>

የፖላቲካችን ጠርዝ መርገጥ እና የመሃሉ ፖላቲካ መዳከም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ትልቅ አደጋ ነው!!! (ብርሀነ መስቀል አበበ - ዶ/ር)

የፖላቲካችን ጠርዝ መርገጥ እና የመሃሉ ፖላቲካ መዳከም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ትልቅ አደጋ ነው!!!
ብርሀነ መስቀል አበበ (ዶ/ር)
 
* መጠላላት እና ጥላቻዎችን ከሚወልደው ስሜታዊ ጥፋቶች ራሳችንን  አርቀን እንዲሁም የፖላቲካ ትርክቶቻችንን እና እራሳችንን የዚህ ፖላቲካ ትርክት ተዋናይ አድርገን ብንመለከት፣ እያደረግን ያለው ነገር  አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ያበዱ ሰዎች አገር እንዳያስብለን እጠራጠራለሁ!!
ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ የመን እና ሶሪያ የፈረሱት አዋቂው እና አስተዋዩ ህዝብ ደንዝዞ በመቀመጡ እና በለው ባዩ ፅንፈኛውና ጀብደኛው ክፍል አብዶ አገሮቹ ወደ ለየለት ግጭት እንዲገቡ በማደረጋቸው ነው። በግጭት ጊዜ ደግሞ የሚሰማው በለው ባዩ የጎበዝ አለቃው ቡድን እንጂ ምክንያታዊው እና አዋቂ የሆነው የህብረተሰብ ክፍል አይደለም። ግጭት ከተጀመረ አንዱ ግጭት ሌላ ግጭት እየወለደ ማቆሚያ የለውም።  ስለዚህ ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ የመን እና ሶርያ አስተዋዩ ህዝባቸው ዳንዝዞ ቁጭ ባለበት አገር በጥቂት እብዶች እጅ ስለወደቀች ፈረሱ።
ኢትዮጵያም ውስጥ በሶማልያ፣ በሊቢያ፣ በየመን እና በሶርያ የታየው የአብዛኛው ህዝብ መደንዘዝ እና የጥቂቶች ማበድ አዝማሚያና ምልክቶች ይታያሉ። ዱሮ የወጣቱን አስተሳሰብ አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ይገሩታል። አሁን ዲጅታል ዲቫይድ (digital divide)  ተፈጥሯል። ወጣቱ የሚውለው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ነው። አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስለማይውሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች አስተሳሰብ እና እይታ በሚገበ በእውቀት እና በጥበብ የመግራት ቦታቸውን አጥተዋል። ይህም በመሆኑ  ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በተፈጠሩ ግዴለሽ የጦር አበጋዞች(social media warlords) ተጠልፏል። የጦር አበጋዞቹ ደግሞ ወጣቱን ስድብ እና ውሸት እያስተማሩ  የእነርሱ ጋሻ ጃግሬ እንዲሆን ለማድረግ እየጣሩ ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ ወጣቱን እነርሱ ቹ የሚሉት የራሳቸው የግል ዘበኛና  ውሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ባህል እያጠፉ፣ወጣቱን መረን እያወጡ ነው። የህዝብ ግጭትም የሚቀሰቅሱ አሉ። የሚያሳዝነው በስማ ፖላቲካ ድርጅት ተደራጅተው ውሸት እና  ስድብን እንደ ዋነኛ የፖላቲካ መሪህ በመቅረፅ ወጣቱን እና ካድሬዎቻቸውን   ለውሸት እና ለስድብ ብቻ የሚያሰማሩ የፖላቲ ድርጅቶችም አሉ።
እነዚህ ሁኔታዎች ህዝቡን መረን ሳያወጡ እና አገር ሳያፈርሱ ፖላቲካችን በእውነት እና በእውቀት ላይ የተመሰረተ እና የህዝባችንን ባህል እና ወግ የጠበቀ እንዲሆን መንግስት እና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ መስራት አለበት። ግልፅ እና አገር ገንቢ ውይይቶች በየሚዲያው እንዲቀርቡ መደረግ አለበት። ፖላቲካውም ሰይወሳሰብ እና በሰው ስሜት ላይ ቁማር መጫወትን አላማ ሳያደርግ  አቅለን እና ጥሬውን እንደወረደ  በጤናማ አእምሮ መቅረብ መቻል አለበት።  ለምሳሌ፣
1ኛ) የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት በኢትዮጵያዎያን መካከል የቋንቋ፣ የባህል እና የታሪክ መቀባበልን እና መከባበርን አምጥቶ፣ ኢትዮጵያን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የእኩል አገር ማድረግ እንጂ ህዝቡን በቋንቋ እና በመልከኣ ምድር ከፋፍለን  ማቀማማት፣ ማባላት እና ማጣላት አይደለም። ሁሉም ሰው ከስሜታዊ እብደት ተመልሶ፣ ራሱን፣ ንግግሩ እና ዲርጊቱን ከዚህ እውነታ አንፃር ቢመረምር ለራሱም፣ ለአገርም ጤና ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ከኛ የሚጠብቀው  ከፋፋይ ወገንተኛነትን ሳይሆን በሰዎች እኩልነት የሚያምን ሚዛናዊነት እና ለእውነት እና  ለፍትህ የቆመ አሳቢነትን ብቻ ነው።
2ኛ) የፖላቲካችን አላማ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችን የባህል፣የቋንቋ፣ የታርክ ወዘተ መናናቅ እና ጥላቻን አስወግደን በኢትዮጵያዊያን ዜጎች  መካከል እኩልነት፣ ፍትህ እና ርትዕ ማምጣት፣ ለዚህ የሚሆን አስተዳደራዊ ቀመር እና ህግ አውጥቶ ህዝብን በእኩልነት እና በፍትህ ማስተዳደር እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብን በቋንቋ፣ በባህል፣ በታርክ እና በመልካ ምድር ከፋፍሎ አገር መበተን እና አገር ማፍረስ አይደለም። ንግግሮቻችን እና ድርጊቶቻችን የህዝቦችን እኩልነት፣ ፍትህ እና ርትዕ የማያራምዱ እና ህዝቦችን ከፋፍሎ ለማባለት ከሆነ ቆም ብለን አስበን ከክፉ መንገዳችን እንመለስ። በዚያ መንገድ የምንጎዳው ህዝብ እንጂ የምንጠቅመው አንድም የለም።
3ኛ) በኢትዮጵያ ያሉ የፌዴራል ክልል አስተዳደሮችን እንደ ሉዓላዊ አገር እየቆጠርን  የአለም አቀፍ ህግ እና የአለም አቀፍ ግንኙነት መሪሆዎችን ለአገር ውስጥ ፖላቲካ መጠቀም እናቁም። የአለም አቀፍ ህግ እና የአለም አቀፍ ግንኙነት መሪሆዎች የወጡት በሉኣላዊ አገሮችን እና መንግስታት  መካከል የሚኖሩ ግንኙነቶችን ለመዳኘት የወጡ መሪሆዎች ናቸው። የፌዴራል አደረጃጀትን ጨምሮ የአገር ውስጥ ህጎች እና የአስተዳደር መሪሆዎች ደግሞ በአንድ ሉኣላዊ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን  እኩልነት፣ ፍታዊ እና ርዕታዊ አስተዳደር ለማምጣት የሚወጡ መሪሆዎች ናቸው። አሁን በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ ሁኔታ የፌዴራል አደረጃጀቱን ሉኣላዊ አገር በማስመሰል የአለም አቀፍ ህግ እና የውጭ ግንኙነት መርሆዎችን ለአገር ውስጥ ፖላቲካ በመጠቀም አገር የማፍረስ አዝማሚያ ይታያል። ይህ በአስቸኳይ መገታት ብቻ ሳይሆን መሉ ለሙሉ መቆም አለበት። መገናኛ ብዙኋንም ክፍፍል እና ልዩነት መራገብ ትተው በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲሰሩ ከአደራ ጭምር ጥሪ እናቀርባለን።
4ኛ) በኢትዮጵያ የተነሱ የማንነት እና ሌሎች ተጓዳኝ ጥያቄዎች  የሁሉንም የኢትዮጵያ ዜጎችን አንድነት እና እኩልነት በሚያረጋግጡ መልኩ በግልፅ በተደራጀና በተጠና መልኩ ለህዝብ በውይይት ቀርበው አገራዊ የፖሊሲ እና የህግ መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ እንጂ አንድም ነገር በስውር ከተደረገ በህዝቦች መካከል መጠራጠር እና መጠላላትን ይፈጥራል። ያ ደግሞ በህዝቦች መካከል ግጭት ይፈጥራል፣ ኢኮኖሚውን ያወድማል፣ በሂደትም አገር ያፈርሳል። በህወሃት ዘመን እንዳየነው ለኢትዮጵያ ህዝብ የውሸት እና የስርቆት ፖላቲካ አይጠቅምም፣አያስፋልግም። ለማንነቱ የታገለ የትኛውም ብሄር መብቱን በእውነት፣ በክብር፣ እና በፍትህ ሰው ሁሉ አውቆና አክብሮለት  ማስከበር እንጂ በውሸት፣ በስርቆት እና በጉልበት ሌላውን ጎድቶ ወይም ቀምቶ ማግኘት አይሻም።  ለምሳሌ የኦሮሞ ህዝብ የቋንቋ እና ወንጀል የተሞላበት የመሬት ነጠቃ ጉዳይ ሁሉም ነገር በግልፅ ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅረብ እና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የኦሮሞን ህዝብ በደል ይፍረድ። እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የኦሮሞን ህዝብ በደል እና የፍትህ ጥያቄ ሰምቶ፣ የኦሮሞ ህዝብ ላይ ከወሰነ የኦሮሞ ህዝብ ያንን ውሳኔ ያከብራል። ከዚያ ውጭ የኦሮሞ ህዝብ ሰርቀህ እና ዋሽተህ ወይም በጉልበት ሌላውን ኢትዮጵያዊ ወገኑን ቀምተህ እኔን ጥቀም ብሎ የኦሮሞ ህዝብ የላከው ግለሰብም ሆነ ድርጅት የለም። የአማራ፣ የትግሬ፣ የሲዳማ፣ የሱማሌ እና የሌሎችም የኢትዮጵያ ህዝቦች ፍላጎት እና ጥያቄ ከላይ ለኦሮሞ ህዝብ ካልኩት በፍፁም የተለየ አይደለም። ስለዚህ በኢትዮጵያ የውሸት፣ የስርቆት እና የመድሎ ፖላቲካን እንደ ነፈሰ ገዳይ የነቀርሳ ወይም ኤድስ በሽታ ቆጥረን ከአገራችን እና ከህዝባችን መካከል በጋራ እንዋጋው፣እናጥፋው።
5ኛ) በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ያሉትን የመንግስት ሰራተኞችን እና ተሿሚዎችን የኢትዮጵያ ህዝብን ሁሉ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በትውልድ አከባቢ ሳይከፋፍሉ እና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት እና ያለ ምንም መድሎ ህዝብ የሚያገለግሉ የህዝብ አገልጋዮች እንጂ የየብሄራቸው ተወካዮች አድርጎ ማየት እስከ ዛሬ የተገነቡትን የመንግስት ተቋማት ሙሉ በሙሉ ያፈርሳል። በመንግስት ሰራተኞችም ስነ ልቦና ውስጥ በራስ አለመተማመንን እና ገለልተኛ ሆኖ በህግ በተቀመጠ አግባብ ህዝብን እንዳያገለግሉ ያደርጋል።  የኢትዮጵያ ፖላቲከኞች እና አክቲቪስቶች በስሜት እና ማስተዋል በጎደለው ጊዚያዊ ጥቅም ተነድተው በኢትዮጵያ የመንግስት ተቋማት ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አመኔታ እንዲያጣ እና እነዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ተቋማት እንዲፈርሱ ከሚያደርግ ተግባር መታቀብ አለባቸው። ህዝብም ከእንደዚህ አይነት ሰዎች ራሱን መጠበቅ አለበት።
6ኛ) የክልልም ሆኑ የዞን፣ የወረዳ፣ የቀበሌ የአስተዳደር ወሰኖች የቋንቋ እና  የአኗኗር ስብጥሮቻችንን ከግምት በመውሰድ ለአስተዳደር፣ ለግብር ለቀማ፣ እና ፖሊስ አከባባዊ ፀጥታ እንዲያስከብር የተከለሉ የስራ ክፍፍል እንጂ በዜጎች መካከል ልዩነት ለመፍጠር እና ዜጎች ከቦታ በታ ሲሄዱ ባይተዋር እንዲሆኑ እና እንዲገለሉ ለማድረግ አይደለም። ከአስተዳደራዊ የስራ ክፍፍል ውጭ እና ቋንቋን እና ባህልን በተመለከተ በኢትዮጵያዊያን መካከል መከባበርን ለማምጣ እንጁ  መላው ኢትዮጵያ የሚተዳደረው በአንድ ህግ እና በአንድ መንግስት ነው። ይህ የአስተዳደር ክልሎችን የባዕድ አገር አድርጎ እና ነገ ለመበታተን የተዘጋጀን ይመስል ዜጎች መሬት እንዲቀራመቱ፣ ቢሮ ውስጥ በጎሪጥ እንዲተያዩ፣ እርስ በርሳቸው እንዲፈራሩ፣ አንዱ በአንዱ ላይ በቃል እና በአካል እንዲዘምት የሚደረግ የጥላቻ እና የመከፋፈል ፖላቲካ ሳያባላን እና ሳያጠፋን በአስቸኳይ መቆም አለበት።
7ኛ) በኢትዮጵያ ፍትሃዊ የስልጣን እና የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከኢትዮጵያ የፖላቲካ መሪዎች የሚጠብቀው ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት፣ በፍትህ እና በርትዕ እንድያስተዳድሩ ነው። ህዝቡ በአንድ መሪ ትግሬነት፣ አማራነት፣ ኦሮሞነት፣ ሲዳማነት፣ ሶማሌነት እና ወዘተ ከፋፍሎ ማየት አይፈልግም። ኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊ መሆኗን ያውቃል። ይህ ህዝብ አንድ መሪ ከራሱ ብሄር ካልሆነ በጥርጣሬ እና መድሎ ፈፃሚ አድርጎ እንዲያይ የሚያደርገው መርዘኛ የስልጣን ፈላጊዎች ፖላቲካ መቆም አለበት። ህዝቡ ይህ አካሄድ እንደማይጠቅም አውቆ እንደዚህ አይነት ሰዎችን በልካቸው መያዝ አለበት።
8ኛ) ኢትዮጵያ ራስን በራስ የማስተዳደር እና ቋንቋን በተመለከተ የሚነሱ የማንነት ፖላቲካ ጥያቄዎችን በግልፅ ፖሊሲ፣ህግ እና ተቋማት እኩልነት እና መከባበርን፣ መቀባበልን ልያመጣ በሚችል መልኩ ፈታ ከማንነት ፖላቲካ ሙሉ ለሙሉ ወጥታ ወደ ሃሳብ እና እውቀት ፖላቲካ  መሸጋገር  አለባት። የማንነት ፖላቲካ በዜጎች መካከል መድሎን አስወግዶ እኩልነትን ለማምጣት እንጂ ሌላ ግብ የለውም። ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግሬነት፣ ወዘተ በራሱ ፖላቲካ አይደለም። ማንነት ነው። የሚፈልገው መድሎን አስወግዶ፣ እኩልነት እና መከባበርን ማስፈን ብቻ ነው። አንድ ኦሮሞ አንድ ኦሮሞ ያልሆነን ኢትዮጵያዊ በእኩል አይን እርሱን ተቀብሎ ያገለግለኛል ብሎ ማሰብ ትቶ መድሎ ይፈፅምብኛል ብሎ እንዲያስብ ከደረግን አገር እያፈረስን ነው። ለሌሎች ብሄር ተወላጆችም እንደዚሁ። ስለዚህ ምርጫ፣ ቤት እና ህዝብ ቆጠራ ወዘተ የሚሉትን አጃንዳዎችን ለጊዜው አስቀምጠን የማንነት ፖላቲካው የእኩልነት መልስ አግኝቶ ወደ ሃሳብ እና እውቀት ፖላቲካ ለመግባት ሁላችንም በጋራ እንስራ።
9ኛ) የኢትዮጵያ ህዝብ ችግሮች እዘው ተወልዶ፣ እዚያው ኖሮ፣ እዚያው በሚሞተው ከ80% በላይ ከሚሆነው የኢትዮጵያ የገጠር ነዋሪ ህዝብ አይመነጭም። የኢትዮጵያ ህዝብ ችግሮች ጉልበቱን እና እውቀቱን ሽጦ ከሚኖረው 15%  አከባቢ ከሚሆነው የከተማ ሰርቶ አደር እና ደሃ ህዝብም አይመነጭም። የኢትዮጵያ ችግሮች የሚመነጩት 5% አከባቢ ከሚሆነው ከህዝብ ግብር እና መሬት እየቀማ፣ ወይም በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ከፈረንጆች እርዳታና ብድር እየለመነ  መኖር ከለመደው በፖላቲካ ድርጅቶች፣ በሃይማኖት ድርጅቶች፣ በመንግስት ተቋማት፣ በሚዲያ ተቋማት በምላሳቸው ወሬ እየቆሉ ከሚውሉት እና በግል የንግድ ተቋማት ስም ህዝብ እየበዘበዙ ለግል ጥቅማቸው የሚሮጡ ጥቂት መዥገሮች እና ሌቦች የሚፈጥሩት እና የሚወልዱት ችግሮች ናቸው። እነዚህ  እጅግ በጣም ጥቂት መዥገሮች እና ሌቦች አዛኝ፣ ቅቤ አንጓች መስለው ለግል ጥቅማቸው ህዝብን ከህዝብ እንዳያባሉ ህዝብ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። መንግስትም ህግ የማስከበር ግዴታውን በሚገባ በመጠቀም በፖላቲካ ድርጅቶች፣ በመንግስት ተቋማት፣ በሃይማኖት ድርጅቶች፣ በሚዲያ ተቋማት እና በግል የንግድ ድርጅቶች ውስጥ ተሰግስገው ህዝብ የሚያባሉትን ለመቆጣጠር በግልፅ ህዝባዊ ውይይት ተደርጎበት፣ ባለሙያዎች በግልፅ ህዝብ ፍት መክረውበት ትክክለኛ ህጎች እና የስነ ምግባር ደንቦች በየዘርፉ ወጥቶ ተቋማዊ ቁጥጥር ልደረግባቸው ይገባል። ይህ የዴሞክራሲ ግንባታው አንደኛው ምሰሶ ተደርጎ  መወሰድ አለበት።
10ኛ) የአሁኑ ለውጥ  የጭቆና ስረዓትን ማፍረስ ብቻ ሳይሆን ህዝባዊና ጠንካራ መንግስት የመቋቋምን ግብ ያደረገ ነው። ኢትዮጵያ በማንነት ፖላቲካ ተወጣጥራ ባለችበት በአሁኑ ወቅት የዚህ ለውጥ ከግብ መድረስ ለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልሁና(የመኖር እና ያለመኖር) ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትር አብይን የለውጥ መንግስት መደገፍ እና ማገዝ ከዚህ የኢትዮጵያ ህልሁና ጋር የተያያዘ እና ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ አገራዊ ግዴታ ነው። በለውጥ ሂደቱ የተጀመሩት በጎ ጅምሮችም ተጠናክሮ እንዲቀጥሉ ማድረግ እና አንዳንድ የሚታዩ መንገራገጮች በአስቸኳይ መስተካከል አለባቸው። ለዚህም የለውጥ መንግስቱ፣ 1ኛ) የለውጥ ኃይሎች አሰባስቦ ለውጡን ማስቀጠል እና ለውጡ በፅንፈኛ ኃይሎች እንደይነጠቅ ወይም እንዳይደናቀፍ ማድረግ፣ 2ኛ) የመንግስት ዋነኛ ተግባር የሆነውን ህግ የማስከበር ኃላፊነት በሚገባና በቆራጥነት መወጣት። ህግን በማስከበር ስረዓተ አልበኝነትን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር፣  3ኛ) እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ተቋማዊ ለማድረግ አሁን ውዥንብር ከፈጠረው የምርጫ ፖላቲካ ሂደቱን ወደ ሁሉ አቀፍ  አገር ግንባታ ፖላቲካ ማሸጋገር። ጠንካራ መንግስት እና ተቋም ባሌለበት ምርጫ ማከሄድ ትርፉ ብጥብጥ ብቻ መሆኑን ግንዛቤ በመውሰድ፣ ከምርጫ በፊት አገር ግንባታ እንዲቀድም ማድረግ። 4ኛ) አሁን ባለው ሁኔታ የለውጡ በውስጥ እና በውጭ በተፈጠሩ ምክንያቶች መንገራገጭ እና የተቋማት መዳከም አንፃር ሳጤነው  የለውጡ የአጭር ጊዜ ግብ  managed liberalization እንጂ ሙሉ democratization መሆን አይችልም። ከዚህ አንፃር የመንግስት priorities ተሻሽሎ አገራዊ የህግ መስከበር እና የተቋማት ግንባታ ሁሉንም የለውጥ ኃይሎች ባካተተ መልኩ ቅድሚያ ተሰጥቶት  ልሰራ  ይገባል። ከላይ እዳልኩት ጠንካራ መንግስት እና ተቋማት ባልተገነቡበት ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ብጥብጥ እና ስረዓተ አልበኝነትን በአገር ውስጥ ማንገስ ነው። ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ይህን አይፈልግም!
Filed in: Amharic