>
5:13 pm - Wednesday April 20, 4253

"ህዝቡ ግፈኞችን "አይሆንም!" ማለትን፤ እየተደራጀ ሃሳቡንና እምነቱን መግለፅን መልመድ አለበት!!"' (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)

 

“ህዝቡ ግፈኞችን “አይሆንም!” ማለትን፤ እየተደራጀ ሃሳቡንና እምነቱን መግለፅን መልመድ አለበት!!”‘

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

 

በማህሌት አብዱል

ከ ዛሬ 81ዓመት በፊት አዲስ አበባ ከተማ ነው የተወለዱት። ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እትጌ መነን ተምረዋል። ከ1955 ዓ.ም ጀምሮ በለንደንና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ትምህርት ተከታትለዋል። እንዲሁም በመምህርነት አገልግለዋል። ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ መንግሥታትን በመተቸትና ሂስ በመስጠት የሚታወቁ የፖለቲካ ሰው ናቸው። ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲን ከመሰረቱት ሰዎች አንዱ ናቸው። በተለይም ኢህአዴግን ፊት ለፊት በመቃወም ይታወቃሉ።የዛሬው የዘመን እንግዳችን አንጋፋው ምሁርና የሰብዓዊ መብት ተማጓች ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም። መኖሪያ ቤታቸው በመገኘት ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው እናቀርበዋለን።

አዲስ ዘመን፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣን ያነባሉ?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ኢህአዴግ ከገባ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ አንብቤ አላውቅም። ለመጨረሻ ጊዜ የጻፍኩትም ሆነ ያነበብኩት ለአቶ መለስ ዜናዊ ግልጽ ደብዳቤ ስፅፍለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስለምን ጉዳይ እንደፃፉ ያስታውሳሉ?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ወደ ውጭ ለመሄድ ቪዛ ፍለጋ ሳመለክት የደርግ ደህንነት ውስጥ አለመኖርህን፤ እዳ እንደሌለብህ አስመስክር የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን ካልመለስኩ እንደማይሰጠኝ ነገሩኝ። እኔም በራሴ ላይ የምመሰክረው ነገር እንደሌለ፤ ግን ደግሞ እነሱ መረጃ ካላቸው እንዲያስመሰክሩ መልሼ ጽፌላቸው ነበር።

አዲስ ዘመን፡- እናም ይሄ ምላሽዎ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ተስተናግዶ ነበር?

ፕሮፌሰር፡- አዎ ወጥቷል። እናተም ብትሆኑ መንግሥት የአቋም መዋዠቅ ውስጥ ሲገባ ትበረታላችሁ። መንግሥት ሲነቃነቅ አቅም ታገኛላችሁ። እናም ምላሼን የሰጡት ደርግ እንደወረደ ሰሞን በመሆኑ ሊወጣልኝ ችሏል። ከእኔ በኋላ ደግሞ አቶ መለስም ምላሹን ሰጥቶኛል። እኔም ዳግመኛ ለምላሹ ምላሽ ሰጥቼዋለሁ። ከዚያ ወዲህ ከአዲስ ዘመንም ሆነ ከሌሎቹ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ጋር ያለኝ ግኑኝነት ተቋረጠ።

አዲስ ዘመን፡- ይሄ ብቻ ነው ምክንያትዎ ወይስ ሌላ ነገር አለ?

ፕሮፌሰር፡- ከዚያ በኋላ ደግሞ ምን ለማድረግ ነው የማነበው? ምን አዲስ ነገር ለማግኘት? ደግሞም ከእናንተ ይልቅ የግሉ ፕሬስ ደፋር ፅሑፎችን ይዞ ስለሚቀርብ አነባለሁ። የግሉ ሚዲያ ወኔ አለው፤ እናንተ ጋር ያለው የእንጀራ ጉዳይ ብቻ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ሆኖ በድሮ መነፅር እያዩ መፍረድ አይከብድም?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ድሮም ሆነ ዛሬም ያው ነው። ዛሬ ተለወጠ ተብሎ ነገ እዚያው መስመር ውስጥ ነው ያላችሁት። ለእውነት ብላችሁ ሳይሆን የምትሠሩት ለእንጀራ ብላችሁ ነው። ድሮ ድሮ እነብርሃኑ ዘርይሁን በነበሩበት ወቅት አምደኛ ሆኜ እፅፍ ነበር። ነገር ግን ጥቂት እንደፃፍኩ በፅሑፌ የከፋቸው ሰዎች እንዲቆም አደረጉ። እኔም አቆምኩ።

አዲስ ዘመን፡- ስርዓቶቹን የሚነቅፉ ፅሑፎች ነበር የሚፅፉት?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- አዎ፤ ያልተነቀፈ ስርዓት እኮ ይበሰብሳል። ይወድቃል። እኛም አብረን እንበሰብሳለን።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ካሳለፏቸው ሦስት መንግሥታት ውስጥ በየትኛው ዘመን ነው የመገናኛ ብዙሃን ደፋር ፅሑፍ የፃፉት?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ሚዲያው ልክ እንደፖሊሲው፣ እንደጦር ሰራዊቱ ሁሉ የአገዛዙ መሳሪያ ነው። እኛም እስከዛሬ ስንታገል የነበረው ሚዲያው ነፃ እንዲሆን ነው። ሚዲያው በመንግሥት ቁጥጥር ስር መሆኑ፤ የምትተዳደሩት በመንግሥት ባጀት መሆኑ፤ሐላፊዎችም የሚሾሙትና የሚሻሩት በመንግሥት መሆኑ ነፃና ገለልተኛ እንዳይሆን አድርጎታል። እነ ቢቢሲና ሲኤንኤን ምንአልባትም ድጎማ ሊደረግ ቢችልም እንኳ ራሳቸውን የቻሉ ናቸው። እዚህ አገር ግን ድፍን ያለነገር ነው ያለው። ሁሉም ነገር የመንግሥት ስለሆነ መንግሥት መቆጣጠሩ አይቀርም። ደግሞስ የትኛው መንግሥት ነው ገንዘብ እየከፈለ መሰደብና መወቀስ የሚፈልገው? እናንተም ደመወዝ መንግሥት ስለሚከፍላችሁ ብቻ የሱ አፍ ለመሆን ፈቃደኛ ሆናችሁ ነው የምትገቡት። አብዛኛው ባለሙያ እበላ ባይ ነው። ሁላችሁም ወፍራም እንጀራ ለማግኘት ነው ጥረታችሁ። በበላችሁት መጠንም ይበልጥ ታመሰግናላችሁ። ካላመሰገናችሁ ግን እንጀራው ይቀጥናል። ያ ነው እውነታው።

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ለዶክተር ዐብይ ጥሩ የሆነ አስተያየት ሰጥተዋል። ከዶክተር ዐብይ ምን የተለየ ነገር ቢያዩ ነው ባልተለመደ ሁኔታ የድጋፍ እስተያየት የሰጡት?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- የተለየ የሆነው ነገር የወያኔ አገልጋዮች ሎሌዎች ሆነው ከዚያ አስተሳሰብ አፈንግጠው መውጣታቸው ነው። ራሳቸውን ነፃ አድርገው በነፃነት ለመምራት መነሳታቸው ከሌሎቹ የተለየ ያደርጋቸዋል። በየመድረኩ የሚናገሩትም በጣም የሚያስደንቅ ንግግር ሆኖ ነው ያገኘነው። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ችሎታ ያላቸው ከመሆናቸው በላይ ዋናው ነገር ወኔያቸው፤ ራሳቸውን ነፃ አድርገው ሌላውን ነፃ ማድረጋቸው፤ እስረኞችን መፍታታቸውና ሌሎችም ተግባራት አስደሰተኝ። እናም እውነት መሰለኝ። ግን ሁልጊዜም እውነት እየመሰለን ነው የምንታለለው። ኋላ ላይ አጠራጣሪ ነገሮች ይመጣሉ።

አዲስ ዘመን፡- ጥርጣሬ ውስጥ ካስገባዎት ጉዳይ አንዱ ከአዲስ አበባ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል። ምክንያትዎ ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- በህገ መንግሥቱ እንደተቀመጠው አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት። እናንተ ግን በጋዜጣችሁም ሆነ በሌሎች መገናኛ ብዙኃን ፊንፊኔ ወይም ሸገር ምናምን እያላችሁ የምትፅፉት ለምንድን ነው? ለአዲስ አበባ በህግ ከተሰጠው ስያሜ ውጪ ለምን በሌላ ስም ትጠራለች? አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ነች። በዓለም ትታወቃለች። ማንም ቡድን የሰከረለት ተነስቶ የክርስትና ስም ለአዲስ አበባ ሊያወጣላት አይችልም። መንግሥት መፍቀድ የለበትም። ህዝብም መፍቀድ የለበትም። ባለቤት የሚባለው ነገር አይገባኝም። እኔ የማምነው ማንም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ መሬት ላይ ባለቤት ነው። ምክንያቱም አንድ ነገር ቢመጣ የሚሞትላትና ደሙን የሚያፈስላት ሁሉም ዜጋ ነው። ማንም መጥቶ የዚህ ጎሳ ነኝ ብሎ ሊያፈናቅለኝ አይችልም። ዋናው ነገር ህግ አለ፤ ግን የሚያስፈፅመው ነው የጠፋው። የአዲስ አበባን ለአንድ ጎሳ የሰጠው ህግ የለም። ደግሞስ ያ ጎሳ የኔ ነች የሚልበት ምን መሰረት አለው? ምን ታሪክ አለው? ምንም!

አዲስ ዘመን፡- እንደሚያውቁት በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የዜግነትና የብሄር ፖለቲካ የሚሉ ሁለት ፅንፍ የወጡ አስተሳሰቦች የገነኑበት ወቅት ነው። እርስዎ ለኢትዮጵያ ምን ይበጃታል ይላሉ?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- እንዳልሽው እኔም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ ፅፌያለሁ። እናንተ ጋዜጠኞች ስትባሉ ግን አታነቡም። ችግራችሁ ይሄ ነው። ወደ አነሳሽው ፖለቲካ ስንመጣ የጎሳ ፖለቲካ ኢትዮጵያን ለመበተን ይረዳ እንደሆነ እንጂ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ በፍፁም አይረዳም። ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የሚረዳው የዜግነት ፖለቲካ ነው። ትክክለኛውም መንገድ ይሄ ነው። ዜግነት ማለት አንቺም እኔም ጎሳ፣ ፆታ፣ ሃይማኖት ሳይለይ እኩል ደረጃ ላይ በአንድ ህግ ያቆመናል። መጀመሪያ ነገር ጎሳ ሰው አይደለም። ዓይን፣ ጆሮ፣ ልብ፣ አንጎል የለውም። ዝም ብሎ የጅምላ ስም ነው። ልትናገሪው አትችይም፣ ልትሰሚው አትችይም። ዜጋ የሆነ እንደሆነ በሰው ነው የምንነጋገረው። ስለአንድ ግለሰብ ነው የምንነጋገረው። ጎሳ ደግሞ አንድ ግለሰብ አይደለም። ጅምላ ነው። አሁን ኦሮሞ ብቻውን እንኳ ብንወስድ የሽዋ፣ የወለጋ፣ የጅማ ኦሮሞ እያልን እንከፋፍለዋለን። አማራም እንዲሁ ወሎዬ፣ ጎንደሬ፣ ጎጃሜ፣ መንዜ እያልን እንለያለን። በዜግነት ስንሄድ ግን አንድ ኢትዮጵያዊ ነው። የትም ቢሄድ ኢትዮጵያዊ ነው። ማደግ፣መተባበርና መስማማት የምንችለው በአንድ ህግ ሊሚያፋቅረን የሚችለው የዜግነት ፖለቲካ ነው። ከዚያ ውጪ ያለው ዝም ብሎ ትርምስ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ለአገሪቱ ስጋት ይሆናል ብለው ያምናሉ?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ስጋት እየሆነ ነው፤ አደጋም እየፈጠረ ነው። መቼ አደጋው ይመጣል? መቼ ሰዎች ተናደው ድንጋይ ይወረውራሉ? ጥይት ይተኩሳሉ? በሚል ስጋት ውስጥ እኮ ነው ያለነው። ነገሮቹ እየተጋገሉ ነው። እናም እስከምን ድረስ መሄድ እንደሚችልና ማንስ ሊያቆመው እንደሚችል አላውቅም። ጥርጣሬ ላይ ነው ያለነው የምልሽ በዚህ ምክንያት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ የዚህች አገር ችግር መድሃኒት የለውም ብለው ነው የሚያምኑት?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- መድሃኒትማ አለው። አንዱ መድሃኒት ህዝቡ ነው። አይሆንም ብሎ እየተደራጀ ሃሳቡን እምነቱን መግለፅ አለበት። አሁን ግን እቤቱ ተኝቶ አደጋ እና ሽብር እስኪመጣ ድረስ እየጠበቀ ነው። ሲመጣ ግን አይቀርለትም። ሲመጣ ከየቤቱ እና ከያለበት ሲያፈናቅሉት እዬዬ እያለ ይወጣል። ከሆነ በኋላ ምንም ማድረግ አይችልም። ስንት ሺ ህዝብ ነው የተፈናቀለው? ህዝቡ መድረሻ ያጣው አስቀድሞ መተባበር ባለመቻሉ ነው። ከዚህ የበለጠ ምን ይመጣበታል? ስለዚህ እምቢ ማለት አለበት። ለብቻው ቆሞ እምቢ ማለት ግን ውጤት ስለማይኖረው በጋራ ሊቆም ይገባዋል። የዜግነት ፖለቲካ አንዱ ጥቅም ይህ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አንድ ወቅት ላይ አማራ የሚባል የለም ብለው ነበር። ይህንን ያሉበት ታሪካዊ ዳራ ምንድን ነው? 

ፕሮፌሰር መስፍን፡- አሁንም ቢሆን አማራ የሚባል ጎሳ የለም። ይህንን ለማለት የደፈርኩት ካነበብኩትና ካጠናሁት ተነስቼ ነው። ይህንን ደግሞ ከፃፍኳቸው ፅሑፎች አንብበሽ መረዳት ትችያለሽ። እኔ የማውቀውና ያደኩበት እውነታ ይሄ ነው። እናትና አባቴ አማራ ነህ እያሉ አላሳደጉኝም። ይሄ አማራ ነው ሲባልም ሰምቼ አላውቅም። እኔ የማውቀው አማራ የሚባለው ክርስቲያን ነው። በጎንደርም ሆነ በጎጃም በወሎ አማራ የሚለው ቃል የክርስትና እምነት ተከታይ መሆንን ነው የሚያሳየው። በጎንደርም ሆነ በአርማጭሆ በአማራነት ተጮሆ ምንም የተገኘ ነገር የለም። ያላደኩበትን ያላወቅሁትን ነገር ልናገር አልችልም። ተመራምሬ ያገኘሁት ነገር እንጂ የራሴ ሃሳብ አይደለም።

አዲስ ዘመን፡- መግባቢያ ቋንቋቸው በራሱ አማርኛ መሆኑ አማራ ለመባል አያበቃቸውም?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- አያበቃም። ቋንቋ ጎሳ አይሰጥሽም። ለምሳሌ አሜሪካን አገር ጥቁሮች አሉ። እንግሊዝኛ ነው ቋንቋቸው ግን እንግሊዞች አይደሉም። በላቲን አሜሪካም እንዲሁ ፖርቹጊዝና ስፓኒሽ የሚናገሩ ብዙ ጥቁሮች አሉ። ምን ሊባሉ ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ ቋንቋ ከሚናገሩ ቤተሰቦች የተፈጠሩ ዜጎች አሉ። የቤተሰቦቻቸውን ቋንቋ አያውቁም። አማርኛ ነው የሚናገሩት በአማርኛ እየተግባቡ ነው ያደጉት። ሌላው ቢቀር በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ወያኔ ወደ ኤርትራ የላካቸው ኤርትራውያን ቋንቋቸውንም አገራቸውንም አያውቁም ነበር። ስለዚህ ቋንቋ ጎሳ አይሰጠንም።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ይህንን ቢሉም በአሁኑ ወቅት የአማራ ብሄርተኝነት ጉዳይ የምንነጋገረው…

ፕሮፌሰር መስፍን:- ስለአንድ ግለሰብ ነው የምንነጋገረው። ጎሳ ደግሞ አንድ ግለሰብ አይደለም። ጅምላ ነው። አሁን ኦሮሞ ብቻውን እንኳ ብንወስድ የሽዋ፣ የወለጋ፣ የጅማ ኦሮሞ እያልን እንከፋፍለዋለን። አማራም እንዲሁ ወሎዬ፣ ጎንደሬ፣ ጎጃሜ፣ መንዜ እያልን እንለያለን። በዜግነት ስንሄድ ግን አንድ ኢትዮጵያዊ ነው። የትም ቢሄድ ኢትዮጵያዊ ነው። ማደግ፣መተባበርና መስማማት የምንችለው በአንድ ህግ ሊሚያፋቅረን የሚችለው የዜግነት ፖለቲካ ነው። ከዚያ ውጪ ያለው ዝም ብሎ ትርምስ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ለአገሪቱ ስጋት ይሆናል ብለው ያምናሉ?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ስጋት እየሆነ ነው፤ አደጋም እየፈጠረ ነው። መቼ አደጋው ይመጣል? መቼ ሰዎች ተናደው ድንጋይ ይወረውራሉ? ጥይት ይተኩሳሉ? በሚል ስጋት ውስጥ እኮ ነው ያለነው። ነገሮቹ እየተጋገሉ ነው። እናም እስከምን ድረስ መሄድ እንደሚችልና ማንስ ሊያቆመው እንደሚችል አላውቅም። ጥርጣሬ ላይ ነው ያለነው የምልሽ በዚህ ምክንያት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ የዚህች አገር ችግር መድሃኒት የለውም ብለው ነው የሚያምኑት?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- መድሃኒትማ አለው። አንዱ መድሃኒት ህዝቡ ነው። አይሆንም ብሎ እየተደራጀ ሃሳቡን እምነቱን መግለፅ አለበት። አሁን ግን እቤቱ ተኝቶ አደጋ እና ሽብር እስኪመጣ ድረስ እየጠበቀ ነው። ሲመጣ ግን አይቀርለትም። ሲመጣ ከየቤቱ እና ከያለበት ሲያፈናቅሉት እዬዬ እያለ ይወጣል። ከሆነ በኋላ ምንም ማድረግ አይችልም። ስንት ሺ ህዝብ ነው የተፈናቀለው? ህዝቡ መድረሻ ያጣው አስቀድሞ መተባበር ባለመቻሉ ነው። ከዚህ የበለጠ ምን ይመጣበታል? ስለዚህ እምቢ ማለት አለበት። ለብቻው ቆሞ እምቢ ማለት ግን ውጤት ስለማይኖረው በጋራ ሊቆም ይገባዋል። የዜግነት ፖለቲካ አንዱ ጥቅም ይህ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አንድ ወቅት ላይ አማራ የሚባል የለም ብለው ነበር። ይህንን ያሉበት ታሪካዊ ዳራ ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- አሁንም ቢሆን አማራ የሚባል ጎሳ የለም። ይህንን ለማለት የደፈርኩት ካነበብኩትና ካጠናሁት ተነስቼ ነው። ይህንን ደግሞ ከፃፍኳቸው ፅሑፎች አንብበሽ መረዳት ትችያለሽ። እኔ የማውቀውና ያደኩበት እውነታ ይሄ ነው። እናትና አባቴ አማራ ነህ እያሉ አላሳደጉኝም። ይሄ አማራ ነው ሲባልም ሰምቼ አላውቅም። እኔ የማውቀው አማራ የሚባለው ክርስቲያን ነው። በጎንደርም ሆነ በጎጃም በወሎ አማራ የሚለው ቃል የክርስትና እምነት ተከታይ መሆንን ነው የሚያሳየው። በጎንደርም ሆነ በአርማጭሆ በአማራነት ተጮሆ ምንም የተገኘ ነገር የለም። ያላደኩበትን ያላወቅሁትን ነገር ልናገር አልችልም። ተመራምሬ ያገኘሁት ነገር እንጂ የራሴ ሃሳብ አይደለም።

አዲስ ዘመን፡- መግባቢያ ቋንቋቸው በራሱ አማርኛ መሆኑ አማራ ለመባል አያበቃቸውም?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- አያበቃም። ቋንቋ ጎሳ አይሰጥሽም። ለምሳሌ አሜሪካን አገር ጥቁሮች አሉ። እንግሊዝኛ ነው ቋንቋቸው ግን እንግሊዞች አይደሉም። በላቲን አሜሪካም እንዲሁ ፖርቹጊዝና ስፓኒሽ የሚናገሩ ብዙ ጥቁሮች አሉ። ምን ሊባሉ ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ ቋንቋ ከሚናገሩ ቤተሰቦች የተፈጠሩ ዜጎች አሉ። የቤተሰቦቻቸውን ቋንቋ አያውቁም። አማርኛ ነው የሚናገሩት በአማርኛ እየተግባቡ ነው ያደጉት። ሌላው ቢቀር በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ወያኔ ወደ ኤርትራ የላካቸው ኤርትራውያን ቋንቋቸውንም አገራቸውንም አያውቁም ነበር። ስለዚህ ቋንቋ ጎሳ አይሰጠንም።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ይህንን ቢሉም በአሁኑ ወቅት የአማራ ብሄርተኝነት ጉዳይ ገኖ እየወጣ ነው። አማራ ባለፉት መንግሥታት ለአገሩ አንድነት ቢዋደቅም ማንነቱን ማሳደግና መጠቀም ባለመቻሉ የአማራ ብሄርተኝነትን ማስፋፋት አለብን የሚሉ ሰዎች አሉ። እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ አይገባኝም። አልረዳውም። የደንቆሮ አስተሰሰብ ነው። ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ነች። ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሰው ሁሉ የዚህች አገር ነው። እኔ የማምነው ይሄን ነው። በዚህ ጎሳ ገብቼ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሰው ሁሉ ደንቆሮ ነው። ታሪኩን አያውቅም። የመጣበትንም አያውቅም። ግን ቅድመ አያቱ ከየት እንደመጡ ቢጠይቅ ኖሮ እውነተኛውን ነገር ያገኘዋል። ወላጆቻችን ለማን ብለው ሞቱ? እነዚህ ዛሬ የሚጠሩት ነገሮች ስሞች ከዚህ ቀደም አልነበሩም፤ አልተሰሙም ነበር። መሬት ላይ የሌሉትን ከየት ነው የሚያመጡት። እነዚህ ዛሬ የሚጠሩት ነገሮች አልተሰሙም፤ ታሪክ ላይ የሉም። እናም ያልነበረ ነገር ከየት ይመጣል? እነሱም ዛሬ አዲስ አገር ፈጥረው ህዝብን በማጋጨት ለመንገሥ ነው የሚሮጡት። ግን ህዝቡ ዛሬ ቢተኛ ነገ ይነቃል፤ ከታሪኩ የሚቃረን ነገር መምጣቱን ሲገነዘብ ዘራፍ ብሎ መነሳቱም አይቀሬ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ደግሞ የአማራና የኦሮሞ የዘር ግንድ አንድ ነው የሚል መከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል። ሌሎች ግን ተረት ነው ይሏቸዋል። የእርስዎ እምነት የቱ ጋር ነው?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- የፕሮፌሰር ፍቅሬ አስተሳሰብ ከእኔ ሃሳብ ጋር አይጣረስም። እኔ በማላውቀው ነገር ላይ አልናገርም። ፍቅሬ የተናገረው ነገር ከሺ ዓመታት ወዲያ ሄዶ ቆፍሮ አገኘሁ ያለውን ነገር ነው የተናገረው። አንዳንድ ታሪክን እናውቃለን የሚሉ ሰዎች ተረት ነው ብለው ፅፈዋል። እኔም ለዚያ መልስ ሰጥቻለሁ። በእኔ እምነት ታሪክ ሁሉ ተረት ነው። አንዱ በልቦለድ አድርጎ ይወስደዋል። ሌላው እውነተኛ አድርጎ ይወስደዋል እንጂ ተረት ሁሉም ታሪክ ውስጥ አለ። ያንን የማያውቅ ሰው ነው የፍቅሬን አስተሳሰብ ተረት ነው ሊል የሚችለው። ለምሳሌ ሩቅ ሳንሄድ የትናትናውን የመንግሥቱ ሐይለማርያምን የገዛበትን የ17 ዓመት ወስደን ብናይ ማንም ሰው በእነዚህ ዓመታት ቀርቶ በአንዱ ዓመት ብቻ የተፈፀመውን ሁሉንም ተግባር ሊነግረንና ሊተርክልን አይችልም። ምክንያቱም አዕምሮው ሊይዝለት የሚችለው የተወሰነ በመሆኑ ነው። ሌላው ይቅርና በ24 ሰዓታት ውስጥ ያለውን ሁሉ የመናገር ችሎታ ያለው ሰው የለም። ስለዚህ ታሪክ ጸሃፊም ሊያደርግ የሚችለው አሟልቶ በራሱ ስሜት በራሱ አስተሳሰብ ሞልቶ ነው። ደግሞም ተደርድሮ የሚጠብቀው ድርጊት የለም። ታሪክ ብሎ የሚያመጣልን ያንን እየለቀመና እየሰካካ አይደለም። እንግዲህ እዚህ ጋር ልዩነቱ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ሺ ዓመት ወደኋላ ሄዶ ነው አጥንቶ የፃፈው። እኔ እንዴት እንደሆነ አላውቀውም። አትጠይቂኝ። ምክንያቱም ቋንቋዎች ማወቅና ሁኔታዎች መመቻቸት ያስፈልጋል። ሌላው እዚህ ቁጭ ብሎ ምንአልባትም የታሪክ መፅሐፍትን አገላብጦ «ይሄ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው፤ ይሄ ተረት ነው» የሚልበት ሁኔታ አግባብነት የለውም። በእኔ እምነት አላውቅም ማለት ትልቅነት ነው። በተጨማሪም ልክ አይደለም የምትይው እኮ ፕሮፌሰር ፍቅሬ የደረሰበት ቦታ ላይ መድረስ ስትቺይና ያነበበውን ሁሉ ስታነቢ ነው። እንደዚሁ በሾላ ድፍን ልክ አይደለም፤ ተረት ነው ማለት ግን አይቻልም። ፕሮፌሰር ፍቅሬ አንድ ጊዜ እንደውም «መፅሐፌን አንበኸዋል ወይ?» አለኝ። ግማሽ ደርሻለሁ አልኩት። ምክንያቱም እኔ የማላውቀው ስለበዛብኝ ነው። ጭንቅላቴ ውስጥ አስገብቼ የምክብበት ነገር ባለማግኘቴ ማንበቤን አቋርጫለሁ። ያ ግን የኔ ጉድለት ነው። የፍቅሬ ጉድለት አላደርገውም። እኔ እሱ የደረሰበት ደርሼ ብሆን የምናገረውን እናገር ነበር። ግን የምናገረው የለኝም። ስለዚህ አርፌ መቀመጥ ነው ያለብኝ።

አዲስ ዘመን፡- ፕሮፌሰር መስፍን መንግሥታትን ከመደገፍ ይልቅ መተቸት ይመርጣሉ ይባላሉ። ይህ የሆነበት የተለየ ምክንያት ይኖርዎት ይሆን?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- እኔ መጀመሪያ ትምህርቴን የጀመርኩት ፍልስፍና ነው። አንዱ ጭንቅላቴን የነካውና ያነፀው ነገር እውነት ነው። እውነትን ደግሞ የኛ ማህበረሰብ አይወድም። እኔ በዚያ ማህበረሰብ ውስጥ ነው ያደኩት። የተንሸዋረረ አስተሳሰብ ይዤ። ያንን ለማቃናት ስሞክር ከእውነቱ ጋር መጋፈጥ ግዴታ እንደሆነ ተገነዘብኩና ይህንን ልማዴ አደረግሁ። አንድ እውነት ሳይ አልሸሸውም። እውነት የሆነውን ማስረጃ ሳይ እቀበላለው። ካላገኘሁ አልቀበለውም፤ እጥለዋለሁ። ከህሊናዬ ውጪ በትዕዛዝና በጫና «ይህንን በል፤ ይህንን አድርግ፤ አታድርግ» የሚል ነገር አልቀበለውም። ባህሪዬም ከዚያ የመጣ ይመስለኛል። ከዚያ በተረፈ ግን ማንም ሰው እንደሚማር አዕምሮውን እንደሚያጎለብት ነው እኔም ያደግሁት። መንግሥታትን በድፍረት የመናገር ልምድ ያገኘሁትም ይህንን እውነት በማወቄ ነው። አንቺም የምታውቂ ከሆነ ትደፍሪያለሽ። ምን ያስፈራሻል? እውነቱን ለመናገር የምትፈሪው ውስጥሽ ጥርጣሬ ያለ እንደሆነ ነው። ግን ደግሞ ልብ እንዲባልልኝ የምፈልገው ነገር ማንንም ለመጉዳት ብዬ የመተቸት አባዜ እንደሌለብኝ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች የፃፏቸው አብዛኞቹ መፅሐፎች ርዕሳቸው ከባድና ጨለምተኛ በመሆናቸው ለማንበብ አይጋበዙም ይላሉ። በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- መፅፎቼንም ስፅፍ ሰው ይወዳቸዋል፤ ወይም አይወዳቸውም ብዬ ርዕስ አላወጣላቸውም። ለምሳሌ «የክህደት ቁልቁለት» የሚለው ርዕስ ማንም ሰው መፅሐፉን ሲያነበው እንዴት የክህደት ቁልቁለት እንደሆነ ያየዋል። ወያኔና ሻዕብያ ሲመጡ ክህደታቸውን ነው የገለፅኩት። ያ ደግሞ እንዴት አድርጎ ወደ ቁልቁለት እንደሚወስዳቸው ነው በመፅሐፌ የገለፅኩት። እናም እንዳየነው ወሰዳቸው። ስለዚህ እኔ ፈልጌ አይደለም ርዕስ የምሰጠው የእነርሱ ሥራ ነው ርዕስ የሚያሰጠኝ። በሌላ በኩል ያየሽ እንደሆነ አብዛኞቹ የታሪክ መፅሐፎቻችን ያለፈውን ረግሞ የአሁን አወድሶና አሞካሽቶ ነው የሚፃፈው። እናም ያንን ተወላግዶ የተጻፈው ታሪካችንን ነው የከሸፈ ታሪክ የምለው። እናም ይህንን የማይረዳ ሰው አያውቅም። ደግሞ የሚያስደንቀው ነገር አለማወቁ ሳይሆን ለማወቅ አለመፈለጉ ነው። ለማወቅ የማይፈልግን ሰው ደግሞ ምንም ልታስተምሪው አትችይም። በዚህ አዝናለሁ። በአጠቃላይ ግን እኔ እንደ ልቦለድ እስቲ ለሰዎች የሚያስደስትና የሚያምር መፅሐፍ ልፃፍ ብዬ ልነሳ አልችልም። ስለዚህ ሁሉም ሊገነዘብ የሚገባው ጉዳይ እኔ ሳልሆን ጨለምተኛው ታሪካችን ነው። ያንን ታሪክ እንዳለ ማቅረቤ እኔን ጨለምተኛ ሊያሰኘኝ አይችልም። እኔ ምን ላደርገው እችላለሁ? መነካካት ነበረብኝ?

አዲስ ዘመን፡- በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሽልማት ታጭተው አልቀበሉም ማለትዎ ለረጅም ጊዜ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። አልቀበልም ያሉበት ተጨባጭ ምክንያት ይኖር ይሆን?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- እሱ ጉዳይ ውስጥ የሚገባ ነገር አይደለም። በድሮ ስሙ የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ስሙ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ30ኛ ዓመት በዓሉን ሲያከበር ኒሻን ትሸለማለህና በዚህ ቀን እንድትገኝ ተባልኩ። እኔም እንደማልገኝ ገለጽኩላቸው። በወቅቱ የዩኒቨርሺቲው ፕሬዚዳንት የነበረው ዱሪ መሃመድ ሽልማቱን የሚሰጠው ሻምበል ፍቅረስላሴ በመሆኑ ሄጄ ሽልማቱን እንድቀበል ብዙ ወተወተኝ። እኔ ግን እንደማልመጣ ስነግረው ባትኖርም እኔ ስምህን እጠራለሁ አለኝ። ያን ጊዜ ለምንድን ነው የምትሸልሙኝ ስላቸው «ብዙ ዓመት ስላገለገልክ» ሲሉኝ እኔም እንግዲያው ከእኔ ይበልጥ 30 ዓመት የቆየች ኤሊ በጊቢው ውስጥ ስላለች እሷን ሸልሟት አልኳቸው። በዚሁ ተለያየን። ከፅህፈት ሚኒስቴርም እንደዚሁ ሽልማት ሲሰጥ አልሄድኩም፤ አልተቀበልኩም። እኔ የማምንበት አንድ ነገር አለ። የኢትዮጵያ ህዝብ የፈጠረውና ያቋቋመው መንግስት ቢመሰ ረት የኢትዮጵያን ህዝብ የሚወ ክል ሆኖ እዚህ ቦታ ሥራ ቢለኝ በግዴ እሠራዋለሁ። ግን የኢትዮጵያን ህዝብ የማይወክል መንግሥት እዚህ ቦታ ሥራ ቢለኝ እሺ አልልም። በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ሁለት ጊዜ የአውራጃ ገዢ ሁን ተብዬ አልተቀበልኩም። ደርግም ቢሆን በተለየያ ጊዜ ለመሾም ሞክሯል። ያልሞከረው ወያኔ ብቻ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ምክንያቱ ምን ይመስልዎታል?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ምክንያቱም ወያኔ እንደማይሆን ያውቀዋልና ነው። እኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ያልወከላቸውና ያልመረጣቸው አካላት ቢያዙኝም አልቀበልም። ቢሰጡኝም ኒሻን ኮርቼ አላደርገውም።

አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ህዝቡ መንግሥቴና ንጉሴ እያለ ለእነሱ ሲገዛ ነበር የኖረው?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- እሱማ ህዝቡ ምን ሊያደርግ ይችላል? ለእንጀራ ብሎ ይቀበላቸዋል። ጉልበትም ስለሚጠቀሙ ይፈራል። አምኖባቸው አይደለም ፈርቶ እንጂ። ምክንያቱም እዬዬ እያለ ሲያለቅስ ነው የኖረው። በቅርቡ እንኳን ከሰበታም ሆነ ከሌሎች አካበቢዎች ዜጎች ሲፈናቀሉ ከማልቀስ ውጪ ምን ፈየዱ? ምንም! በአንድ ላይ እንኳ ሆነው ቅሬታቸውን የሚያቀርቡበት ዕድል የላቸውም። እነሱም አንዳንድ ሆነው ጉልበት እንደሌላቸው አያውቁም። ይሄ ህዝብ እኮ ፀሐዩ ንጉሥ እያለ መኖር ነው የለመደው። መንግሥታቱን እሱ እየሞተላቸው ነው ያኖራቸው።

አዲስ ዘመን፡- ብዙ ዘመናትን በትግል፣ በምርምርና በመፃፍ ማሳለፉ በግል ህይወትዎ ላይ ተፅእኖ አልፈጠረበዎትም?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ያለምንም ጥርጥር የቤተሰብ ሁኔታን ይነካል። ፍላጎቶች ይጋጫሉ። በተቻለኝ መጠን ሁሉም በሚገባና በእኩል መልኩ ለማስኬድ ሞክሪያለሁ። ይህንን ስታነሺ እንዳውም አንድ ነገር ትዝ አለኝ። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሰዎቻቸው ቤተሰቤን እንደምወድ ነግረዋቸው ኖሮ አንድ ቀን «ልጆችህን ትወዳለህ አሉ?» አሉኝ። እኔም አሁን ይህንን ወሬ ብለው የሚነግሯችሁ ብዬ ተገረምኩ። ለማንኛውም በተቻለኝ አቅምና ይሆናል በምለው መንገድ ልጆቼን ባሳድግም ዛሬ ግን ልጅ የለኝም። የዘመኑ ሁኔታ ነው። በአሁኑ ወቅት እነሱ ሌላ ዜግነትና ሌላ አገር አግኝተው ጥለውኝ ሄደዋል። አሁን እነሱ የሌላ አገር ሰዎች ናቸው። አገራቸውንም ጠልተዋል። በአሁኑ ወቅት ብቻዬን ነው የምኖረው።

 አዲስ ዘመን፡- ልጆችዎ በእርስዎ የፖለቲካ ተሳትፎ ምክንያት ጫና ደርሶባቸው ነው የተሰደዱት?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እኔ እዚህ አገር ይሄ ነገር ተፈጠረ ብዬ አገሬን ትቼ አልሄድኩም። ሌላውም እንደዚህ ማድረግ አለበት ብዬ ነው የማምነው። ይሄ በየአገሩ የተሰደደው ሁሉ እኮ ኢትዮጵያ ያሳደገቻቸው፣ ያስተማረቻቸው፣ ትልቅ ደረጃ ያደረሰቻቸው ናቸው ዛሬ ሙልጭ ብለው ሄደው አሜሪካና አውሮፓ የፈረንጅ አሽከር የሆኑት። የእኔ አባት ማይጨው ዘምተው ቆስለው የተመለሱ ሰው ናቸው። የባለቤቴ አባት ከአፄ ኃይለስላሴ ጋር ለንደን ድረስ ሄደው ንጉሡን አድርሰው «እኔ ወደ አገሬ መመለስ ይሻለኛል» ብለው ተመልሰው መጡ። እዚህ እንደደረሱም ጣሊያን ያዛቸውና አሰቃይቶ ገደላቸው። እንግዲህ ከእነዚህ ሰዎች የተፈጠሩ ልጆች ናቸው ዛሬ የሌላ አገር ዜግነት ይዘው የሚኖሩት። አገራቸውን ጠልተዋል የምለውም ይህንኑ ነው። በነገራችን ላይ እስከዛሬ ይህንን ታሪክ ከዚህ ቀደም ተናግሬ አላውቅም ነበር። ግን እውነት ነው። እናም ያሳዝናል። አባቶቻችንና እናቶቻችን ለኛ ሲሉ ያወረሱንና እነሱ ያለፉበትን ስቃይ ረስተን ለልጆቻችን እንኳን ማስተላለፍ አልቻልንም። ያ ነው እንግዲህ የቤተሰቤ ታሪክ። ሦስት ልጆች ብወልድም ዛሬ አንዳቸውም ከአጠገቤ የሉም። አንዷ እንዳውም ያለችበትንም አላውቅም። እዚሁ ልትሆን ትችላለች ግን አላውቅም። ሁለቱ አሜሪካ ነው ያሉት። ትልቋ ግን ህሊናዋን እየቆጫት ይመስለኛል በየቀኑ ትደውልልኛለች። እናም በአጠቃላይ ስደት ዛሬ ዋና ነገር ሆኗል። ፈረንጅ አገር ሄዶ የፈረንጅ አሽከር ለመሆን የሚደራደር ህዝብ ተፈጥሯል። በተለይም በአሁኑ ወቅት በየቀኑ በርካታ የአገራችን ሴት ወጣቶች በየአረብ አገሩ ገረድ ሆነው ለመኖር እየጎረፉ ነው። በእዚህ ዓይነት ውርደት ውስጥ ደርሰናል። ስደት አዲስ ፈሊጥ፣ አዲስ ዘዴ ሆኖ ሳያበቃ ትንሽ ቆየና ጠገራ ብር ተለመደ። አሁን እንኳን ያለው መንግሥት ከኛ ይልቅ ጠገራ ብር ስላላቸው እነሱን ነው የሚፈልጋቸው። የድሮ እናት አባቶቻችን ያስተላለፉልን ኩራትና ክብር አጥተናል።

አዲስ ዘመን፡ – ወደ ቅንንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ቆይታዎ ልመልስዎ? ፕሮፌሰር መስፍን፡- እሱ የሞተ ነገር ነው። ስለሱ ጉዳይ ማንሳት አልፈልግም።

አዲስ ዘመን፡- እንግዲያውስ በፖለቲካ ውስጥ እንደቆየ ሰው አሁን ላሉትና በትንሽ የሃሳብ ልዩነት ብቻ ተለያይተው ጥንካሬያቸውን ላጡ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመክሩት ነገር ካለ ዕድሉን ልስጥዎ?

ፕሮፌሰር መስፍን፡- በመጀመሪያ ደረጃ ፓርቲዎች የሉም። እነዚህ አንቺ ፓርቲ የምትያቸው የጎሳ ድርጅቶች ናቸው። በዚህ የጎሳ ድርጅቶች ውስጥ መሪ ነን የሚሉት ንጉሥ ለመሆን የሚፈልጉ ናቸው። ሁሉም ንጉሥ መሆን የሚፈልግ ባለበት ድርጅት ውስጥ ደግሞ መስማማት አይችልም። ምክንያቱም ወንበሩ አንድ ነው። ስለዚህ ስምምነት ላይ ሊደርሱ አይችሉም። ጎሳዎቹ ብዙ ስለሆኑ በቁጥርም ሊያንሱ አይችሉም። እናም የሚያዋጣው ነገር የጎሳ ፓርቲን መሰረዝ ነው። በእኛ አገር የሃይማኖት ፓርቲ እንደሌለ ሁሉ የጎሳ ፖለቲካም ሊከለከል ይገባል። የፖለቲካ ፓርቲ የሚባለው የሚጣጠሙ ሰዎች አንድ ላይ ሆነው የሚመሰርቱት የፖለቲካ ቡድን ነው። ማንም ሰው ሊገባ ይችላል። ክፍት ነው። የጎሳ ቡድን ዝግ ነው። ለምሳሌ አሜሪካ ጥቁሮች ፓርቲ የላቸውም። ያ ሁሉ ስቃይ የደረሰባቸው ደቡብ አፍሪካ እንኳ የጎሳ ፓርቲ የላቸውም። እኛ ጋ ፖለቲካውም አዲስ ነው። ፖለቲካ ምን እንደሆነ አናውቅም። ዋናው ነገር ስልጣን አግኝቶ ለመደፍጠጥና ረጋጭ መሆን ነው የሚፈልገው። ስለዚህ ፓርቲ በሌለበት የምመክረው የለኝም።

አዲስ ዘመን፡- በህመም ላይ ሆነው፤ ጊዜዎትን ሰውተው ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ለማድረግ ስለፈቀዱልን በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልቤ አመሰግናለሁ። ወደ ሙሉ ጤናዎ ሲመለሱ በቀጣይ በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንደምንጨዋወት ተስፋ አደርጋለሁ።

ፕሮፌሰር መስፍን፡- እኔም አመስግናለሁ። እንዳልሽው ሌላ ጊዜ በሰፊው ጊዜ ወስደን የምናወራቸው ጉዳዮች ይኖራሉ የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011

Filed in: Amharic