>
5:13 pm - Wednesday April 19, 8389

አወዳደቅን የሚያከፉ የትዕቢትና የዕብሪት መልሶች (ነፃነት ዘለቀ)

አወዳደቅን የሚያከፉ የትዕቢትና የዕብሪት መልሶች

ነፃነት ዘለቀ

“He knows nothing; and he thinks he knows everything. That points clearly to a political career.”   George Bernard Shaw
“ምንም ነገር አያውቅም፤ ነገር ግን ሁሉንም ነገር የሚያውቅ ይመስለዋል፡፡ ያ ዓይነቱ ጠባይ ለፖለቲከኞች የሚስማማ የግትርነት ተፈጥሯዊ ዐመል ነው፡፡” ጆርጅ በርናንድ ሻው

Don’t confuse confidence with arrogance. Arrogance is being full of yourself, feeling you’re always right, and believing your accomplishments or abilities make you better than other people. People often believe arrogance is excessive confidence, but it’s really a lack of confidence. Arrogant people are insecure, and often repel others. Truly confident people feel good about themselves and attract others to them. Christie Hartman

በራስ መተማመንን በዕብሪትና ትምክህት ከመወጠር ጋር አናያይዘው፡፡ ዕብሪት ወይም ትምክህትና ትዕቢት ራስህን ብቻ አጉልቶ የሚያሳይ መስታወት ነው፤ በዚህ መስታወት ውስጥ አንተ ብቻ ዐዋቂ፣ አንተ ብቻ ሁልጊዜ ትክክል፣ ያንተ የሥራ ክንውኖችና ችሎታህ ሁሌም እንከን የለሽ ሆነው ሲታዩህ ሌሎች ግን ባንተ ዕይታ ምንጊዜም ስህተተኞች ናቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ዕብሪትን ከመጠን ያለፈ የራስ መተማመን እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡ ነገር ግን የዚያ ተቃራኒ ነው – ማለትም ዕብሪትን የሚወልደው በአንድ ሰው ውስጥ በራስ የመተማመን ስሜት ሲጠፋ ነው፡፡ ሰዎች ዕብሪተኛ ወይም ትዕቢተኛ ሆነው ሌሎችን ለስቃይ የሚዳርጉት በነሱ ውስጥ የደኅንነት ስሜት ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡ ፈሪዎች ስለሚሆኑ ዕብሪተኛነትን ለድክመታቸው መሸፈኛነት ይጠቀሙበታል፡፡ በራሳቸው የሚተማመኑ ሰዎች ግን ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ተገቢው ክብርና ፍቅር ይኖራቸዋል፡፡ በሰው ስቃይም ለመደሰት አይዳዳቸውም፡፡ ክርስቲ ሃትማን
(ተዛማጅ ትርጉም – ራሴው)

መጨረሻህ እንዲያምር ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ከሚከተሉት ባለጌዎችና ዕብሪተኞች ተማር፡፡ (ዝርዝር ኪስ ይቀዳል)፡፡ ከፈለግሁት እጀምራለሁ፡፡ በፈለግሁትም እጨርሳለሁ፡፡ እነዚህ “ደምቦች” እኔን ብቻ አይመለከቱምና ከኔ ጋር አታያይዙብኝ፡፡ የታየኝን ስናገር ጥቅሙ ለሁላችንም ይሆን ዘንድ ነው፡፡)
1. “እኔ አላስረገዝኳትም” – ሰሞኑን በለገጣፎ ላይ እየተካሄደ ባለው የዜጎችን ቤት የማፍረስ ኦህዲዳዊ ዘመቻ ላይ አንድ ካድሬ “ከወለደች ገና ሦስት ቀኗ ነው” ለተባለላት አንዲት ተበዳይ የሰጠው መልስ – የግፍ ግፍ ነው፤ በጌታዋ የተማመነች በግ ዓይነት ሆነብኝ፡፡ (Adding an insult to injury ይለዋል ፈረንጁ)
2. “ገና 12 ሽህ ቤቶችን እናፈርሳለን” – ይህንኑ የማፍረስ ተግባር በቅርብ አለቃነት የምትቆጣጠረው የሰንዳፋና አካባቢው ከንቲባ በጋዜጠኞች ስትጠየቅ በልበ-ድፍንነት የሰጠችው መልስ፡፡ (ፊቷ ላይ የደስታ የብርሃን ፀዳል እየተንቦገቦገ – እንዴቱን ያህል ተለያይተናል ለካንስ፡፡ እኛ የአንዲት ሀገር ዜጎች ነን ብለን ስንጃጃል የተደገሰልን ድግስ ደግሞ በአንድ ዩኒቨርስም ውስጥ አባል ነን የሚያስብል አይደለም፡፡ የታደሉ ሰዎች ለኢንተርጋላክቲክ ፌዴሬሽን (Intergalactic Federation) ምሥረታ ዕቅድ ያወጣሉ – እዚህ ግን ከእንስሳዊ አስተሳሰብ ያልወጡ ድኩማን ዜጎች ወንድምና ወንድሞች መሀል የቻይና ግምብ ይሠራሉ፤ የዘመናት ሀብት ጥሪትንም በዶዘር ያወድማሉ፡፡ ሲነጋ ለማፈር፡፡ ለነገሩ ሀፍረቱን የሸጠ አያፍርም፡፡)
3. “የተዘጋ ስልክ….” -ይህችው ከንቲባ የአማራ ቴሌቪዥን ስለቤቶች መፍረስ ቃለ መጠይቅ ሊያደርግላት ፈልጎ ቢደውልላት ስልኳን ባለማንሳትና ፈቃደኛ ባለመሆን ያሳየችው ትዕቢት (ባለመናገር መናገርም ይቻላልና)፡፡
4. “ኦቦ ለማን ማናገር አትችሉም” – ቤት የፈረሰባቸው አቤቱታ ሊያቀርቡ ሲሄዱ የተሰጣቸው የዕብሪት መልስ፡፡ (ዘመቻው ከላይ እስከታች የተቀናጀ ስለመሆኑ በግልጽ የሚያስረዳ ግጥምጥሞሽ፡፡)
5. “ በክልል አሠራር አያገባንም” – የጠ/ሚኒስትር አቢይ ቢሮ ቤት ለፈረሰባቸው አቤት ባዮች የሠጠው አጭርና ግልጽ መልስ፡፡ (ለሕዝብ የሚያለቅስ መሪ ማግኘት ማለት እንደዚህ ነው ታዲያ! ወይ ኢትዮጵያ!)
6. “ መጀመሪያውኑ ማን ጭንሽን ክፈች አለሽ?” – በየማዋለጃው ምጥ የያዛቸውን እህቶቻችንን የሚያዋርዱ አዋላጅ የህክምና ባለሙያዎች ዘወትር የሚናገሩት አጸያፊ ንግግር፡፡ ( አዲዮስ የሙያ ሥነ ምግባር!)
7. “አማራን መንገድ ላይ ቁጭ ብሎ ሲለምን ማየት እፈልጋለሁ፡፡” – ክቡር ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በየሕወሓት ስብሰባው እንደውዳሤ ማርያም ይደግመው፣ እንደጣዕመ ዜማም ያቀነቅነው የነበረው የማይሞት ንግግር፡፡ አልጠቀመውም – ቃሉ ሥጋ ሆኖ አፈራረሰና ብዙ አምባገነንነቶች በሚጀምሩበት እንጭጭ ዕድሜው ቀጨው፡፡)
8. “እሱን ‹እንትንህን› ጥረግበት” – “ህገ መንግሠቱ እኮ እንዲህ ይላል፤ ለምን አታከብሩትም?” ሲባሉ የወያኔ ባለሥልጣናትና ወታደራዊ መኮንኖች የሚሰጡት መልስ፡፡ (ኢትዮጵያ ያለ ህገ መንግሥትና ያለ መንግሥት የምትኖር ሀገር እንደሆነች የምንናገረው ከዚህ አኳያ ነው፡፡ ለ27 ዓመታት እንደፈለጋቸው ሲደፈጥጡት የኖሩትን ህገ መንግሥት፣ አንድን ሰው ለማሰር ፈልገው በአንድ ጀምበር ዐዋጅ አርቅቀው በዚያው ጀምበር የሚያጸድቁበትን ዕንቅልፋምና ማይም ዘረጦ የተመሰገበት ፓርላማ እንደሌለ የምንቆጥረውም ለዚህ ነው፡፡ አሁንም ያሉት የፓርላማ አባላት እንዳሉ አይቆጠሩም፡፡ ከግዑዝ ነገር የሚሻሉት በሰው አምሳል ስለተፈጠሩ ብቻ ነውና፡፡)
9. “አማራንና ኦርቶዶክስን አርቀን ቀብረናቸዋል፡፡” አቦይ ስብሃት ነጋ መቀሌ ከመመሸጉ በፊት አዲስ አበባ ላይ ሲደነፋበት የነበረ የዕድሜ ልክ መፈክሩ፡፡
10. “ አየኸው ይሄን ሁሉ የተከመረ አጥንት? የዘመዶችህ ነው፡፡ ትግራይን ነፃ ስናወጣ ማዳበሪያ የምናደርገው ነው፡፡” – አንዱ ጥጋበኛ የትግራይ ወታደራዊ መኮንን አንዱን ወልቃይቴ ወደ አንድ ሸለቆ ጫፍ ወስዶ ቀደም ሲል በወያኔ ያለቁትንና ዐፅማቸው የተሰባሰበበትን ቦታ እያሳየ “አንተንም እንደነሱ ገድለን እንጥልሃለን” በሚል እንዳስፈራሩት በኢሳት ከተናገረው የወሰድኩት፡፡ ያ ሰው በዕድል ከትግራይ ኦሽትዊዝ አምልጦ አሁን ውጪ ያለ ይመስለኛል፡፡)

በአጭሩ ጥጋበኞች የማይሉት የለም፡፡ የዓለምንና የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፍ ሁሉ በእጃቸው የጨበጡ ይመስላቸዋል፡፡ አንተ ግን ከፍ ሲል ከተጠቀሱትና ከቀጣዮቹም አባባሎች ራስህን ጠብቅ፡፡ ለአንተ የወደፊት ካርማም ሆነ ለትውልድህ የምታተርፈው ዕዳ እንዳይኖርህ ይህችን የሦስት ቀን የስደት ዓለም በብልኃት እለፋት፡፡

1. “እሱ ያንተ ጉዳይ ነው፡፡”
2. “በዚህ ጉዳይ አንተን ምን ጥልቅ ያደርግሃል?” (ጉዳዩ የሀገርና የጋራ ከሆነ ማለቴ ነው)
3. “እሱን ተወው!”
4. “ እና አሁን ምን ይጠበስልህ?”
5. “እኔን አያገባኝም፡፡”
6. “ምን ታመጣለህ?” “ምንም አያመጡም….”(ምን እንደሚያመጡማ አየን! የናቁት ወንድ እኮ ማስረገዙ ያለ ነው)
7. “እንትንህን አትመታበትም!” (መሣሪያ ለያዘ ሰው የሚባልና ጎጂ የሆነ የአፍ እላፊ – እንዲህ በማለታቸው ብዙዎች በአፋቸው ጠፍተዋል፤ ንዴትን ስለሚያግል መሣሪያን ማስተኮስ ቀርቶ በድንጋይ ያስወግራል)
8. “‹አማራ› ዱሮም ይሄው ነው!” (አትጠቅልል! ስትፈልግ “‹ዓለማየሁ› ዱሮም ይሄው ነው” በል፡፡ ሮጠህ በማትዘልቀው ማሣ ውስጥ ገብተህ አትዳክር፡፡ የአንድን ነገድ ጠባይ በአንድ ወይ በጥቂት ሰዎች ደግም ይሁን ክፉ ጠባይ ማወቅ አትችልም – ለትዝብት ይዳርግሃል እንጂ ይህ ዓይነቱ ነገር ጭራሽ አይጠቅምህም፡፡)
9. “ዝም በል፣ ዝም በል፡፡” “ባክህ አሳጥረው!” “አትጩህብኝ፡፡” “ዝጋ!” (ለአወንታዊ ፍጻሜ በጭራሽ አይጠቅሙም)
10. “ቱሪናፋ፣” “ቱልቱላ”፣ “ቀባጣሪ”፣ “አንተ ምን ታውቃለህ!” “ደደብ!” (ነገሮችን በሰላማዊ ቋንቋ መጨረስ ሲገባን እነዚህ አባባሎችና የቁጣ ንግግሮች ወደ ስድብና እልህ እንድንገባ ያደርጋሉ፡፡ ስድብና ዘለፋ የጫጨ አእምሮ መገለጫ ነውና ግንኙነታችን አስቀድሞ ከተያዘ የነገር አንከላፋና ቂም በቀል ነፃ መሆን አለበት፡፡ በንጹሕ ኅሊና መወያየት፣ በአግባቡ መደማመጥ፣ ስሜትን ላለመጉዳት መጠንቀቅ፣ መልካም ቃላትን መጠቀም…. ለግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ሕይወታችን መሠረት ነው፡፡ አለበለዚያ ከእንስሳት በምን ተለየን?)

በመጨረሻም ወደ ሀገራችን ሊገቡ የአየር ትኬት ቆርጠው የተሣፈሩትንና ሰንዳፋ አካባቢ የደረሱትን ሦርያንና ሶማሊያን አየር ላይ የሚቀልባቸው መለኮታዊ ሚሳይል በአፋጣኝ እንዲልክልን ለቸሩ ፈጣሪ አጥብቀን እንጸልይ፡፡

Filed in: Amharic