ ነጸብራቅ ነው። እርሶ በተቀመጡባት መዲና አዲስ አበባ ሳይቀር ሰዎች ሜጫ፣ ድንጋይ፣ ሚስማር የተመታበት ዱላ ይዘው አደባባይ ለፍልሚያ በየቀኑ በሚወጡበት እና ዜጎች በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት የማይችሉበት አደጋ መሬት ላይ እየታየ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያልው ጦርነት እንብዛም ትኩረት ሊስብ አይገባውም።
አገሪቱን እንደ ጨርቅ ያሳሳት እንደ እኔ እምነት የመርፌው ጥንካሬ ሳይሆን የመንግስት የሕግ የበላይነት በመላ አገሪቱ ማስፈን አለመቻል ነው። እባክዎ ቅድሚያ አየር ላይ ካለው የቃላት ጦርነት በፊት መሬት ላይ ህግ ያስከብሩ። የእርሶ ጽ/ቤትም አይደል እንዴ በአደባባይ እና በማህበራዊ ሚዲያ በሕዝብ ላይ የእልቂት እና የግጭት አዋጅ አውጆ ለቄሮ የክተት ጥሪ ያደረገውን ጃዋር መሃመድን በሕግ ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ በቅርቡ በኢሲኤ አዳራሽ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ በአገሪትይ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምን አስመልክቶ ትምህርት እንዲሰጥ ዋና ተናጋሪ አድርጎ ያቀረበው።
ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ያሉት ችግሮች እና ስጋትዎን እኔሙ ሙሉ በሙሉ እጋራዎታለው። ጽንፈኝነት ነግሷል። የሃሰት መረጃዎች ሕዝብን እያደናገሩ ነው። እኔም ሆንኩ ሌሎች ሚዲያውን የሚጠቀሙ አካላት እርሶንም ጨምሮ ለችግሩ አስተዋጽኦ ይኖረን ይሆናል። ይህ ችግር አገር ሳያሳጣን በፊት በአግባቡ እና  በአፋጣኝ ሊፈታ ይገባል። ኢትዮጵያን እንደ አለት የጸናች አገር ማደረግ ከቻልን ግን የማህበራዊ ሚዲያው ጩኸትም ሆነ ትርምስ ንፋስ ይወስደዋል ወይም እየነጠረ ይመለሳል እንጂ አገር አያፈርስም።
አዎ እርሶ እንዳሉት ኢትዮጵያ ጽኑ መሰረት ያላት አገር ስለሆነች በማህበራዊ ሚዲያ ወሬ አትፈርስም። መሬት ላይ ያለው ሕግ አልባነት፣ የመንጋ እንቅስቃሴ እና በሕግ ያልተገራና ልቀ የሆነ የግለሰቦች እና የፓርቲዎች እንቅስቃሴ ግን የሞት አፋፍ ሊያደርሳት ይችላል።
የሕግ የበላይነት ትኩረት ይሰጠው!
Filed in: Amharic