>

በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለነዋሪዎች መተላለፋቸው ተገቢ_አይደለም!" የኦ.ብ.ክ.መንግስት መግለጫ

በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለነዋሪዎች መተላለፋቸው ተገቢ_አይደለም!”
የኦ.ብ.ክ.መንግስት መግለጫ
ፋና ብሮድካስቲንግ
* በአዲስ አበባ ጉዳይም ከወሰንና ቤቶች ጉዳይ በዘለለ የከተማዋን የኦሮሞ ባለቤትነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን!!!
በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳደር የወሰን ጉዳይ እልባት ሳይሰጠው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ ለባለ አድለኞች መተላለፋቸው ተገቢ አለመሆኑን የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልልዊ መንግስት ገለፀ።
የክልሉ መንግስት ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ባወጣው መግለጫ የኦሮሚያ ክልል ጥያቄ እያነሳባቸው ባሉና የክልሉን ወሰን አልፈው የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ ለተጠቃሚዎች የማስተላለፍ ሂደት እንዳይተገበርም አቋም መያዙን ነው የገለፀው።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በሁሉም አቅጣጫ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ደረጃ በደረጃ እየሰራ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫው አንስቷል።
በዚህም ትላልቅ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ነው መግለጫው የጠቆመው።
የአዲስ አበባ ጉዳይም ይሁን ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች በሙሉ በቅደም ተከተላቸው መልስ እንዲያገኙ በተሃድሶ ከስምምነት ላይ የተደረሰበት መሆኑን በማንሳትም ይህም እየተሰራበት መሆኑን ነው ገልጿል።
በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳደር የወሰን ጉዳይ ጉዳይ አልባት እስከሚያገኝ የኦሮሚያ ክልልን ጥያቄ እያነሳባቸው ያሉ የክልሉን ወሰን አልፈው የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለተጠቃሚዎች በእጣ ማስተላለፍ ትክክል እንዳልሆነ የክልሉ መንግስት ያምናልም ነው ያለው።
በመሆኑም ይህ ውሳኔ ስራ ላይ እንዳይውል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጠንካራ አቋም መያዙን በመግለፅ፥ ይህ አቋም በቀዳሚነት የህዝቡን ተጠቃሚነት በማስጠበቅ የመነጨ እንጂ የሀገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦች አብሮ የመኖር እሴት ከመጥላት የመነጨ አለመሆኑ ከግንዛቤ ሊገባ ይገባልም ብሏል።
የክልሉ መንግስት ከአዲስ አበባ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ማንኛውንም አጀንዳዎችን እና ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ እንደሚመለከተውም ነው በመግለጫው ያስታወቀው።
በአዲስ አበባን እና በዙሪያዋ ተያይዘው የሚከናወኑ ስራዎች ከክልሉ መንግስትና ህዝብ እውቅና ውጪ ለመስራት መታቀዳቸው ህጋዊ ነው ብሎ እንደማያምንም አስታውቋል።
“ትናንት ከህዝብ ጋር የታገልነው የህዝቡን ችግሮች ለመቅረፍ እና ህዝቡን ወደ ተሻለ ብልፅግና ለማሸጋገር ነው ያለው መግለጫው፥ ዛሬም ቢሆን ትናንት ለህዝቡ ቃል የገባናቸውን ድሎች እያስመዘገብን መተናል፤ ይህንንም በማስቀጠል ማንኛውንም የህዝብ ጥያቄ በትግል ለማስመለስ አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን” ብሏል የክልሉ መንግስት።
የኦሮሞ እና የኦሮሚያ መብትና ጥቅምን በማስከበር ወደተሻለ ብልፅግና ለማሸጋገር እንሰራለን በማልትም ለዚህም በህጋዊ መንገድ እንሰራለንም ነው ያለው።
በአዲስ አበባ ጉዳይም ከወሰንና ቤቶች ጉዳይ በዘለለ የከተማዋን የኦሮሞ ባለቤትነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ብሏል የክልሉ መንግስት በመግለጫው።
Filed in: Amharic