>
5:13 pm - Monday April 19, 3976

ለሽብርተኞች፣ ለወንበዴዎችና ዘራፊዎች የጠፋ መንግሥታዊ ኃይል ለንጹሐን ወጣቶቸ ከየት ተገኘ? (ይኄይስ እውነቱ)


ለሽብርተኞች፣ ለወንበዴዎችና ዘራፊዎች የጠፋ መንግሥታዊ ኃይል

ለንጹሐን ወጣቶቸ ከየት ተገኘ?

ከይኄይስ እውነቱ

በዘመነ ወያኔ ኢትዮጵያ የአገር መከላከያና የሕዝብ ደኅንነት ኃይል አልነበራትም፤ አሁንም የላትም፡፡ የዐቢይ አገዛዝ ትልቅ ሥራ ሠርቼ እንደገና አዋቅሬዋለሁ ያለው የወያኔ ሠራዊት (በተረኞች መንደርተኞች የበላይነት መዋቀሩን ሳንዘነጋ) አገራችን መንግሥት አልባ ስትመስልና መሀሉ ዳር ሲሆን ቁጭ ብሎ በዝምታ የሚመለከት፤ ባዶ እጃቸውን በሚወጡ ንጹሐን ላይ እና ቤት አፍርሶ ዜጎችን በማፈናቀል ጉልበቱን በግፉአን ላይ የሚፈትሽ ኃይል እንደሆነ እየታዘብን ነው፡፡ በየክፍላተ ሀገሩም የሚገኙ የወያኔ አገዛዝ ያቋቋማቸውና ዐቢይና ለማም ቡራኬ ሰጥተው ያሰቀጠሏቸው ‹ልዩ ኃይል› የተባሉ ሕገ ወጥ ጉልበተኞች እና በሕግም ተቋቋሙዋል የሚባሉ የፖሊስ ኃይሎች በጐሣ አለቆች የሚመሩ ጐሣን መሠረት አድርገው የሚሠሩ ‹ተናካሽ ውሾች› መሆናቸውን በተደጋጋሚ በተግባር አሳይተዋል፡፡

በየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት በሰላም ወጥቶ መግባት የሚባል ነገር ካለ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ቸርነትና ጥበቃ እንጂ የኔ ነው የሚለው፣ የሚተማመንበትና የሚኮራበት የፖሊስና የደኅንነት ኃይል የለም፡፡ እንዲያውም ከተራ ቀማኛና ዱርዬ ይልቅ በ‹ሕግ አስከባሪነት› ሽፋን ያሉትን ጉልበተኞች መሸሽ የተለመደ ሆኗል፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የተደራጀ ዝርፊያ ፈጻሚና አስፈጻሚ እስከመሆን ተደርሷል፡፡

በተለይም የአዲስ አበባ ወጣት ቀደም ሲል ለወያኔ ትግሬ አሁን ደግሞ ለወያኔ ኦሕዴድ ባደሩ ‹ሕግ አስከባሪ› ተብዬዎች የቡጢ መሠንዘሪያ ከረጢቶች (punching bags) ሆነዋል፡፡ በቡራዩው ‹ድንገት› በአነጣጣሪዎች ሲገደሉና ታፍሰው በርሃ ሲጣሉ፤ ባለፈው እሑድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ደግሞ ስለ አዲስ አበባ ጉዳይ በተጠራው ሕጋዊና ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ላይ ተካፍለው ወደየቤታቸው የሚመለሱ የከተማዋን ወጣቶች እነዚሁ በግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ የሚተዳደሩ ‹ተናካሽ ውሾች› የተለመደ ነውራቸውን ሲፈጽሙ፤ የተፈጸመው ነውርና አሳፋሪ ድርጊት ከዐቢይና ለማ ዕውቅና ውጪ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ በተሰፋ የሚኖርን ወጣት በዱላ መቀጥቀጥ፣ ‹አሥረን መክረን ለቀቅን› ማለት ከየት የበቀሉ ጉዶች ቢሆኑ ነው? ሕግን ለሚያስከብር እውነተኛ ፖሊስ ዱላና ጠብመንጃ ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ተፈጥሮ ሰላማዊ ዜጎችንና ራስን ለመከላከል በመጨረሻ አማራጭነት ሥራ ላይ የሚውል እንጂ በፈለገ ጊዜ ዜጎችን ለመቀጥቀጥና ለመግደል በየትኛውም መመዘኛ መብት የለውም፡፡ በተቃራኒው በቡራዩ ጭፍጨፋ ተጠርጣሪ የሆኑ ወንበዴዎችን፣ እንደ ጀዋር ያሉ ማን አለብኝ አሸባሪዎችን፣ ሌሎችን ለመጉዳት ባደባባይ ገጀረና ዱላ ይዘው የወጡና በሕዝብ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ዛቻ ሲያሰሙ የነበሩ ጋጠ ወጦችን ለፍርድ ለማቅረብ ፍላጎቱ የሌለውና ከተማዋን የማያውቋት ‹ፖሊሶች› ነው አዲስ አበባ ላይ የተጫኑት፡፡

ለመሆኑ ጠ/ሚ ዐቢይ ‹‹ለውጡን እንደግፍ ዴሞክራሲን እናበረታታ›› በሚል መሪ ቃል የአዲስ አበባና አካባቢው ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም. በመስቀል ዐደባባይ በተደረገው ሕዝባዊ ሰልፍ ላይ ያቀረበውን ንግግር ያስታውሰዋል? አንዳንዴ በተናገራቸው ንግግሮች ላይ በጥንቃቄና ጥልቀት ማሰቡ (reflect ማድረጉ) ከትክክለኛው ሐዲድ ላለመውጣት ይጠቅም ይሆን? የንግግሩ ዋና ይዘት እንደሚከተለው ተጠቅሷል፤
‹‹በፍቅርና ባንድነት ጀምሮ መጨረስ የተሳነው ስለሌለ የዛሬው የፍቅርና የምስጋና ቀን መድረስ ከሚገባን ማማ የሚያደርሰን የመጀመሪያው ጡብ መቀመጡን ያሳያል፡፡ .. መሪ ያለ ሕዝብ ፍቅር ባዳ ነው፤ መሪ ያለ ሕዝብ አንድነት ባዶ ነው፡፡ …መሪ ያለ ሕዝብ አለኝታነት ከንቱ ነው፡፡ … ይሄ ክልል የኔ ነው፤ ይሄ ወሰን የኔ ነው፤ ውጡልን መባባል አቁመን በፍቅር ተግተን ለሀገራችን መሥራት የጀመርን ዕለት ያኔ ምሥጋናችሁ በሌለንበት እንደደረሰን ቁጠሩት፡፡ … ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ገናናነቷ እንደምትመለስ ቅንጣት ጥርጣሬ አይኑራችሁ፡፡ … የእምነት አባቶች ዘረኝነትንና ሙስናን አጥፍታችሁ ደሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ በሉ፡፡ … አገራችንን ከወደድን ግዴታችንን እንወጣ መብታችንን እንጠይቅ፡፡ … ሹመት ማገልገያ እንጂ መገልገያ አይሁን፡፡ … አገራችንን ከወደድን የሚፈናቀለውና የሚንገላታው እያንዳንዱ ዜጋ ኢትዮጵያ ነው ብለን እንቁም፡፡ … አገራችንን ከወደድን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል አንድ ኢትዮጵያዊ መብቱ ሲጣስ ብሔሩን ወይም ሃይማኖቱን ወይም ሌላ ማንነቱን ሳንመለከት ወገኔ ተነካ ብለን እንቁምለት፡፡ ኢትዮጵያ ተነካች…ብለን እንቁምለት፡፡››
ከፍ ብለን የጠቀስነው የጠ/ሚ ዐቢይ የፖለቲካ ንግግር በጊዜው የኢትዮጵያን ሕዝብ አንጀት ‹ቅቤ ያጠጣ› እና ባለተስፋ እንዲሆን ያደረገ ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ ቢያንስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን አክብሮት ለመግለጥ እና ከልቡሳነ ሥጋ አጋንንት ሕወሓት ጋር ፍቺ መፈጸሙን በማሳያነት (as a gesture of respect to Ethiopian people and divorce with the devil incarnate TPLF) ከአዲስ አበባ ጀምሮ ብሔራዊ የዜግነት መታወቂያ ለሕዝብ ይሰጣል የሚል እምነት ነበረን፡፡ እግረ መንገዴን ላዲስ አበባም ሆነ ለተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላሳስብ የምፈልገው ከእንግዲህ ወዲህ የጐሣ ማንነት የተለጠፈበት የመታወቂያ ካርድ መቀበል የለብንም፡፡

አሁን ከ10 ወራት በኋላ ምድር ላይ ያለው ጽድቅ የቁልቁለቱን መንገድ ዳግም መጀመራችንን በዓይናችን በብረቱ ዕያየን ነው፡፡ መሠረትና ጉልላቱ ጐሠኝነት የሆነው የዐቢይ ድርጅት ለማ በሚገዛው ክ/ሃገር አስተባባሪነት ጐሠኝነትን አንግሦ ለመቀጠል የተፈጣጠመ ይመስላል፡፡ ለቁልቀለቱ መንገድ በቂ ምልክቶች ታይተዋል፡፡ (ሕግና ሥርዓትን ማስከበር አለመቻል/ዳተኝነት፤ በከፍተኛ ደረጃ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በንቅዘት ተጠርጣሪ የሆኑ በ‹ግንባሩ› ውስጥ የሚገኙ ድርጅቶች አመራር አባላትን ወደ ፍርድ ለማቅረብ አለመፈለግ ወይም በጅምር መቅረት፤ ሹመት ጐሣን መሠረት ከማድረጉ በተጨማሪ በከፍተኛ ወንጀል ተጠርጣሪዎችን ሚኒስትር፣ አምባሳደር አድርጎ ከመመደብ አንስቶ እስከ ተራ መንግሥታዊ ቅጥር የሚታየው ብልግና፤አንዳንዶቹን ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቅጥር ሽፋን ማሸሽ፤ በአዲስ አበባና ድሬደዋ ላይ በተቀነባበረ መልኩ የሚደረጉ ሕገ ወጥ ተግባራትና የአሸባሪነት ድርጊቶች፤ ሊሠሩ የማይችሉ ኮሚሽኖችንና ኮሚቴዎችን በማቋቋም የማዘናጊያ ርምጃ መውሰድ ወዘተ. ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡)
ይህንን ዓይቶ ራስን ማስተካከል፣ ከግፍ እና ጐሠኝነት አዙሪት ወጥተን ኢትዮጵያን ባንድነቷና በክብሯ ለማስቀጠል የምንፈልግ እያንዳንዳችን ዜጎች በተናጥልና የኢትዮጵያ ሕዝብ በወል ባገራችን ዕጣ ፈንታ ላይ ድርሻ እንዳለን በሚገባ ተረድተን ኃላፊነታችንን ባግባቡ መወጣት ይኖርብናል፡፡ ጉዳዩን ራሳቸው ኮስሰው አገርን ለሚያኮሰሱ መንደርተኞች ከተውነው 89 መንደሮች እንጂ አገር አይኖረንም፡፡ መንደሮቹም ለመቀጠላቸው ዋስትና አይኖርም፡፡

ወደ ቀደመ ነገሬ ስመለስ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ከከተማው የወጣና የተመረጠ ከንቲባና የፖሊስ ኃይል እንደሚያስፈልገው የወሰነውና ለዚህም ተደራጅቶ በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀስ ቃል የተገባባው ከተማዋ ባለቤት አልባ ሆና በመቆየቷና አሁን ደግሞ በፌደራሉ መንግሥት፣ በኦሮሞ ክ/ሃገር ገዢዎች፣ በገዢው ‹ፓርቲ› (ኦሕዴድ) ተረኛ መንደርተኞች እና በ‹ተረፈ ወያኔዎች› (ኦነጋውያንና ጀዋራውያን) ኅብረት የኢትዮጵያን መናገሻ ነዋሪ አልባ ለማድረግ ‹የባለቤትነትና የልዩ ጥቅም› ጥያቄ አንግበው አዲስ አበባን እንደ ፍልፈል የመቦርቦር ድርጊት ከጀመሩ ውለው ማደራቸውን በሚገባ ስለተረዳው ነው፡፡ እስካሁንም የታገሠው ‹የለውጡ መሪዎች› የተባሉት የለማና ዐቢይ አማላይና የሽንገላ ንግግር (rhetoric) በማመን እና በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የፈጸሟቸውን በጎ ርምጃዎች በቀናነት በመመልከት ነበር፡፡ በነዚህ ‹የለውጥ መሪዎች› ተሟጥጦ ያላለቀ ተስፋ ካለ በቀጣይ የምናየው ይሆናል፡፡ የለማም ሆነ የዐቢይ እውነተኛ ‹ቀለም› የትኛውም ይሁን፣ እኛ ግን ያለመጠባበቅ ለአገር ይበጃል የሚለውን ከመሥራት አንቦዝን፡፡

ሲጀመርም በግለሰቦች (ቅንና አስተዋይ ቢሆኑ እንኳ) መታመናችን የአብዛኞቻችን ስህተት ነው፡፡ ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራም እንደተባለው ከእንግዲህ ወዲህ በኢትዮጵያ ባጠቃላይ በአዲስ አበባ እና በድሬደዋ በተለይ ለሚደረገው የአገር ህልውናን የማስከበር፤ ፍትሕ፣ እኩልነትና፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት የሕዝብ መንግሥት የመመሥረት ሕዝባዊ ጥያቄና ፍላጎት ከሌሎች በችሮታ የሚሰጠንና መልስ የሚያገኝ አለመሆኑን በሚገባ ተገንዝበን የፖለቲካ ማኅበራትን ሳንጠብቅ በራሳችን ተደራጅተን መንቀሳቀስ አንገብጋቢ አጀንዳችን ነው፡፡ ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ!!!

Filed in: Amharic