>

የሚታየው የሚሰማው ሁሉ ደስ-አይልም!!! (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

የሚታየው የሚሰማው ሁሉ ደስ_አይልም!!!
ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን
ደስ አይልም!
በኮንዶሚኒየም ጉዳይ የተጀመረው ውዝግብ ደስ አይልም፡፡ ውዝግቡ እየጦዘ የሚሄድበት ሁኔታ ደስ አይልም፡፡ በአጉል ብሄርተኝነት የነበዙ አክቲቪስት ተብዬዎች የሚያሰሙት ዲስኩር ደስ አይልም፡፡ መብትን መጠየቅና ማስከበር አግባብ ቢሆንም መብትን በማስከበር ስም የሚሰነዘሩት ዛቻዎች ደስ አይሉም፡፡ “ፊንፊኔ ኬኛ” እና “በረራ የኛ” ባዮች ወዲያና ወዲህ ቆመው የሚደልቁት የነገር አታሞ ደስ አይልም፡፡ የምንሰማቸው “ሊበላህ ነው”፣ “ልትበላ ነው”፣ “ልንበላ ነው” ወዘተ ዓይነት ትርክቶች ደስ አይሉም፡፡
.
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የአማራ እና የትግራይ ክልል በሚያወጡት መግለጫ የሚቆራቆሱት ነገር ደስ አይልም፡፡ ሁለቱም ክልሎች በህዝብ ስም እየማሉ ጣት የሚቀሳሰሩት ነገር ደስ አይልም፡፡ እነዚህን እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች “አንድ በሬ ብቻ ያላቸውን የቂሎቹን ባልና ሚስት” ታሪክ ነው አስታውስ ዘንድ ግድ አለኝ፡፡
.
ታሪኩ እንዲህ ነው፦
ቂሎቹ ባል እና ሚስት አንድ በሬ ብቻ ነበራቸው፡፡ ያቺኑ በሬ አርደው ለመብላት ተስማሙ፡፡ … በሬውን ከገፈፉና ሥጋውን ጎጆአቸው ካስገቡ በኋላ ቀቅለው፣ የቀቀሉትን በመግላሊት ከድነው ወጡ፦ ለጥርስ መጎርጎሪያ ስንደዶ እናምጣ ብለው ነው ቤታቸውን ዘግተው የወጡት፡፡
.
መንገድ ላይ ….
ብዙ ወታደሮች በአጠገባቸው ተፍ ተፍ እያሉ ሲያልፉ አዩና እንዲህ አሏቸው፦
“…በመንገዳችሁ ስታልፉ የተዘጋ ጎጆ ታገኛላችሁ፤ በሬ አርደን፣ ሥጋውን ቀቅለን … ነውና የወጣነው እንዳትነኩብን”
.
ወታደሮቹ እንኳንስ ተነግሮአቸው፣ እንዲያውም እንዲያው ናቸውና የተዘጋውን ጎጆ ከፍተው ገቡ፡፡ የሚበሉትን ያህል በልተው፣ የሚችሉትን ያህል ቋጥረው ወጡ፡፡
.
እነሱ እንደወጡ ቂሎቹ ባልና ሚስቶች መጡ፡፡ የቤታቸውን በር ከፍተው ሲገቡ መግላሊቱ ተንከርፍፎ፣ የዝናብ መዓት በዋዲያቱም በአፍላሉም …ወዘተ ላይ ሰፍሮበት አዩ፡፡ … እናም የተንከረፈፈውን መግላሊት ብድግ አደረጉት፡፡ ጋኑ ውስጥ አጥንት እንጂ ሥጋ የሚባል አጡ፡፡ ይኼኔ “የቀቀልነውን ሥጋ የበላብን ዝንብ ነው” አሉ፦ አሉ፡፡
.
ከዚያስ?
.
ከዚያማ ….. የዝንቡን መዓት ለመግደል መሯሯጥ ያዙ፡፡ የዝንቡን መንጋ ለመግደል እያንዳንዱን የቤታቸውን ዕቃ ሁሉ፣ አነካክተው፣ ሰባብረው ጨረሱ፡፡
.
በመጨረሻ፦
.
.
በመጨረሻ …. አንዲት ዝንብ ሚስቱ አፍንጫ ላይ አረፈች፡፡ እናም…አፏን አሞጥሙጣ አፍንጫዋ ላይ ያረፈችውን ዝንብ ለባሏ በምልክት ጠቆመችው፡፡ ባሏ “ቆይ ባክሽ፤ እኔ እንዳንቺ አላዋዛትም” አለና የሙቀጫ ግልገል አነሣ፡፡
አነሳና ሰርኗን አደቀቀው ሞተችም፦ ይላል ተረቱ፡፡
.
.
አሁን በሀገራችን የምናየው ሁኔታም እንደዚያው ያለ የቂልነት ላይ የደረሰ ይመስለኛል። ሀገርን እንደ ቂሎቹ ድስት የሚሰባብር ይመስለኛል፡፡ የጋራ ቤታችንን በዝንብ ማስወረር ይመስለኛል፡፡ ከዚያም እንደቂሎቹ ባልና ሚስቶች ዝንቡን ለማጥፋት አፍንጫ ለአፍንጫ መሳበር የሚያስከትል ይመስለኛል፡፡
.
እናም…ከዚህ መስል የቂልነት ተግባር ለመታቀብ ቆም ብለን ማሰብ ያለብን ይመስለኛል፡፡
ሰከን ማለት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ሰከን!!
Filed in: Amharic