>

የአዲስ አበባ መዘዝ!!! (ያሬድ ጥበቡ)

የአዲስ አበባ መዘዝ!!!
ያሬድ ጥበቡ
የአዲስ አበባን መዘዝ አመራሩም ሆነ ፖለቲካ ያገባኛል የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ በደንብ ሊያጤነው ይገባል። የሃይል አሰላለፍ ለውጥ ሊያስከትል የሚችል አደጋ ያዘለ መስሎ ይሰማኛል። እነለማ በኦሮሞ ብሄርተኝነት እየተገፉ ሰሞኑን በጀመሩት ከገፉ፣ አዴፓ ላይ የአማራ ልሂቅ የሚያሳድረው ተፅእኖ ሊጨምር ይችላል። ይህም ተፅእኖ በኦዴፓና አዴፓ መሃል መፈራቀቅን ሊፈጥር ይችላል። ይህም መፈራቀቅ፣ ከሁለቱ አንዳቸው ወይም ሁለቱም የህወሓትን ድጋፍ ወደመሻት ሊገፋቸው ይችላል። አዴፓ በወልቃይትና ራያ ጉዳይ ከህወሓት ጋር ያለው ቅራኔ ትልቅ በመሆኑ ወደምንም ዓይነት ስምምነት የመድረስ እደሉ ጠባብ ነው። ኦዴፓ ግን በወልቃይትና ራያ ጉዳይ ከህወሓት ጎን ሊቆም ተደራድሮ፣ ወያኔ አዲስአበባ የኦሮሞ ነው ብሎ እንዲስማማ በመጠየቅ፣ በምላሽ ጌታቸው አሰፋንም ሆነ ሌሎች በህግ የሚፈለጉ የቀድሞ ባለሥልጣናትን ላያሳድድና አርፎ ሊቀመጥ ሊስማማ ይችላል።
ከላይ የሳልኩት ቢሆን ተቀባይ ሊሆን ከቻለ አዴፓ የፈለገውን ለማግኘት ብዙም ድጅኖ (ሌቨሬጅ) የለውም ማለት ነው። ከአዴፓም አልፎ የአማራ ብሄርተኝነት ኦዴፓን ሊስብ የሚያስችለው ወደ ድርድር ጠረጴዛው ይዞት የሚቀርበው ነገር ከሌለው፣ አሁን በአዲስአበባ ጥያቄ ዙሪያ የጦዘው ጉዳይ መልክ እንዲይዝ ቀን ከሌት መሥራት ይኖርበታል። አዴፓ እነ አቶ ለማ የነጃዋርን የአዲስአበባ ባለቤትነት ጥያቄ በግልፅ አወግዘው አዲስአበባ የመላ ኢትዮጵያውያን መዲና መሆኗን እንዲያረጋግጡ በመጠየቅ በምላሽ  አዲስአበባ ውስጥ ኦሮሙኛ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ለመደገፍ አዴፓ ሊስማማ ይችላል። ይህ የአዴፓ የዘንባባ ዝንጣፊ በቂ መስሎ ካልታየውና “እናንተ ከምትሰጡኝ ከወያኔ የማገኘው ይበልጣል ብሎ ኦዴፓ ካመነ ግን መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ ብሎ ረግሞ ከመሸኘት ውጪ አዴፓ ማድረግ የሚችለው ያለ መስሎ አይሰማኝም። ይህ የሆነ ቀን ግን የለውጡ የጀርባ አጥንት የነበረው ሃይል ተሰነጠቀ፣ ለውጡም ተሰናከሎ ወደቀ ማለት ነው። ከዚያ በኋላ ኢህአዴግ ውስጥ አዲስ የተቀላቀሉትን የሱማሌ ቤኒሻንጉልና አፋር ንቅናቄዎች ድጋፍ ይዞ ወያኔ ወደሥልጣን የሚመለስበት እድል ዝግ አይደለም። ያኔ እስክንድርም ሆነ ለማ ፣ አቢይም ሆነ ደመቀ ሰላም አይኖራቸውም።
ይህን ከመሰለው ሁሉም ከሚሸነፍበት መንገድ ሆን ብለን እንራቅ። ከስሜት ይልቅ በህሊናችን እንገዛ ። ከላይ በተሳለው ቢሆን ውስጥ ህወሓት ሃይሉን ቆጥቦ መቐለ ላይ መቀመጡ የፈጠረለትን እድል እንድናይ ያደርገናል። ዝም ብሎ የሚተውና የሚናቅ ሃይልም እንዳልሆነ ይገባን ይሆናል። ምን ይሻል ይሆን? የተሻለው መንገድ ወያኔን አግልሎና ከዳር አቁሞ በመሄድ ሳይሆን፣ የኢህአዴግ አመራር በ17 ቀናት ስብሰባው የመከረባቸውንና ውሳኔዎች ያስተላለፈባቸውን ጉዳዮች እንደመነሻ ይዞ፣ ከስብሰባው ወዲህ ባሉት የአንድ አመት ወራት የተፈጠሩትን አዲስ ውጥረቶች ግምት አስገብቶ፣ የለውጡን አመራር ሃላፊነት የሚወስዱ ከኢህአዴግ ምክርቤት የተውጣጡ ቀን ተቀን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በፖለቲካ የሚያማክሩ በግልፅ የታወቁ ሰዎች እንዲኖሩ በማድረግ፣ የለውጡ አመራር የሰፋና ብዙ ባለድርሻዎችን ያቀፈ ማድረግ የተሻለ መንገድ ሊሆን ይችላል። ይህን ዓይነቱን ለውጥ ለማድረግ ኢህአዴግ ውስጣዊ አንድነትም ሆነ ዝግጅት ከሌለው ግን፣ በ1983 ኢህአዴግ የሽግግር ምክርቤት ያቋቋመበትን ልምድ መሠረት በማድረግ የትኛውንም ሃገራዊ ሃይል ያላገለለ የሽግግር ምክርቤት በማቋቋም፣ ከዚህ ምክርቤት ውስጥ የፖለቲካ ብስለትና ተአማኒነት ያላቸውን ከ7 እስከ 9 የሚደርሱ አባላት ያሉበት የፖለቲካ ኮሚቴ አቋቁሞ ቀን ተቀን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይን እንዲያማክሩ በማድረግ ሽግግሩ አሁን የገጠመውን   በተለምዶ ቲም  ለማ ብለን ስንጠራው የነበረው የሽግግር አመራር ድክመትና ጠባብ ብሄርተኛ ማሰላሰሎች ልንሻገር ይገባ ይመስለኛል። ለውጡ የተደራጀ አመራር የሚፈልግበት እርከን ላይ የደረሰ ይመስለኛል።
Filed in: Amharic