>

ከኦዴፓ የባለቤትነት ጥያቄ ጀርባ የሚጠብቀን መራር እውነታ!! (ወንድወሰን ተክሉ)

ከኦዴፓ የባለቤትነት ጥያቄ ጀርባ የሚጠብቀን መራር እውነታ!!
ወንድወሰን ተክሉ
* ከነገደ ኦሮሞ በስተቀር መላው የአዲስ አበባ ሕዝብ «የመጤነት Status » ሊሰጠው ነው!!!
**ይድረስ ለመላው የአዲስ አበባ ሕዝብ በሙሉ-በህልውናህ ላይ የተደገሰልህን ታውቃለህን??
   —-
የጠ/ም ጽ/ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ ጉዳይ በኦዴፓና በከተማይቱ መስተዳድር መካከል ለሚደረገው ድርድር ከሁለቱም ወገን የተወከሉ የስምንት ሰዎችን ስም (አራት ከኦዴፓ እና አራት ከአዲስ አበባ መስተዳድር) ይፋ አድርገዋል፡፡ ከስምንቱ ውስጥ አምስቱ የኦሮሞ ተወላጆች ሲሆኑ ሶስቱ ደግሞ የሌላ ብሄር ተወላጆች ናቸው፡፡ በከተማዋ ላይ በዓለም የዋና ከተሞች ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያና ልዩ የሆነውን የአንድ ነገድ ባለቤትነትን ጥያቄ አንስቶ በይፋ ከተማይቱ የ«እኛ ናት» ባለው ኦ.ዴ.ፓ እና አዲስ አበባን በመወከል ደግሞ በራሱ በዚህ ድርጅት ማለትም ኦዴፓ ከፍተኛ አመራር በሆነው ኢንጂነር ታከለ ኡማ የሚመራ መስተዳድር መካከል ድርድር የተባለው ቧልት ይካሄድ ብሎ መወሰን ፍጹም የሆነ ኢ-ፍትሃዊነት ከመሆኑም ባሻገር ሂደቱ ቀደም ብሎ በዚሁ ሳምንት በኦዴፓ በኩል «በአዲስ አበባ ጉዳይ መወሰን የሚችለው ባለቤቱ የሆነው የኦሮሞ ህዝብ ብቻ በመሆኑ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሳያውቀውና ሳይፈቅድ የሚካሄዱ ማናቸውም አይነት ግንባታዎች ተቀባይነት የላቸውም » ብሎ የአዲስ አበባን ባለቤትነትን ያወጀውን ድርጅትና ኃይልን ተግባር ህጋዊነትን የማላበስ የፎርማሊቲ ስራን ለመስራት ካልሆነ በስተቀር በአዲስ አበባዊያን ላይ ለተደቀነው አደጋና ችግር መፍትሄ ያመጣል ብሎ መጠበቅም ሆነ ማሰብ የሚቻል አይደለም፡፡
እስቲ ይህንን ጉዳይ በጥሞና፤በሰከነ ስሜትና ከወገናዊነት መንፈስ በራቀ እይታ ለማየትና ጉዳዩን በጥልቀት ለመረዳት እንሞክር፡፡
**የአዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስር መውደቅ የሚያመጣው ለውጥ ምንድነው ??
    የመጤነት እጣፈንታና መብትና ግዴታው
የኦሮሚያ መሬት ጉዳዮች ምኒስቴር የተባሉት ዶ/ር ምልኬሳ ሚደቅሳ «በአዲስ አበባ ጉዳይ መወሰን የሚችለው ባለቤቱ የሆነው የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ነው፡፡ ሌላው እዚያ ነዋሪ ነኝ የሚለው መጤ ባለቤት ስላልሆነ ምንም የሚያገባው ነገር የለም» ሲሉ በዚህ ሳምንት የድርጅታቸውን አቋም አሳውቀዋል፡፡
    አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስር ስትሆን የመጀመሪያው ለውጥ የነዋሪዎቻ Status ዛሬ ካላቸው የዜግነትና የከተማይቱ ባለቤትነት መብት ከመቅጽፈት ወደ መብት አልባነት «መጤ» Status ሙሉ በሙሉ ይለወጣሉ፡፡ ይህ የ«መጤነት Status » የሚመለከተው የከተማይቱ ነዋሪ የሆነውን አጠቃላይ የኦሮሞ ተወላጅ ያልሆነውን አማራ፣ጉራጌ፣ትግሬ፣ሲዳማ፣ጋምቤላ፣ሱማሌ፣ጋሞ ወዘተን በሙሉ የሚያጠቃልል ነው፡፡
**የመጤነት Status መብትና ግዴታ ምንድነው?
በዛሬይቷ ኢትዮጵያ በኦሮሚይ ክልል ውስጥ የሚኖሩ የነገደ አማራ ተወላጆች ቁጥር ከአስር ሚሊዮን በላይ ቢሆንም አንድም የነገደ አማራ ተወላጅ የህዝብ ተመራጭ፣ሹመኛ ሆኖ ተወልዶ ያደገበትን ሀገርና ህዝብ ሲያገለግል ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ ይህ ምሳሌ እንጂ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ማለትም በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በሱማሌ፣ በጋምቤላና ወዘተ ክልሎች ውስጥ የየክልሎቹ ነገዶች ተወላጅ ካልሆነ በስተቀር አንድም የዚያ ክልል ነገድ ተወላጅ ሳይሆን ግን በዚያው ክልል ውስጥ ለሶስትና አራት ትውልድ ጀምሮ ቤተሰቦቹ እየተወለዱ የኖሩበት ክልል ቢሆን እንኳን ፖለቲካዊ መብቱ ተገፎ በመጤነት Status እንዲኖር የተደረገበትን ሁኔታ ነው የምናውቀው፡፡
የመጤነት Status  የፖለቲካዊና ማህበራዊ መብቶችን ይገፍፍና የዚያ አከባቢ ባለቤት ነኝ ብሎ በተቆጣጠረው ገዢ ኃይል እንደ ባእድ የውጪ ዜጋ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር፤በተፈለገበት ማንኛውም ሰዓትና ወቅት የያዝከውን መሬትና ንብረት ልቀቅ ሲባል እየለቀቀ የሚኖር መብት አልባ ጥገኛ ማለት ነው፡፡
ይህ ማለት አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ስር ውስጥ ብትጠቃለል በከተማዋ አስተዳደር ውስጥ ተሾሞ እሚሳተፈው የኦሮሞ ተወላጅ ብቻ ይሆንና የተቀረው የኦሮሞን ህዝብ አስጠብቃለሁ እያለን ባለው ኦዴፓ በጎ ፈቃድ ብቻ እንዲኖሩ የሚደረግ ሲሆን ይህም ድርጅቱ ደስ ባለው ጊዜና ደስ ያላለውን ማንኛውንም «መጤ» ያለውን የከተማዋን ነዋሪ እንዳሻው የማፈናቀል መብት ይጎናጸፏል ማለት ነው፡፡
በቅርቡ ከለገጣፎ ቤታቸው በላያቸው ላይ እየተደረመሰ የተባረሩት ዜጎች ህግ ስለጣሱ ሳይሆን በኦዴፓ አንደበት «መጤ ሰፋሪዎች » ስለሆኑ ነው፡፡
የአዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስር መውደቅ ከነገደ ኦሮሞ ተወላጅ በስተቀር አጠቃላይ የከተማይቱን ህዝብና ኢትዮጵያዊያኖችን በመጤነትStatus  ይፈርጅና በማንኛውም መንግስታዊና ማህበራዊ ኃላፊነት ቦታ ላይ የመመረጥን መብት በማገድ በኦዴፓ በጎ ፈቃድ ብቻ የሚኖር መብት አልባ ዜጋ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ይህ አይደለም ለአዲስ አበባ ነዋሪ ይቅርና ለማንኛውም ክቡር ለሆነ የሰው ልጅ እማይገባና እጅግ አስጸያፊ የሆነ ፋሺስታዊና አፓርታይዳዊ ስልት ነውና መላው የአዲስ አበባ ህዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በንቃትና በትጋት በርትቶ የታቀደውን ኢ-ፍትሃዊ የሆነውን የባለቤትነት ሴራን ማፍረስና ማክሸፍ ይጠበቅበታል፡፡
**ለምንድነው የኦዴፓ ፓርቲ አዲስ አበባን ሊቀራመት እንዲህ አሰፍስፎ የቸኮለው ? ይህ ሁሉ ችኮላ ለምን አስፈለገ?  
   ሐሙስ መጋቢት 8ቀን 2019 የአምቦ ህዝብ ከልጅ እስከ አዋቂ እቤት የተገኘ ይቀጣል ተብሎ የታዘዘ ይመስል ግልብጥ ብሎ በመውጣት ከተማዋን አጥልቅልቋት ውሏል፡፡ የሰልፉም መንስኤ የኮንደሚኒየም ቤቶችና የአዲስ አበባ ጉዳይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ አምቦን ለተምሳሌትነት ጠቀስኩ እንጂ በመላ ኦሮሚያ አንዲትም ከተማና መንደር ሳትቀር ተመሳሳይ የሆነ ሰልፍ ለተመሳሳይ ጥያቄ ተስተናግዶ ታይቷል፡፡
ልብ በሉ እንግዲህ ይህ ሁሉ ሰላማዊ ሰልፍ የተካሄደው በኦሮሚያ ሲሆን በማን ላይ ተሰለፈ ብለን ስንጠይቅ በኦሮሞ መንግስት ላይ የሚለውን መልስ እናገኛለን፤ ለጥቆም ማነው ሰልፉን የጠራውና ያስተባበረው ብለን ስንጠይቅ መልሱ እራሱ መንግስት የሆነው ገዢው ኦዴፓ እንደሆነ ስናይ የዚህ ቲአትር ዓላማ ምንድነው ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡
ኦዴፓ ለጊዜው የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የሆነ መንግስት ቢሆንም ይህ Status  ግን ልክ እንደ የነፍስ አባቱ ህወሃት አንድ ቀንSooner or later ይህንን ስፍራ እንደሚነጠቅ ያወቀ መስሏል፡፡ እናም ያቺ ቀን ብቻ ሳትሆን ድርጅቱ የሚንቀሳቀስበትን ዓላማ እሚቃወሙ ባላንጣ ኃይሎች በእነሱ ቋንቋ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሳይጠናከሩና አዲስ አበባም የራሱንና በትክክል የሚወክላትን አስተዳደር መርጣ ከመጠናከራ በፊት ዛሬ ጠንካራ ተፎካካሪ በሌለበት ከተማዋም ባልመረጠችውና በማይወክላት አስተዳደር ስር በምትማቅቅበት ወቅት ኦዴፓ ጠቅልዬ በእጄ ላስገባ በሚል ስሌት እየተጣደፈ እንደሆነ ሁሉም አዲስ አበቤያዊና ኢትዮጵያዊ እንዲያውቀው ያስፈልጋል፡፡
**ምን መደረግ አለበት??
ከሁሉ በፊት አዲስ አበቤዎች በአስቸኳይ መደራጀት ይገባናል፡፡ይህንንም ማድረግ የሚገባን ምክንያት በዚህ ሰዓት አንድም የፖለቲካ ድርጅት ስለህልውናችን ብሎ ድምጹን ሲያሰማ ስላልታየና ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ በግል ድርጅታዊ ተራ ጥቅም Compromise አድርገው ያደፈጡ ስለሆነ እኔ ለእኔ በሚል አቋም ከላይ እስከታች እራሳችንን ማደራጀት ይገባናል፡፡
መደራጀት የሚገባንም አጠቃላይ ኢትዮያዊያንን በሚያቅፍና በሚያሳትፍ መልክ እንጂ በነገድ ክፍፍል ላይ ተመርኩዘን መሆን አይገባውም፡፡
የወጣት፣የሴቶች፣የነጋዴው ማህበራሰብ፣የመምህራንና ምሁራን ባለሙያዎች፣የመንግስትና የግል ሰራተኞች በአጠቃላይ የከተማዋ ነዋሪ እራሱን ማደራጀት የመጀመሪያው እርምጃ ማድረግ ይገባዋል፡፡
እራሳችንን ካደራጀን በኃላ ወሳኝ የሆነ አጀንዳ ቀርጸን እና የማስፈጸሚያ የትግል እስትራቴጂ ነድፈን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡
Filed in: Amharic