>

አጥፊዉ- ወታደር ነዉ : ግን-ግን ገበሬ ይካስ! ይላል ያገሬ ሰዉ! ኦዴፓም ይቀጣ!!! (ቹቹ አለባቸው)

አጥፊዉ- ወታደር ነዉ : ግን-ግን ገበሬ ይካስ! ይላል ያገሬ ሰዉ! ኦዴፓም ይቀጣ!!!
ቹቹ አለባቸው
ሰሞኑን ODP ህግን ለማስከበር በሚል ሰበብ : በአዲስ አበባ ዙሪያ የመኖሪያ ቤቶችን በስፋት ማፈራረሱን ተያይዞታል። ይሄን ድርጊት ተከትሎ : የተለያዩ አስተያየቶች እየተደመጡ ነዉ: ለምሳሌ ድርጊቱ የሆኑ ዘሮችን/ብሄሮች መሰረት ያደረገና እነሱን ታርጌት ያደረገ ነዉ: ይህ ካልሆነ ለምን ከአዲስ በራቁ የኦሮምያ ከተሞች ማፍረሱ አልተጀመረም? የክልሉ መንግስት ዝም ብሎ ኖሮ ዛሬ ለምን? ወዘተ የሚሉ  ናቸዉ።
የማፍረሱ ስራ በዋነኛነት ማንን እንዳጠቃ: በአጭር ጊዜ ስለምናዉቀዉ:በዚህ በኩል አቋም ለመያዝ  ብዙም አንቸኩልም። ድርጊቱ ራሱ  አፉን አዉጥቶ መናገሩ አይቀርም። ተጨባጭ መረጃ ከያዝን በሁዋላ አፋችንን ሞልተን እንናገራለን። ለጊዜዉ ግን ብዙዉ ሰዉ:  እየወሰድነዉ/ ለወደፊቱም የምንወስደዉ እርምጃ : ህግን ለማስከበር ሲባል እንጅ ሌላ አጀንዳ የለዉም የሚለዉን የኦዴፓ አባባል በጥርጣሬ ተመልክቶታል። ይሄን ጥርጣሬ የማጥራት ሀሊፊነት የኦዴፓ ነዉ።
በዚህ ድርጊት ተጎጅዎቹ እነማንም ይሁኑ  እነማን: ODP  አንድ መሰረታዊ ጥያቄ መመለስ አለበት: እንዲመልስም ግፊት ማድረግ ያለብን መስሎ ይሰማኛል። ይሄዉም እዉነትም እንደሚባለዉ የሚፈርሱት ቤቶች በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ ከሆኑ: ህገ ወጥ ግንባታዉ ሲገነባ: ኦህዴድና ካድሬወቹ የት ነበሩ? ዜጎች በዚህ ድርጊት ሲሳተፉ በወቅቱ  ለምን ማስቆም አልተፈለገም/  አልተቻለም? ዜጎች: በራሳቸዉ አካሄድ የተሳሳቱት ስህተት ካለ : እሱ እንዳለ ሆኖ: በክልሉ ገዥ ፓርቲና አመራሮቹ ቸልተኝነት የተነሳ:  እየደረሰባቸዉ ላለዉ በደል አዴፓና የክልሉ መንግስት ሀላፊነት እስከምን ድረስ ነዉ? በክልሉ አመራር ድክመት : በህዝቦቻችን ላይ ለተከሰተዉ በደልስ ማካካሻዉ ምንድን ነዉ?
እንግዲህ ኦዴፓ: “የህገ-ወጥ” ግንባታዉ ሂደትና የስህተቱ አካልም ቢሆን: ራሱን ሳይቀጣ: መንግስታዊ ሀይሉን ተጠቅሞ :ቤቶችን አፈራርሷል:ዜጎችም ሜዳ ላይ ተበትነዋል። አሁን ጥያቄዉ መፍትሄዉ ምን ይሁን የሚለዉ  ነዉ?
በእኔ እምነት : በዚህ የኦዴፓ  እርምጃ: ሁለት ነገሮች ተፋጠዋል። እነሱም ” የህግ የበላይነትን ማስከበር” የሚለዉ ነገርና: የዜጎች አዉላላ ሜዳ ላይ መበተንና ለማህበራዊ ቀዉስ መጋለጥ። እነዚህ ጉዳዮች እንዴት ይታረቁ?
እርምጃየ ” ህግን ለማስከበር” ነዉ የሚለዉን የኦዴፓን  አባባል እዉነትነት በሂደት የምናረጋግጠዉ ሆኖ: በህግ የበላይነተ መከበር ላይ ግን ሁላችንም መስማማት አለብን። ዜጎች ሀግን አክብረዉ መንቀሳቀስ አለባቸዉ: ይሄ ለጥያቄ አይቀርብም። ነገር ግን ደግሞ: ዜጎች አዉቀዉም ሆነ በመደናገር: እንዲሁም የኦዴፓን ዝምታ ፍቃድ እንደመስጠት ቆጥረዉ: እንዲሁም ያለባቸዉ የመኖሪያ ቤት ችግር  ግፊት አድርጎባቸዉ:  በግልጽ  ባልተፈቀደ  ቦታ ላይ ቤት ግንባታ ማካሄዳቸዉ ብቻ ለመከራ ሊዳርጋቸዉ አይገባም። ዜጎችን ለዚህ መሰሉ ችግር/ደረጃ ያበቃቸዉ ዋነኛዉ ምክንያት የኦዴፓ አመራር ችግር ነዉ። ስለሆነም ኦዴፓ ሀላፊነቱን ለዜጎች ብቻ ሳይሆን እሱም አብሮ ሀላፊነቱን  ይሸከም።
ለዚህ አማራ ክልል ጥሩ ተሞክሮ አለ። በአማራ ክልል በአንድ ወቅት( ዛሬም ይኖራል ) ተመሳሳይ ችግር ገጥሞን ነበር።  ህገ-ወጥ ግንባታዉን ዝም ብለን እንዳናየዉ : ችግር ነዉ: ያን ሁሉ በሽህወች የሚቆጠር ህዝብ ከቤቱ አፈናቅሎ አፍንጫህን ላስ ማለትም ችግር ነዉ። ስለሆነም መፍትሄ መፈለግ ነበረብን። ፈለግን።
የወሰድነዉ መፍትሄም: በህገ ወጥ መንገድ ቤት የገነቡ: ምንም ሌላ ቦታ የለሰላቸዉን በጥናት ለየን። ይሄ ጥናት ለክልሉ ካቢኔ ቀረበ። የክልሉ መንግስት ሁለት መሰረታዊ ዉሳኔወችን አስተላለፈ:
1. ህግ ይከበር: ይሄም ማለት ህገ ወጥ ግንባታ ይፍረስ አለ።
2. ምንም እንኳን ዜጎች በህገ ወጥ ግንባታ ተሳትፈዉ ቢገኙም: መንግስትም ቢሆን የችግሩ ባለቤት ነዉ : በወቅቱ መከላከል ባለመቻሉ። ስለሆነም አማራጭ ስለሌላቸዉ ብቻ በህገ ወጥ ግንባታ የተገኙ ዜጎች: የሊዝ አዋጁ  በሚፈቅደዉ መሰረት: በማህበር ተደራጅተዉ  መሬት በምደባ እንዲያገኙ ሲል ወሰነ። ለአንዳንድ አካባቢወች ደግሞ የመሬቱን ካሳ ጭምር ከፍሏል።
የአማራ ክልል ካቢኔ ይሄን ያደረገዉ:ዜጎች በህገ ወጥ ግንባታ ስላልተሳተፉ አልነበረም:ተሳትፈዋል። ነገር ግን ለዚህ ስህተት መንግስትም ድርሻ ሰለነበረዉ ነዉ። ይሄ በመሆኑ አስፈሪ የነበረዉ ሁከት በረደ :ዜጎችም ምንም እንኳ ቤታቸዉ ቢፈርስም:  ቢያንስ ግን መሬት በህጋዊ መንገድ  በማግኘታቸዉ ያን ያክል ቅሬታቸዉ ከባድ አልነበረም: እነሱም ስህተታቸዉን ያዉቁት ነበር። መንግስትም ስህተቱን ስላወቀ : ህግ ማስከበሩን ወደ ጎን ሳይል: ራሱን ጨምሮ ቀጣ።
ይሰማል ኦዴፓ!!! እዉነትም እርምጃህ ቅንነት ያለበት: ማንነትን ታርጌት ያላደሰገና “ህግን ለማስከበር” ብቻ ከሆነ: እስኪ ቢያንስ ወደሁዋላ መመለስ ባትችልም: ይችን የአማራ ክልል ተሞክሮ ተጠቀምባት።
Filed in: Amharic