>

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እየተጓዘችበት ያለው መንገድ በምዕራባውያኑ ምሁራን እይታ!!! (ዘ መንፈስ አክሱማዊ)

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እየተጓዘችበት ያለው መንገድ በምዕራባውያኑ ምሁራን እይታ!!!
ዘ መንፈስ አክሱማዊ
በአገሪቱ ወደ ወደ 3 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ የእነዚህ ዜጎች በምርጫው ላይ የሚኖራቸውም የብሔር ድርሻ ጥያቄም በምርጫው ፍትሀዊነትና ተዓማኝነት ላይ ጥያቄ መፍጠሩ አይቀርም!!
እንደ መግቢያ
—————–
የዶር አብይን የፖለቲካ ለውጥ በሚመለከት እስከአሁን ከምዕራባውያን የተሰጡት አስተያየቶች በሁለት ከፍለን ማየት አንችላለን፡፡  በአንደኛው ወገን የምዕራባውያኑ ሚዲያዎች ለውጡን እያንቆለጳጰሱ ነው፡፡ በሌላኛው ወገን ደግሞ የምዕራባውያኑ ምሁራን የዶሩን ለውጥ በሰላ ትችት ለማየት እየሞከሩ ነው፡፡ የምዕራባውያኑ ሚዲያዎች አንድም የፖለቲከኞቻቸው ጥቅም አራማጅ መሆናቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ለጉዳዮ የጠለቀ እውቀት አላቸው በሚል መውሰድ ያስቸግራል፡፡ ከዚህ አንፃር ከሚዲያዎቻቸው ሙገሳ ጀርባ ምሁራኖቻቸው በጥናታቸው ያገኙት ውጤት ምንድን ነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ለዛሬ ለውይይት መነሻ የማደርገው RENÉ LEFORT  እና  KJETIL TRONVOLL  የሚባሉ የውጪ ምሁራን በዶሩ የፖለቲካ ለውጥ ዙሪያ Ethiopian elite lost in electoral maze under Abiy’s gaze በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ትንታኔ ነው፡፡
1. መሪ ጥያቄው
ምሁራኖቹ ለፖለቲካ ትንታኔያቸው መነሻ ያደረጉት ጥያቄ የዶር አብይን የፖለቲካ መሰረት መነሻ በማድረግ ነው፡፡ የዶሩ የፖለቲካ ድጋፍ የተፈጠረው በመስመር ፖለቲካ ሳይሆን ዶሩ ባላቸው የፖፒሊስት አቀራረብ ነው፡፡ አሁን ጥያቄው ይላሉ ምሁራኑ ዶር አብይ በዚህ የፖፕሊስት አቀራረብ ያላቸውን የፖለቲካ ድጋፍ አስቀጥለው መሄድ ይችላሉ ? መልሱ ግን ቀላል አይደለም፡፡
 2. ዴሞክራሲያዊ ሽግግር
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች ቀድሞ የነበራቸውን የፖለቲካ ድምፅ እየደገሙ ነው፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች አሁንም በአገሪቱ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ ማድረግ የሚቻልበትን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ይፈልጋሉ፡፡ ይሁን አንጂ ዶክተር አብይ የምርጫ ቦርድ ሹመት ከመቀየር ውጪ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ  ማድረግ የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማድረግ የወሰዱት እርምጃ አነሰተኛ ነው፡፡
በዚህ የተነሳ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ  ማድረግ የሚቻልበት ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ከብሔር ስብጥር ጋር ተያይዞ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ በአገሪቱ የህዝብና ቤት ቆጠራ ጉዳይ በጋራ መግባባት ላይ በተመሰረተ መልኩ አልባት የማግኘቱ ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡ በአገሪቱ ወደ ወደ 3 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ የእነዚህ ዜጎች በምርጫው ላይ የሚኖራቸውም የብሔር ድርሻ ጥያቄም በምርጫው ፍትሀዊነትና ተዓማኝነት ላይ ጥያቄ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ በዚህ ችግር ላይ የአብይ አስተዳደር እፈተዋለሁ በሚል ሲንቀሳቀስበት የነበረው የወሰንና የማንነት ጉዳይም አልተፈታም ፡፡ በአዲስ አበባና ድሬደዋን በመሳሰሉ ከተሞች ባለው የብሔር ስብጥር ጥያቄም በምርጫው ሂደት ላይ የራሱ አልታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ አይቀርም፡፡  ሲዳማን በማሳሰሉ የደቡብ ክልሎች ዘንድ የራስን አድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ተጋግሎ ቀጥሏል፡፡ ስለዚህ በምሁራኑ እይታ እነዚህ ወሳኝ ችግሮች  ሳይፈቱ በአገሪቱ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ የማድረጉ ጉዳይ አስቸጋሪ ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ ደግሞ በርካታ የፖለቲካ ኃይሎች ሲታገሉለት የቆዩበትና አሁንም ድረስ የሚፈልጉት ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ውሀ በላው ማለት ነው፡፡
3. የለውጡ ሰማዕት
በምራሁኑ እይታ አብይ ራሳቸው ይዘውት በመጡት ፖለቲካ ለውጥ ራሳቸው  ሊጠፉ የሚችሉበት አድልች ሰፊ ናቸው  ይላሉ፡፡ ለምን?  በቅርቡ የስያሜ ለውጥ ያደረገው አዴፓ በክልሉ ያለውን የፖለቲካ ድጋፍ በግንቦት 7 እና በአብን ከተነጠቀ ዶር አብይ በአማራ ላይ ያላቸውን ድጋፍ ያጣሉ ማለት ነው፡፡  በሌላ በኩል ዶር አብይ መሰረት ባደረጉበት የኦሮሞ ፖለቲካ ላይ በኦነግና በኦዴፓ መካከል ያለው ፖለቲካዊ ፍጥጫ አልተፈታም፡፡ ዶር አብይ በሊቀመንበርነት የሚመሩት ኦዴፓ የወጣው እየፈረሰ ካለው ኢህአዴግ ጉያ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ኦነግ ከሌላ የአሮሞ ፓርቲ ከሆነው ኦፍኮ ህብረት ከፈጠረ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቀባይነት መፍጠሩ ማይቀር ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ  በሚቀጥለው ምርጫ ዶር አብይ በሊቀመንበርነት የሚመሩት  ኦዴፓ በምርጫው ከፍተኛ ሽንፈት ያጋጥመዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ  ዶር አብይ ይዘውት በመጡት የፖለቲካ ለውጥ አብይንና ፓርቲውን ይዞ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ካየነው ዶር አብይ ራሳቸው ይዘውት በመጡት የፖለቲካ ለውጥ መስዋዕት ሆነው ያልፋሉ ማለት ነው፡፡
4. የአብይ ብዥታ
እንደምሁራኑ እምነት ዶር አብይ በህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ያላቸው አቋም በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ ብዥታን እየፈጠረ ነው፡፡  የዚህ ብዥታ መነሻ ደግሞ ዶር አብይ በህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ባህሪ ላይ ጥረት ያለ አቋም አለመያዛቸው ነው፡፡  ከዚህ  ይልቅ ዶሩ በሁለት ቢላ የመብላት ጨዋታ እየተጫወቱ ይመስላል፡፡ በዚህ ፖለቲካዊ አካሄዳቸው ሁለት ሊታረቁ የማይችሉ ጎራዎች መካከል ተንጠልጥለው ቀርተዋል፡፡ በአንድ በኩል ህገ-መንግስቱ ሊሻሻል የሚችለው ይህን ማድረግ የሚችሉ ወገኖች በምርጫው ሂደት ስልጣን ከያዙ በኋላ ነው የሚል አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ በሌላ በኩል በኢህአዴግ አማካኝነት ያገኙትን የፖለቲካ ስልጣን መነሻ አድርገው ወደ ፕሬዝንዴንሺያል ስርዓት የመሸጋገር ፍላጎት እንዳላቸው  ምልክት እያሳዩ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ህገ-መንግስቱን ማሻሻል ላይ በሚመለከት ደር አብይ ግልፅ አለመሆናቸው  አሸናፊ ሆኖ ከሚወጣው ጎን ለመሰለፍ እየተዘጋጁ  እንጂ በራሳቸው ለውጡ ላይ ለመወሰን የተቸገሩ ያስመስላቸዋል፡፡
5. የፌዴራሊስቶቹ ህብረት
በሌላኛው ጫፍ የዶሩን የአሀዳዊነት(የፕሬዝዴንሽያል)  ፍላጎት የማይቀበሉ የፌዴራሊስቶች ህብረት መጠናከራቸው የዶር አብይ ፖለቲካዊ ለወጥ አንዱ ፈተና ነው፡፡  እነዚህ ወገኖች የብሔር ፌዴራሊዝሙ የፖለቲካ ጥቅማቸውን ለማስከበር እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርገው የተቀበሉ ናቸው፡፡  ለምሳሌ በአፋር ፣ በሶማሌ ፣ በትግራይ ፣ በደቡብ ክልሎች ያሉ ኃይሎች የብሔር ፌዴራሊዝሙ እንዲነካካ የማይፈልጉ ናቸው፡፡ በእነዚህ ፌዴራሊስቶች እምነት የዶሩ ፖለቲካዊ ለውጥ በየቦታው የሚታዩ ሰላም ችግሮችን ሳይፈታ ፣ እየወደቀ ያለውን የአገሪቱ ኤኮኖሚ እና መሰል ወሳኝ አገራዊ ችግሮች ላይ ትኩረት ሳይሰጥ የብሔር ፌዴራሊዝሙ ላይ መንጠላጠል አስፈላጊ አይደለም፡፡ ከእነዚህ የፌዴራሊስቶቹ ህብረት አንፃር ካየነው የብሔር-ፌዴራሊዝሙን መለወጥ ላይ ትኩረት ያደረገው የዶሩ ፖለቲካዊ ለውጥ ይሰካል ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡
6. መሬት ያልነካ ፖለቲካ 
ምሁራኖቹ አንደሚሉት የዶሩ ፖለቲካዊ ለውጥ መሬት ያልነካ እና በአየር ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡  አሁን አገሪቷ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ መሆኗ ላይ ልዩነት የለም፡፡ ነገር ግን ዶሩ ይኸን ችግር ለመፍታት እየሄዱበት ያለው የፖለቲካ አካሄድ የአገሪቱ ነባራዊ የፖለቲካ ችግር ያገናዘበ የፖሊሲ አማራጭ የለውም፡፡
ዶሩ ወሳኝ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መዋቅር ገንብተው ተግባራዊ የፖለቲካ መፍትሄ ከማስቀመጥ ይልቅ ከአንዱ ጉዳይ ወደ ሌላ ጉዳይ እዘለሉ ነው፡፡  ምሁራኑ አንደሚሉት ጠንካራ የፐርቲ መዋቅር የነበረው ኢህአዴግ አሁን አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ አለ ቢባል አንኳ ከበፊቱ በተለዬ መልኩ በፅንፈኛ ፖለቲከኞች የተሞላ በመሆኑ እንደ ጠንካራ መዋቅር አይወሰድም፡፡ በክልሎችና በፌዴራል ስርዓቱ መካከል ያለው ግንኙት የተበጣጠሰ በመሆኑ ጠንካራ መንግስታዊ መዋቅር መገንባት አይችልም፡፡  ምሁራኖቹ እነዚህንና መሰል ጠቃሚ አሳቦችን በስፋት በማንሳት በዶሩ ለውጥ ላይ ያላቸውን ትንታኔ ይቀጥላሉ፡፡
Filed in: Amharic