>
5:13 pm - Wednesday April 18, 3984

የኦሮሞ ብሔርተኞች ግብዝነት  [Hypocrisy]! [ክፍል ፬] (አቻምየለህ ታምሩ)

የኦሮሞ ብሔርተኞች ግብዝነት
 [Hypocrisy]! [ክፍል ፬]
አቻምየለህ ታምሩ
የኦሮሞ ብሔርተኞች  አጀንዳ አድርገው ከሚንቀሳቀሱበት የፖለቲካ ጉዳያቸው ቀዳሚው  የኦሮሞ ገበሬ «ከመሬቱ» አይፈናቀል የሚል ነው።  ለዚህም ነው የገበሬውን መፈናቀል  ተከትሎ  በገበሬው ላይ  ደረሰ ስለሚሉት የኑሮ ችግር፣ የማንነት መጥፋትና የክብሩና ኩራቱ መገፈፍ ከፍ አድርገው የሚያስጮሁት።  ሆኖም ግን ግብዞች ስለሆኑ በኦሮሞ ገበሬ ላይ ይህ ሁሉ ግፍና መከራ የሚደርስበት  እነሱ ካልተተገበረ ሞተን እንገኛለን በሚሉትና  እኛንም አክብሩት በሚሉን ሕገ መንግሥት እንደሆነ ሊታያቸው አይችልም።
ሲጀምር የኦሮሞም ሆነ የተቀረው ኢትዮጵያ  ገበሬ መሬት የለውም፤ የመሬት ባለቤትም አይደለም። ስለዚህ የኢትዮጵያም ሆነ ኦሮሞ ገበሬ የሚፈናቀልበት መሬት የለውም። ገበሬው እየተፈናቀለ ያለው ከራሱ ሳይሆን ከመንግሥት መሬት ነው። የኦሮሞም ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ገበሬ የመሬቱ ባለቤት ያልሆነው  ደግሞ የኦሮሞ ብሔርተኞች ካላስከበርነው ሞተን እንገኛለን በሚሉት ሕገ መንግሥት ነው። በዋናነት ከኦነግና ከሕወሓት ፕሮግራሞች  የተቀዳውን  የዛሬው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት  የኢትዮጵያን ገበሬ መሬት አልባ አድርጎታል።
ባጭሩ  የኦሮሞ ገበሬ ከኦነግ ፕሮግራም በተቀዳው ሕገ መንግሥት የመሬት ባለቤት እንዳይሆን በመደረጉ  «ከመሬቱ ተፈናቀለ» መባሉ ስህተት ነው፤  አልያም  የኦሮሞ ብሔርተኞች  የሚምሉበትን ሕገ መንግሥት የሚጥስ  ነው።
የኦሮሞ ብሔርተኞች ግብዞች ስለሆኑ፣ ፖለቲካቸው መለየታቸውን በመቃረን መግለጽ ስለሆነ  «የኦሮሞ ገበሬ ከመሬቱ መፈናቀል የለበትም» ሲሉ እኛ እንድናከብረው የሚጠይቁንን፣ እነሱም ካላከበርነው ሞተን እንገኛለን የሚሉትን ሕገ መንግሥት እየጣሱ መሆናቸው አይታያቸውም።  የኦሮሞ ገበሬም  ከሚያርሰው  የመንግሥት መሬት እየተፈናቀለ ያለው የኦሮሞ ብሔርተኞች ካላካበርነው ሞተን እንገኛለን የሚሉት ሕገ መንግሥት  በሚፈቅደው መሠረት መሆኑ የተገለጠለት አይመስልም። ግብዞቹ የኦሮሞ ብሔርተኞች ግን እነሱ ካላከበርነው ሞተን እንገኛለን በሚሉት ሕገ መንግሥት መሠረት የኦሮሞ ገበሬ እየተፈናቀለ  ስለሚያፈናቅሉት ገበሬ የኑሮ ችግር፣ የማንነት መጥፋትና የክብሩና ኩራቱ መገፈፍ ከፍ አድርገው ይጮሀሉ።
በኮዬፈጨ የአዲስ አበባ አስተዳደር   አዲስ አበቤዎች  በቆጠቡት ገንዘብ የሰራቸውን  የጋራ ቤቶች መኖሪያ ቤቶች  ለባለቤቶቹ  እንዳይሰጥ የኦሮሞ ብሔርተኞች ያገዱት ኮንዶዎቹ «የኦሮሞ ገበሬ ተፈናቅሎ የተሰሩ ናቸው» የሚል  ካላከበርነው ሞተን እንገኛለን የሚሉትን ሕገ መንግሥት የሚጥስ ምክንያት ፈጥረው ነው። ቀደም ብዬ እንዳልሁት የኦሮሞ ገበሬም ሆነ ቀሪው የኢትዮጵያ ገበሬ የሚፈናቀልበት መሬት የለውም።  የኦሮሞ ብሔርተኞች በሰጡን ሕገ መንግሥት አማካኝነት ገበሬው የመሬት ባለቤትነቱን አጥቷል። ገበሬው ከሚያርሰው የመንግሥት መሬት መንግሥት በፈለገው ጊዜ ሕገ መንግሥቱ የሚፈቅደውን ካሳ ከፍሎ  ገበሬውን ማፈናቀል እንደሚችል  የኦሮሞ ብሔርተኞች ካላከበርነው ሞተን እንገኛለን የሚሉን ሕገ መንግሥት ይደነግጋል።
እንደሚታወቀው  የኮዬፈጨ ገበሬዎች ከሚያስሩት የመንግሥት መሬት የተነሱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕገ መንግሥት ተብዮው በሚፈቅደው መሠረት ካሳ ተከፍሏቸው ነው። የተዘረጋው ስርዓት ይፋዊ አፓርታይ ካልሆነ በስተቀር በሕገ መንግሥቱ መሠረት ካሳ ተከፍሏቸው ልክ እንደሌላው የኢትዮጵያ ገበሬ ከሚያርሱት የመንሥት መሬት ላይ  የተነሱት የኦሮሞ ገበሬዎች በምንም ተዓምር የተለየ ተጠቃሚ የሚሆኑበትና ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ከተቀመጠው ካሳ ተጨማሪ ቤት በነጻ ሊያገኙ የሚችሉበት   ምክንያት ሊኖር አይችልም።
ሕገ መንግሥቱ ይከበር ከተባለ ለሁሉም በሁሉም ይከበር።  በሕገ መንግሥቱ መሠረት  ከሚያርሱት የመንግሥት መሬት ካሳ ተከፍሏቸው  ከተነሱት የኢትዮጵያ ገበሬዎች በተለየ የኮዬፈጨ ገበሬዎችና  ልጆቻቸው  አፓርታይድ ካልሆነ በስተቀር ያለ እጣ  ቤት ሊሰጥበት የሚያስችል አንዳች ሕገ መንግሥታዊ  ምክንያት የለም።
አፓርታይድ በይፋ እስካልታወጀ ድረስ  የኮዬፈጨ  ገበሬዎች ከሌሎች  የኢትዮጵያ ገበሬዎች የተለዩ ሊሆኑ አይችሉም። ልክ እንደ  ኮዬፈጨ ገበሬዎች ሁሉ በመቶ ሺዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ገበሬዎች ከሚያርሱት የመንግሥት መሬት ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ካሳ እየተከፈላቸው መንግሥት ቤት ሳይሰራላቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ተጥለዋል።
 ከኮዬፈጬ የተነሱት የኦሮሞ ገበሬዎች  የተነሱት ከመንግሥት መሬት እንጂ ከራሳቸው መሬት ስላልሆነ፤  የመሬት  ባለቤትነት ሕጉም ገበሬዎች ከሚያርሱት የመንግሥት መሬት ሲነሱ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ካሳ ይከፈላቸዋል እንጂ ለኦሮሞ ገበሬዎችና ልጆቻቸው  በተለየ ቤት ይሰራላቸዋል ስለማይል፤ ለኮዬፈጨ ገበሬዎችም ካሳ ስለተከፈለ  “ሁሉም እንስሶች እኩል ናቸው አንዳንድ እንስሳ ግን ከሌሎቹ የበለጠ እኩል ናቸው”  በሚል ያልተጻፈ ሕገ እየተገዛን ካልሆነ በስተቀር  የኮዬፈጨ ገበሬዎች በሕገ መንግሥቱ  መሠረት ከተፈናቀሉ የኢትዮጵያ ገበሬዎች በተለየ ለልጆቻቸው ጭምር  ቤት ሰርቶ የሚሰጥበት አንዳች ሕጋዊ   ምክንያት  ሊኖር አይችልም።
የኢትዮጵያ ገበሬዎች ሕገ መንግሥቱ የወለደውን ድህነት እኩል መካፈል ይኖርባቸዋ። ስለዚህ  ወይ ሕገ መንግሥት ተብዮው ለሁሉም እኩል ይከበር፤ አልያም ባለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት ምክንያቱ በበዛ  ዘረኛነት ከየቦታው ሲፈናቀል የኖረው የኢትዮጵያ ገበሬ ሁሉ እንደኮዬፈጨ ገበሬዎችና ልጆቻቸው  መንግሥት ቤት ሰርቶ  ይስጣቸው።  በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተፈናቀሉ የኮዬፈጨ ገበሬዎች በሕገ መንግሥቱ መሠረት ካገኙት ካሳ በተጨማሪ  መንግሥት ከነልጆቻቸው ቤት በነጻ ሰርቶ የሚሰጥበትና  በሕገ መንግሥቱ መሠረት የኮዬፈጬ ገበሬዎች ያገኙት ካሳ  ያህል እንኳ ሳይከፈላቸው ከሚያርሱት መሬትና ከቤታቸው  ተፈናቅለው ሜዳ ላይ የወደቁ ገበሬዎች  ባድን አገር ውስጥ  ሊኖሩ አይችሉም።
በአዲስ አበባ ከተማ  ተፈናቅለው  ሜዳ ላይ የወደቁ አዲስ አበቤዎች ልክ እንደኮዬፈጨ ገበሬዎች ሁሉ መንግሥት በነጻ ቤት ሰርቶ ይስጠን ብለው የእኩልነት ጥያቄ ማንሳት አለባቸው። በአንድ አገር ውስጥ የኮዬፈጨ ገበሬዎች  በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሚገባቸው ካሳ ተሰጥቷቸው ተነስተው  በተጨማሪ  ቤት በነጻ ከነልጆቻቸው የሚሰጣቸው ከሆነ ከአዲስ አበባ  ከተማ   በተለያየ ጊዜ የኮዬፈጨ ገበሬችን ያክል እንኳ ሕገ መንግሥት ተብዮው የሚፈቅደውን ካሳ ሳያገኙ  ከቤታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ለወደቁት አዲስ አበቤዎች  መንግሥት ቤት ሰርቶ ለልጆቻቸው ጭምር  በነጻ  የማይሰጥበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም!
ስለዚህ የአዲስ አበባን ሕዝብ እያደራጃችሁ ያላችሁ ድርጅቶች    ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው  መሠረት ካሳ ተሰጥቷቸው ለተነሱ የኮዬፈጨ ገበሬዎችና ልጆቻቸው መንግሥት ቤት በነጻ  ከሰጠ  ከአዲስ አበባ ከተማም የኮዬፈጨ ገበሬዎችን ያህል እንኳ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ካሳ ሳይከፈላቸው ቤታቸው ፈርሶ ሜዳላይ ለወደቁ አዲስ አበቤዎችም  መንግሥት ቤት  ሰርቶ ለልጆቻቸው ምችር በነጻ  ይሰጥ ዘንድ የእኩልነት ጥያቄ ጠይቁ። በዚህ የእኩልነት ጥያቄ ዙሪያ ሕዝቡን አደራጁ!  በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለተፈናቀሉት የኮዬፈጨ ገበሬዎችና ልጆቻቸው የተደረገው ቤት ሰርቶ በነጻ  መስጠት ለአዲስ አበባ ከተማ  የልማት ተነሺዎችም  ይደረግ ዘንድ አገዛዙን ወጥሩ!
Filed in: Amharic