>

አማራን ለጥቃት ከዳረጉ መሠረታዊ ችግሮች ጥቂቶቹ (ይነጋል በላቸው)

 

አማራን ለጥቃት ከዳረጉ መሠረታዊ ችግሮች ጥቂቶቹ

ይነጋል በላቸው

ይህችን አጭር ማስታወሻ ካነበቡ በኋላ ዘመድኩን በቀለ የጻፈውን > በትግራይ እና አማራ መሀከል ,,, ጠቃሚ መረጃ በአትኩሮት እንዲመለከቱ በትኅትና እጋብዛለሁ፡፡

ዓለምን ከጥንት ጀምሮ እየዘወራትና ወደሞቷ እያዳፋት ያለው የሤራ ፖለቲካና የመሠሪዎች ሸርና ተንኮል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በግሌ ይህን ዓይነቱን ሤረኝነት እጠላለሁ፡፡ በዚያም ምክንያት ወደ ፖለቲካው መድረክ መቅረብን አልወደውም፡፡ በዚህ መልክ የምንጨረጨረው ግን ያለ ሀገር መኖር የማይቻል በመሆኑና አንድ እንኳን አንባቢ ባገኝ የሚሰማኝን ለማስተላለፍ ነው – ቢያንስ እንደጣሊያኑ ሊቀ ጳጳስ ላለመሆን፤ ኢጣሊያ ሀገራችንን በወረረችበት ወቅት የነበሩት ሊቀ ጳጳስ በአንድ ታዛቢ እንደተተቹት “ዝም ማለት በሚገባቸው ወቅት ተናገሩ፤ መናገር በሚገባቸው ጊዜ ደግሞ ዝም አሉ”፡፡ ግፍና በደል በምድራችን ናኝቶ ሕዝብ እያለቀሰ ዝም ማለት ስህተት ነው፤ ሌላ ማድረግ ባይቻል ስለሚፈጸሙ ግፍና በደሎች መጮህ ይገባል፡፡ ሰሚ ካለ እሰዬው – ከሌለም ላድባሯ፡፡

በመሠረቱ የፖለቲካ ሰው ለመሆን መዋሸት ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲካ መስሎ ማደርን፣ መቅጠፍጠፍን፣ ሃቅን ሸምጥጦ መካድን፣ አሽከርነትን፣ ተለማማጭነትን፣ እግር እስኪተክሉ ድረስ አድር ባይነትንና መለሳለስን፣ እንዳስፈላጊነቱ ለሕዝብ የወገኑ መምሰልንና እንዲያ ሲል ደግሞ ሕዝብን መካድን ያካትታል፡፡ ይሁዳንም ጴጥሮስንም መሆን፣ እንደየሁኔታዎች አስገዳጅነት ሰይጣንንም እግዜርንም ሆነ መተወን፣ መስቀል ከሰላጤ ግራና ቀኝ መታጠቅ… ፖለቲካው አጥብቆ ይፈልገዋል፡፡ ይህን የፖለቲካ ተፈጥሮ በተለይ በአሁኑ ፍጥገታዊ ተለዋዋጭ የሀገራችን ሁኔታ በግልጽ እያየነው ነው – ለዚያውም በከፍተኛ አግራሞት፡፡ በፖለቲካ የ“ኩኑ ከማሆሙ” ሰው መሆን የግዴታ ያህል ነው፡፡ ፈረንጆች When in Rome, do as Romans do. ይላሉ፡፡ ብዙዎች ግን ይህ ዓይነቱ እስስታዊ ጠባይ አይሆንልም፡፡ ስለሆነም እውነቱን ተናግረን በመሸብን ማደርን፣ መቸገርና መራብ መጠማትም ካለብን ያን በፀጋ ተቀብለን በሰላም መኖርን እንመርጣለን፡፡ እንጂ ሀገር እንዲህ የሤረኞችና የሸፍጠኞች መጫወቻ ስትሆን ዕድሉን ቢያገኙ እናት ምድራቸውን ከአደጋ ሊታደጉ የሚችሉ የየዘርፉ ባለሙያዎች ጠፍተው አይደለም፡፡

“አማራው አሁን ለሚገኝበት አጣብቂኝ የበቃው ለምንድን ነው? ‹የተደገመበት› አፍዝ አደንግዝ ምን ይሆን? ከዚህ አዙሪትስ እንዴት ሊወጣ ይችላል?” ተብሎ ቢጠየቅ በበኩሌ የሚከተሉትን አስተያየቶች እሰነዝራለሁ፡፡ የምታውቁትን ለማስታወስ ያህል እንጂ አዲስ ግኝት አይደሉም፡፡
1. የአማራ ሥነ ልቦና በኢትዮጵያዊነት የተቃኘ እንጂ በዘርና በዘውገኝነት ዘመን አመጣሽ ወረርሽኞች የተበከለ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ላለፉት 30 እና 40 ዓመታት ይህን ሕዝብ ጎጠኛ ለማድረግ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ መንገድ ዘመቻ ቢካሄድበትም ከሞላ ጎደል ከሽፏል፡፡ ክሽፈቱ ግን ሁለት ተቃራኒ ጎኖች አሉት፡፡ አንደኛው አማራን ጎድቶታል፡፡ ሁለተኛው ጠቅሞታል፡፡ የጎዳው – በአንድነት ተሰባስቦ የዘር ግንዱን በጥቂቶች ሳይቀር ከመጠቃት ሊያድነው አለማድረጉ ነው፡፡ እንደዐይጥ በተገኘበት ከመጨፈጨፍና በመንግሥት በጀት ታግዞ በህክምና ሽፋን ከተካሄደ የዘር ማምከን ዘመቻ አላዳነውም፡፡ የጠቀመው -በመከራ ውስጥ ሆኖም ኢትዮጵያዊነቱን እንዳይክድ ማድረጉ ነው፡፡ ይህም ለመጪዋ ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ነው – አማራው ለኢትዮጵያ ዳግም ትንሣኤ እንደ እርሾ ሆኖ ሊያገለግል መቻሉ ፍንጩ እየታዬ ነው፡፡ እንደ ሌሎች ብዙ ዘውጎች በሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ አማራው አለመኮማተሩና ወደ እንስሳነት አለመውረዱ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የከፈለው መስዋዕትነት ነው – ይህም ያስመሰግነዋል፡፡
2. አማርኛ ቋንቋ የመላዋ ኢትዮጵያ የሥራና የመግባቢያ ቋንቋ መሆኑ አማራውን ክፉኛ ጎድቶታል፡፡ እርሱን መስለውና የተኩላ ልብስ ደርበው እርሱን “ሆነው” ላለፉት በርካታ ዓመታትና አሁንም ድረስ አማራው ሳይወክላቸው በጠላቶቹና በአጥፊዎቹ አማካይነት በኩራዝ እየተፈለጉ አማርኛንና የአማራን ባህልና ወግ የሚያውቁ መሠሪዎች ከየነገዱ ተመርጠው አማራውን እንዲያስተዳድሩ መደረጉ አማራን ክፉኛ ጎድቶታል፡፡ በመልክም፣ በቋንቋም፣ በባህልም፣ በአነጋገር ላሕይም አንተን የሚመስልን ግን አንተን ያልሆነንና አንተን ለመጉዳት በሥውር የተተከለብህን ጠላት መለየት ከባድ በመሆኑ ይህ አካሄድ አማራን እንደኤድስ ቫይረስ ክፉኛ አጥቅቶታል፡፡ አማራ ፈረንሣዊ ነው፤ ወያኔ-ትግሬ እንግሊዝ ነው፡፡ እንግሊዝና ፈረንሳይ ደግሞ ለዬቅል ናቸው፡፡ በስሙ ብአዴንን የመሰሉ የጠላት ድርጅቶች አሽከሮችና ጉዳይ አስፈጻሚዎች ተፈጥረው አማራን ያስጨፈጨፉት በዚህ የሤረኞች ደባ ነው፡፡ አማራ በልማት መራመዱ ይቅርበትና በድህነት እንኳን እንዳይኖር ከቀየውም ከሌሎች አካባቢዎችም እንዲሳደድ አድርገውታል – ያሳዝናል፡፡ አሁን ከእግዜሩ ከሚጠበቀው የድኅነት ዘመን ውጪ በሰዎች ተስፋ የማንጥልበት ግልጽ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ “ቂጣም ከሆነ ይጠፋል፤ ሽልም ከሆነ ይገፋል” እንዲሉ አሁን ላይ ያልተገለጠ የተሸፈነ እውነት የለም፡፡ ማወቅ ያለመፈለግ ካልሆነ በቀር፡፡ ይህ ደግሞ ዐውቆ የተኛን እንደመቀስቀስ ነው፡፡ አንድ ሰው ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ዐውቆ የተኛ የመምሰል መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡
3. ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት አማራው በትምህርት እንዲቀጭጭ መደረጉ ሌላው የአማራው ልማትና ዕድገት ፀር ነው፡፡ በትምህርት የወደቀ ማኅበረሰብ በሁሉም ይወድቃል፡፡ ከትምህርቱም ባለፈ በልማትም የተበደለ ነው፡፡ አማራ ሆነህ ራሱ ከትግራይ ውጪ ኢንዱስትሪና ፋብሪካ የማታቋቁምበት በምፀት እያሣቀህ የሚያስለቅስህ ዘመን ነበር፡፡ ደሴ አካባቢ ሊሠራ የነበረው ቴርሼሪ ሆስፒታል እንኳን – ለምሣሌ – ተሰነካክሎ የቀረው ሕወሓት “በአማራው መሬት ይህን መሰል ልማት የሚሠራው እኔ ሞቼ ስቀበር ብቻ ነው” በሚለው ፀረ-አማራነት አቋሙ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ማይምነትና በላዩ ላይ ሳይወድ በግዱ አማርኛን እየተናገሩ የተሾሙበት “ሌሎች” ጊንጦች የአማራን ጣዕረ-ሞት አባብሰውታል፡- ግን አይዟችሁ ይነሣል፤ ሲነሳ ደግሞ በልዩ ክብርና ሞገስ ነው – እመ አምላክን ነው የምላችሁ፡፡ የዚህ ትምክህቴ መነሻ ደግሞ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ ነው – አንተ ስትፈልግ “ይህ ሰው ዐብዷል” ወይም “በቁም እየቃዠ ነው” ልትል ትችላለህ – እኔ የማየውን ባለማየትህ ባዝንም ስለኔ ባለህ ማንኛውም ዓይነት ግምትና አስተያየት አልከፋም፡፡ “ምድር ክብ እንጂ ጠፍጣፋ አይደለችም” ብሎ የተናገረ እንደኔው “ዕብድ”ም በድንጋይ ተቀጥቅጦ ሞቷልና የኔው ቀላል ነው፡፡
4. አማራው ለራሱ ወገን አይሆንም፡፡ ምቀኝነት ይበዛዋል፡፡ በአማራው መሬት ለምሣሌ አማራ በሀብትም ሆነ በሥልጣን ከሚያድግ ይልቅ የሌላ ነገድ አባል ቢያድግ መሰናክሎች ይቀሉለታል፡፡ አወቅሁሽ ናቅሁሽ ይበዛል፡፡ መናናቅ ይበዛል፡፡ አንድ ሰው ሲያልፍለት “እሰይ! ወፌ ቆመች” ከማለትና ከመደገፍ ይልቅ በምቀኝነት በየደብተራውና ቃልቻው ቤት በመሄድ ያንን ሰው በድግምትና በአንደርብ ማሰነካከል ይበልጥ ይዘወተራል፡፡ ይሄ ችገር ቀላል አይደለም፡፡ የምለውን ለማረጋገጥ ጠበሎችንና የባህል መድኃኒት ቤቶችን ደጅ መጎብኘት ይቻላል፡፡ ይህም ከዕውቀት የመቆራረጥ ውጤት ነው፡፡ መስተካከል አለበት – ዛሬውኑ፡፡ መሸፋፈን ይቅር፡፡

ብዙ መናገር ይቻላል፡፡ ወደ መፍትሔው እንምጣ፡፡ አሁን ምን ይደረግ? ከችግሮቹ መፍትሔውን መገመት ቢቻልም ትንሽ ልበል፡፡ ሥራ ከፈታሁ አይቀር …

1. አማራ ዘረኛ አለመሆኑ ጥሩ ነው፤ በጊዜያዊ ወረርሽኝ የዘላለም ባሕርይን አለመለወጥ ደግ ነው፡፡ በዚሁ መቀጠሉም ለአማራ ሰፊ ሕዝብ ይጠቅመዋል፡፡ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ ራሱን ሊያውቅ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊነቱን ይዞ ወገኖቹን ከሚደርስባቸው እንግልትና ስቃይ ሊታደግ ካልቻለ ይህ በኢትዮጵያ መሬት በሕዝብ ብዛት ከአንደኛነት እስከ ሁለተኝነት ቦታ የሚወስድ ሕዝብ እንደቀላል ተበታትኖ መቅረቱ ነው፡፡ “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” እንዲሉ ለምሣሌ የኅልመኞቹ ሰሞነኛ ድርጊት መነሻው የአዴፓ ተብዬው መመረዝና ካብ አይገባ ድንጋይነት እንጂ አንድም አማራ ዝምቡን እሽ ሊለው የሚገባ ግፈኛ በተለይ በአሁኑ ወቅት ሊኖር ባልተገባ – “ፍየል ከመድረሷ..” ዓይነት ነው የሆነብኝ፤ እስካሁን ላምነው ያልቻልኩት መራር እውነት፡፡ እነደመቀ መኮንን ከመስመጥ ያዳኑት ዋናተኛ ከድንጋጤው አገግሞ ገና አንድ ዓመት እንኳን ሥልጣን ላይ ሳይቆይ ይህን መሳይ ቀሽም ድራማ እንዲመደረክ መፍቀዱ በአንድ በኩል ጥሩ ሆኖ በሌላ በኩል ግን የበሉበትን ወጪት መስበርን በግልጽ የሚጠቁም ወራዳ ተግባር ነው – ከኢትዮጵያዊ ጨዋት በእጅጉ ያፈነገጠ ነውረኝነት፡፡ “ጥሩ ነው” ያልኩት ቀንድ የሚነክስ ጅብ ሥጋ የማግኘት ዕድሉ ጠባብ መሆኑን ከመረዳት አኳያ እንጂ የ12 ሽህ አባወራ ቤት መፍረሱ አስደስቶኝ ሊሆን እንደማይችል ሊታወቅልኝ ይገባል፡፡ ስለሆነም ከሌሎች በመማር አማራ ራሱን ይፈልግ፡፡ እንደባህሉ “ሞረሽ! ሞረሽ!” ይባባል፡፡ በሞረሽ እየተጠራራ ለአማራ ባላቸው ጠላትነት ብቻ ለሥልት ሲሉ የተፋቀሩ የሚመስሉት ጠላቶቹ ከደገሱለት የዕልቂትና የውድመት ድግስ ራሱን ይታደግ፡፡ ለነገሩ “ስለት ድግሱን ደባ ራሱን” ይባላልና ሁሉም የየሥራውን አያጣም – በጊዜው፡፡ ያው መቼም በፋሲካ የገባችን ገረድ አኳኋን ስለምታውቁ … ምን ይባላል እንግዲህ፡፡
2. የአማራ ድርጅቶች በአማራ ድርጅትነት መታማታቸው ካልቀረ አማራ ባልሆኑ ሰዎች ድርጅቶቻቸውንና የቆሙለትን ዓላማ ማስመታት የለባቸውም፡፡ አማራው እየተጎዳ ያለው ከጅብ በማያስጥሉ የአህያ ባል አስተኔዎች በመሆኑ ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ አዴፓ መጋጃ እንደሆነ መቅረት የለበትም፡፡ ነፍስ ይወቅ፡፡ በወያኔና በሌሎችም የተዞረበትን አፍዝ አደንግዝ መበጣጠስ የሚችለው የተሰገሰጉበትን ጎታቾችና ሰላዮች መንጥሮ ሲያስወጣ ነው፡፡ በዚህ መልክ እንቅፋቶቹን ጠራርጎ ካላስወገደና ለአማራው በትክክል ካልቆመ ሕዝቡ እምነት እንዳጣበት ይቀጥላል፡፡ በአዴፓ ውስጥ የመሸጉ የማንኛውም (ሌላ) ድርጅት የውስጥ አርበኞችን ዛሬ ነገ ሳይል ፈልፍሎ ያውጣ፡፡ ቅቤ አንጓች አስመሳዮችን ይለይ፡፡ ደግሞም በስሞችና በፈጠራ ታሪኮች አይታለል – ወያኔ “ፍትዊ”ን “አገሩ አበረ” ማለት አያቅታትም – “ግደይ”ን “ዋቅቶላ” ብላ ጊምቢ እንደላከችው ሁሉ፡፡ አዴፓ ከሠርጎ ገቦች ጋር እየሠራ የአማራ ይቅርና የድርጅቱ ኅልውና ራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ ይህን ያህል ግዙፍ ሕዝብ የሚወክል ድርጅት አሽከርና ገረድ ሆኖ የሚገኘው በድርጅቱ መቦርቦርና በጠላት እንደራሴዎች ነውና ይህ ጉዳይ በይደር የሚቆይ አይደለም፡፡ ሸረኞችና ሆዳሞች በሃቀኛ የአማራ ልጆች መተካት አለባቸው፡፡ ለምሣሌ አለምነው መኮንን ያለበት ድርጅት የአማራ ድርጅት ነው ቢሉኝ መቀበል ይቸግረኛል፡፡ ባጭሩ አማራን አታዋርዱት፡፡ በቁመቱ ልክ የተሰፋችሁ ካባዎች ለመሆን ገና ብዙ ይቀራችኋል፡፡ ሥነ ልቦናችሁን ለመለወጥ በጸሎትም በንባብም መታገል ነው፡፡ እርግጥ ነው – ወያኔ አማራን ስትጫወትበት የምትሾማቸው ሰዎች በአብዛኛው ከዕውቀትና ከትምህርት የተቆራረጡትንና ዘገምተኝነት የሚያጠቃቸውን የአእምሮ ህመምተኞችን ሳይቀር ነው፡፡ ነቃ ያለ ከሆነማ ነገር ሊያመጡ ነዋ! በታሪክ የተመዘገበ ብዙ ጉድ አለ – ብዙዎች አወራርደው የማይጨርሱት፡፡
3. አዴፓ በማዕከላዊው መንግሥት ያለውን ውክልና ያረጋገግጥ፡፡ አሁን እየታዬ ያለው አማራን ከየቦታው የማፈናቀል ሂደት በአስቸኳይ እንዲቆም ማድረግ ካልተቻለ ነገ ለሚፈጠረው ሀገራዊ ትርምስ ዋናው ተጠያቂ ቀን ሰጠን የሚሉት ልበ-ቢሶች ብቻ ሳይሆኑ አማራን እወክላለሁ የሚለው ድርጅት ነው፡፡ ነገ የራሱን ሰዎችና የራሱን ታሪካዊ ፍርድ ይዞ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ይህች ሀገር ጠፍታ አትጠፋም፡፡ ልደትን የፈጠረ ሞትንም ፈጥሯልና አንዘናጋ፡፡

ከእምነት ኣባቴ አንድ ማለፊያ አነጋገርን ልዋስ – እውነት እውነት እላችኋለሁ – አማራን አሳምሬ አውቀዋለሁ – ጉራየን ልጨምርበትና ከመወለዴም በፊት አማራን ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ የያዘ ይዞት እንጂ እንኳን ለራሱ ለሰውም የሚተርፍ አቅም አለው፡፡ በላይ ዘለቀን አስብ፡፡ የትናንቱን የሸንኮራውን ጀግና አስማረን አስታውስ፡፡ (የጎጃሙን?)ስንዴውን አስታውስ፡፡ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴን አስታውስ፡፡ አንድ ጀግናው ብቻ ብዙ ታሪክ የሚሠራ ሕዝብ ነው፡፡ ያስቸገረው ከፍ ሲል የገለጥኩት የሠርጎ ገቦች ደንቃራና የጠላት ተንኮል ነው – ዓለማቀፉ የኢሉሚናቲዎች ድብቅ ሤራ ጭምር፡፡
በመሠረቱ ሁሉም ሕዝብ ጀግና ነው – ፀጉር አትሰንጥቁብኝ፡፡ የሕዝብ ፈሪ የለም፡፡ ይሁንና በመከራና በችግር መሀል ብዙ የተጓዘ፣ በገልቱና ዕንቅላፍም ልጆቹና በነባራዊ ሁኔታዎች ጥመት የተነሣ ብዙ ተስፋ የቆረጠ ሕዝብ ይበልጥ ጀግና ቢሆን ከሚያሳልፈው ተሞክሮ አንጻር አይፈረድበትም፡፡ እስራኤሎች እንዲህ እሳት የሆኑትና በ18 ሚሊዮን አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ዓለምን በሁሉም ረገድ የተቆጣጠሩት መገፋትና መበደል ኅብረታቸውን ስላጸናው ነው – ምን ሩቅ አስኬደኝ በቅርብ ትግራይ ክፍለ ሀገር እያለችኝ…፡፡ ስለዚህ ነገሩ የሎሚ ተራ ተራ ጉዳይ እንጂ የጀግንነት ብቻም አይደለም – ከመንፈስና ከውዝፍ ዕዳ ክፍያ ጋር የሚያያዙ ብዙ ምሥጢሮችም አሉበት፡፡ እናም ሤረኞችም ሆናችሁ ጊዜያችን ነው ባዮች እያስተዋላችሁ ብትጓዙ ትንቢትን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻልም የመስዋዕትነትን መጠን መቀነስ ይቻላልና በጊዜያዊ ድል እየፈነደቃችሁ መጠጊያና መሸሻ የሌለውን ሕዝብ ከማስለቀስ ተቆጠቡ፡፡ ለዚህ ያልተባረከ ወንበር የበቃችሁት በአማራውም መስዋዕትነት ነውና ብዙ አትነብርሩ፡፡ ወንድማዊ ምክሬ ነው – ነገ የለሁም፡፡ ዛሬ እያለሁ ስሙኝ፡፡
ዝም ብዬ እንደነበር ዝም እላለሁ፡፡ ዕድለኞች ከሆን … እንገናኝ ይሆናል፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ፤ ዕንቅልፋሙም ዕንቅልፉን ይድቃ፡፡ ሲሞት ይነቃና ይነሳል፡፡ ቻው፡፡
ለማንኛውም አስተያየት yinegal3@gmail.com

11 “በምትገቡበት ማንኛውም ከተማ ወይም መንደር መልእክቱን መስማት የሚገባውን ሰው ፈልጉ፤ እስክትወጡም ድረስ እዚያው ቆዩ። 12  ወደ ቤትም ስትገቡ ቤተሰቡን ሰላም በሉ።13  ቤቱ የሚገባው ሆኖ ከተገኘ ሰላማችሁ ይድረሰው፤ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስ። 14  የሚቀበላችሁ ወይም ቃላችሁን የሚሰማ ሰው ካጣችሁ ከዚያ ቤት ወይም ከተማ ስትወጡ፣ የእግራችሁን አቧራ አራግፉ።  15  እውነት እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ+ ይቀልላቸዋል። ማቴወስ 10፡ 11 – 15

Filed in: Amharic