>

በግልጽ እንነጋገር!!! (ያሬድ ሀይል ማርያም)

በግልጽ እንነጋገር!!!
ያሬድ ሀይል ማርያም
* የተጀመረው ለውጥ በሁለት አደገኛ አስተሳሰቦች መካከል እየተዋከበና አቅጣጫውን እንዲስትም እየተናጠ ይመስላል። አንደኛው ‘ጌዜው የኛ ነው’ የሚል ቂላቂል አስተሳሰብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‘የእኔ ጥያቄ በቅድሚያ ካልተመለሰ ለውጥ የለም ወይም ለውጡ የጥቂቶች ብቻ ነው’ የሚል ጥሬ አስተሳሰብ።    
የጌዜ ነገር፤
ጊዜ ባለቤት የለውም። ጊዜው የኛ ነው የሚል ስሜት በአንዳንድ የኦሮሞ ተወላጆች ዘንድ በአደባባይ ሲንጸባረቅ እየተስተዋለ ነው (በአንዳንድ የሚለው በደንብ ይሰመርበት)። እንዲህ ያለ የጠባብነት ስሜት እጅግ አደገኛ እና አጥፊም ነው።  በህውሃት ዙሪያ ተኮልኩለው የነበሩ ባለጊዜዎች ዛሬ ከምን እንደደረሱ ማየት በቂ ነው። ጊዜ ባለቤት የለውም። ጊዜ የሁሉም ነው። ጊዜ ብሔር፣ ኃይማኖት፣ ቀለም፣ ጽዎታ ወይም የሃብት መስፈሪያ የለው። ያከበረውን ያከብራል፤ ያዋረደውን ያዋርዳል። እነ ዶ.ር አብይ እና አቶ ለማ የሚመሩት ለውጥ ከዚህ እሳቤ የጸዳ እንደሆነ አሁንም በድፍረት እናገራለሁ። እነዚህ ሰዎች ሕዝብን እያታለሉ እንደሆነ ተደርጎ በየመድረኩ የሚገለጸውንም ነገር ሙሉ በሙሉ አልቀበለውም። አሁንም የዶ.ር አብይ አስተዳደር ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እና የሁሉም የምትሆን አገር አድርገው እንደሚያስቀጥሏት ሙሉ ተስፋ አለኝ።
ነገር ግን ይህን የፖለቲካ ሽግግር እንደ አጋጣሚ ለመጠቀም፣ ቁርሾ ለመወጫነት እና እንደ ከሸፉት የኽውሃት ካድሬዎች ግዜውን የራሳቸው ብቻ ለማድረግ ያሰፈሰፉ ጥቂት የኦሮሞ ፖለቲከኞች ለውጡን መስመር እንዳያስቱት ግን እሰጋለሁ። አሁን ባለችዋ ኢትዮጵያ ‘ጊዜ ኬኛ’ አያዋጣም። ወያኔ ሃያ ሰባት አመት የፈነጨበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል። ዛሬ ሁሉም ባለጊዜ ለመሆን አሰፍስፏል። ሁሉም የነጻነትን ጣእም ቀምሷል። ማንም በማንም ላይ ባለ ጊዜ ሊሆን የሚችልባት ኢትዮጵያ አልፋለች። ስለዚህ ባለ ጊዜ ለመሆን የቋመጣችሁ ሁሉ ይህን የከሰረ እሳቤ ወደ ጎን ትታችሁ እነ ዶ.ር አብይ የጀመሩትን ትልቅ አገራዊ እራይ የሰነቀውን ለውጥ በታግዙ ትንሳዔያችን ቅርብ ይሆናል።
የለውጥ ነገር፤
ከላይ ከጠቀስኩት ችግር ባልተናነሰ እና እንደውም በከፋ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ የሆነው ነገር ሁሉንም የማጠልሸት እና ጨለምተኛ የመሆን ነገር ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ በማህበረሰባችን ውስጥ ይስተዋላል። እጅግ በርካታ እና የሌላውን አለም ትኩረት ጭምር የሳበ ለውጥ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ተከናውናል። ይሁን እና ገሚሶቻችን ቅዱስ መስሐፉ እንደሚለው የምንጠይቀውንም የምናውቅ አይመስለኝም፤ ገሚሶቻችን ደግሞ ለጥያቄዎቻችን የጊዜ ቅደም ተከተል የለንም። አንድ ሺ ጥያቂዎችን በየቀኑ እየፈለፈልን ሁሉም ተመልሰውልኝ ካላደርኩ ለውጥ የለም ብሎ መደምደም አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን ጨለምተኝነትም ነው።
የጨለምተኝነት እሳቤ ክፋቱ የጠየቅነው ጥያቄ ቢመለስም አንረካም። ምክንያቱም አይምሯችን ጥያቄ መፈብረክ እንጂ ምላሾችን መቀበል ወይም ማዳመጥ አቁሟል ወይም እርካታ እርቆታል። ከሕገ መንግስት መሻሻል አንስቶ አንድ ሺ ጥያቄዎችን የሚጠይቀው አካል ለጥያቄዎቹ መመለስ ምን እየሰራህ ነው ቢሉት አብዛኛው መልስ ያለው አይመስለኝም። መጠየቅ ብቻውን መልስ አያስገኝም። በአገር ጉዳይ መልሱንም አብሮ መፈለግ የግድ ይላል። የሰላማዊ ትግሉም ዋነኛ አላማ ይሔው ነው። ከግጭት ትግል ነው እንጂ እፎይ ያልነው የሰላማዊ ትግሉ እኩ ገና ሊጀመር ነው። የትግሉ አመክንዮ ደግሞ ያልተመለሱ ወይም ሥርዓቱ ሊመልሳቸው የማይችላቸው ጥያቄዎች መኖራቸው ነው። ይህ ሁሉ ሚዲያ በነጻነት የሚወያየው፣ ይህ ሁሉ ፖለቲካኛ እንዳሻው የሚደራጀው እና የሚንቀሳቀሰው፣ ይህ ሁሉ ብሶት በመንግስት ሚዲያዎች ጭምር የሚቀርበው ለውጥ ቢኖርም አይደል። ለውጥ እማ አለ። የሚደነቀውን እናድንቅ፤  የሚነቀፈውን በምክንያት ከነመፍትሔ ሃሳቡ እንንቀፍ። ጨለምተኛ መሆን ግን አገርንም ያጨልማል።
ጊዜው የኛ ነው የምትሉም ሆነ ለውጥ ጭርሱኑ የለም የምትሉ ወገኖች ትንሽ ትንፋሻችውን ሰብሰብ አድርጋችው እና ጊዜ ወስዳችው ወደ ውስጥ ብታስቡ መልካም ነው።
Filed in: Amharic