>

ይህን ዩኒቨርስቲና እነዚህን መምህራን ይዘን ነው ሀገራችንን የምናሳድገው! (ይሄይስ አእምሮ)

ይህን ዩኒቨርስቲና እነዚህን መምህራን ይዘን ነው ሀገራችንን የምናሳድገው!

ይሄይስ አእምሮ

ፖለቲካው እየተበለሻሸብን በሚሄድበት በአሁኑ ወቅት ወደ መንግሥት እያንጋጠጥን “ፍትህ፣ ፍትህ፣ የፍትህ ያለህ!” እንላለን – በየቀኑ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በሌሎች ብዙ የግልና የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚሠራው ወንጀልና በተማሪዎች በተለይም በሴት ተማሪዎች የሚፈጸመው በደል ግን እጅግ የሚዘገንን እየሆነ ቀጥሏል፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዱሮውንም የቅሌትና የዘረኝነት ልክፍት የተጣባቸው ቡችሎችን ማምረቻ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ አንድ የትምህርት አምባ የዕውቀትና የጥበብ መፍለቂያ፣ የፍትህና የርትዕ ቁንጮ መሆን ሲገባው በተገላቢጦሹ በመምህርነትና በአስተዳደር ሠራተኝነት በሚቀጠሩ ውርጋጦችና ኅሊናቢሶች ቅጥረ ግቢዎችን የዋልጌዎችና የወስላቶች መፈንጫና መጫወቻ ሲሆኑ ማየት በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ በነዚያ ቅዱሳን ሊሆኑ በሚገባቸው ቦታዎች የጀመረ ብልግናና ውስልትና ቤተ መንግሥት ቢያቆም አይፈረድበትም፡፡ በአሁኑ ወቅት ቤተ አምልኮዎችና ቤተ መንግሥት የስዶችና የባለጌዎች መንቦራቦሪያ መሆኑ የሚያመለክተን አንድ ብቸኛ ሃቅ የትምህርት ሥፍራዎች ክፉኛ መበላሸታቸውንና ትውልድ እየዘቀጠ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ትውልድ ፍትህንና ርትዕን መጠበቅ ከንቱ ነው፡፡ “እንትና የተባለው መምህር እገሊት የምትባለችዋን ተማሪ በግሬድ አስፈራርቶ ለፆታዊ ግንኙነት ጠየቃት”፣ ሲባል “So what?` የሚሉ ዲኖችና የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች ካሉ – እንዳሉም ይታመናል – የሚኖሩት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ግማት ክርፋታችን በትምህርት ተቋማትም ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ሙስናውና ምዝበራው በነዚህ ተቋማት ይቀንሳል ሲባል የባሰ ሆኗል፡፡ ግማሽ ሚሊዮን የማትፈጅ ትንሽዬ ድልድይ በስምንት ሚሊዮን ብር እንደተወራረደች አንድ ወቅት አንድን የመንግሥት ዩኒቨርስቲ ጠቅሼ መጻፌ ትዝ ይለኛል፡፡ ከጠፉ አይቀር እንደዚህ ነው – የተሟላ ጥፋት! አቤት ኢትዮጵያ! መጨረሻሽ ምን ይሆን?

የልጄ ጓደኛ በሚማርበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሰሞኑን ስለ ተፈጸመ የፆታ ትንኮሳ ልንገራችሁ፡፡ መምህሩ አንዷን ተማሪውን “ከ ‹B› ወይም ከ‹D› ምረጭ” ይላታል፡፡ ይህ አማራጭ በግልጽ ቋንቋ ሲቀመጥ “… ከሰጠሸኝ ‹B› ካልሰጠሸኝ ‹D› አስታቅፍሻለሁ›” ማለቱ ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን መምህር ህግ የለም እንጂ ህግ ኖሮ፣ ዳኛ የለም እንጂ ዳኛም ኖሮ የሠራው ወንጀል በህጉ መሠረት ተረጋግጦ በፍርድ ቤት ብያኔ በገመድ ቢንጠለጠል አንድም አዘኔታ የለኝም፡፡ በላይ ዘለቀ እንኳን ካለ ኃጢኣቱ ተሰቅሎ ሞቷል፡፡ ይሄን ዓይነቱን ትምህርትንና ትውልድን ገዳይማ ማንጠልጠል ነው እንጂ! ለማንኛውም ያ መምህር ለልጂቷ “ኤፍ” ሰጣትና በኮርሱ ጣላት፤ እርሱ ወደቀ – እርሷ ግን አለፈች – ኮርሱን ሳይሆን የሕይወትን ዲያብሎሳዊ ፈተና፡፡በዚህ መልክ ብዙ ሴቶች የአልጋ ፈተናውን እየወደቁ ኮርሱን ያልፋሉ ወይም ኮርሱን እያለፉ የአልጋ ፈተናውን ባለማለፋቸው ምክንያት ኤፍ አምጥተው ኮርሱን ይወድቃሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ክስና ወቀሳ የለም፡፡ ማን ለማን ይከሰሳል? ሁሉም ጠፍቷላ! ሁሉም ምናልባትም አብዛኛው በፍትወት ቁስል የነፈረ በመሆኑ በ“ለኔ ባረገው” ቁጭት ውስጥ ውስጡን ከመብሰልሰል ባለፈ የሴት ተማሪን አቤቱታ ተቀብሎ ፍትህን የሚሰጥ ባለሥልጣን እምብዛም የለም፡፡ የጠፋ ማኅበረሰብ አንዱ መገለጫ ደግሞ ይሄው ነው፡፡

እግዚአብሔር ይህችን ሀገር በምሕረት ዐይኑ ይጎብኛት፡፡ ተገቢ ፍርዱንም ይስጥ፡፡ በሁሉም ረገድ ጠፍተናልና አሁንም ልድገመው ፍርዱን በቶሎ ይስጠን፡፡ የሚሰማውና የሚታየው ሁሉ የሚሰቀጥጥ ነው፡፡ ማንኛችንም ማናችንንም በክፉ ሥራ ለምሣሌ በጎጠኝነት ወይ በሙስና ለመውቀስ የማንችልበት አሳዛኝ የሞራልና የመንፈስ ድቀት ላይ እንገኛለን፡፡ ከሳሹም ተከሳሹም ዳኛውም የተሣፈርንበት ጀልባ የኖኅ ሳትሆን የሶዶምና ገሞራ የእሳት ዝናብ ናት፡፡ ፍርድ ከፊታችን አለ፡፡ እቶን ከፊታችን አለ፡፡ ገደል እፊታችን አለ፡፡ ማንናችን እንሆን ከዚህ እሳት የምንወጣው? ትልቅ ሰው ጠፋ፤ ሽማግሌ ጠፋ፤ ቅሌታሙና ወራዳው እየገነነ መጣ፡፡ ዕድሜም የእንጨት ሽበት ሆነ፡፡
በየትምህርት ተቋማቱ የሚደረገውን የመምህራንን ብልግና ስትሰሙ ያሳብዳችኋል፡፡ ሕግ ብሎ ነገር ደግሞ የለም፡፡ ከሞላ ጎደል በአንድ ወይ በሌላ ረገድ አብዛኛው መምህርና የአስተዳደር ሠራተኛ ሙስና ውስጥ ስለሚዘፈቅ ተማሪዎች ቢከሱ እንኳን የሕግ ድጋፍ አይደረግላቸውም፡፡ ግም ለግም እንዲሉ ዋልጌዎቹ እርስ በርስ እየተደጋገፉ ተማሪዎችን መና ማስቀረት ባህል እየሆነ ነው፡፡ ኡፍፍፍፍ… የት እንግባ?!

Filed in: Amharic