>
5:13 pm - Friday April 19, 8278

ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ክፍል ፪ (ውብሸት ሙላት)

ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ክፍል ፪
ውብሸት ሙላት
 
2.1
* የመንግሥት ድርጅቶች ወደ ግል አዟዟር ሒደት
በዐጼ ኃይለሥላሴ ዘመን የተቋቋሙ የንግድ ድርጅቶችን ደርግ ወርሶ የመንግሥት አደረጋቸዉ፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ ወደ ግል አዞራቸዉ፡፡ ወደ ግል ለማን አዞራቸዉ ቢሉ ባዶ እጃቸዉን ለመግዛት ለሔዱ ታጋዮችና ወዳጆች ነዉ፡፡ የተወሰኑትም ኢንዳዉመንቶች ገዟቸዉ፡፡ እንዴት ባዶ እጃቸዉን ሔደዉ ገዟቸዉ ካላችሁ መልሱ እንዲህ ነዉ፡፡ ለዚያም በጣም ግልጽና ቀላል፡፡
 የሕወሃት ወዳጅ እስከሆንክ እና ኢሕአዴጋዊ ቡራኬ እስካገኘህ ድረስ በፕራይቬታይዜሽን ወደ ግል የሚዞረዉን መንገድ ይሸጥልሃል፡፡ ከዚያ ወደ አንዱ ባንክ ሄደህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፍቶ ያገኛትን ገንዘብ ባንክ ካስቀመጠዉ ብር ተዘግኖ ብድር ይሰጥሃል፡፡ ድርጅቱ ከሚያስገኘዉ ገቢ ብድሩን ትከፍላለህ፡፡ አለቀ፡፡ በባዶ ኪስ ሔደህ አንድ የትልቅ ድርጅት ባለቤት ትሆናለህ፡፡ ሆኑ፡፡
ነገሩን የበለጠ አሳዛኝ የሚያደርገዉ ከጃንሆይ ዘመን ስንት ለፍተዉ ያቋቋሙትን የንግድ ድርጅት ደርግ ያለ ካሳ ወርሶት፣ በኢሕአዴግ ለታጋዮችና ለሕወሃት ወዳጆች በነጻ የተላለፈዉ የስንት ድሃ ሰዉ ገንዘብን ከባንክ ወስደዉ መሆኑ ነዉ፡፡ በድሃ ገንዘብ ኢሕአዴግ ስንት ወዳጆቹን ሃብታም አደረገበት መሰላችሁ! ፖሊሲዉ ግን ፕራይቬታይዜሽን ነዉ፡፡ ለማን እንደሚዛወር፣ እንዴት እንደሚዛወር የማይጠይቅ አመራር ሥልጣን ላይ ተጎልቶ ዐይኑን ቢያፈጥም ሳይገባዉ ሕወሃት ሰዎቿን አከበረችበት፡፡ የራሷን ከበርቴ ፈጠረች፡፡
2.2
የአክሲዮን ገበያ ለምን እንዳይኖር ተፈለገ?
ዜጎች ባጠራቀሟት ገንዘብ አክሲዮን በመግዛት በየዓመቱ የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ፣ በቸገራቸዉም ጊዜ አክሲዮናቸዉን የሚሸጡበት ሥርዓት ከተዘረጋ ኢሕአዴግ ለወዳጆቹ ከባንክ እንዲበደሩ የሚያደርገዉ ገንዘብ ይቀንሳል፡፡ የአክሲዮን ገበያ ከተስፋፋ ሰዎች ገንዘባቸዉን ባንክ በማስቀመጥ፣ በዓመት አምስት ፐርሰንት ወለድ እያገኙ፣በየዓመቱ እየናረ በሚሔደዉ የብር የመግዛት አቅም መውረድ ጋር ቆጣቢነት አትራፊም ሳቢም አይደለም፡፡ ይልቁንም የምስኪኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ እንዳሻቸዉ ከባንክ ለመበደር እንዲመቻቸዉ አክሲዮን ገበያን ሳይፈቅዱ ቀሩ፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በብዙ ከተሞች ሕንጻ ገነቡበት፡፡
ለአገራዊ ትራንስፎርሜሽን የማይጠቅም ነገር ላይ አዋሉት፡፡ የአክሲዮን ገበያ ቢኖር ኖር በየከተማዉ እንደ ጅብራ የተገተሩ ሕንጻ ብቻ ታቅፈን አንቀርም ነበር፡፡ በአምስት ፐርሰንት ወለድ በየባንኩ የቆጠብነዉን፣ኢሕአዴግ ለወዳጆቹ ባሰኛቸዉ ቦታ ሕንጻ እንዲገነቡ እና ሌላም ቢዝነስ ዉስጥ እንዲገቡ ሲለፈለገ፣የራሱን የከበርቴ መደብ ለመፍጠር፣ ከድሃዉ ጉሮሮ እየፈለቀቀ ገንዘብ አመቻቸላቸዉ፡፡ ለዚያ ነዉ ወዳጄ የአክሲዮን ገበያ እንዲኖር ያልተፈቀደዉ!
ለምሳሌ ባለፈዉ ዓመት ብቻ ፣2010 ላይ፣ አማራ ክልል ዉስጥ ብቻ 52 ቢሊዮን ብር ተቆጥቧል፡፡ ባንኮች ይሄን ያህል ብር ሰብስበዋል፡፡ በክልሉ የነበረዉ የብድር ፍላጎት 26  ቢሊዮን ብር ገደማ ቢሆንም የተሰጠዉ ብድር 14 ቢሊዮን ብር አካባቢ ብቻ ነዉ፡፡ ለዚያዉም 10 ቢሊዮን ገደማዉን የሰጠዉ አብቁተ ሲሆን ከቀሪዉ አራት ቢሊዮን ዉስጥ ሦስት ቢሊዮኑን አባይ እና ዳሽን ባንኮች ናቸዉ ያቀረቡት፡፡ 52 ቢሊዮን ብር በተቆጠበበት ክልል 26 ቢሊዮን እንኳን ለማበደር አልተፈቀደም፡፡ ወደ ሌላ እንጂ ወደ ክልሉ አልመጣም! ቆጥበህም አይፈቀድልህ ወዳጄ! አክሲዮን ገበያ አለመኖር ምክንያቱ ይገባን ዘንድ ፣ ማን በቆጠበዉ ማን እየከበረበት እንደሆነ ለማሳየት የቁጠባና የብድር አቅርቦቱን መጻፌ!
2.3
 
ከቀረጥ ነጻ የራስን ሰዎች ለመጥቀም አገርን የመግደል ብርቱ ሴራ ….
በተለያዩ ጊዜያት በተሻሻሉት የኢንቨስትመንት አዋጆች፣ደንቦችና መመሪያዎች አማካይነት ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ሲባል ለኢንቨስተሮች ከቀረጥ ነጻ የሆኑ ግብአቶችን ከዉጭ አገር እንዲያስገቡ ሲፈቀድ ኑሯል፡፡
እነዚህ ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች የኢሕአዴግ መንግሥት ትኩረት መስኮቼ ናቸዉ ብሎ ለለያቸዉ የልማት ዘርፎች ላይ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ነዉ፡፡ በሆነ ወቅት ለሆቴልና ቱሪዝም ነዉ በማለት እንደ ግሪሳ ግርርርር በማለት በርካታ ባለሃብት ለሆቴል ግንባታና አገልግሎት የሚዉሉ ብረታብረትም መኪኖችም እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶችን በገፍ ከቀረጥ ነጻ አስገቡ፡፡ በጥቂቱ ለኢንቨስትመንት ያዉሉታል፡፡ በጣም ብዙዉን ይሸጡታል፡፡ ብዙዎቹ ጀምረዉ ለተወቱ ኢንቨስትመንት ጓፈዉ ጓፈዉ አስገብተዉ ሽጠዉታል፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ ትኩረቴ ኮንስትራክሽን ዘርፍ ነዉ ይልና እንዲሁ ለመረጣቸዉ ባለሃብቶች ከቀረጥ ነጻ ማሽነሪና መኪና እንዲያስገቡ ይፈቅዳል፡፡ አስቀድመዉ የተቋቋሙ፣ ወይም እንዲያቋቁሙ የተፈለጉ፣ኢሕአዴጋዊ ቡራኬ ያገኙ ልማታዊ ባለሃብቶች በተከፈተዉ የጊዜ መስኮት ከቀረጥ ነጻ ያስገባሉ፡፡ ከዚያ መስኮቱ ይዘጋል፡፡
በአንዱ ዘርፍ የሚሠማሩት ሰዎች ሲበቃቸዉ በሌላዉ ደግሞ ከቀረጥ ነጻ ማስገባት ይፈቀዳል፡፡ ከዚያም ያስገባሉ፡፡ የገባዉም የሚሸጠዉ ይሸጣል፡፡ በተረፈዉ ይሠራሉ፡፡ ላይሠሩም ይችላሉ፡፡ በዚህ መንገድ፡- ሆቴልና ቱሪዝም፣ ኮንስታራክሽን፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ግብርና ወዘተ ሰበብና ስም ከቀረጥ ነጻ ያስገቡት የትየለሌ ናቸዉ፡፡
ምሳሌ አንድ፡- የአዲስ አበባ – ጂቡቲ የመኪና መንገድ እንደ አዲስ እንደሚሠራ መረጃ እንደወጣ  አንድ ደሴ የሚገኝ ሕወሃታዊ ቡራኬ የተቸረዉ ሰዉ፣ ከእጅ ወደ ከሚባል ትንሽ ከፍ ያለ ሃብት ያለዉ ሰዉ፣ አፋር ክልል ዉስጥ መንገዱ በሚያልፍበት ላይ ከወረዱ ይልቅ በመንገዱ አቅጣጫ ረጅም የሆነ መሬት ለኢንቨስትመንት እንዲወስድ ተደረገ፡፡ ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገባ የሚፈቀድለትን ቁሳቁሶች በፍጥነት አስገባ፡፡ በተለይ ለግንባታ የሚሆን ብረት ደግሞ በገፍ አስገባ፡፡ ትንሽ ቆይቶ መንገድ ሊሠራበት ስለሆነ ካሳ ተከፍሎት እንዲነሳ ተወሰነ፡፡ መሬቱ ላይ ምንም ዓይነት ኢንቨስትመንት ባይኖረዉም ከፍተኛ የብረት ክምችት ግን ቆልሎበታል፡፡ በመጨረሻም፣ ካሳዉን ተቀበለ፡፡ ብረቱንም ሸጠ፡፡ በአንድ ጊዜ የናጠጠ ሃብታም ሆነ፡፡
ልክ እንደዚሁ ሁሉ በርካታ ሰዎች ብረታብረትን ከቀረጥ ነጻ በማስገባት፣እንዲሁም የብረት ንግድ ፈቃድ በማዉጣት የንግድ ሥርዓቱን በማዛባት፣ ሆን ተብሎ በተመቻቸና በተዘረጋ የኦሊጋሪኪ መረብ አማካይነት የቀረጥ ነጻ የኢንቨስትመንት ማትጊያ ሥርዓት ኢሕአዴጋዊ ባለሀብቶችን ሲፈጥሩ ኑረዋል፡፡
ለኢንቨስትመንት ከቀረጥ ነጻ በማስገባት ሰበብ አገርን ጎድቶ፣ የንግድ ሥርዓትን አዛብቶ፣ ከንግድ መርሕ የዘለለ ትርፍ አጋብሶ፣ የተወሰኑ ብሔር ተወላጆችን ብቻ ነጥሎ በሁሉም ዘርፍ ባለሃብት ፈጥሮ፣ ሕወሃታዊ እርግማን ካረፈባቸዉ ብሔሮች ደግሞ ቀድሞም ባለሃብት የነበሩትን ሁሉ ከኢንቨስትመንት እንዲወጡ አደረጓቸዉ፡፡ በርታ ኮንስትራክሽንንና ማሩ ብረታ ብረትን በምሳሌነት ያስታዉሷል፡፡ በዚህ መንገድ ባለሃብት የሆኑትንም ሆነ ከንገዱ ዉጭ የሆነ ሰዎችን ስንዘረዝር ዉለን ብናድር አያልቅም፡፡
ምን ለማለት ነዉ?  እንዲህ ዓይነት አሻጥሮች ሲሠሩ ኑረዋል፡፡ በአንድ በኩል በሻጥሩ ምክንያት የተፈጠረዉ ኢኮኖሚያዊ አለመመጣጠንን ለማጥበብ መትጋት አስፈላጊ ሲሆን፣በሌላ በኩል ደግሞ ፖሊሲ እና ሕግ ማዉጣት ላይ ተሳታፊ የሆናችሁ ከእንደዚህ ዓይነት ስህተቶች ተምራችሁ የእያንዳንዱን ፖሊሲና ሕግ የብሔር አንድምታ፣ትርፍና ኪሳራ እያሰላችሁ እንጂ የተነገራችሁን የቀረበላችሁን ሁሉ በእምነት ብቻ አትቀበሉ፡፡ ፖለቲካ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ስትቀበሉ አዉጥታችሁ አዉርዳችሁ ይሁን ለማለት ነዉ፡፡ የቻላችሁትን በራሳችሁ፣ ያልቻላችሁትን ምክር እየጠየቃችሁ ተጓዙ!
(ሁሉም ባለሃብት ሕወሃታዊ ቡራኬ ደርሶት ይሄን አድርጓል ማለት ግን አይደለም! በጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ሕግን ሳያዛንፉ፣ ወለም ዘለም ሳይሉ- ቢሉ ምን እንደሚከተላቸዉ ስለሚያዉቁ- ኢንቨስት ያደረጉ አሉ፡፡ ምስጋና የሚገባቸዉ ናቸዉ!)
Filed in: Amharic