>

ሎሌው ሄዶ አሽከሩ መጣ!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ሎሌው ሄዶ አሽከሩ መጣ! 
አቻምየለህ ታምሩ
አምባቸው መኮንን  ሣህለ ወርቅ ዘውዴን ለመሆን ተዘጋጅቶ  የነበረ ሰው ነው። ይህንን እሱ ራሱ በሰጠው ቃለ መጠይቅ አረጋግጧል። መቼም የአማራ የኅልውና አደጋ  እንቅልፍ የሚነሳው  አንድ ሰው ፖለቲካን ርግፍ አድርጎ በተመው የግሉን ድሎት ሊኖር ጫማ ሰቅሎ ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ለመሆን  ፍቃደኛ ይሆናል ብላችሁ ሙግት የምታነሱ አይመስለኝም።
አምባቸው መኮነን አሜሪካን በመጣ ጊዜ  «ተስፋ የፈነጠቀ» ያለው  የዐቢይ ለውጥ  እንዲመጣ ከፈልነው ካለው መስዕዋትነት ትልቁ «ጓዶቻችን» ካላቸው ከነ በረከት ሰምዖን ጋር መቆራረጣቸውን ነው።  ይታያችሁ!  «የአማራው ባለጉዳይ»  ነኝ የሚል አንድ ሰው ለውጥ ያለው  እንዲመጣ  ከፈልሁት ያለን ትልቁ መስዕዋትነት የአማራ ጠላቶች ከሆኑት ከነ በረከት ሰምዖን ጋር መቆራረጡን ነው። ኤርትራዊነት እንዳለበት ባላረጋግጥም አንድ ወዳጄ ኤርትራዊነት ስላለበት ነው ለነበረከትና ኅላዌ  ስስ ልብ ያለው ብሎኛል።
አምባቸው የብአዴን ሰው ነው። አካሄድነው ያለውን የውስጥ ትግል ውጤት የለካው የኦሕዴዱን ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚንስትር አድርገው መምረጣቸውን ነበር። በሌላ አነጋገር የብአዴን  ትግልና ስኬት ኦሕዴድን መሪ ማድረግ ነው። ይህ ማለት የብአዴኑ አምባቸው የአማራን ሕዝብ ሲመራ ቅድሚያ  የሚሰጠው ለኦሕዴድ ጉዳይ ነው ማለት ነው።
በነገራችን ላይ አምባቸው  ፈረንጆቹ the king’sman የሚሉት አይነት የዐቢይ አሕመድ ታማኝ አሽከር  ነው። አንዳንዶች አምባቸውን የዐቢይ የጭን ገረድ ይሉታል። የጭን ገረድ  ሰውዬው ሲፈልግ አልጋ ላይ የሚሰቅላት  ሳይፈልግ ደግሞ  የሚያወርዳት ናት። አምባቸውም ዐቢይ ሲፈልግ ሚንስትር፣ ሲሻው በሣህለ ወርቅ ዘውዴን ቦታ፣ ሲከጅለው ከንቲባ፣ በመጨረሻ ላይ ደግሞ አማካሪ ብሎ ያለስራ  አስቀምጦት ነበር ። መቼም ዐቢይ አሕመድ  እንዲህ  በፈለገው ቦታ ሁሉ የሚሾጉጠው  እንደ እስክንድር ነጋ አላማ ያለው  የሕዝብ ወገን የሆነን የስለት ልጅ  ነው አትሉኝም። ቴያትረኞችን እነ ሽመልስ አበራን  ያስናቀው ቲያትረኛው ዐቢይ አሕመድ  የሚወደው  ልክ መለስ ዜናዊ  ይወዳቸው እንደነበሩት እንደነ አዲሱ ሰገሰ  አይነት የጭን ገረዶችን  ነው። አንዳርጋቸው ጽጌና ዳዖድ ኢብሳም የኢሳያስ አፈወርቂ ታማኞች ነበሩ።
ከአምባቸው የዛሬው ንግግር በጣም የገረመኝ  የአማራን ተጋድሎ  የወለደውን «ለውጥ» ተከትሎ «ፕሬዝደንት» ሆኖ ከተሰየመ በኋላ  የባጥ የቆጡን እያነሳ እየጣለ አክሰፕታንስ ስፒች ሲያደርግ  የአማራ ተጋድሎን ያፈነዳውን  የወልቃይት የአማራ ማምነት ጥያቄንና የተከተሉትን  ራያን፣ የመተከልን፣ ወዘተ ሕዝባዊ ጥያቄዎች በሚመለከት አንዲት ነገር ትንፍሽ ሳይል  መቅረቱ ነው! የአማራ ባለጉዳይ የሆነ ሰው በዚህ ሰዓት የወልቃይት፣ የራያ፣ የመተከተል ወዘተ የአማራ ማንነት ጥያቄዎች እንዴት ከሕሊናው ይከለሉበታል?
አምባቸው ንግግሩን የጨረሰው አማራ ሳይወከል የተጫነበትን  ሕገ መንግሥት ተብዮ እንዴት እንደሚያስከብር  ሲደሰኩር ነው። ገዱም  ልክ እንደ  አምባቸው የተመረተው   ከአንድ የብሎኬት ፋብሪካ ስለነበር በቴሌቭዥን መስኮት በወጣ ቁጥር ሁልጊዜ የሚያሰለቸን  የአማራ ያልሆነውን የአማራ በማድረግ ወያኔ የሰጠውን ተልኮ ሲያስፈጽም  ነበር።  ዛሬ የሆነው ሎሌው ሄዶ አሽከሩ መጣ ነው!
Filed in: Amharic