>
5:13 pm - Thursday April 19, 2153

ግድ የላችሁም ከፍ እንበል! (ኢዩ ማ ሙሉ)

ግድ የላችሁም ከፍ እንበል 
ኢዩ ማ ሙሉ
ኢፍትሀዊ  ነገር በማንም ላይ ሲደርስ ጉዳዩ የተወሰኑ ሰዎች ወይም  የአንድ አካባቢ ወይም የአንድ ብሔር  ብቻ አድርገን አንወሰድ። በኛ ላይ እስኪደርስ አንጠበቅ።  ሕግ በአደባባይ ሲጣስ፣ ፍትህ ሲዛባ፣ ሚስኪኖችና ድምጽ ማሰማት የማይችሉ ሲጎዱ አይተን ዝም! ሰምተን ዝም አንበል።  ድምጻችንንእናሰማላቸው። ተነጣጠለን፣  በፍርሐት ተከበንና በዝምታ ፍትህ አይመጣም!!!
ከጥቂት ቀናት በፊት ዕጣ የወጣበትና በኃላም ‘የታገደው’ የኮንደሚኒየም ቤቶች አጀንዳ ብዙ ያነጋገረ ሲሆን በሂደቱም ጥሏቸው ያለፋቸው ጉዳዮች ነበሩት።
እንዲህም ሆነ። ሕዝቡ ብሩን ለአመታት ቆጠበ። ‘ጊዜው ደርሶ’ መስተዳደሩ ‘ዕጣ’ አወጣለት/አወጣበት። የደረሰው ደሰ አለው። ግን ሳይቆይ ግርግር ተከተለ። ተቃውሞ ተነሳ። ኦዴፓ ከች ብላ የቤቶቹ መተላላፍ ‘አግጃለሁ’ አለች። ምክንያት? ‘በኦሮሚያና በአአ ወስን አልተሰመረም’ ተባለ።
ምንም እንኳን የአአ ከንቲባ ምላሽ አስፈላጊ ቢሆንም እራሳቸውም የፌስቡክ ፔጃቸውም ዝም ። ጸጥ።
በቀጣይስ ከንቲባው ሕዝቡን በምን ድፍረት ያዩት ይሆን? ምንስ ይሉታል?
የኦዴፓ መግለጫም ዲፕሎማቲክ ቃና ያልጎበኘው
ምንም ኃላፊነት ያልወሰደና ሌሎች አማራጮችን ያልጠቆመ ፣ ለተፈጠረው mess እንኳን ይቅርታ አልጠየቀም።
በዛሬዋ አለም እንዲህ አይነት mess መፍጠር ብቻውን ከስልጣን ያስባርራል።  ኦዴፓ ጭራሽ  አንዱን ወገን ከጠየቃችሁት በላይ አደርጋለሁ ሲል ለሌላኛው ወገን ስሜት ያልተጠነቀቀ ነበር።
ከዚያም ጥያቄዎች ጎረፉ። የሴራ ፖለቲካ ትንተና ከየአቅጣጫው ተግተለተለ።
ምንም እንኳን ሰዎች ቀደመው የገመቱትና የጠረጥሩት ነገር ባይኖርም ክስተቶቹ  ሲቀጣጠሉ የሆነ ድራማ ለመሰራቱ ፍንጭ ሰጠ። ግን ለምን? ብዙዎች ከዕለት ጉርሳቸው ለአመታት ቆጥበው፣ ማንንም አፈናቅሉልኝ ሳይሉ፣ ቅድሚያ ለማረፊያ  ብለው፣ ቤት እሰጣለሁ ያለን  አካል አምነው፣ እርሷንም በዕጣ አግኝተው በድራማ ሲከለከሉ  አያሳዝንም?
*በግልጽ የሚታወቅና እንደ ድንገት ከሰማይ ያልወረደው  ኮንዶሚነየም ለዚያው በኮዬ ፈጬ ላይ  ቀድሞውኑ በማህበራዊ ሚዲያ እየተነሳ  ዛሬ ኦዴፓ ምንም እንደማያወቅ ለመምሰል ለምን ፈለገ? ጭራሽ ረቡዕ  ዕጣ ሊወጣ ሰኞ ማስታወቂያ ሲነገር አልሰማሁም ነው?
በነገራችን ላይ እሺ ኦሮሚያ ክልል  በዕጣ መተላለፉን መቃወም ይችል ይሆናል። ‘አግጃለሁ’ ማለት ይችላል? ጉዳዩስ ለብቻው አይቶ የመፍረድ ስልጣን አለውን?  የፌዴሬሽን ም/ቤት ወይም የፍርድ ቤት ውሳኔ አይቀድምም? እስቲ ባለሙያዎች በዚህ ጉዳይ ጥቂት በሉን! ነው ወይስ ግንበኞችም እኛ!  የፋይናንስ  ምንጭ እኛ! የሚሉት ጨዋታ ዞሮ መጣ?!
መልስ የለም እንጂ ጥያቄዎች ቀጠሉ….
*ከካሳም ባሻገር ‘ከልጆቻቸው ጭምር የኮንደሚኒየም ቤት ዕድል ያለ ዕጣ ተሰጣቸው’ ከተባለ ”ገበሬ ያለ ካሳ የተፈናቀለበት” የሚባለው ነገር አይጋጭም?
*ለመሆኑ ለምንድነው ብዙ ጊዜ ‘ከሳሽም ተከሳሽም’  ለግልጽ በሆነ በተጨባጭ መረጃዎች ተመስርተን የማንነጋገረው? ጥያቄዎች ብዙ ጊዜ ይምታታሉ! ገበሬው በግድ ያለካሳ ተፈናቀለ ነው? ፈጽሞ መፈናቀል የለባቸውም ነው?  ያለበቂ ሲባል ስንት በመረጃ? ለመሆኑ ስንት ገበሬ ተፈነቀለ? ምን ያህል ሔክታር ተለቀቀ?  የተከፈለ የካሳ ብር መጠን? ደግሞስ ከኮንደሚኒየሙ ለምን ያህል አባወራ ያለዕጣ ተሰጠ?የልጆቻቸውስ ብዛት? ወዘተ የሚሉት ለምን ግልጽ አይደረጉም?#transparency  #transparency
*ኮንዶሚኒየሙ ኦሮሚያ ክልል ነው ያረፈው ከተባለ እሺ ምን ይሁን? ኦሮሚያ ውስጥ ነውና ኦሮሞ ብቻ ይከፋፈለው ነው? የአስተዳደሩ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ  ኦሮሚያ በመሆኑ ለቤት እድለኞችም ሆነ ለክልሉ መንግስት በተለየ ምን የሚያሰጋ ነገር ይኖራል? አዲስ አበባ ሆነ ኦሮሚያ፦ የኢትዮጽያ! የኢትዮጳውያን !
እውነት ያ ሁሉ ቁጣ ኮንዶሚኒየሙ በኦሮሚያ ወይም በልዩ ዞን ስር ይካለል ለማለት ብቻ ነውን?  የኦሮሚያስ ክልል ወሰን ጉዳይ ከነለማ፣ ከነአብይና ታከለ ይልቅ እነ ጃዋር በጣም ‘የሚያንበግባቸው’ ለምን ይሆን???
*ተቃውሞስ በአመዛኙ የተገለጸበት መንገድ እውን አግባብ ነውን?ዱላ ገጀራ ጎራዴ እየያዙ ‘ሰላማዊ ሰልፍ’ አለን?
ጭራሽ ‘ሀገር እያስተዳደርን ነው’ የሚሉ እነጃዋር  ቦታው ድረስ ሔደው ወጣቶችን በስሜት በማነሳሳት ኮንደሚንየም ወይሞ ሞት አይነት ቀስቀሳ፣ በአአ ነዋሪ ላይ  የነበረው የጥላቻ ዘመቻና ቁጣ ዛቻ እጅግ አያስተዛዝብምን?   ወጣቶቹን እንደዚህ አታድርጉ ፣ እንዲህ አትበሉ  የሚል መካሪ ምነው አልታየም?
አሁን አሁን በነጃዋር በተለይም ውጪ የሚገኘው ጸጋዬ አራርሳ የሚባለው ነውጠኛ የሚያነሱት የ ‘ማስተር ፕላን፣ የኦሮሞ ገበሬ መፈናቀል፣ ያለበቂ ካሳ ” የሚሉት ግርግር ሽፋን እንጂ የዘመቻቸው አስኳል ‘ንጠቅ፣ ውረስ’ ‘ሌላው አንዳይደረስብ’ በሚል በተለይ ወጣቶቹን ስርዐተ አልበኛ እንዲሆኑና በጥላቻ ተሞልተው ሌሎችን ዜጎች ‘መጤ፣ ሰፋሪ’ በሚል  የመግፋት  እርምጃ መሆኑ ግልጽ እየሆነ ነው። ይህ እጅግ አደገኛ አካሔድ ከሚፈጥረው ማህበራዊ ቀውስ ባሻገር  በተለይ በኦሮሞና በሌላው ማህበረሰብ ጋር የሚኖረውን መልካም ትስስር  የማበላሸት አደጋ  ደቅኗል።ስለሆነም ችግሮችና አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ከተራ ስሜት ወጥተን ሁሉንም በሰከነና በሠለጠነ መንገድ የመፍታት አማራጭን በማስቀደም የአጥፊዎች ሴራ ማምከን የሁላችን ኃላፊነት  ሊሆን ይገባል።
የኔን አቋም ሲጠቃለል፦የገበሬዎች ኑሮ ፈጽሞ እንዲቃወስ አልፈልግም። ሲፈናቀሉም ተገቢ ካሳ እንደሚገባቸው አምናለሁ። ሲበደሉም ከጎናቸው እቆማለሁ። ቆሜም አውቃለሁ። ደግሞሞ በዚህኛው ጎራ ዜጎች አሰቸጋሪው ሕይወት ታግለው በመርፌ ቀዳዳ ዕድል  ለነርሱና ለቤተሰባቸው ማረፊያ የማግኘት መብታቸው ከነርሱ ጋር ፈጽሞ በማይገናኝ ምክንያት ሲነጠቁ ፍትህ ሲጓደልባቸውና ልባቸው ሲሰበር ማየት ክፉኛ ያሳዝነኛል።
ስለሆነም ለባለዕጣዎቹ መንግስት ሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ ተገቢና  ፈጣን መፍት በማምጣት ሊክሳቸውና የተፈጠረውን መጥፎ ድባብ እንዲያስወግድ እመክራለሁ።
በመጨረሻም፦ ኢፍትሀዊ  ነገር በማንም ላይ ሲደርስ ጉዳዩ የተወሰኑ ሰዎች ወይም  የአንድ አካባቢ ወይም የአንድ ብሔር  ብቻ አድርገን አንወሰድ። በኛ ላይ እስኪደርስ አንጠበቅ።  ሕግ በአደባባይ ሲጣስ፣ ፍትህ ሲዛባ፣ ሚስኪኖችና ድምጽ ማሰማት የማይችሉ ሲጎዱ አይተን ዝም! ሰምተን ዝም አንበል። ድምጻችንን እናሰማላቸው።
ተነጣጠለን፣ በፍርሐት ተከበንና በዝምታ ፍትህ አይመጣም። ግድየላችሁም ከፍ እንበል!!
#ክብር_ለዜጎቻችን_በሙሉ
Filed in: Amharic