>

አገር በአንድ ጠንቀኛ ‹‹ሰነድ›› ምክንያት ስትጠፋ እያየን እንዴት ዝም እንላለን? (ከይኄይስ እውነቱ)

አገር በአንድ ጠንቀኛ ‹‹ሰነድ›› ምክንያት ስትጠፋ እያየን እንዴት ዝም እንላለን?

ከይኄይስ እውነቱ

ወያኔ ትግሬ ከዛሬ 24 ዓመት በፊት የራሱን የጥፋት ዓላማ ለማስፈጸም ሲል በኢትዮጵያ ምድር በ‹‹ሕገ መንግሥት›› ስም ስለተከተለው ነቀርሳ በተለያዩ ጸሐፍት ብዙ ተብሏል፡፡ የአሁኑ አስተያየት አቅራቢም በርእሰ ጉዳዩ ላይ የሚከተሉትን አስተያየቶች አቅርቧል፡፡
• የወያኔ የማስመሰያ ‹‹ሕገ መንግሥት›› (façade constitution) ፤ በማር የተለወሰ እሬት [ከይኄይስ እውነቱ] 29/11/2016 | https://www.ethioreference.com/archives/7242
• እውን የወያኔ የይስሙላ ‹‹ሕገ መንግሥት›› ችግር አንቀጽ 39 ብቻ ነው? [ከይኄይስ እውነቱ] Posted by admin | 16/04/2018 http://www.zehabesha.com/amharic/archives/89902 April 16, 2018 | Filed under: News Feature,ነፃ አስተያየቶች | Posted by: Zehabesha
ሰነዱን በጻፉት ሰዎች አስተሳሰብ መርዘኝነት ሰነዱን መርዘኛ/ጠንቀኛ ብሎ መጥራቱ ስህተት የለውም፡፡ ይዘቱና ያስከተለው አገር የማጥፋት ውጤት ምስክር ነውና፡፡ ወያኔና ሎሌዎቹ ይህንን ሰነድ በመንደርተኝነት አስተሳሰብ ተወስነው የጻፉት ጐሣ በሚባል ጣዖት ጉያ ተሸሸገው ሕዝብን ከፋፍለው፣ ጥላቻን አንግሠው፣ እርስ በርሱ እያገጩ፣ ሀብቱን ዘርፈው በሥልጣን ለመቆየት ብቻ ሳይሆን፤ ጐሠኞች የማይሠለጥኑባት ኢትዮጵያ ደግሞ እንድትበታተን በመፈለግ ጭምር ነው፡፡ ወያኔዎችና ‹ተረፈ ወያኔዎች› ያዘጋጁት ሰነድ ይህንን የጥፋት ተልእኮ ለማስፈጸም የተዘጋጀ ጦማረ ሞት ነው፡፡ በየክፍላተ ሀገሩ ቀብረውት ጊዜ ጠብቆ እየፈነዳ ያለው የጥፋት ፈንጅ (ሞቱ፣ የአካል ጉዳቱ፣ በገፍ መፈናቀሉ፣ በሽታው፣ ረሃቡ) ለዚህ ማረጋገጫ ነው፡፡

የወያኔ ጠንቀኛ ሰነድ በሕግ፣ በፖለቲካም ሆነ በሞራል ረገድ ተቀባይነት (legitimacy) እንደሌለው ምሁራን ጽፈውበታል፡፡ እኔም በቀደሙት አስተያየቶቼ ሙከራ አድርጌአለሁ፡፡ በግሌም ይህ የወያኔ ሰነድ በየትኛውም መመዘኛ ‹የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት› ነው ብዬ የመቀበል ቢያንስ የሞራል ግዴታ እንደሌለብኝም በቀደሙት ጽሑፎቼ ገልጬአለሁ፡፡ ስለሆነም እነዚህ ጉዳዮች የዛሬ አስተያየቴ ትኩረት አይሆኑም፡፡

ይሄ ጠንቀኛ ሰነድ ኢትዮጵያን እንደ አገር ተቀብሎ የተነሳ አይደለም፡፡ ወያኔ ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው የፈጠራቸው 9 ‹የአትድረሱብኝ ጋጣዎች› ኢትዮጵያ ቀደምት ታሪክ እንደሌላት ቆጥሮ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ መልክዐ ምድራዊ ወዘተ. ትስስር የሌላቸው ማኅበረሰቦች የሚኖሩባቸው 9 ራሳቸውን የቻሉ አገሮች በዘፈቀደ የተጠራቀሙባት አገር እንደሆነች አድርጎ ነው፡፡ በመሆኑም ሰነዱ መሻሻል አይደለም የሚያስፈልገው፡፡ የተዘጋጀበት ፀረ-ኢትዮጵያዊ መንፈስና የዘረኝነት ነቀርሳው በመላ ‹አካላቱ› በመሰራጨቱ ሙለ በሙሉ መቀየር አለበት፡፡ የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥቱ›፣

• ኢትዮጵያዊ ዜግነትን አጥፍቶ፣ የሕዝቡንም ሉዐላዊነት ቀምቶ በምትኩ ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› የሚል ዓይን፣ ጆሮ፣ አንደበት፣ አእምሮ የሌለው ‹ልዩ ፍጥረት› ፈጥሮ አገሪቱን ያለባለቤት ያስቀረ፤ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ‹ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› በሚለው ምትክ ‹ልዩ ፍጥረት› በሚለው እጠቀማለሁ፡፡ (በሰነዱ መግቢያ አንቀጽና በተለያዩ ድንጋጌዎች ውስጥ ተጠቅሷል)
• ፌዴራሊዝም የአብሮነት ሥርዓት መሆኑ ተዘንግቶ፣ የመለያየት ሥርዓትን (የጎሣ ፌዴራሊዝምን) የተከለ፤ (አንቀጽ 47፣ 48 እና 39/3/)
• ለይስሙላ የፖለቲካ ድርጅት እያለ ሾላ በድፍኑ ቢናገርም ፖለቲካ በደም ቋጠሮ እንዲደራጀ የፈቀደ፤ በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን ኢትዮጵያ በጎሣ አለቆች እንድትገዛ በማድረግ የድንቁርና መገለጫ ወደሆነው ኋላቀርነት የጎተተ፤ በዚህም አገራችን ሕዝብን ለማስተዳደር የሃሳብ፣ የፕሮግራም፣ የርዕዮተ ዓለም፣ የፍልስፍና አማራጮችን የሚያቀርቡ የፖለቲካ ማኅበራት (ፓርቲዎች) እንዳይኖራት ያደረገ፤ (አንቀጽ 56 ከአንቀጽ 47 ጋር በጣምራ ሲነበብ የሚያስከትለው ውጤት)
• አርሶ አደሩን በተለይ÷ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ባጠቃላይ መሬት አልባ በማድረግና የመሬትን ባለቤትነት ቀደም ብዬ ለጠቀስኩት ‹ልዩ ፍጥረት› በመስጠት ሽፋን ታላቁን የሀገር ሀብት ለሌቦች መጫወቻ እንዲሆን ያደረገ፤ (አንቀጽ 40)
• ‹ልዩ ፍጥረት› ያልኳቸው ባሰኛቸው ጊዜ ራሳቸውን የቻሉ ክ/ሃገር መመሥረት እንደሚችሉ ፈቃድ መስጠቱ፤ እያንዳንዱ ‹ልዩ ፍጥረት› የሠፈረበት መልክዐ ምድር ባለቤት መሆኑ፣ በተዘዋዋሪ መልክዐ ምድሩን በባለቤትነት ከተሰጠው/ከያዘው ነገድ/ጐሣ ውጪ ያለ ኢትዮጵያዊ ባይተዋርና መጤ መሆኑ፤ (በአንቀጽ 39 /3/)
• በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ የኦሮሞ ክ/ሃገር ‹ልዩ ጥቅም› ይጠበቅለታል በማለት ሆን ተብሎ ግጭት የሚፈጥር ድንጋጌ መሰንቀሩ፤(አንቀጽ 49)
• ማንም በራሱ ጉዳይ ዳኛ አይሆንም የሚለውን ዓለም አቀፍ የሕግ መርህ በተፃረረ መልኩ የሕገ መንግሥትን ትርጓሜ ለወያኔ ‹ሕግ አውጪ› አካል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መስጠቱ፤ባጠቃላይ ለዚህ ምክር ቤት የተሰጡ ሥልጣንና ተግባራት የወያኔ የጥፋት ተልእኮ ዋና ማስፈጸሚያ መሆናቸው፤ (አንቀጽ 83፣ 62)
• የመከላከያ መርሆ በሚለው ክፍል የመከላከያ ሠራዊት የጐሣን ተዋጽኦ መሠረት ያደረገ በሚል ሽፋን በተግባር እንደሚታየው ኢትዮጵያዊ መንፈስና አቋም ያለው የአገር መከላከያ ሠራዊት እንዳይኖር ማድረጉ፤ (አንቀጽ 57)
ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አንዳንዶች ይሄ የወያኔ ሰነድ መቀየር አለበት ሲባል አገር እንደምትናጋ ወይም ከፍተኛ ቀውስ እንደሚፈጠር አድርገው ያስባሉ፡፡ የተወሰነ ጊዜ መውሰድ እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ፡፡ ጎበዝ ከመነሻውም አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያልተሳተፈበት መሆኑን ካመንን፣ በተግባርም እንዳየነው ሕዝብና መንግሥት ቃል ኪዳን የተፈጣጠሙበት ሰነድ ሳይሆን የወያኔና ‹ተረፈ ወያኔዎችን› ሥልጣን ማደላደያና ሳይመቻቸው ሲቀር አገር ማፍረሻ ሰነድ መሆኑን ከተገነዘብን፣ ተደራጅተን ጫና ማሳደርና ለሁላችን በእኩልነት የሚያገለግል አገር ማስተዳደሪያ የቃል ኪዳን ሰነድ (ሕገ መንግሥት) መጻፍ ምን ይከለክለናል?
‹የለውጥ መሪዎች› የተባሉት ሁለትም ይሁኑ ሦስት ግለሰቦች ዓላማቸው የወንጀለኛ ድርጅታቸውንና የጐሣ ፖለቲከኞችን ተልእኮ ማስፈጸም ሳይሆን የአብዛኛውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ሥራ ላይ ማዋል ከሆነ፣ ሊያመጡት የሚፈልጉትም ለውጥ መሠረታዊ/ሥርዓታዊ ከሆነ የመጀመሪያ ተግባራቸው ትርጕም ባለው አሳታፊነት አገራችን በወያኔ ዘመን ለገባችበት ሁለንተናዊ ቀውስ በተለይም የአገር ህልውና አደጋ ቀዳሚ ምክንያቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ወያኔ ያቆመው የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› በመሆኑ የመጀመሪያ ሥራቸው ሊያደርጉት በተገባ ነበር፡፡ በተቃራኒው አገራችንን ያለምርጫ የሚገዛው (ሽግግሩን በብቸኝነት መምራት አለብኝ ባለው ሊቀመንበሩ ከለላነት) ኦሕዴድ የተባለው የጐሣ ድርጅት ከአሳዳሪው ሕወሓት በተማረው መሠረት በጐሣ ፌዴራሊዝም (በጐሣ ፖለቲካ) አልደራደርም ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡ የዚህ ድርጅት መሪዎች ደግሞ ‹የለውጡ ፊታውራሪዎች› የተባሉት ግለሰቦች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን ነካቸው እያልን ምክንያት ስንደረድርላቸውና መላምት ስናስቀምጥ ጊዜአችንን ማጥፋት ያለብን አይመስለኝም፡፡ ዐቢይ ወጥቶ አቅቶኛልና አግዙኝ ይላል ብሎ መጠበቁም የማይመስል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከሦስት ሺህ ዘመን በላይ ታሪክ ያላት አገር መሆኗን ካመን፣ በለስ ቀንቶት ሥልጣን በያዘ ባንድ ወንበዴ ቡድን ከዛሬ 20 ዓመት በፊት የተጻፈ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› (የሕወሓት መግለጫ) መቀየር ምክንያት አገር ትበተናለች ብለን እናስባለን? በጭራሽ፡፡ በሕዝባችን ላይ የግፍ ጽዋው ሞልቶ ሲፈስ የምዕራባውያን አሳዳሪዎቻቸውን ዕርጥባንና ብድር ለማግኘት በ‹እመጫትነት› ያስገቡት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች ጭንጋፍ መሆናቸው፤ በተቃራኒው አገር አጥፊ ድንጋጌዎች ተመርጠው ሥራ ላይ እንዲውሉ መደረጋቸው የሰነዱን ዓላማና ተልእኮ ግልጽ የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡ እዚህ ላይ የሰነዱ ችግር የአፈጻጸም ነው ከሚሉ ባንድ ወገን ብልጣ ብልጥ የወያኔ ደጋፊዎች÷ በሌላ በኩል ዐላዋቂ ጅላ ጅሎችን ወሬ ከመስማት መጠንቀቅና መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እውነተኛና ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት የጥቂቶች (ሥልጣን የያዘ ቡድንና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው) ፍላጎት ማስፈጸሚያ፣ ሲመች ማን ነክቶት÷ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚያስብል፣ ሳይመች እስከነአካቴው መኖሩ የማይታወቅ አይደለም፡፡ ይሄ ደጋግሞ እንደተገለጸው ‹ሕገ አራዊት› ነው፡፡
ወገኔ! የአገር ህልውናና የሕዝባችን ደኅንነት ስላስጨነቀን ነው እኮ ይህ ጠንቀኛ ሰነድ አያስፈልገንም የምንለው፡፡ የተለመደውን ጫጫታና ኹከት የሚፈጥሩ ቊጥራቸው ቀላል የማይባል ጥቅማቸው የተነካባቸው ሰዎችና ተከታዮቻቸው መኖራቸው እኮ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ አሁን ከደረሰውና እየተፈጸመም ካለው ጥፋት የበለጠ ይመጣል እያልን ግን ብንዘገይ ለመደራጀቱም፣ ለመምከሩም ብሎም ጦማረ ሞቱን ወደ ጦማረ ሕይወት ለመቀየር የማንችልበት የከፋ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከዛ በኋላ ጸጸቱም ጩኸቱም የማይጠቅም ይሆናል፡፡ ስለሆነም አገርን የማዳን ዐቢይ ተግባር አድርገን ልንወስደው ይገባል፡፡ የጐሣ ፌዴራሊዝሙና የጐሣው ፖለቲካ ከቀጠለ አገራችን የእልቂት መናኸሪያ፣ የአሸባሪዎች መፈንጫ፣ የሥርዓተ አልበኞች መራኮቻ፣ የወንበዴዎች ዋሻ ከመሆን አልፎም የአገር ህልውና ራሱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ እየሆነም ያለው ይኸው ነው፡፡

ይሄ ‹ክልል›፣ ‹ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›፣ ‹የጐሣ ፖለቲካ›፣ ‹የጐሣ ፌዴራሊዝም›፣ ‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›፣ ‹ልማታዊ…እስከነ ጓዞቹ› የሚለው የወያኔ ትግሬና ሎሌዎቹ ዕብደት አላፊ ጠፊ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
ስለሆነም ሕዝብ በየአካባቢው በመደራጀትና ኅብረት በመፍጠር ፍላጎቱን በግልጽ በማስማት መንግሥትን ያለማቋረጥ መገዳደር አለበት፡፡ ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት ወያኔ ጠንቀኛ ሰነዱን ካዘጋጀበት ዓላማና መንፈስ አንፃር የጐሣ ስብስቦች እንጂ የፖለቲካ ድርጅቶች ባለመኖራቸው ያደራጀናል ብለን የምንጠብቀው የፖለቲካ ማኅበር አለመኖሩን ተገንዝበን እንደ እስክንድር ባሉ (የሥልጣንና የዝርፊያ አጀንዳ የማይስማማቸውን ይዘን) በምንተማመንባቸው ግለሰቦች ዙሪያ እየተሰባሰብን መላ አገራችንን የሚሸፍን አደረጃጀት መፍጠር እንችላለን፡፡ ለዚህም የግድ የመንግሥትን ቡራኬ መጠበቅ የለብንም፡፡ ያለ ዋጋ የሚገኝ ነገር አለመኖሩንም መገንዘብ ያሻል፡፡ ከዚህ ቀደም ሕዝብ እጅግ በተበታተነ መልኩ እዚህም እዚያም ሲያሳይ የነበረው ኩርፊያና ተቃውሞ ለአቅመ ትግልነት ሳይበቃ ተበትኖ ቀርቷል፡፡ የተከፈለውን መሥዋዕት ማቅለሌ አይደለም፡፡ በጭራሽ፡፡ የትግል ቅርፅ ይዞ ተደራጅቶ ባለመመራቱ ሕዝቡ የለውጡ ባለቤት ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ውጤቱንም አሁን እያየነው ነው፡፡ ትግል ድርጅትን ይጠይቃል፡፡ ለመደራጀት ደግሞ የግድ የፖለቲካ ፓርቲ አያስፈልገንም፡፡ ለሥልጣን የምንወዳደር ፖለቲከኞች መሆንም አይጠበቅብንም፡፡ በማኅበረሰብ ተቋምነት ማካሄድ ይቻላል፡፡ አገራዊ የመደራጀት እንቅስቃሴው የመንግሥት አካላት ትብብር ይኑረውም/አይኑረውም በሕጋዊና ሰላማዊ መልክ መመራቱን ሁላችንም አምነንበትና መርሀችን አድርገን ልንይዘው ያስፈልጋል፡፡

ይህን የመደራጀቱን ጉዳይ ቅድሚያ ስንሰጥ ብቻ ነው ወደ ዋናው የለውጥ ምዕራፍ ሳይገባ ከሀዲዱ የወጣውን ‹ለውጥ› ፈር አስይዘን መቀጠል የምንችለው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን እንደ ‹ቪዥን ኢትዮጵያ› እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያሳስባችሁ እንደ ‹የክፍላተ ሀገራት ኅብረት› ያላችሁ ስብስቦችና ምሁራን በተለይም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ የሕግ ሊቃውንት (እስከዛሬ የተደረጉ ሙከራዎች ካሉ እሰየው!ያንን መልክ ማስያዝ ነው) መክራችሁና ዘክራችሁ በዚሁ የሽግግር ወቅት መነሻ የሚሆን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ረቂቅ ከነመግለጫው ባስቸኳይ አዘጋጅታችሁ ሕዝብ እንዲወያይበት ማድረግ ይጠበቅባችኋል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ መቼም ቢሆን አገርን ያለአንዳች በጎ ሰው አይተዋትምና ምስክር የሆኑ እንደ ጋሼ መሥፍን ወ/ማርያም፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ያሉ ዐዋቂዎችን/ዋነኞቻችንን ጤናውን ሰጥቶ በሕይወት ያቆይልን፡፡ በየትኛውም እምነት በኩል ያላችሁ ንጹሕ ልብ ያላችሁ፣ ለእውነት ያደራችሁ፣ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ የማትሉ፣ ፊት ዓይታችሁ የማታዳሉ፣ ከሁሉም በላይ ለሰው ልጅነት ትልቅ ክብርና ዋጋ የምትሰጡ እንዲሁም ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን የምታፈቅሩ እግዚአብሔር የሚያውቃችሁ እኛ የማናውቃችሁ አባቶችና እናቶች በያላችሁበት በኣት እንደ ራሔል እምባ መልስ የሚያስገኝ ጸሎት በማድረግ ትጉልን፡፡ አሁን የመጣብን አገር ፈታኝ ‹‹ዘመድ›› የምንገላገለው ሕዝብ ተደራጅቶ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ሕይወት ኗሪ ከመንቀሳቀስ በላይ በእውነተኛ ፆምና ጸሎትም ስንታገዝም ነው፡፡

ወከንቱ ተአምኖ በሰብእ፡፡ እንዳለ መጽሐፍ በሰው መታመን ከንቱ መሆኑን ተረድተን በእግዚአብሔር አምነን ለአገራችን የድርሻችንን ባግባቡ እንወጣ፡፡

Filed in: Amharic