>

ህወሓት ያቦካውን ሊጥ ኦህዴድ ሲጋግር፤ ,... (አሥራደው ከፈረንሳይ)

ህወሓት ያቦካውን ሊጥ ኦህዴድ ሲጋግር፤ ብአዴን ማገዶ ያቀብላል!!
ጎበዝ ! በኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ ከመሸ ተመልሶ አይነጋም !!

 

(አሥራደው ከፈረንሳይ)

መግቢያ :
በዚህ መጣጥፌ ያለወትሮዬ በጥያቄ መጀመሩን መርጫለሁ :
– ለመሆኑ ሶርያ ከኢትዮጵያ ምን ያህል ትርቃለች ?!
– የመንስ ከኢትዮጵያ ርቀቷ ምን ያህል ነው ?!
– ጎረቤታችን ሶማሊያስ ?!
– የነዚህን አገራት ሁኔታ ያጤነ፤ የማንኛውም አገር ሕዝብስ በእሳት መጫወት ይገባዋል ?!
ደግሞስ !
* የኦቦ ለማ መገርሳ ” ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ! ” አባባል በቅጽበት ወዴት ተነነ ?! ወይስ ከበፊቱም ለሽንገላ ነበር ?
* የጠ/ምኒስትር አብይ አህመድ “ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ !” የሚለው ምኞትና ህልም ምነው ባጭሩ ተቀጨ ?!
ወይስ ባንድ ወቅት፤ አቶ መለስ ዜናዊ ለትግራይ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፤ “እንደ ወርቅ በዕሳት ከተፈተነው ከትግራይ ህዝብ በመፈጠሬ እኮራለሁ” ብለው፤ የትግራይን ህዝብ የአፍ ጮማ እንዳስቆረጡ፤ አብይ አህመድም በተራቸው፤ በዚያው በሚያዳልጥ ጭቃማ መንገድ፤ መጓዙን መረጡ ?!
የመደመሩ አባዜ :
ከጠ/ ምኒስትር አብይ አህመድ ጋር አብረን ተደምረናል እያሉ፤ አብይና የለውጥ ፈላጊው ቡድን ቀን ሲገነቡ የዋሉትን፤ ማታ ማታ እንደ ጃርት እየቆፈሩ በማፍረስ፤ ከሕዝብ አጣልተው፤ የተጀመረውን ለውጥ ለመቀልበስ፤ ሌት ተቀን የሚሠሩ፤ መሰሪዎች መኖራቸውን አጢነዋል ?!

የመደመሩ አባዜ በጎሣ ኮታ ብቻ እየተሰላ፤ ዕውቀትና ችሎታ ለሌላቸው ሰዎች፤ እንደ ጠበል መታደሉ፤ የሚያመጣውን ችግር፤ የለገጣፎ ሕዝብ መፈናቅል፤ በቂ ማስረጃ ሆኗል::

የመደመር ጭንብል አጥልቀው፤ ከመሬት ስበት በከፋ፤ ጠ/ምኒስትሩንና ቡድናቸውን ወደ ታች የሚጎትቱ፤ ቦርቧሪዎችን በብብታቸው አቅፈው ብዙ ርቀት መጓዙ እንደማይችሉ በመረዳት፤ ከጎሣ ኮታ ይልቅ፤ ሥልጣን ዕውቀትና ችሎታ ለተካኑ፤ አገራዊና ወገናዊ ፍቅር ለተላበሱ ዜጎች በመስጠት፤ ተነጣጥለን ከመጥፋት ይልቅ፤ አብረን በመደጋገፍና በመከባበር እየሠራን፤ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን እድናገለግል ቢያደርጉ፤ ያን ጊዜ ” ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርካል ” !!
ክቡር ጠ/ ምኒስትር ! ጎሠኝነትና ዘረኝነት በሚሰበክባት አገር አንድነትን፤ ሌቦች በነገሡበት ምድር ብልጽግናን፤ ጦር በሚሰበቅባት አገር ሠላም፤ አይኖርምና: ኢትዮጵያን በምርቃት ብቻ እንደማያቀኑ ተገንዝበው፤ የህወሓትን ብቻ ሳይሆን፤ የኦህዴድ፤የብአዴንና የደህዴን፤ ቱባ ቱባ ሌቦችን፤ በልመና ሳይሆን በተግባር በሕግ የበላይነት ለፍርድ በማቅረብ፤ ኢትዮጵያን በብዙ ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ዘፍቀው፤ ድሃው ሕዝባችንን እያስራቡ፤ የዘረፉትን የኢትዮጵያ ሃብት እንዲመለስ ያድርጉ::
ሌላው ግልጽ እንዲሆንልን የምንሻው ጉዳይ :

* ለመሆኑ! ጠ/ ምኒስትሩ ማነው ?! አብይ አህመድ ወይስ ጃዋር መሃመድ ?!
ልክ እንደ አቶ መለስ ዜናዊ፤ በፈለገው ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እያለ፤ በመቀመጫው ላይ በመቁነጥነጥ፤ እጆቹን እያወናጨፈ፤ ጣቶቹን ቀስሮ ሕዝብ ሲያስፈራራና፤ ሁሉንም አክሳሪ የሆነ የጎሥና የዘር ፖለቲካ ሲረጭ፤ ምነው አደብ ግዛ የሚል መካሪ፤ ወይም ህግ ጠፋ ?!

* ጃዋር የሚድያ ባለቤት ነኝ ባይ ነው ፤ መልካም እንኳን ሆነ ! ለመሆኑ የገንዘቡ ምንጭ፤ ከየት ? ከማንና ? እንዴት ተገኘ ?!
* ከጃዋር በስተጀርባ አብሮነታችንን እየናዱ ፤ የጎሣና የዘር ግንብ የሚገነቡልንስ እነማን ናቸው ?!
* ጃዋርና የጃዋር አይዞህ ባዮች፤ ከምርጫው በፊት፤ በምርጫው ወቅትና፤ ከምርጫው በኋላስ ምን እየደገሡልን ነው ?! ጎበዝ ! ጠርጥር፤ በገንፎ ውስጥ አይጠፋም ስንጥር፤ እንዲሉ ሆኗልና::
ከራሳቸው በስተቀር፤ ማንንም የመወከል ህጋዊ መብት የሌላቸው፤ የፖለቲካ አመንዣኪዎች፤ የስልጣን ቋንጣ ለመቀላወጥ ስለፈለጉ ብቻ ፤ ከያሉበት ተጠራርተው ሕዝባችንን በጎሣና በዘር ፖለቲካ ሲያምሱ ምነው ሃይ የሚል አካል፤ ወይም ህግ ጠፋ ?!
ተዘቅዝቀው የሚያነቡ የእናት ጡቶች፤ ለጆሮ የሚሰቀጥጥ የሕፃናት ለቅሶ፤ የሃዘን ጉም የቋጠረ የአባቶች ትካዜ፤ ደስታን ሳይሆን ሃዘን ለማጨት የተደገሠለት ወጣት፤ በማህፀኗ ተስፋን ሳይሆን ሞትን አርግዛ፤ መከራን ለመውለድ የምታጣጥር እንስት ለማየት ምነው ተቻኮልን ?

በሕብረ ብሄር ልጆቿ ተጎናጉና ውብና ያማረች፤ ጠንካራና ጤናማ ኢትዮጵያን በማየት ፈንታ፤ በጎሣ ካራ ተገዝግዛ የተበጫጨቀች፤ድሃና ደካማ ኢትዮጵያን ማየት፤ የማንኛችንም ምርጫ ይሆናል ብዬ ስለማላምን ተስፋ አልቆርጥም :: አሁንም ጊዜው ገና ስላልመሸ፤ ለአንድነታችን አብረን ዘብ እንቁም:: አንድም ቀን ብትሆን ዕድሜ ናትና !!
ወገኖቼ ! ለሠላም እንጂ ለጠብ ምክንያት ሞልቷል፤ ውሃ ቀጠነም ብሎ መጣላት ይቻላል:: ትልቁ አደጋ
ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚፈጠረው ችግር፤ አሸናፊና ተሸናፊ አይኖርም፤ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ነገር ቢኖር፤ ሁላችንም ተሸናፊዎች እንደምንሆን ነው ::

በዚህ ሁላችንም ከሳሪዎች በምንሆንበት የጥፋት ጎዳና፤ የጎሳና የዘር ፖለቲካ እያፏጩ፤ ሌላውን አግላይ በሆነ ንፉግ ፖለቲካ፤ እሽኮለሌ በመጨፈር፤ ተራው የእኛ ነው፤ ወይንም ጊዜው የእኛ ነው የሚሉን፤ የአስተሳሰብ ድንክዬዎች፤ ያልተረዱት ወይም ያልታያቸው ጉዳይ ቢኖር፤ የአስተሳሰብ አድማሳቸውን ሳያሰፉ፤ የጎሣ ጥብቆ ለብሰው ፤ የዘረኝነት ጋቢያቸውን እያራገቡ፤ አብሮነታችንን በመናድ፤ ብዙ ምዕተ ዓመታት ወደ ኋላ ጎትተው በድቅድቅ ጨለማ፤ እኛንና እራሳቸውንም ጭምር፤ ሁላችንም አብረን የመቃብራችን አፋፍ ላይ መቆማችንን ነው::

ጠባብ በሆነ አስተሳሰብ፤ ሁሉን አግላይና፤ አብሮነትን የሚሸረሽር፤ አገር አጥፊ የጎሣና የዘረኝነት ፖለቲካ እያቀነቀኑ፤ ኢትዮጵያን የመሰለ ሕብረ ብሔር፤ ትልቅና ባለ ብዙ ታሪክ፤ ብሎም የአፍሪካውያን የነፃነት ቀንዲል፤ በጀግኖች ልጆቿ ድል አድራጊነት፤ የዓለም አቀፍን ቀልብ የሳበች፤ ውብ አገር ማስተዳደር በእጅጉ ያዳግታል ::

ሰሞነኛ የፖለቲካ ሱቅ በደረቴዎች፤ ጊዜው ያለፈበት የፖለቲካ ሸቀጣቸውን፤ ከያለበት ሸክፈው በመምጣት፤ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን፤ ቤተ ሙከራ ለማድረግ ከሚያደርጉት አጉል መሯሯጥ፤ እንዲቆጠቡ ከወዲሁ እንመክራለን እናሳስባለንም ::
ምን ቢቸግረው፤ ምንም ያህል ቢራብ፤ ይህ ኩሩ ሕዝብ፤ አክ! ብሎ ወደተፋው አስከፊ ስርዓት ዳግም እንደማይመለስ፤ ጉሮሯቸውን እየተናነቀ፤ ሆዳቸውን እየጎረበጠ፤ ቢያስቸግራቸውም ሊውጡት የሚገባ ሃቅ መሆኑን እንነግራቸዋለን ::
ለ27 ዓመታት የችግራችን መንስኤ የሆነውን፤ የዘርና የጎሣ ፖለቲካ የሚያራምዱ፤ የዛሬው የመፍትሔ አካል ለመሆን እንደሚቸገሩ ስለምናውቅ፤ በጎሣ አንቀልባ እንደታዘሉ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ ላይ እሹሩሩ እያልን እንደማናቀብጣቸው፤ ቁርጣቸውን ከወዲሁ ይወቁ :: አገርና ሕዝብ፤ የሚገባውን ክብርና እንክብካቤ ማግኘት ሲገባው፤ በአጠያፊ የጎሣና የዘር ፖለቲካ ሊታመስ አይገባም::

ጥላቻ ሲነግሥ ፍቅር ይኮስሳል፤ ጎሠኝነት ሲያብብ አብሮነት ይጠወልጋል፤ በመንደርና በክልል ደረጃ ብቻ ስናስብ፤ አገር ይከስማል፤ ህዝብ ከህዝብ ይጋጫል፤ ደም መቃባት ይመጣል፤ ይህ እንዳይሆንና በወገኖቻችን ላይ ግፍና መከራ የምንጋብዝ፤ አገር ገዳይ ትውልድ እንዳንሆን በእጅጉ እንጠንቀቅ ::

ባለንበት በዚህ 21ኛው የስልጣኔ ዘመን፤ ዓለም ወደ ትንሽ መንደርነት ተቀይራ፤ ሁሉም ነገር በፀሐይ ፍጥነት፤ በሚለዋወጥበት፤ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዘመን፤ በጎሣ አጥር ተከልለው፤ በመንደር ደረጃ በመተራመስ፤ ጥላቻ የሚያገሱ ኮርማዎችን፤ ልንጠየፋቸው ይገባል:: በአገር፤ በክፍለ ዓለምና:በዓለም አቀፍ ደረጃ፤ በሁለንተናዊነት ( universalist ) ደረጃ ማሰብ የተሳናቸው፤ የአስተሳሰብ ሰንካላዎች በመሆናቸው፤ ሰው ብቻ ሳይሆን፤ ግኡዟ መሬትም በእጅጉ ትጠየፋቸዋለች ::

ማሳረጊያ

ህወሓት በ’ራሱ አምሳያ ጠፍጥፎ የፈጠራቸው፤ ጎሣንና ዘርን መሠረት ያደረጉ፤ ኦህዴድና ብአዴን የተባሉ የጎሳ ድርጅቶች፤ በቅርቡ ኦዴፓ እና አዴፓ የሚል የዳቦ ስም አውጥተናል ቢሉም፤ ሁለቱም የተፈጠሩት፤ እንደ ህወሓት ከጅብ ቆዳ በመሆኑ፤ ቅኝታቸው አሁንም ያው የጥንቱ ዓይነት፤ እንብላው እንብላው የሚለው ስለሆነ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ በዘርና በጎሳ ፖለቲካ እያባሉ፤ አንዱ በሌላው ወገኑ ላይ ጦር እየተማዘዘ፤ ህይወት በየዕለቱ ይቀጠፋል፤ ብዙዎች ከመኖሪያ ስፍራቸው እየተፈናቀሉ ሜዳ ላይ ፈሰዋል:: ዛሬ በአራቱም የአገሪቷ ማዕዘን፤ የሚቃጠል ቤት፤ የሚቀጠፍ ሕይወት፤ የሚዘረፍ ሃብት፤ ከስፍራው የሚፈናቀል የህዝብ ብዛት አግሪቱን አጥለቅልቋል ::

ህወሓት ከነ ደንደሳም ሌቦቹ፤ የትግራይን ሕዝብ እንደ ዋሻ ወይም እንደ ጫካ ቆጥሮ፤ በትግራይ ሲወሸቅ፤ አሽከሮቹ ኦህዴድና ብአዴን ደግሞ፤ ህወሓት ያቦካውን ሊጥ (የጎሣና የዘር ፖለቲካ) ኦህዴድ ሲጋግር: ብአዴን ደግሞ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ፤ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ለማገዶነት በማቅረብ ይማግዳል ::

አክሳሪ የሆነውን፤ የጎሣና የዘር ፖለቲካ፤ ሂትለር በጀርመን፤ ሞሶሎኒ በጣሊያን፤ ሞክረውት ትርፉ፤ ለብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ዕልቂት፤ ለመላው ዓለም የኢኮኖሚ ድቀት እንደነበር፤ ከታሪክ መማር ያቃታቸው፤ የአስተሳሰብ ድሃዎች፤ ዛሬ በኢትዮጵያ እንደ መፍትሔ በመቁጠር፤ እንደ ኮሶ ሊግቱን ሲፈልጉ፤ እንቢ ! የማለት አቅምና ድፍረቱ፤ ሊኖረን ይገባል ::

የአስተሳሰብ ድህነት ከድህነቶች ሁሉ በእጅጉ የከፋ በመሆኑ፤ በአንድነታችን አብረን፤ ጠንካራና፤ የበለፀገች አገር ዜጎች መሆን ስንችል፤ ሁላችንም ተበታትነን ደካሞችና ድሆች ሆነን ለመሞት አንቸኩል::

በአንፃሩ፤ ለኢትዮጵያ አንድነትና ልዖላዊነት፤ ለዜጎች ሰብአዊ መብት መከበርና ለእኩልነት፤ ቆመናል የሚሉት የአንድነት ኃይሎች፤ ግማሾቹ ቆመው ማንቀላፋት ብቻ ሳይሆን፤ ተኝተው ሲያንኮራፉ፤ ሌሎቹ ደግሞ፤ ከጎሣ ፖለቲካ አቀንቃኞች ጋር፤ የተቧደኑ በመሆናቸው፤ ቀን ጠብቀው ሚዛን ወደ ደፋበት ለመለጠፍ፤ ወይም ለመንሸራተት፤ ያደፈጡ መሆናቸውን ስናይ በእጅጉ እናዝናለን::

ድሃው ገበሬና ሠራተኛ፤ እራሱ ሳይማር፤ ግብር እየከፈለ በነፃ ያስተማረው፤ ምሁር ተብዬ በበኩሉ፤ አድፍጦ አጎንብሶ እየበላ፤ አገሩና ወገኖቹ፤ እራሱም ጭምር አስጊና ቀውጢ ወቅት ላይ ሆነው፤ ከምቾት ክልሉ ስንዝር ታህል ርቀት እንኳን ፈቀቅ ለማለት ያለመድፈሩ፤ በጣም ከማሳዘኑም በላይ በእጅጉ ያሳፍራል !!

Filed in: Amharic