>

‹ በሠፈሩት ቁና  መሠፈር  አይቀርምና . . . ! ››   (አሰፋ ሀይሉ)


‹ በሠፈሩት ቁና  መሠፈር  አይቀርምና . . . !
››
አሰፋ ሀይሉ
“የበቀለበትን የዛፍ ዘር እንደሚነድል ሞኝ ዛቢያ አንሁን፡፡ ራሱን እንደሚቀጠቅጥ ጅል መዶሻም አንሁን፡፡ ቢወለድም ወገን፣ ቢረግፍም ወገን ነውና!!!
ሰው ሆይ — አስተውል፡፡ ደግሞም ልጠይቅህ፡፡ ንገረኝ፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ስትኖር — መልካም ሰብዕናን ተላብሰህ መኖሩ — ያስፈለገህ ለምንድነው? ለሌሎች መልካም ታደርግ ዘንድ ብቻ ይሆን?? ወይስ ሌላ ሌሎችን ከመጥቀም የላቀ ፋይዳ አለው???
ጠቢባን እንዲህ ይሉሃል ፦ አዎ — መልካምነት ሌሎችን ከመጥቀም የላቀ ፋይዳ አለው፡፡ መልካምነት ያስፈለገው — ሌላን እንድትጠቅም ብቻ ሣይሆን — ከምንም በላይ — በዋነኛነት — ለራስህ እና ለራስህ ጥቅም ሲባል ነው፡፡ መልካምን እንድትዘራ የሆንከው ትኖር ዘንድ ነው፡፡ ይሉሃል ብዙ ጠቢባን።
ለምሳሌ ያህል ራስህን እንደ አንድ ራሱ የዘራውን (ራሱ ያመረተውን) እየተመገበ ህይወቱን እንደሚመራ ትጉህ ገበሬ አድርገህ ተመልከተው እስቲ። ለጤና መልካም የሆነውን የእህል ዘር ትተህ – ለሰውነትህ መርዛማ የሆነውን ዘር መርጠህ በደከምክበት እርሻህ ላይ ትዘራለህ?? — ያለጥርጥር አትዘራም። ብትዘራስ ኖሮ ? — እስካሁን በጤንነት (እና በሕይወት) ልትሰነብትስ ትችል ነበር? — አትችልም ነበር፡፡
እና አየኸው? መልካምን የምትዘራው — ራስህ መልካምን ታጭድ ዘንድ ነው። እና በዚያ በዘራኸው መልካም ዘርም ትኖርበት ዘንድ ነው። መልካምን የምትዘራው ለሌላ ሰው ብለህ ሳይሆን — ላንተው ለራስህ ነው፡፡ ይህ የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ ምድሪቱን ባፀናት ሰማያዊው አምላካችን የተደነገገ —የማይናወጥ የምድራውያን ህግ ነው፡፡ እና በቃ — ከሌሎች መልካምን እንድታገኝ ከፈለግህ — አንተ ለሌሎች መልካም ሁን፡፡ መልካምን ዘር ዝራ።
ጠቢቡ ሠሎሞን — በምሳሌ መፅሐፉ ላይ — እንዲህ ይላል፡— “ለሌላው ጉድጓድን የሚቆፍር — ራሱ ይገባበታል”፡፡ አክሎም እንዲህ ሲል እናገኘዋልን፡— “የሰው ደም ያለበት ሰው፣ ዕድሜ ልኩን ሲቅበዘበዝ ይኖራል፣ ማንም ሰውም አይረዳውም”። ይህ ጠቢቡ — በምሳሌ መጽሐፍ፤ በምዕራፍ 28፤ በቁጥር 17 ላይ — ከሺህዎች ዓመታት በፊት የጻፈው ነው፡፡ እንግዲህ ስማ የጠቢቡን ቃል። ይህ የእኔ የጠባቡ ቃል አይደለም። የጠቢቡ ቃል ነው።
የጠቢባን ቃል እንግዲህ ይሄን ነው የሚለን፡፡ በሠማዩም፣ በምድሩም፣ በታሪኩም፣ በአፈ-ታሪኩም፣ በያሰስንበት የጥበብ ሥፍራ የምናገኘው እውነት ይህንኑ ነው፡፡ ነገሩ ሊገርመን ይችላል። በሁሉም የዓለም የጥበብ አፍላቂዎች በየዘመኑ የተሰበከው እውነት መልካምነት ነው፡፡ ሁሉም ተናግረውታል። መልካምነት ለራስ መሆኑን፡፡
በዚህች ከንቱ ዘመናችን — ብዙዎች ሲመጡ አይተናል፡፡ ብዙዎች ሲሄዱም አስተውለናል፡፡ ያገኘንም፣ ያጣንም፣ አግኝቶ ያጣንም፣ አጥቶ ያገኘንም፣ አጥቶ የቀረንም — ሁሉንም ዓይነት ማግኘትና፣ ማጣት አስተውለናል።
በዚህች ከንቱ አላፊ ዘመናችን — ክፋትንና በጎነትን — ኃያልነትንና ውድቀትንም — ሁላችንም አብረን ተመልክተናል — አስተውለናል፡፡ ከዚህች ካሳለፍናት እፍኝ ከማትሞላ ከንቱ ዘመናችን — ከሁሉም ነገር ባሻገር የምንቀስመው ታላቁ ትምህርት — ያንኑ የጠቢባኑን በትልቁ፣ በደማቁ፣ የተፃፈ አንድና አንድ ቃል ነው። መልካም መሆን — በስተመጨረሻ — ጥሩነቱ — ለሌላ ለማንም ሳይሆን — ለራስ እና ለራስ የመሆኑ እውነታ፡፡
ታሪካችን ራሱ — መልካም ሁን — ለራስህ ብለህ — የሚለውን እኮ — በግላጭ ይናገራል፡፡ ከዘመነ ቴዎድሮስ እስከ ዮሐንስ፣ ከዘመነ ምኒልክ እስከ እያሱ፣ ከዘመነ ዘውዲቱ እስከ ኃይለሥላሴ፣ ከዘመነ አማን እስከ ተፈሪ፣ ከዘመነ መንግሥቱ እስከ መለስ፣ ከዘመነ ኃይለማርያም እስከ አሁን ድረስ ያለውን ዘመን፣ የተነሱትንና የወደቁትን፣ ግፍ የዋሉትንና መልካም የዋሉትን፣ እና እያንዳንዳቸው የዘሩትን እና ያጨዱትን ሁሉ ጭምር — እስቲ ልብ ብለህ ተመልከተው???
ይህን ሁሉ — የተነሳና የወደቀን — የኖረና የሞተን ሁሉ — ሳይኖርም የሞተ፣ ሞቶም ያላረፈን ጭምር — ሁሉንም — አይተሃል፡፡ ግን እስቲ ከማየትም ዘለግ ብለህ — ልብ ብለህ እስተውላቸው??? ከፍ ያሉት ሲዋረዱ አላየህም? የተናቁት አስገልብጠው ሲያስገርፉ አላየህም?? ክፉ የሰሩትስ ውሎ አድሮ — ከሠሩትም የባሰውን መቅሰፍት ሲሰበስቡስ አላየህም??
ሰዎቻችንን…ቀን ሲያነሳቸው፣ ቀን ሲበላቸው፣ ማንም አሌ ያላለው ተራፊ ዕድሜን ሰጥቶት ሲፋንን፣ አለ የተባለው ሳይኖር፣ የለም የተባለው ሲመጣ፣ የተሾመው ሲሻር፣ — ይህን ሁሉ — አንተ ለጉድ የፈጠረህ — በማግኘትና በማጣት ውስጥ ሆነህ የምትኖር ኢትዮጵያዊ — ይህን ሁሉ፣ ሌላውንም ተቆጥሮ የማያልቅ ስንቱን አላሳለፍክም? ስንቱን??!!!
እናስ ካሳለፍከው ምን ተማርክበት?? ‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ… አሊያ ድንጋይ ነው ብለው ይወረውሩሃል››ን ካልተማርክ — የእውነት — መቼውኑም አትማርም። መልካምነት ለራስ መሆኑን ከኖርነው ካልተማርን ምንም አልተማርንም፣ ወደፊትም ከመከራ በቀር ከጥበብ ቃል አንማርም ማለት ነው እኛ ኢትዮጵያውያን፡፡ እልሀለሁ።
አሁን ታሪካችን ይብቃን፡፡ አሁን ወደ አሁናችን እንመለስ፡፡ አሁን ወደ ገዛ ወገኖቻችን እንግባ፡፡ አሁን ወደ ራሳችን ዘመን እና ወደ ቋሚ ሕዝቦቻችን ምስኪኒቱን ነፍሳችንን እንቀልስ፡፡ ጉራጌዎች አንድ የሚሉት ድንቅ ምሳሌያዊ አነጋገር አላቸው፡- ‹‹ወሄነት የገጉ›› የሚል፡፡
‹‹ወሄነት የገጉ››ን ብዙ ጊዜ እጠቅሰዋለሁ፡፡ ብዙ የሚባሉ የረገጥኩባቸው ቦታዎችም ላይ እንደ ቅዱስ ጥቅስ ተሰቅሎ አግኝቼዋለሁ፡፡ ‹‹ጥሩነት ለራስ!›› እንደማለት ነው ትርጉሙም ተብያለሁ፡፡ አዎ፡፡ ይህ እውነትም የተቀደሰ ቃል ነው፡፡ እውነትም ከፍ ብሎ እንደ አርማ፣ እንደ ሰንደቅ ለሁላችንም በሚታይ ከፍ ያለ ሥፍራ ላይ ሊሰቀል ይገባዋል፡፡
እንዲያውም ይህ የጥበብ ቃል ሁሉንም እውነታችንን፣ ሁሉንም ታሪካችንን፣ ሁሉንም ነገራችንን ሁሉ ጥቅልል የሚያደርግልን ጭማቂ ቃል ሳይሆን አይቀርም መሠል፡፡ ‹‹ወሄነት የገጉ›› — ‹‹ጥሩነት ለራስ ነው!››፡፡ ትልቅ እውነት፡፡
አሁን ላይ ሆነህ — ይህ እውነት አይገለጥልህ ይሆናል — ተጎዳሁበትም ባይ ትሆናለህ፡፡ ግን ግድ የለህም — እመነው፡፡  አይታወቅህ ይሆናል እንጂ — ካንተ የቀደሙትንም፣ ባንተ ዘመን የኖሩትንም አስተውለህ ብትመለከት — አንዳች ጥያቄ የለውም — ጥሩነት ለማንም ሳይሆን — ጥሩነት ለራስ የመሆኑ እውነታ — በገሃድ አለ፡፡
ጥሩ ብትሠራ — ራስህን! ክፉ ብትሠራም — ራስህን! ነው፡፡ ጥሩ ዘርተህ፣ ጥሩ ማፈስ ስትችል — ስለምን መጨረሻ በክፉ ተመልሶ ወደራስህ የሚመጣብህን የክፋት መንገድ ትመርጣለህ??? ምድር እንደሁ ጠባብ ነች፡፡ የትም ሄደህ አታመልጣትም። የምድሪቱን ዙር፡፡
ከምድሪቱ በሚሊዮኖች ብርሃን ዘመናት ርቀው በህዋ ጋላክሲዎች ላይ ከፍ ከፍ ከፍ ብለው የሚኖሩ — ታላላቅ ከዋክብት እንኳ — በስተመጨረሻ መውደቂያቸው ሲደርስ — ከነስብርባሪያቸው የሚያርፉት በዚህችው ምድር ላይ ነው፡፡
አንተም የቱንም ያህል ታላቅ ሥፍራ ብትደርስ፣ የቱንም ያህል ወደላይ ከፍ ከፍ ብትል — መጨረሻህን የምትጎናፀፋት ግን — በዚህችው ምድር ላይ ነው፡፡በዚህችው ባለ የብስ፣ በዚህችው ባለ ባህር፣ በዚህችው ባለ ዓየር፣ በዚህችው ባለ ፀሐይ፣ በዚህችው ባለ ከዋክብት ድቡልቡል ምድር ላይ ነው — ያንተም፣ የእኔም፣ የእሱም፣ የእሷም፣ የሁላችንም፣ የሁሉም ሰው መጨረሻ፡፡
እና ዞረህ ዞረህ — ይፍጠንም ይዘግይ — ጊዜህ ሲደርስ — በዚህችው ምድር ላይ ነውና መመላለሻህ — በዚሁ ምድር ከሚኖርና — መልካምን ነገር ካደረግክለት ሰው ጋር አሊያም ክፉን ነገር ባደረግክበት ሰው እጅ መውደቅህ አይቀርም፡፡ ይህ የዓለም አስገራሚ የ”ዞሮ-ዞሮ አዳም” የግጥምጥሞሽ ህግ ነው፡፡
ይህ — የአዳማዊ ኳንተም — ዘለዓለማዊ ፎርሙላ ነው፡፡ ይህ — የምድሪቱ — ያልተጻፈ — ግን በእውን ያለ — የሰው ልጆች ይተዳደሩበት ዘንድ የተሰጠ — ምድራዊ ፎርሙላችን ነው፡፡ ዞረህ ዞረህ አዳም ነህ፡፡ በየትም አቅጣጫ ብትጓዝ ትገናኛለህ፡፡ እናም ያን ጊዜ — መልካሙ ሥራህ — ይበጅሃል፡፡ እልሀለሁ።
አስተውል ወንድሜ፡፡ አስተውዪ እህቴ፡፡ ሁላችን እናስተውል፡፡ ‹‹በሠፈሩት ቁና — መሠፈር አይቀርም››ን እናስብ፡፡ ጊዜው ለማንም አልረፈደም፡፡ ፍፃሜያችን እነሆ በእጃችን ላይ ናት፡፡
መልካም የመሆን — መልካምን የመዝራት — ከክፋት የመራቅ — ታላቅና ምንም የተሻለ መተኪያ የማይገኝለት — እጅግ የከበረ ዕድል — ታላቅ የመልካምነት ምርጫ — እነሆ በፊታችን — በእጃችን አለ፡፡ እንጠቀምበት፡፡
አሊያም ደግሞ — መጥፎ የመሆን — መጥፎ መጥፎውን የመዝራት — ወደ መጥፎው የመቸኮል — ታላቅ እርግማን — ታላቅ ገሃነማዊ ምርጫ — ታላቅ የፍዳ በለስ — እነሆ እርሱም — በእጃችን አለ — በፊታችን ተንጠልጥሏል፡፡ እርሱን በለስ — ተጠንቅቀን እንምረጥ፡፡
አንድ ነገር ግን እውን ነው፡፡ ዛሬ በመረጥነው እንለማለን፣ ወይም በመረጥነው እንጠፋለን፡፡ አሁን — ለምርጫ ብዙ ጊዜ አለ፡፡ ገና አልረፈደብንም፡፡ አሁንም — ምርጫው — በእጃችን ላይ ነው፡፡ አንድ ነገርም ደግሞ — አንርሳ፡፡ መጥፎም ሠራን ጥሩ — በስተመጨረሻ — ለራሳችን — ለትውልዳችን — ለወገናችን — የምናቆያት — ያቺኑ የመረጥናትን — ያንኑ የዘራነውን የመሆኑን አይቀሬ እውነት፡፡
ሰው — እንዳሰበው ብቻ ሳይሆን — እንደዘራውም — በዘራው ልክ — እንደዚያው ያጭዳል፡፡ ያጨደውን ያወራርዳል። ምድሪቱ እንደሁ ለሁሉ ያው አፈር ነች፡፡ ምድር ለሁሉ መረገጫ ናት — ላንዱ ከፍ ላንዱ ዝቅ ያላለች — ከሁሉም በታች እየተረገጠች የምትኖር — በኳንተሟ መጨረሻህን — እንደሥራህ አወራርዳ የምትከፍልህ — ምሥጢራዊዋ “ፍትሃ ነገሥት” ነች — ምድር፡፡ ‹‹እግዚአ-ብሔር›› የምንለውስ — ‹‹የምድሩ-ገዢ›› ለማለትም አይደል?? የእርሱ ግዛት — የእኛ ማረፊያ — ምድር!!!!
የምድሪቱ ጌታ — መልካም መልካሙን ያስመርጠን፣ — መጪ የጋራ ዕጣ ፈንታችን — አሁን በምንወስናት — የክፋትና የመልካምነት ውሳኔ ላይ የሚወሰን ነውና — አንድዬ — በየልቦናችን — ቀና ቀናውን አብዝቶ፣ አጉልቶ፣ አንግሦ — ያሳስበን — ያስዘራን — ያሳጭደን — ማለት — ከመቼውም በላይ — አሁን ነው፡፡
የመዶሻ ገጽ የገዛ ራሱን እጀታ በምስማር ሲጠቀጥቅ ቢውል — በስተመጨረሻ መያዣ መጨበጫ የሚያጣው፣ ያጣመመውን ለማቅናት በፈቸሉ ሲታገል የሚኖር፣ አካሉ በብስ መዓት ተሸነቋቁሮ አይሆኑ ሆኖ የሚቀር ራሱ መዶሻው ነው — እንጂ ማንም አይደለም — ራሱ እና ራሱ፡፡ በገዛ ራሱ — በገዛ ጭንቅላቱ — በገዛ ጉልበቱ — ራሱን የሚደበድብ መዶሻ  — የሚሰነጣጥቀው — የገዛ ራሱን አካል ነው፡፡
እና እኛም የዛሬ ኢትዮጵያውያን — እንደ መዶሻው — ራሳችንን በራሳችን አንምታ፣ አናጉድል፣ አንገዳደል፡፡ ራሱ የበቀለበትን የዛፍ ዘር እንደሚነድል ሞኝ ዛቢያ አንሁን፡፡ ራሱን እንደሚቀጠቅጥ ጅል መዶሻም አንሁን፡፡ ቢወለድም ወገን፣ ቢረግፍም ወገን መሆኑን እናስተውል፡፡
የወገን ያለህ እንዳንል —  ወገን ከወገን —  እጅና ጓንት እንሁን፡፡ ወገንን የሚያጎድል ነገር ሁሉ — አንድም ቢሆን — አንድ ሺህም — ገና ያልተወለደም ጽንስ ቢሆን — ሃገርን ያጎድላል — ወገንን ያጎድላል — ራስን ያጎድላል፡፡ ጎዶሎአችንን እንሞላላ እንጂ — የጎደለውን ከጎደለው በላይ አናጉድል፡፡
አንድ ላይ እናብር — መዶሻና እንጨት እንሁን፡፡ ማጭድና መዶሻ እንሁን፡፡ ብርኩማና ምሰሶ እንሁን፡፡ አፍና ጠፍር እንሁን፡፡ ምርኩዝና ዘንግ እንሁን፡፡ ባላና እጀታ እንሁን፡፡ ኣማዛኝና ኣመዛዛኝ እንሁን፡፡ ጆሮና ጉትቻ እንሁን፡፡ እርፍና ድግር፣ ማረሻና ሞፈር እንሁን፡፡ አብረን እንረስ፡፡ አብረን እንብላ፡፡ አብረን እንጠጣ፡፡ አብረን እንስራ፡፡ አብረን እንኑር፡፡
ዕድርህ ወገንህ ነው፡፡ ዕቁብህ ወገንህ ነው፡፡ ሰርግህን አድማቂ ወገንህ ነው፡፡ ቀባሪህ ወገንህ ነው፡፡ ሃገር ማለት ያለ ወገንህ ምንም ነው፡፡ ከንቱ ነው። ፍዝ የከንቱ ከንቱ፡፡ በባዶ ኦና ብቻውን እንደሚንሸዋሸው የመጋረጃ መርገፍ — ባዶ ኦና ነው ሰፈር ያለ ሰው፣ ያለ ጎረቤት፣ ያለ እድር፣ ያለ ወጭ ወራጅ ወገን!!!
ምድሪቱ እንደሁ — ኢትዮጵያችን እንደሁ — ምን ሊያጠቧት ቢተጉባት — አሁንም አርበ-ሰፊ ናት — ለሁላችን የምትበቃ፡፡ እንኑር በፍቅር ባንድላይ፡፡ ከራሳችን አንጣላ፡፡ ወገናችንን አናቁስል፡፡ የገዛ ወገናችንን አናጉድል፡፡ አንድ እንሁን፡፡ እርስ በርስ ከምንጫረስ — እርስበርስ አብረን ቆርጠን እንነሳ — ነፍጣችንን እንጣል — ይቅርታን አንነፋፈግ — ምህረትን እንለምን — ምድራችንን ቢያፍሱባት የማትራቆት ታላቅ ምስራቃዊ የዳቦ ቅርጫት እናድርጋት፡፡ ሃገራችንን ታላቅ የልምላሜ ሰገነት እናድርጋት፡፡
ለመጪ ትውልዶቻችን — የጎደለ አካልንና — የተቀባበለን ጠብመንጃ ሳይሆን — ታላቂቱን የእህል ጎተራዋ የማይነጥፈውን — ታላቋን ኢትዮጵያን በተባበረ ክንድ እናስረክባቸው፡፡ ሃገራችንን — ታላቅ የለቅሶ ድንኳን ሳይሆን — ታላቅ የእህል ስልቻ እናድርጋት፡፡ መዶሻችንን የጋራ ቤታችንን ለመሥራት እናውለው፡፡ አንደማማበት፡፡ የመጣብንን ጠላት “ሆ!” ብለን ለመቀጥቀጥ እናውለው፡፡ ለራሳችን መጥፊያ አናድርገው፡፡ አምላካችን ፀሎታችንን ይሰማን ዘንድ፡፡
“ኅብረትን እርቅን የማይወድ ይጠፋል፤ ጠብን የሚዘራ እሳት ውስጥ እንደሚደባለቅ ገለባ ነው፤ ከቶውኑም በፍለጋ አይገኝም” ይላል የጠቢቡ ቃል፡፡ ደግሞም “ሰው የዘራውን እ-ን-ደ-ዚ-ያ-ው ያጭዳል” ይላል ፡፡ እና ዛሬ በሀገር ላይ፣ በመንደር በቀዬ ላይ፣ በትውልድ ላይ የምንዘራውን እንምረጥ፡፡ ሕይወትን እንዲበዛልን እንፀልይ፡፡ ኅብረትን እንዲሆንልን እንትጋ፡፡ መጠፋፋትን እንዲከድንልን እንነሳ፡፡
ይህ የጠቢቡ ሠሎሞን የቀደመ የጥበብ ድምጽ ነው፡፡ ይህ የቀደምት ያገራችን ሽማግሌዎች ድምፅ ነው፡፡ ይህ የእርቅና የሠላም ድምፅ ነው፡፡ ይህ የወደፊቱን ራዕይ የሚያስተጋባ የተስፋ ድምፅ ነው፡፡ ይህ በማይረባ አንድ ምስኪን ወገን አንደበት የተነገረ የኢትዮጵያችን የመዳን ቃል ነው፡፡ አምላክ መስማትና መስማማትን ይስጠን፡፡ ልባችንን ወደ ቅንነቱ ይመልስ፡፡
ኢትዮጵያ በወገኖቿ ፍቅር ለዘለዓለም ትኑር፡፡
አሜን፡፡
አሜን፡፡
ምስጋና ለምስሉ እና ለጥበብ ሥራው፡-
ራሱን የሚወጋውን፣ አሊያም ሌላውን ሲወጋ ኖሮ በስተመጨረሻ ራሱ የተወጋጋውን፣ ይህን ግራ የገባው መዶሻ በረቂቅ ጥበባዊ ለዛ አሳምሮ (እና አስቀይሞም) ላቀረበልን – እና በዚህ ክፉ ዕጣ — የወደፊቱን መልካሙን አርቀን እንድናይ ለረዳን — ለአርቲቱ ሲዮ ኪዝሚክ ባለበት ልባዊ ምስጋናችን ይደርሰው ዘንድ ተመኘን፡፡
የጥበብ ሥራው መግለጫ፡-
Filed in: Amharic