>
5:13 pm - Thursday April 20, 8169

ኢትዮጵያዊነት ሲፋቅስ? (ደረጄ ደስታ) 

ኢትዮጵያዊነት ሲፋቅስ?
ደረጄ ደስታ 
ኢትዮጵያዊ ለመሆን የሚሊዮን ህዝብ ጋጋታ፣ የአጀብና የመንጋ ኳኳታ አያስፈልግም። ኢትዮጵያዊ ሆኖ የተወለደ ሰው ብቻውን ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሳይቀይራት፣ ሌላ የብሄር ድሪቶ ሳያለብሳት፣ ብቻውን ሆኖ እንዳወደሳት፣ ታሪክን ትዝታውን እየጠጣ ሊሞት ይችላል።
*  መገንጠል የግድና አይቀሬ ከሆነ ኩሩና ሙሉ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ጎዶሎና ስንኩል አስተሳሰብ ካላቸው ኢትዮጵያውያንም መገንጠል ይቻላል!!!
የኢትዮጵያ ድምፅ፣ በኋላ ደግሞ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ከበደ አኒሣ እንደ እናቴ ልጅ የምቆጥረው ነው።  በንጉሡ ዘመን በየሳምንቱ ቅዳሜ ወደ አራት ሰዓት ይመጣና “ና ቡና ጠጥተን እንመለስ” ይልና ይዞኝ በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት በኩል ይነዳል። ልክ ቤተ መንግሥቱ አጠገብ ስንደርስ እኔም እሱም አንገታችንን አውጥተን ግቢውን እንቃኛለን። ሁለት የሰንደቅ ዓላማ መስቀያ የብረት ምሶሶዎች አሉ። አንደኛው አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ የሚውለበለብበት ነው። ሁለተኛው (አጠር ያለው) ደግሞ አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ዓርማ ሆኖ ከመሐል አንበሳ አለው። ያ የጃንሆይ ሰንደቅ ዓላማ ሲሆን እሳቸው በከተማው ከሌሉ አይውለበለብም። የንጉሠ ነግሥቱ በከተማው መኖር አለመኖር ምልክት ያ ነበር። ስለዚህ ትንታጉ ጋዜጠኛ ከበደ አኒሣ “ ዛሬ ጃንሆይ በአዲስ አበባ ስለሌሉ መንግሥት በሌለበት ከተማ ምን እናደርጋለን ?” እያልን እብስ ማለት እንደ ባህል ተያዘ። በ እኛ ዘመን ቡድናችን (የእግር ኳስ አለዚያም ጊዮርጊስ) ቢያሸንፍም በደስታ፣ ቢሸነፍም በንዴት በቢራው ማዝገም የተለመደ ነበር። ስትናደድም ትጠጣለህ፣ ሲከፋህም ትጠጣለህ። (ስንሻው ተገኝ/ሙሉጌታ ሉሌ ፌብርዋሪ 27/2014)
ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ ትዝ አለኝ። ከሁሉ በላይ ደግሞ እሱ ያጫወተኝ የከበደ አኒሣ ታሪክ ታወሰኝ። ለዛሬው ዘመን ያስፈልግ ስለመሰለኝ መዘዝኩት። በግርማዊነታቸው ዘመን “ኢትዮጵያ ትቅደም!” እሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ  “ኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ላይ” የተጠቀሙት አዘጋጁ ከበደ አኒሣ ነበሩ ። ከሚያዘጋጅዋት ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጻቸው አናት ላይ ከፍ አድርገው እንደ መፈክር አኑረዋታል ይባላል። ደርግ መጥቶ ኢትዮጵያ ትቅደምን “አቆርቋዥዋ ይውደም!” እሚል ጨምሮበት ትንሽ ደም ቀባባት እንጂ ነገርዮዋስ ውብ ነበረች።
እንደመሠረት ቸኮል ጥናታዊ ሥራ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር ለማቋቋም በ1950ዎቹ እስከ 60 ዎቹ ሶስት ያህል ሙከራዎችን አድርገዋል። በመጨረሻው ተሳክቶላቸው በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የጋዜጠኞች ማህበር “EJA” የካቲት 23/1961/ወይም ማርች 1 1969 ሲመሰረት ፕሬዚዳንት አድርጎ የመረጠው ከበደ አኒሣን ነበር። ከበደ የኢትዮጵያ ድምጽ ዋና አዘጋጅ ነበሩ። ማህበሩን የጠነሱስት እነ ማዕረጉ በዛብህ፣ አሳምነው ገ/ወልድ ፣ ከፊያለው ማሞ፣ ሙሉጌታ ሉሌ፣ መርስ ኤሐዘን አበበ፣ አጥናፍ ሰገድ ይልማና ነጋሽ ገ/ማሪያም ነበሩ። በጋዜጠኝነቱም ሆነ በሌላም የሙያ ዘርፍ የዚያው ዘመን ታላላቅ ሰዎች የነበሩ ኢትዮጵያውያን ያስቀኑ ነበር። ኢትዮጵያን እንደ አስቀደሙት እንደነ ከበደ አኒሣ ያሉ በዛሬው የማንነት ገበያ ኦሮሞ እየተባሉ ተነጥለው እሚሞገሱ ወይም በጅምላ ያልተከሰሱ ቋጥኝ ሰዎች ብዙ ነበሩ።
ቴዎድሮስን በአዲሱ ትውልድ አእምሮ ውስጥ በመድረክ አምጥቶ ልዩ ገጽታ የዘራበት ኢትዮጵያዊው ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድን ቀዊሣ ነው።
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ውስጥ እነ ይልማ ደሬሣ ቡልቻ ደመቅሣ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።
በስነ ግጥምና የአማርኛ ጽነሑፍ ውስጥ እንደ ሰሎሞን ዴሬሣ ያሉት ከፍ ያለ ቦታ አላቸው።
አማርኛን በኪነጥበብ የሞዘቀውና በዩኒቨርስቲ ሳይቀር አማርኛ ለስነጽፍሁ ማስተማሪያነት ያበቃው አፉን በኦሮምኛ የፈታውና ለኢትዮጵያው የተሰዋው በዓሉ ግርማ ፤ እነ ብዙነሽ እና ጥላሁን ገሠሠ ተወዳጅ ዜማዎች በመድረስና ማቀናበር የታወቁት እነ ሣህሌ ደጋጎ ይጠቀሳሉ። በእነምኒልክ ዘመን የነበሩ የጦር አበጋዞችን የአድዋ ጀግኖችን ይዘን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያዊነት በሰሜንና ደቡብ የወደቁ በርካታ የሠራዊት አባላትና ጀግኖች የጦር መኮንኖችን እናስታውሳለን። በኢትዮጵያዊነታችን “እንደራደራለን” እያሉ ያልተመጻደቁ ጓሮ ለጓሮ ህዝብ እያፈናቀሉ እማያስጨንቁ፣ ግን ደግሞ አክራሪ ዘመንተኛ ጋር ተጨፍለቀው በሌላው አክራሪ ዘረኛ እማይወገዙ ቢሆን እንደምን ፍትህ በሆነ ያሰኛል። ቢሆንም ግን ታዲያ ገና ለገና ጃዋር ቀባዠረ ተብሎ፣ በጸረ ጃዋር ጃዋሮች ጭምር ሞቅታ ተነሳስቶና ተሳስቶ፣ አንድን ህዝብ ነጥሎ ጦርነት ለማወጅ መሟሟቅ እብደት ነው። ወይ ኦሮሞ፣ ወይ አማራ፣ ወይት ትግሬ ብቻ ሁን ብሎ ጥድፊያና ግፊያም ያው ገደል ነው።
ይህ መባሉ ያው መቸም ኢትዮጵያዊነትንም ሆነ ጎሰኝነትን በሞኖፖል የያዘ ብሔር የለም ለማለት ነው። በዛሬው የዘር ገበያ ኦሮምያ፣ በትላንቱ የሰው ዘር ኢትዮጵያ የነበሩ እነዚህ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውንም ለማስታወስ ነው። አገርና ነገር የመረረው አይጠፋም። በዚያ ላይ ደግሞ የጨነቀው እርጉዝ እያገባ፣ አማራው ከኦሮሞው፣ ወይም ትግሬው ከአማራው፣ ወይም ትግሬው ከኦሮሞው ድርጅት እየተጋባ አንዱ አንዱን አግልሎ ሌላኛውን ጥሎ እንዲገፋ የጥንድነት አጋር መረጣ ምክር ሲሰነዘር እየታየ ነው። ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አይደለም እሚል አዋጅ ሊታወጅም ትንሽ የቀረ እስኪመስል ድረስ “በአይደለንም እና አዎ አይደላችሁም” ባዮች ጭፍን ግልቢያ ነገር እየተበላሸ ስሜት እየታሸ ነው። ኢትዮጵያዊ አይደለሁም እሚሉትን መናገር አንድ ነገር ነው፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ ያለውን ደምሮ መግፋት ግን ሌላ መጥፎ ነገር ነው።
ይህ ዓይነቱ ጭፍን አካሄድ፣ ትናንትም ሆኖ እንደታየው፣ ኢትዮጵያውያንንም ከኢትዮጵያውያን እንዲገነጠሉ ሊያስደገድዳቸው ይችላል። ጭፍንና የጥላቻ አመለካከት ካላቸው ኢትዮጵያውያን ለመገንጠል ብሔርና ጎሳ ውስጥ መወተፍ አያስፈልግም። እሚይዙት መሬት እሚከልሉት ክልል ላይኖርም ይችላል። ኢትዮጵያዊ ስሜቱንና ማንነቱን ብቻ ታቅፎ፣ በአገር ውስጥ ተጠርንፎ በስደትም ቢሆን አኩሮፎ ያለ ቡድን ተገንጥሎ መኖር ይቻላል። ኢትዮጵያዊ ለመሆን የሚሊዮን ህዝብ ጋጋታ፣ የአጀብና የመንጋ ኳኳታ አያስፈልግም። ኢትዮጵያዊ ሆኖ የተወለደ ሰው ብቻውን ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሳይቀይራት፣ ሌላ የብሄር ድሪቶ ሳያለብሳት፣ ብቻውን ሆኖ እንዳወደሳት፣ ታሪክን ትዝታውን እየጠጣ ሊሞት ይችላል። መገንጠል የግድና አይቀሬ ከሆነ ኩሩና ሙሉ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ጎዶሎና ስንኩል አስተሳሰብ ካላቸው ኢትዮጵያውያንም መገንጠል ይቻላል። ካለፉትም አሁን ካሉትም ሆነ ተራ እየጠበቁና እየተጠመቁ ካሉ መጪዎቹ ዘረኞች ጭምር። ቁም ነገሩ ኢትዮጵያዊነትን በሞኖፖል የያዘ ማንም አለመኖሩን አበክሮ ማመኑ ላይ ነው።! ኢትዮጵያዊ ማለት ኢትዮጵያዊነቱ ሲፋቅ ያው ኢትዮጵያዊ ብቻ ሆኖ የሚገኝ ማለት ይመስለኛል። በትልቅ መላጊያ ከተላገ ደግሞ ሰውና ሰው ብቻ ሆኖ ይገኛል። ከሰሜን ከደቡብ ሁሉም ወገነኑ እየገበረ ባለበት ወቅት ተነጥለው እሚያብዱለትም ሆነ ነጥለው እሚገድሉት ህዝብ መኖሩ ፍትህና ሚዛን አይደለም። ያው ከሰውነት ያነሰ ከኢትዮጵያዊነት የተቀነሰ ማንነት ነው። ስትፋቅ ምንድነህ?
Filed in: Amharic