>

አዲስ አበቤን፤ ነፃ የማውጣት ፍኖተ ካርታ!  (ቹቹ አለባቸው)

አዲስ አበቤን፤ ነፃ የማውጣት ፍኖተ ካርታ!
 ቹቹ አለባቸው
ትግላችን መልክ እየያዘ ነው፡፡ መልክ መያዝ ብቻ ሳይሆን፤ጥልቀትና ብስለት እየተላበሰ ነው፡፡ በተለይም በቅርቡ ኦህዴድ/አዴፓ የፈጠረው ብልሽት፤ ትግሉን በብስለትና በተደራጀ ምልኩ የመምራትን አስፈላጊነት ከመቸውም ጊዜ በላይ አጉልቶ አውጥቶታል፡፡ አሁን ለደረስንበት የትግል ምዕራፍ በሁሉም ክልለሎች የሚገኙ አክቲቪስቶች ድርሻቸው ትልቅ ቢሆንም፤ በተለይም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የአማራ አክቲቪስቶች የተጫወቱት ሚና በታሪክም ተመዝግቦ ሊኖር የሚችል ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ኦህዴድ/አዴፓን ጥሩ አድርጎ ማንነቱን በማሳየት፤ሰሚ አጥቶ የነበረውን የጌዲዮ ህዝብ መከራ አለም እንዲሰማውና ፤ የደኢህዴን ሊ/ምንበርና ዶ/ር ጠሚ አብይ አህመድ ቦታው ድረስ ተጉዘው የህዝቡን መከራ በአይናቸው እንዲመለከቱ ለማድረግ የተፈጠረው ጫና ቀላል አይደለም፡፡
ሌላው የአማራ አክቲቪስቶች ከሰሩትና ውጤት ካመጣው ነገር አንዱ ፤”አዲስ አበበባ የአዲስ አበቤዎች” እንጅ የማንም አይደለችም የሚለው መፎክር ነው፡፡ይሄን ጉዳይ በስፋና ጥልቀት ሰርተንበታል፡፡ እኔ እስከማስተውስ እኔ እንኳን ይሄን ጉዳይ  አቶ ጀዋር ወደ ባህርዳር መርቶት ለመጣው ቡድን በግልጽ ነግሬው ነበር፡፡ ወንድም ጁሀርም ይሄንን ጥያቄ “በከፊል ነው የምቀበለው” ብሎ ነበር፡፡ ጀዋር በወቅቱ  “አዲስን ለአዲስ አበቤዎች” የሚለውን ጥያቄ፤ በከፊል ነው የምቀበለው ማለቱ፤አንድ የገባው ነገር ስለነበረ ነው፡፡ይሄውም የአዲስ አበባ ህዝብ ፖለቲካ አይገባውም፤ያልነውን ይቀበላል ከሚል የተሳሳተ ሃሳብ በመነሳት ነው፡፡
እኛም የአቶ ጀዋርን መልስ ካወቅን በኋላ፤የራሳችንን ስራ መስራ እንዳለብን አቅደን መንቀሳቀስ ነበረብንና አደረግነው፡፡ በእኔ እምነት አዲስ አበባና አዲስ አበቤዎች ራሳቸውን ነጻ ለማድረግ ከፈለጉ፤በሦስት ምእራፍ የተከፈለ ትግል ማካሄድ እንደሚኖርባቸው በማመን ቀደም ሲል ጀምሬ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር አወራ ነበር፡፡ አሁን ነገሮችን ሳያቸው በዚሁ መልኩ እየሄዱ ይመስላል፡፡እነዚህ ን እሳቤዎቸን በእሩ እንደሚከተለው አነሳለሁ፡፡
ምዕራፍ አንድ፡- የአዲስ አበባን ህዝብ በተለይም ወጣቱን ማንቃት !
የአዲስ አበባ ህዝብ ጠንካራ ነው፤ አይደክመውም፤ 27 አመታት ሙሉ ከትግራይና ኦሮሚያ በሚላኩለት ምስለኔዎች ነው ሲገዛ የኖረው፡፡  በቃ ኢህአዴግ ካድሬ ከየትም ያመጣል አዲስ ትቀበላለች፡፡ ይሄ የተራዘመ ዝምታው ለሌላ ነገር እንዲታጭ አደረገው፡፡ ስለሆነም የመጀመሪያው ስራ ይሄንን በአዲስ አበቤዎች ዘንዳ የከረመውንና እስቅርብ ጊዜ የሚታየውን የግድ የለሽነት አመለካት መስበርና፤ ህዝቡ ለመብቱ እንዲነሳ ማድረግ አስፈላጊ ነበር፡፡ በዚህ መልኩ የአማራ አክቲቪስቶችና አንዳንድ የአዲስ አበባ ብርቅየ ልጆች  በሰሩት እልክ አስጨራሽ ስራ ውጤት መመዝገብ ችሏል፡፡ አሁን አዲስ አበባ የትግል መሪና ባለቤት አግኝታለች ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ስለሆነም ምዕራፍ አንዳንድ፤አንዳንድ የተስረከረኩ ነገሮች ባይጠፉም፤ ከሞላ ጎደል በጥሩ ሁኔታ ሂዷል ማለት ነው፡፡ ቀሪ ስራዎቹን( በተለይም ያልነቁትን ማንቃት) በቀጣዮቹ ምእራፎች አብሮ ደርቦ መስራታ ያስፈልጋል፡፡
ምዕራፍ ሁለት፡- ሙሉ የስልጣን ባለቤት መሆን!
ከላይ እንዳነሳሁት አዲስ አበባ፤ ላለፉት 27 አመታ ተገዝታ እንጅ ገዝታ አታውቅም፡፡ አዲስ አበቤዎች በ1997 ዓ.ም ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር እድሉን አግኝተው የነበረ ቢሆንም፤ ድላቸውን ማጣጣም ሳይችሉ ቀሩ፤ ኢህአዴግ አበላሸባቸው፤ ከዚያ ወዲህ አዲስ አበቤ ፖለቲካ ለምኔ ብሎ ቁጭ አሉ፡፡ ለዚህ ዋነኛው መንስኤ ኢህአዴግ ቢሆንም፤የአዲስ አበባ ህዝብ የትግል ወኔ መዳከም፤ ተስፋ መቁረጥ፤የወጣቱ ነገሩን ቸላ ማለት ወዘተ…ቀላል ግንት የሚሰጣቸው ድክሞቶች አይደሉም፡፡ እነዚህ ድክመቶች ደግሞ፤ ለመጣ ለሄደው የኢህአዴግ ካድሬ፤ ሰጥ ለጥ ብሎ ሲገዛ የኖረውን አዲስ አበባና አዲስ አበቤ፤ ለሌላ ሙሽራት አሳጫቸው፡፡ ይሄውም ፤ “አዲስ አበባ የኦሮሞናት” የሚል መታጨት፡፡
እድሜ ለኦህዴድ እንጅ፤ስልምልም ሲል የከረመውን የአዲስ አበቤ ትግል ወደ ትልቅ ምእራፍ አሸጋገረው፡፡ዛሬ አዲስ አበቤ ነገሩ ገብቶታል፤በአዲስ አበቤ ማንነቱ ላይ የተቃጣ  አደጋ እንዳለ ሁሉም ተገንዝቦታል፡፡ ስለሆነም በአንድ ድምጽ በቃ! ብሎ መነሳት ቻለ፡፡ ይሄ የኦህዴድ ስራ ለአዲስ አበቤዎች መንቃት በጣም ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል፡፡
ነገር ግን መንቃት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ አዲስአበባና አዲስ አበቤዎች፤ሙሉ ነጻነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በተለይም አዲስ አበባን ተረክቦ ማስተዳደር፤ አዲስን ነዋሪዎቿ ብቻ እንዲመሯት ማድረግ፤ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ጉዳይ ወሳኙ የአዲስ አበባ ነዋሪ እንጅ ሌላ ማንም እንዳልሆነ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም፤የአዲስ አበባ ህዝብ አንድም ምርጫ ተሎ ተካሂዶ አዲስን የአዲስ አበባ ነዋሪ፤ ግን ደግሞ የህዝብ ይሁንታ ያገኘ፤ እንዲመራት መደረግ አለበት፡፡ ነገር ግን ኦህዴድ ስላልተመቸው እና ነገር ስለተበላሸበት ለማገገምያ ጊዜ ለመግዛት በማሰብ ምርጫውን ለማራዘም መፈለግ ካለ ደግሞ፤የአዲስ አበባ ህዝብ፤የአዲስ አበባን መንግስታዊ ስልጣን በህጋዊ መንገድ ከመንግስት ተረክቦ በባላደረ አስተዳደር መምራት አለበት፡፡ምክንያቱም አሁን ያለው አስተዳደርም በህዝብ የተወከለ ህጋዊ ተመራጭ አይደለም፡፡ መንግስት ነው የወከለው፤ስለሆነም መንግስት ለአዲስ አበባ አስተዳደር የሰጠውን ስልጣን በመቀማት ለአዲስ አበቤዎች በህጋዊ መንገድ ማስተላለፍ ይችላል፡፡ ይህ  አዲስንና አዲስ አበቤዎችን ነጻ የማውጣት፤ ሁለተኛው የትግል ምእራፍ በፍጥነት በጀመር ጥሩ ነው እላለሁ፡፡
—–==========//////////—=======
ምዕራፍ ሶስት፡- ሕገ-መንግስት እንዲከበርና እንዲሻሻል የመጠየቅ ምእራፍ!
አዲስ አበቤዎች ምእራፍ ሁለትን ተሎ አጠቃልሉና ወደ ሦስተኛው የነጻነት ምእራፋችሁ ተሸጋገሩ፡፡እውነተኛ የስልጣን ባለቤትነታችሁ የሚረጋገጠው በዚህ ምእራፍ የምታደርጉት እልህ አስጨራሽ ትግል ነው፡፡ በዚህ ምእራፍ ትኩረት ሰጥታችሁ ብትታገሉባቸው የምላቸው ነጥቦች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡-
 
1. ሕገ-መንግስት ይከበር፡- 
ይሄም ማለት አዲስ አበባ ፤የነዋሪዎቿ እና የፌደራል መንግስቱ ዋና መቀመጫ፤ እንጅ የላሌ የማንም አይደለችም በሉ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም፤ ኦህዴድ መቀመጫውን ቀደም ሲል በራሱ ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት፤ወደ ናዝሬት እንዲመለስ መጠየቅ ማለት ነው፡፡ የኢህአዴግን በቅንጅት መሸነፍ ተከትሎ፤ በመለስ ቀጭንት ትእዛዝ ሰጭነት ናዝሬት ወደ አዲስ የተመለሰው ኦህዴድ፤ አዲስ አበባን ለቆ በህጋዊ ቦታው ሆኖ ኦሮሚያን እንዲያስተዳደር መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ አዲስ ነገር አይደለም፤ህገ መንግስታዊም ነው፤ተደርጎም ነበር፡፡ስለሆነም እዝች ላይ ጠንከር ያለ ትግል ስፈላጊ ነው፡፡ በኔ ግምት ካሁን በኋላ፤ የኦህዴድ አዲስ መስፈር ፤ አይደለም ለአዲስ አበባና ለነዋሪዎቿ፤ ለኦህዴድ ጭምር ምቾት የሚሰጣቸው አይመስለኝም፡፡ ኦህዴድ ወደ ናዝሬት ቢያመራ ናዝሬትን ለማልማትም ያስችለዋል፡፡
 
2. “ልዩ ጥቅም” መስጠትና “ልዩ ጥቅም መቀበል”፡-
ይች አዲስ አበባ ለኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ትሰጣለች የምትል ወሬ፤እንደገና ተፈትሻ መልክ ካልያዘች ችገር ማምጣቷ አይቀርም፡፡ በነገራችን ላይ ጀዋርና ቡድኑ ባ/ዳር በመጡ ጊዜ፤ይሄ “ልዩ ጥቅም” የሚባል ነገር፤ለትልቁ ኦሮሞ ህዝብ አይጠቅመውምና  ብትተውት ብየ ምክር ለግሸ ነበር፡፡ ነገር ግን እነ ጅዋር ምክራችንን ከመስማት ይልቅ፤ጉዳዩን “ከልዩ ጥቅም” ወደ አዲስ” ኬኛ” አሳደጉት፡፡ ብቻ በአንድ ነገር አምናለሁ፡፡ ይሄውም አዲስ አበባ በከተመዋ ዙሪያ የሚኖሩ አ/አደሮችን ደህንት መጠበቅ አለባት፡፡ ይሄም ማለት አ/አደሮቹ ከአዲስ አበባ የሚያገኙት የተወሰነና ተገቢነት ያለው ጥቅም መኖር አለበት ማለቴ ነው፡፡ ይሄውም በልማት ስም ለሚፈናቀሉት አ/ አደሮች ተገቢውን ማቋቋሚያ መስጠት አለባት ማለት ነው፡፡ ከዚህ ቧላ አ/አደሩ የተሠተውን ብሩን እንዳያባክንና ልማት ላይ እንዲያውል ማድረግ ደግሞ የኦህዴድ ኋላፊነት ነው፡፡ አ/አደሩ በካሳ ስም አንዴ ብሩን ከዛቀ በኋላ ፤ብሩን ሲጨርስ እንደገና መሬቱ ትዝ እያለው አዲስ አበባን እረፍት መንሳት ውስጥ እንዳይገባ፤የክል መንግስት ይሄንን ተገቢነት የሌለው ጥያቄ አብሮ ከማስተጋበት ይልቅ፤ አ/አደሮቹ የተሰጣቸውን ገንዘብ ተጠቅመው እንዲቋቋሙ ቢያግዛቸው ይሻላል፤ አብሮ አላቃሽ መሆን አይገባም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት፤አዲስ አበባ የምትደግፈው በዙሪያዋ ላሉና ጉት ለደረሰባቸው ገበሬዎች ብቻ እንጅ ለመላ ኦሮሞ መሆን የለበትም፡፡ እንደዛ ከሆነ ከጅማና አርሲ አ/አደር ይልቅ፤ የሰሜን ሽዋ( አማራ) እና የጎጃም ገበሬ ለአዲስ ይቀርባል፤ይገብራል፡፡ ይሄ ጉዳይም መታየት አለበት፡፡
ሌላው አዲስ አበባና አዲስ አበቤዎች፤ከህገ መንግስት ይሻሻል አንጻር ቢያነሱት ጥሩ ነው የምለው፤ አዲስና ነዋሪወቿ ከኦሮሚያ ክልል “ልዩ ጥቅም ” ይገባናል  በሉ የሚል ነው፡፡ ልብ በሉ አዲስ ለኦሮሚያ፤የስራ እድል በመፍጠር፤መሰረተ ልማት በማቅረብ ፤ዘመናዊነትን በማዳረስ፤ብቻ በብዙ ነገሮች በማቅረብ እየደገፈች ነው፡፡ አዲስ ይሄን ሁሉ ድጋፍ ስታደርግ ከደሀው ነዋሪዎቿ በምትሰበስበው ገቢ ነው፡፡ስለሆነም አዲስ፤ በምታካሂደው የልማት እንቅስቃሴ ምክንያት ለሚጎዱ የኦሮሞ ገበሬች ብቻ ድጋፍ ማድረግ ያለባት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአንጻሩ ደግሞ ከተማዋ ከሌሎች ክልሎች በተለየ ለኦሮሚያ ክልል የምታበረክተውን እተዋጽኦ አስልታ፤ የኦሮሚያ ክልል” ልዩ ጥቅም ” እንዲያስጠብቅላት ፤ይሄም በህገ-መንግስት ማሻሻያ ሃሳብ እንዲካተትላት መጠየቅ አለባት ባይ ነኝ፡፡
ይሄው ነው!
Filed in: Amharic