>

የአብይ አስተዳደር የእሹሩሩ ፖለቲካ!!! (ሸገር ታይምስ መጽሄት)

የአብይ አስተዳደር የእሹሩሩ ፖለቲካ!!!

ሸገር ታይምስ መጽሄት

ዶ/ር አብይ አህመድ አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሸክማቸው የበረታ ሆኗል፡፡ በሀገሪቱ ካለፈው ስርአት ተጠቃሚዎችና ደጋፊዎች በስተቀር ለውጥ ጠያቂው ህዝብ ብዙ ነው፡፡ በለውጡ እንሳተፋለን የሚሉ የፖለቲካ ሀይሎች ለውጥ ጠያቂ ናቸው፡፡ የተለያዩ ህዝቦችን ወይም ማህበረሰቦችን እንወክላለን የሚሉ የፖለቲካ ልሂቃንና የፖለቲካ አክቲቪስቶችም ለውጥ እያሉ ይጮሀሉ፡፡ ከሁሉም አቅጣጫ የሚቀርበው የለውጥ ጥያቄ አይነቱና ብዛቱ የተለያየ ነው፡፡ ፌደራሊዝሙንም ሆነ ህገመንግስቱን ብታረድ እንኳ ለድርድር የማላቀርባቸው ጉዳዮች ናቸው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ህገመንግስቱንና ፌደራሊዝሙን ያላካተተ ለውጥ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊሆን አይችልም የሚል ፍላጎትም በተቃራኒው ተሰልፏል፡፡ አንዳንዶች ከወዲሁ “አዲስ አበባ የኔ ናት” በሚል ውዝግብ ውስጥ ገብተው ለውጡ ከተማዋን ካልሰጠኝ እያሉ ይሻኮታሉ፣ይወዛገባሉ፡፡

ዲሞክራሲያዊ ሽግግሩ እስኪሰምር ልታገስና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ጥያቄዬን ላቅርብ የሚል ሀይል ሀገሪቱ እያጣች ሄዳለች፡፡ ሁሉም  ለውጡ የምፈልገውን ካልሰጠኝ ሞቼ እገኛለሁ የሚል የጥያቄ ጋጋታውን በየቀኑ ሲወረውር ይታያል፡፡ አንተም እኔም ግማሽ መንገድ እንቅረብ ወይም አጀንዳችንን እናጥብብ የሚል የፖለቲካ ባህል በሌለባት ኢትዮጵያ አሁን የተፈጠረው መጠነኛ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ሁሉም ለውጥ ጠያቂ ወገን ለራሱ ብቻ የሚያስብ ተስገብጋቢ እንዲሆን በር ከፍቶለታል፡፡ ሀገር ባፍንጫዋ ትደፋ፤ የሰፊው ህዝብ ፍላጎትም ገደል ይግባ ባዩ እየበዛ ይገኛል፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑ ፍላጎት ያለቅጥ መለጠጥና ሊታረቅ ወደማይችል ተቃርኖ ውስጥ እየገባ መምጣት የአብይ አስተዳደርን ከፍተኛ ጫና ላይ የጣለ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱንም ለከባድ አደጋ ያጋለጠ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል፡፡

በዚህ ጫና ውስጥ ለህዝብ የገባውን ዲሞክራሲያዊ ስርአት የመገንባት ቃል ለመተግበር ከባድ ፈተና የገጠመው የአብይ አህመድ መንግስት ቁርጥ ያለ አቋም በድጋሚ ማንጸባረቅና በማያወላውል መንገድ ለህዝብ ማሳወቅ መቻል አለበት፡፡ የአብይ መንግስት ግን እስከአሁን በተከተለው መንገድ አንዱን ማስከፋትና ሌላውን ማስደሰት የከበደው ይመስላል፡፡ በብዙ አወዛጋቢ ነጥቦች ላይ ከመንግስቱ ባለስልጣናት የሚደመጡ መግለጫዎች ሁሉንም ሀይሎች ለማስደሰትና አቻችሎ ለመጓዝ የሚደረግ ሙከራ ብቻ ነው የሚንጸባረቅባቸው፡፡ አስተዳደሩ ዘገየም/ፈጠነ የፖለቲካ ልሂቃኑን ፍልጎት የመዳኘት ሀላፊነት አለበት፡፡ መጋፈጡ የማይቀርለትን ይህን ሸክም ፈራ ተባ እያለ ጊዜ ከመግዛት ይልቅ የቤት ስራውን ዛሬ መስራት መጀመር እንዳለበት ሁሉም ያምናል፡፡

የፖለቲካ ልሂቃኑ በአንድ ጠረጴዛ ከመቀመጥና ተወያይቶ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ የጥላቻ ንግግሮችን መወራወር ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ ለዲሞክራሲያዊት ሀገር ግንባታ በሚበጅ መንገድ ስክነትና ብስለት በተሞላበት ሁኔታ ለመፍትሄ ከመነጋገርና ከመግባባት ይልቅ ዛቻና ማሰፈራራት ሲያስተጋቡም ነው የምናየው፡፡ ይህ ሁኔታ በአንድም ሆነ በብዙ መንገድ የአብይ መንግስትን አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተው ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት ሀገር ስትገነባ ማየትን የሚናፍቀው ብዙሀኑ የህብረተሰብ ክፍል በስጋት ውስጥ እንዲኖር እየተገደደ ነው፡፡ አንድ አመት ባስቆጠረው የለውጥ እንቅስቃሴ ብዙ ተስፋ የሰነቀው እጅግ የሚበዛው ህዝብ አሁን አሁን በአብይና አስተዳደራቸው ላይ ያሳደረው እምነት እየተሸረሸረ ይገኛል፡፡ በብዙሀኑ ሰላም ወዳድ ህብረተሰብ ዘንድ ትናንት የታየው ብሩህ ተስፋና በጎ ስሜት እየጠወለገ ይገኛል፡፡

የፖለቲካ ልሂቃኑ ሀገሪቱን እንዳሻቸው ለመጋለብ፤ የሀገር አንድነትንና ህልውናን አደጋ ላይ ለመጣል ሲጣደፉ ይታያል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ “The Vast Majority ወይም The Silent Majority” ተብሎ የሚጠራውን በሰላም ውሎ ማደር የሚችልባት ዲሞክራሲያዊት ሀገር እንድትፈጠር እንጂ የተለየ የፖለቲካ ፍላጎት የሌለውን ሰፊ ማህበረሰብ በስጋት እንዲማቅቅ አድርጎታል፡፡ ይህ የማህበረሰብ ክፍል አሁንም ቢሆን የአብይ አስተዳደር የሰጠውን ተስፋ ጠባቂ ነው፡፡ የአብይ አስተዳደር የብዙሀኑን ማህበረሰብም ሆነ የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ የሚጥል መንገድ ይመርጣል ተብሎ አይታመንም፡፡ ነገር ግን እስከአሁን ድረስ ስጋቱን ለመቅረፍ ያደረገው ጥረት በቂ ሆኖ አናገኘውም፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑን ያወዛገቡ አጀንዳዎችን በሀቀኝነት ከመዳኘት ይልቅ አስተዳደሩ ዝምታን ነው የመረጠው፡፡ የፖለቲካውን ከባቢ አየር ጥቁር ጭጋግ እንዲውጠው እያደረጉ ያሉ ውዝግቦችና ሽኩቻዎች እንዲፈቱ ለሚቃረኑ ሀይሎች መደራደሪያ ወይም የሰለጠነ የውይይት መድረክ ማመቻቸት ከወዲሁ ካልተቻለ ሀገሪቱ ክፉ ይገጥማታል ብሎ መስጋት ሞኝነት አይደለም፡፡

የ ኦዴፓና አዴፓ ጓዳ

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) አሁን የታየው የለውጥ ጭላንጭል እንዲመጣ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ያለፈውን ስርአት በመቀየርና እርቃኑን እንዲቀር በማድረግ ረገድ ሁለቱ ፓርቲዎች የፈጠሩት ጥምረት በቅርም ጊዜያት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ አዲስ ነገር ነበር፡፡ ለውጥ አደናቃፊዎች ሁለቱ ፓርቲዎች አብረው አይዘልቁም ሲሉ ቢያሟርቱም ጥምረታቸው ግን በመጨረሻ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ዛሬ ላይ የሁለቱ ፓርቲዎች ጥምረት እየሳሳ፤ ሽርክናቸውም ወደ ጎሪጥ መተያየት እየተቀየረ መጣ የሚሉ ወሬዎች ቢናፈሱም የሚባለው ነገር በሁለቱም በኩል በይፋ ሲንጸባረቅ አልታየም፡፡ ይሁን እንጂ ጥግ የያዙና የተለየ የፖለቲካ ፍላጎት የሚያራምዱ የፖለቲካ ሀይሎች ያስነሱት ፍጭት መካረር ለኦዴፓና አዴፓ ጋብቻ መፍረስ ጦሱ እንደሚተርፍ ለመገመት አይከብድም፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች በሚመሩት ክልል እንንቀሳቀሳለን የሚሉ የፖለቲካ ቡድኖችንና ልሂቃንን ቀርቦ ለማወያየት ተደጋጋሚ እድሎችን ሲፈጥሩ ታይቷል፡፡ ዛሬ ላይ እጅግ ጽንፍ የወጣ አቋም ይዘው የጥላቻ ፖለቲካ ሲያራምዱ የሚታዩ የፖለቲካ ሀይሎች ኦዴፓንና አዴፓን እናግዛለን የሚል ቃል ሲገቡ ታዝበናል፡፡ ነገር ግን እነዚህ የፖለቲካ ሀይሎች ለውጡ እንዳይደናቀፍ ከመትጋትም ሆነ ለውጡን እየመሩ ያሉትን ኦዴፓንና አዴፓን ከማገዝ ይልቅ እርስ በእርስ ሲናቆሩ ነው የሚታየው፡፡

ዲሞክራሲያዊ ስርአት ተባብረን እንገንባ የሚለውን የኦዴፓንና አዴፓን ግብዣ በጸጋ ተቀብለው ለውጡን እስከአሁንም እየደገፉ ያሉ የፖለቲካ ቡድኖች መኖራቸው አይካድም፡፡ የነዚህ ቡድኖች አርቆ አሳቢነትና የተፈጠረውን ምቹ እድል ለመጠቀም ያሳዩት ጥረት ሳይደነቅ አይታለፍም፡፡ ከቃል ባለፈም በተግባር ጭምር ለውጡን ለመደገፍ ተነሳሽነት እያሳዩ ያሉ የፖለቲካ ሀይሎች ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በለውጡ ላይ ያለውን ተስፋ ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጥቂት የፖለቲካ ሀይሎችና ልሂቃን ከኦዴፓ ወይም አዴፓ ጋር መግባባት የሰፈነበት ውይይት አድርገው በይፋ ከለውጡ ጎን እንደሚሰለፉ ቃል በገቡ ማግስት ታጥቦ ጭቃ ሲሆኑ ነው የታየው፡፡

በሰላማዊ መንግድ እንቀሳቀሳለሁ ብሎ ወደሀገር ቤት የገባ የፖለቲካ ሀይል ለውጡን ለመደገፍ ምሎ በተገዘተ ማግስት ጦር መሳሪያ አላስረክብም ሲል ታዝበናል፡፡ ያነሳው የፖለቲካ ጥያቄ ካልተመለሰ በስተቀር ህዝብ በራሱ መንገድ እንዲታገል እቀሰቅሳለሁ የሚል የፉከራ መግለጫ የሚሰጥ የፖለቲካ ቡድንም አጋጥሟል፡፡ ለውጥን መደገፍ የሚጠይቀውን ቁርጠኝነትና ብስለት ሳይይዙ ከለውጡ ጎን ቆሜያለሁ ያሉ የፖለቲካ ቡድኖች ይሄው ለውጡ ድፍን መንፈቅ አመት ሳይሞላው ፈተናውን መውደቅ ጀምረዋል፡፡

ኦዴፓም ሆነ አዴፓ እነዚህን በፈተና የወደቁ ሀይሎችን በትእግስትና በሆደሰፊነት አግባብተው ለማለፍ ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነበር፡፡ እነዚህ አውቀውም ይሁን ሆን ብለው እንደግፈዋለን ካሉት ለውጥ በተቃራኒ የቆሙ ሀይሎች ግን የአብይ አስተዳደር የተከተለውን ትእግስት የተሞላበት አያያዝ አልተጠቀሙበትም፡፡ የነዚህ ሀይሎች አፈንጋጭነት እየባሰ ሲሄድ ደግሞ እንወክለዋለን በሚሉት ማህበረሰቦች መካከል ልዩነትንና ሽኩቻን መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ከነሱ ጀርባ የተሰለፉ አክቲቪስቶች የሚያርከፈክፉት ቤንዚን የልዩነቱን እሳት አጋግሞ ዛሬ ላይ ሀገሪቱን አስጊ ሁኔታ ላይ ጥሏታል፡፡

አዴፓና ኦዴፓ የሚመሩት የለውጥ መንግስት ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር የገባውን ቃል በተግባር ለማረጋገጥ ብዙ ርቀት ሄዷል፡፡ ይህን ደግሞ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ በርካታ የፖለቲካ ቡድኖችና ሰፊ ቁጥር ያለው ህዝብ ደግፎታል፡፡ ነገር ግን ጥቂት አክራሪ የብሄር ፖለቲካ አቀንቃኝ የፖለቲካ ሀይሎች ነገሮችን እያበላሹ ነው የሚገኘው፡፡ እነዚህ አክራሪ ብሄረተኞች በሀገሪቱ በሚፈጠሩ ወይም በሚደረጉ እያንዳንዱ ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ለቅሶና ሮሮ ያሰማሉ፡፡ እንወክለዋለን የሚሉትን ማህበረሰብ በጥላቻ ፖለቲካ በመመረዝም ለግጭትና ሁከት ይቀሰቅሳሉ፡፡ በየአጋጣሚው በለኮሱት እሳት በርካታ ግጭቶች ተቀስቅሰዋል ብዙ ንብረትና የሰው ህይወትም እየጠፋ ይገኛል፡፡ እንዳሰቡት አልተሳካላቸውም እንጂ የነዚህ አክራሪ ቡድኖች እሳቶች በቀላሉ የሚበርዱ አልነበሩም፡፡

ይሁን እንጂ የነዚህ አክራሪ ሀይሎች ትንኮሳና ሽኩቻ ከእለት ወደ እለት እየሰፋ ነው የሄደው፡፡ ለውጡን የሚቃወሙ ሀይሎች ቀድመው ያደራጁት ጸረለውጥ እንቅስቃሴ ሀገሪቱን እረፍት መንሳቱ ሳያንስ አክራሪ ብሄረተኞች በዚህ ላይ ሲጨመሩበት የሀገሪቱ ፖለቲካ እንደኩርንችት እሾክ በብዙ አቅጣጫ የሚዋጋ ሆኗል፡፡ የአክራሪ ፖለቲካ ቡድኖች እንዲሁም የጸረለውጥ ሀይሎች አፍራሽ እንቅስቃሴም ወደ ህዝቡ እየተጋባ ሄዷል፡፡ በለውጡ ብዙ ተስፋ አሳድሮ የነበረው በርካታ ማህበረሰብ በሚለኮሱ እሳቶች እየተነዳ ለውጡን ከመደገፍ ሲርቅ እያየን እንገኛለን፡፡

አሁን ላይ ጸረለውጥ እንቅስቃሴ ያለፈውን ስርአት ደጋፊ ከሆኑ ቡድኖች ብቻ አይደለም የሚቃጣው፡፡ አክራሪ የብሄር ፖለቲካ ሀይሎች የጀመሩት ትእግስት የለሽ ውጥረትና ውዝግብ ከዛ ይልቅ ለለውጡ ከባድ አደጋ ሆኗል፡፡ በዚህ ውዝግባቸው ህብረተሰቡን የከፋፈሉት እነዚህ ሀይሎች ከዛ አልፈው ለውጡን በሚመሩ ሀይሎች ላይም መርዛቸውን ለማጋባት ሲጣደፉ ነው የምናየው፡፡

በውዝግቦች የተሞሉት አክራሪ ሀይሎች እስከአሁን ድረስ ለውጡን በሚመሩት ኦዴፓና አዴፓ መካከል ሽኩቻ ለመፍጠር አልተሳካላቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን የነዚህ ሀይሎች መርዝ የአብይ አህመድ አስተዳደር ዋነኛ ፈተና አልሆነም ማለት አንችልም፡፡ አክራሪ ብሄረተኞቹ በየአጋጣሚው ሁሉ ከኦዴፓና አዴፓ ጀርባ ለመንጠላጠል ሲሞክሩ አይተናል፡፡ የአብይ አህመድ መንግስትም በዚህ ሲፈተን እያየን ነው፡፡ ሆኖም ግን ሁኔታዎች በዚህ መልኩ እስከቀጠሉ ድረስ የዘር ፖለቲከኞች መርዝ ከአዴፓና ኦዴፓ አልፎ በመላው ሀገሪቱ ህዝቦች ላይ መረጨቱ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ የተናፈቀውን ዲሞክራሲያዊ ለውጥ መና የሚያስቀር ነው፡፡ ሀገሪቱ አንድነቷንና ህልውናዋን ጠብቃ ለመቀጠል ዋስትና ታጣለች፡፡

ከኦዴፓም ሆነ ከአዴፓ ወገን የዘር ፖለቲከኞች በሚያራግቡት የከረረ ፕሮፖጋንዳ የመሳብ ዝንባሌ የሚንጸባረቅባቸው አይጠፉም፡፡ ድርጅቶቹ ከሚያስተሳስራቸው ግንኙነት ባፈነገጠ መንገድ የዘር ፖለቲከኞችን ጫና ለማርገብ ሲሉ የተጣደፈ መግለጫ የሚሰጡ ካድሬዎች ከሁለቱም ወገን ብቅ ብቅ ብለዋል፡፡ አሁን ላይ በአጠቃላይ የአብይ አስተዳደር የዘረኛ ፖለቲከኞችን ፍላጎት አስታርቆ ለውጥን እየመራ ሀገር ማስተዳደር ቀላል እንዳልሆነለት በሚገባ እየተገነዘብን እንገኛለን፡፡ ከኦዴፓም ሆነ ከአዴፓ ካድሬዎች በኩል ግብታዊና ያልበሰሉ ንግግሮች ማድመጥ የተለመደ ሆኗል፡፡ የአብይ አስተዳደር የተጣለበት ሰፊ የህዝብ አመኔታ ሳይሸረሸር ጠብቆ መዝለቅ ከብዶታል፡፡ ከመፈናቀል፣ ከመልካም አስተዳደር በደል፣ ከአፈናና ከጸጥታ ስጋት አውጥቶ የኑሮ ዋስትና ይሰጠናል የሚል የህዝብ አመኔታና ተስፋ የተጣለበት አስተዳደሩ የዘረኛ ፖለቲካ ቡድኖችን ጥያቄ ማስታመም በመቀጠሉ ይህን ሁሉ እያጣ ነው የመጣው፡፡

የአብይ አስተዳደር የእሹሩሩ ፖለቲካ!!!

የአብይ አስተዳደር የሚናገረውና የሚተገብረው አልጣጣም አለማለቱ እንጂ ብዙ በጎ ተስፋዎች ለህዝብ ማስጨበጡ አልቀረም፡፡ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት ጥቂት የሚባሉ ሰዎችን ገድሎና አስሮ የዚህን ሀገር ፖለቲካ ስክነት የተላበሰ ማድረግ ይቻላል፡፡ በፍርሀት ተሸብቦ የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ የለመደውን ቢያቀምሱት ኮሽታ ሳያሰማ ይገዛልኛል ብሎ የአብይ አስተዳደር አለማመኑ በራሱ አንድ በጎ ጎኑ ነው፡፡ አብይ ተዘግቶ የከረመ በር ሲከፈት የሚሰነፍጥ ሽታ ይሸታል እንዳሉትም የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር በጥቂቱ ሲከፈት የተፈጠረው ነገር መልካም አይደለም፡፡ የአብይ አስተዳደር ደም መፋሰስ ሳይከተል በሆደ ሰፊነት ነገሮችን ለመቻል የሚያደርገው ጥረት በርግጥ የሚያስመሰግነው ነው፡፡

ነገር ግን የአስተዳደሩ ታጋሽነትና ቻይነት ሀገሪቱን ለአደጋ እየዳረጋት ነው የሚገኘው፡፡ ዘረኛ የፖለቲካ ሀይሎች በአዲስ አበባ ጉዳይ ፊንፊኔ/በረራ እያሉ ህዝብን ሲከፋፍሉና ውጥረት ሲፈጥሩ በቸልታ ማለፍ የአስተዳደሩን እሹሩሩ ባይነት እንጂ ሌላ ነገር አያሳይም፡፡ የትጥቅ ቡድኖች አንዴ ትጥቅ አንፈታም ሌላ ጊዜ በሰላማዊ መንገድ እንንቀሳቀሳለን እያሉ ማሊያ በመለዋወጥ ህዝብ ሲያስፈጁና ሀገር ሲያተራምሱ አብይና አስተዳደራቸው በቸልታ ማለፉ አቅመ ደካማ የሚያሰኘው እንጂ ሌላ ምላሽ የለውም፡፡

የኦሮሞና የአማራ ዘረኛ የፖለቲካ ልሂቃን የአስተዳደር መዋቅር ለውጥ ወይም ሹመትና ምደባ በተደረገ ቁጥር እንወክለዋለን የሚሉት ማህበረሰብ ተበደለ እያሉ ይጮሀሉ፡፡ ለኦዴፓና ለአዴፓ ያሰቡ ይመስል ከጀርባ ተንጠልጥለው በሀገር አስተዳደር ጉዳይ ላይ ጣልቃ ይገባሉ፡፡ ለዚህ አጨቃጫቂ ጉዳይ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዘዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የኛ ህብረትና አንድነት ከስልጣን ክፍፍል የሚሻገር ነው ብለው በማያዳግም ሁኔታ ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በሁለቱም ጽንፍ ያሉ አክራሪ የዘር ፖለቲከኞችን ፍላጎት አላረካም፡፡

የአብይ አስተዳደር እያንዳንዱ ውሳኔ አጨቃጫቂና መሻኮቻ በሆነበት በዚህ ወቅት ራሱን የሚያጋልጥ እርምጃዎች ከመውሰዱ ጋር ተደማምሮ ሀገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች፡፡ ሁሉንም አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ስርአት ለመገንባት እተጋለሁ የሚለው የአብይ አስተዳደር በርግጥ እነዚህን ጽንፈኛ የፖለቲካ ሀይሎች ለማስታመም መሞከሩ ብዙም አያስከፋም፡፡ እነዚህ ሀይሎች ግን ከዛሬ ነገ ይሻሻላሉ ቢባልም ተስፋው እውን ከመሆን ይልቅ ችግሩ እየከፋ ነው የመጣው፡፡

የቡራዩ ጉዳይ፣ የኦነግ ትጥቅ መፍታት፣ የጎንደር፣ ወልቃይትና ራያ ጉዳይ፣ የለገጣፎና የሌሎች አካባቢዎች የዜጎች መፈናቀል፣ የአዲስ አበባ ባለቤትነት፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወንበርና ሌሎችም አጀንዳዎች ዘረኛ ፖለቲከኞች በከፍተኛ ደረጃ የሚያጮኋቸው አወዛጋቢ ጉዳይ ሆነዋል፡፡ የአብይ አስተዳደር በህገመንግስቱና በትክክለኛ መንገድ እነዚህን ሀይሎች ከመዳኘትና መልስ ከመስጠት ይልቅ የሚቆሰቁሱትን እሳት ዳር ቆሞ መመልከትና መሞቅ ነው የመረጠው፡፡ ይህን መሰሉ የአብይ አስተዳደር ፖለቲካ መደመር የሚል ስም ቢሰጠውም አስተዳደሩ ግን ዘረኞችንና የሀገር አንድነት እንዲሁም የለውጥ ሂደት እንቅፋት የሆኑ ሀይሎችን እሹሩሩ ከማለት የዘለለ መንገድ እንደማይከተል ያስታውቃል፡፡ በዚህ ሁኔታዎች እየተካረሩ በመጡበት ወቅት ታዲያ የአስተዳደሩ የእሽሩሩ ፖለቲካ እስኬት ድረስ ያዘልቀናል የሚለው ጥያቄ ለመመለስ አሁን ላይ ከባድ ነው የሆነው፡፡

Filed in: Amharic