>

ኦዴፓ አልተሳሳተም!!! (ሳምሶን ጌታቸው)

ኦዴፓ አልተሳሳተም!!!
ሳምሶን ጌታቸው
* የግብር አባቱ ህወሀት  “…እርዳኝ አርዳሃለሁ እስካለሁ ልጄ ነህ፣ ስሞት ወራሼ ነህ” ብላ በቃልና በሰነድ ብዙ ነገር ከሕግና ከፍትሕ ውጭ በተስፋ አንበሽብሻዋለች!!!
በአንድ መንደር ውስጥ ይኖር የነበረ አንድ ቂል ገጠሬ ነበረ። በአንድ ገበያ ቀን ይሄ ቂል ሰውዬ ከሩቅ አካባቢ ሄዶ በብዙ አህዮች የእህል ገለባ እህል አስመስሎ ጭኖ ወደ መንደሩ ጉዞ ይጀምራል። ወደ ሠፈሩ ሲደርስ በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ ገበያ ከሚተመው መንደርተኛው ጋር ይገናኛል። ወደ ገበያ የሚያቀናው ሕዝብ ሁሉ “ኧረ.. አያ ቂሎ በጠዋት ምን ቢቀናህ ነው፣ ደግሞስ ይኼ ሁሉ የጫንከው እህል ነው?” ሲሉ ይጠይቁታል።
ቂሉ ሰውዬ፣ ቆይ ልቀልድባቸው አለና ኮራ ብሎ “አልሰማችሁም እንዴ? እህል ነው የጫንኩት፣ ስንዴና ጤፍ እርዳታ በነፃ መንግሥት ገበያ መሃል ያለው መጋዘን እያከፋፈለ ነው። ለአንድ ሰው አስር ኩንታል ስንዴና ጤፍ እየተሰጠ ነው” ብሎ ምሎ ይገዘትላቸዋል። ቂሉ ለጠየቀው ሁሉ ተመሳሳይ መልስ ኮስተር ብሎ መስጠቱን ቀጠለ። ቂል ይዋሻል ብሎ ያልገመተው ነዋሪ ሁሉ፣ የቂሉን ወሬ በአንዴ አዛምቶ ከመንደሯ አልፎ ብዙ አካባቢዎች ተዳረሰ። በጥቂት ደቂቃ የተባለውን የእርዳታ እህል ለመቀበል ገጠሬው ሁሉ የጋማ ከብቶቹን ይዞ ወደ ገበያው ሥፍራ እሽቅድድም ሆነ።
ይኼኔ ቂሉ ያልነገራቸው ሰዎች ሁሉ፣ ከአጎራባች ቀበሌ ያለው መንደርተኛ ሁሉ አጋሰሶቻቸውን ጭነው እርዳታውን ለመቀበል እያሉ ሲተሙ ሲያይ አንድ ሀሳብ ብልጭ አለበት። “እንዴ ይኼ ነገር እውነት ሆነ እንዴ?” የሚል። ወዲያው የራሱን ውሸት ያመነው ቂል ስንት መንገድ ጭኖ ያመጣውን ገለባ መንገድ ላይ አራግፈና የጭነት እንስሶቹን ይዞ ወደ ገበያ ተፈተለከ ይባላል። ከቂልነት ይሰውረን።
ህወሓት፤ ኢሕአዴግን አቡክታ ጠፍጥፋ ስትፈጥረው በሥልጣኗ ላይ ያለተቀናቃኝ ሀገሪቱን ለመቆጣጠር ነው። በዚህም መሠረት ኦዴፓን ደግሞ ከሌሎቹ አጋር ፓርቲዎች የበለጠ ለአላማዋ ማሳኪያነት መርጣዋለች። “እርዳኝ አርዳሃለሁ እስካለሁ ልጄ ነህ፣ ስሞት ወራሼ ነህ” ብላ በቃልና በሰነድ ብዙ ነገር ከሕግና ከፍትሕ ውጭ በተስፋ አንበሽብሻዋለች።
ታዲያ “ሀብቱም፣ መሬቱም፣ ቋንቋውም፣ ታሪኩም፣ ከተማውም፣ ፎቁም፣ ሕንፃውም፣ ወንዙም፣ ሚኒስቴር መ/ቤቶቹ ሁሉ፣ ወታደሩም፣ ፖሊሱንም የቅድም አያቶችህና ያንተ ብቻ ስለሆኑ ትወርሳለህ። ብቻ እኔ የምልህን ስማ” ተብሎ በቂል ተስፋ ያደገ የማደጎ ልጅ ነው። ኦዴፓ፤ ህወሓት ለቀልድ ብላ ስትግተው የከረመችውን ውሸት ቢጠራጠርም፣ በአመታት ድግግሞሽ ለመደውና “ይኼ ነገር እውነት ነው መሰለኝ” ብሎ ሀቁን ለመቀበል የያዘውን ጥሎ በመሯሯጥ ላይ ነው። ለማንኛውም ሀገር በጥበብና በዕውቀት እንጂ በቂል ተስፋ፣ በጠመንጃ እና በማን አለብኝነት አትፀናም። ሁሉን ለመሰብሰብ መሞከር ሁሉን ያስጥላልና፣ ማሰቢያ የሚሰራ ከሆነ ቆም ብሎ ማሰብ ነው። ለማንኛውም ኦዴፓ አልተሳሳተም፣ መሳሳት የተፈጠረለት ዓላማው ነውና። ህወሓት የተረገመሽ ሁኚ።
Filed in: Amharic