>
5:13 pm - Sunday April 18, 9649

የዚህን ሕዝብ ትዕግሥት አትፈታተኑት!!!    (ዳንኤል ክብረት)

የዚህን ሕዝብ ትዕግሥት አትፈታተኑት!!!
  ዳንኤል ክብረት
 
 
 . የክረምት ገበሬ የበጋ ወታደር ሆኖ ለኖረ ሕዝብ ሰላም እንጂ ጦርነት ብርቁ አይደለም!
 
• እንዳይበላ ከከለከልነው ጭሮ ለማፍሰስ የሚያንስ ማንም የለም!!
 
• ወይ ለሁላችንም የምትሆን ሀገር ትኖረናለች ወይም ለማናችንም የማትሆን ሀገር ትኖረናለች!!
 
• የላይ ፈሪ የታች ፈሪ እያላችሁ የዚህን ሕዝብ ትዕግሥት አትፈታተኑት፡፡
 
•••
ማንኛውም ያልተስተካከለ ውሳኔና ተግባር የተስተካከለ ውሳኔና ተግባርን ያስከትላል፡፡ ለእያንዳንዱ ተግባር ተመጣጣኝና ተቃራኒ የሆነ ግብረ መልስ አለውና፡፡ ያልተገባ ውሳኔና ተግባር በፈጸምን ቁጥር የተገባ ውሳኔና ተግባር የያዘ ኃይል በተቃራኒያችን እንዲመጣ መንገድ እናመቻችለታለን፡፡ ይህንን ኃይል ማሸነፍ ግን አይቻልም፡፡ ትክክለኛ ምክንያት ከሌለው ትልቅ ኃይል ይልቅ፣ ትክክለኛ ምክንያት ያለው ትንሽ ኃይል የማሸነፍ ዐቅም አለውና፡፡ ማሸነፍ ከብረትና ከጉልበት ይልቅ ከምክንያትና ከዓላማ ትክክለኛነት ይመነጫል፡፡ በሥልጣኑ ወንበር ላይ ሆነው በስሜት እየተነዱ፣ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ብለው፣ እንደ ጓያ ነቃይ የፊት የፊቱን ብቻ እያዩ፣ የምርቃና መግለጫ የሚያወጡ አካላት ምላሹንም አብረው ሊያስቡበት ይገባል፡፡
•••
ለኢትዮጵያውያን ጦርነት ማለት ሲፈጠሩ ጀምሮ አብሯቸው የኖረ የታሪካቸው አካል ነው፡፡ እዚህች ሀገር ውስጥ ለጦርነት የሚያንስ ማንም ወገን የለም፡፡ እንኳንና ሰው፣ እንስሳውና ተራራው ለጦርነት ሲሰለፍ የኖረባት ሀገር ናት፡፡ ጉልበታችንን አፍስሰን፣ ጊዜያችንን ሠውተንና ዕውቀታችንን አዋጥተን ልንከውነው የሚገባን ተግባር ሰላም ነው፡፡
•••
የክረምት ገበሬ፣ የበጋ ወታደር ሆኖ ለኖረ ሕዝብ ሰላም እንጂ ጦርነት ብርቁ አይደለም፡፡ ‹እንደምን አደርክ፣ እንደምን ዋልክ፣ እንደምን ሰነበትክ› የሚለው ሰላምታ የሚነግረን ነገር ማኅበራዊ ደኅንነትን ማረጋገጥ የሕዝባችን ሁሉ ቀዳሚ ፍላጎቱ መሆኑን ነው፡፡ በጦርነት ሲናጋ ነዋ የኖረው፡፡ አብረን መኖር፣ አብረን መሥራትና አብረን መነጋገር ያለብን ስለ ሰላም እንጂ ለጦርነትማ ወሳኙ ነገር መለያየት ነው፡፡
•••
ለሁሉም የወጣችውን ጨረቃ ‹የእኔ ናት የእኔ ናት፣ እኔ ነኝ መጀመሪያ ያየኋት› ብለው እንደሚጣሉ ሕጻናት ያሉ የፖለቲካ ልሂቃንን ከማየት በላይ አሳዛኝ ነገር የለም፡፡ ልጆች እንደ ዐዋቂዎች ሲሆኑ ያስደንቃሉ፤ ዐዋቂዎች እንደ ልጆች ሲሆኑ ግን ያሳቅቃሉ፡፡ አሁን ባለቺው ኢትዮጵያ የአንድን ወገን ጥቅም፣ ክብርና ልዕልና ለብቻ ለይቶ ለማስከበር በሚቻልበት ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡
•••
እንዳይበላ ከከለከልነው ጭሮ ለማፍሰስ የሚያንስ ማንም የለም፡፡ ወይ ለሁላችንም የምትሆን ሀገር ትኖረናለች ወይም ለማናችንም የማትሆን ሀገር ትኖረናለች፡፡ አብረን መኖሩ የሚያዋጣን – አብረን አለመኖር የበለጠ ጣጣና ፈንጣጣ ስላለው ነው፡፡
•••
አብረን በመኖራችን ምክንያት የማይነሡ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ መለያየት የጥያቄ መዓት ይወልዳል፡፡ አሁን አብረን ሆነን ከምናነሣቸው ጥያቄዎች በላይ ብንለያይ እናነሣለን፡፡ መለያየት – ጥርጣሬ፣ ጥርጣሬ ደግሞ የጥያቄና የይገባኛል መዓት ይወልዳሉ፡፡ ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ትተዋቸው፣ ታግሠዋቸውና ከቁብ ሳይቆጥሯቸው የኖሩትን ጥያቄዎችና ይገባኛሎች ሲጣሉና ሲለያዩ ያነሷቸዋል፡፡ በፍርድ ቤቶች የሚደረጉ የባልና የሚስት ክርክሮችን የሚያይ ሰው ‹እንዲህ ሆነው እንዴት ይሄንን ሁሉ ዘመን አብረው ኖሩ?› ማለቱ አይቀርም፡፡ ምክንያቱ ግን ግልጽ ነው፡፡ አብሮ መኖር መተማመንን ስለሚፈጥር. መተማመን ደግሞ ብዙ ጥያቄዎችን ውጦ የመያዝ ዐቅም ስላለው ነው፡፡
•••
ኢትዮጵያና ኤርትራ ተለያዩ፣ መለያየታቸው ከመለሳቸው ጥያቄዎች ይልቅ የፈጠራቸው ጥያቄዎች ይበዛሉ፡፡ እነዚያ ጥያቄዎች ናቸው ወደ ጦርነት የከተቱን፣ ለብዙ ዘመናትም በጠላትነት ድንበር ዘግተንና ተፋጠን እንድንኖር ያደረጉን፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማንኛውም መሪ አምስት ዕድሎች ይሰጣል፡፡
፩ኛ፦ ማመን –
፪ኛ፦ የማርያም መንገድ –
፫ኛ፦ ጥርጣሬ –
፬ኛ፦ ጥላቻ –
፭ኛ፦ ትግል፡፡
•••
ማንኛውንም መሪ መጀመሪያ ያምነዋል፤ ይከተለዋል፤ ይተባበረዋል፡፡ ይሞትለታል፡፡ ያ መሪ ቃሉን ጠብቆ ከሄደ ያንኑ እያሳደገ  ሞቶ እንኳን እንዲመራው ይፈቅድለታል፡፡ መሪው ቃሉን ካልጠበቀ የማርያም መንገድ ይሰጠዋል፡፡ ከችግሩ ራሱንም ሕዝቡንም የሚያወጣበት መንገድ እንዲፈልግ መንገድ ከፍቶ ይሰጠዋል፡፡ ያ ካልሆነ ይጠራጠረዋል፤ በአንድ ዓይኑ፣ በአንድ ጆሮው፣ በግማሽ ልቡ፣ ይከታተለዋል፡፡ እያንዳንዱን ነገር ያበጥረዋል፡፡ ከዚህ ካለፈ ጠላቴ ነው ብሎ ይፈርጀዋል፡፡ በመጨረሻም  ይታገለዋል፡፡
•••
ሕዝብ ሞኝ አይደለም፡፡ ዝም አለ ማለት ተሸነፈ አይደለም፤ ጸጥ አለ ማለትም ታክቶት አይደለም፡፡ አምስቱን ምእራፎች እስኪያልፍ እያገዘ፣ እየጸለየና እየመከረ ስለሚጠብቅ ነው፡፡ የዘገየ – ቢበዛ አራተኛው ላይ ይነቃል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትዕግሥት ወደ ጎን ሲሄድ፣ የባለ ሥልጣናትም ስሕተት ወደ ላይ እየጨመረ ሲመጣ፣ ሁለቱ የተገናኙ ዕለት – በዚህች ሀገር ምንጊዜም አብዮት ይነሣል፡፡ የላይ ፈሪ የታች ፈሪ እያላችሁ የዚህን ሕዝብ ትዕግሥት አትፈታተኑት፡፡ የታገሠ ሕዝብ ሲነሣ የሚያሳየውን ጠባይ ማንም ቀድሞ ገምቶ አይደርስበትም፡፡
Filed in: Amharic