>
5:13 pm - Friday April 18, 2302

ዜጐችን ማፈናቀል በአስቸኳይ ይቁም!! (ሰ.መ.ጉ - መግለጫ)

ዜጐችን ማፈናቀል በአስቸኳይ ይቁም!!
ሰ.መ.ጉ – መግለጫ
በኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ዙሪያ ልዩ ዞን የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር በ01 እና 02 ቀበሌዎች፣ ጭላሎ፣ ወበሪ፣ ለገዳዲ ቄራ፣ ገዋሳ፣እና በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን “ህገወጥ ግንባታዎች ናቸው፤ ለአረንጓዴ ልማት ይፈለጋሉ” በማለት ከየካቲት 12 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ በሃይል በማፍረስ ላይ ይገኛል። የከተማዋ ከንቲባ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለፁትም በቀጣይም ከ12 ሺህ በላይ ቤቶችን እንደሚያፈርሱም አረጋግጠዋል። ሰመጉ ስለጉዳዩ የከተማዋን ከንቲባ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ሰመጉ ያነጋገራቸው ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው በርካታ ዜጐች እንዳስረዱት ከ1997 ዓም ጀምሮ በመንግስት ላይ እምነታቸውን ጥለው በተለያየ ወቅት በገዙት ቦታ ላይ የገነቡትን መኖሪያ ቤቶች በመገንባት እና አካባቢ በማልማት ከተማዋን ለእድገት አብቅተዋታል። በነዚሁ አመታት ውስጥም የአካባቢው የመንግስት ኃላፊዎች እያወቁት የመብራት እና ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መሆናቸውን፣ ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸውን፤ በተለያዩ አስተዳደራዊና የልማት እንቅስቃሴ ላይ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አስረድተዋል። ይሁን እንጂ የከተማዋ አስተዳደር ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመተባበር ከነዋሪዎች ጋር በቂ ምክክር ሳያደርግ እና ሊመጣ የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ ላይ ምንም አይነት ቅድመ ዝግጅት ሳይኖረው ቤቶችን በማፍረስ ህፃናት፣ሴቶችና አቅመ ደካሞችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች ሜዳ ላይ እንዲወድቁ አድርጓል። በዚህም የዜጐችን ለኑሮ አመቺ በሆነ አካባቢ የመኖርን መብት፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃና ምግብ የማግኘት መብት፣ የአካል ደህንነት መብት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ መብቶች ተጥሰዋል።
የከተማው አስተዳደር የወሰደውን የሃይል እርምጃ ይበልጥ አስከፊ እና አጠያያቂ የሚያደርገው ከመኖሪያቸው በ7 ቀናት የማስጠንቀቂያ ጊዜ በኃይል እንዲፈናቀሉ ለተደረጉ ዜጐች ምንም አይነት አማራጭ የመኖሪያ ስፍራም ሆነ ጊዜያዊ የመጠለያ ስፍራ ያልተዘጋጀላቸውና ሰብዓዊ እርዳታም ያልተደረገላቸው መሆኑ ነው።
የፌዴራል መንግስትም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በዜጐች ላይ እየተፈፀመ ያለውን መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት፤ እየተካሄደ ያለውን የመኖሪያ ቤቶች ማፍረስና ዜጐችን ማፈናቀል በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ፣ መኖሪያቸው ለፈረሱባቸው ዜጐች ተገቢዉን ድጋፍ እና ተመጣጣኝ ካሳ በአስቸኳይ እንዲያደርጉና በሠላም የመኖር መብታቸውን እንዲያስጠብቁላቸው ሰመጉ ይጠይቃል።
Filed in: Amharic