>

የክቡራን ሠማዕታት ወገኖቻችንን ክብር ጠብቀን እናስጠብቅ፣ ከመደፈር እንከላከል!!!

የክቡራን ሠማዕታት ወገኖቻችንን ክብር ጠብቀን እናስጠብቅ፣ ከመደፈር እንከላከል!!!
አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
የዛሬ 82 ዓመት ሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭ ባደረጉት ግራዚያኒን በቦንብ የመግደል ሙከራ ምክንያት የፋሽስቱ (የጨፍጫፊው) ጦር መሪው ግራዚያኒ የአዲስ አበባ ሕዝብ ሕፃን ሽማግሌ ወንድ ሴት ሳይለይ ሁሉም የአዲስ አበባ ሕዝብ እንዲፈጅ እንዲጨፈጨፍ ትዕዛዝ በመስጠቱ የአዲስ አበባ ሕዝብ ሕፃን ሽማግሌ፣ ወንድ ሴት ሳይለይ በጅምላ ተጨፈጨፈ፣ ከነቤቱ እየተቃጠለ ተፈጀ፡፡ የሰው ልጅ ደም እንደጎርፍ ጎረፈ፣ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በሰው ደም ጨቀዩ፡፡ ፈጽሞ በእውን የተፈጸመ የማይመስል የማይታመን አረመኔያዊ ግፍ ተፈጸመ፣ ወደር የለሽ እልቂት ተከናወነ!!!
ይህ እልቂትና ሌላውም የፋሽስት ጥሊያን ጭፍጨፋ የተማረ የነቃ የሰው ኃይላችንንና አምራች የሰው ኃይላችንን ቅርጥፍ ሙልጭ አድርጎ የበላ፣ ወረታችንን እንዳለ ያወደመ ወረራ በመሆኑ በሀገራችን ላይ ያደረሰው ኪሳራና ጉዳት ይህ ነው ብሎ ለመግለጽ የሚቻል አይደለም፡፡ ሀገራችን እንዳታንሠራራና ሕዝባችን በድህነት እንዲማቅቅ ነው ያደረገን፡፡ ካሳ ሲታሰብ ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ወረራው የነቃ፣ የተማረ፣ አምራች የሰው ኃይሏን አረመኔያዊ በሆነ መንገድ በማጥፋት በሀገሪቱ ላይ ያደረሰው ኪሳራ ነው እንጅ የወደሙና የፈራረሱ ንብረቶች ብቻ አይደለም!!! ይሄ ቀልድ ነው!!! ካሳ ተብሎ በተከናወነው ሒደት የተፈጸመው ይሄ ነው፡፡
ውድ ኢትዮጵያውያን! ክልፍልፉና አቅለ ቀላሉ ዐቢይ አሕመድ ይሄንንና መሰል ሌላ በርካታ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ከፍተኛ ጥፋት፣ ውድመት፣ ኪሳራና ጉዳት ያደረሰውን የፋሽስት ጦር ባርካ እና “ይቅናቹህ!” ብላ የላከችብንን የካቶሊክ መሪ ፖፕ ፍራንሲስን ኢትዮጵያን ለማስጎብኘት ዝግጅት ላይ ነው፡፡
የካቶሊክ “ቤተክርስቲያን” ለፈጸመችው ኢክርስቲያናዊ ግፍ ይቅርታ እንድትጠይቅ በተደጋጋሚ ተጠይቃ በከፍተኛ ንቀት ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች፡፡ ይህ ክብረነክ የሆነ ጉዳይ ወይም ብሔራዊ ክብራችንን የተዳፈረና ያዋረደ ጉዳይ ባለበት ሁኔታ ፖፕ ፍራንሲስን ተቀብሎ ማስተናገድ ማለት ምን ዓይነት ትርጉም እንዳለው ለብሔራዊ ክብሩና ለሉዓላዊነቱ ትልቅ ግምት ለሚሰጠው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለመንገር መሞከር መቀለድ ነው የሚሆነው፡፡
ቫቲካን ተገቢ ይቅርታ ሳትጠይቅና ተገቢ ካሳ ሳትከፍል ፖፗን መቀበል የዛሬ 82 ዓመት ሕፃን ሽማግሌ፣ ሴት ወንድ ሳይለይ አረመኔያዊ በሆነ ሁኔታ በጅምላ የተጨፈጨፉ ወገኖቻችንንና ባጠቃላይ በወረራው ጥቅም ላይ እንዳይውል በዓለም በተከለከለው የመርዝ ጭስ የተፈጁ ወገኖቻችንን ደም ደመ ከልብ ማድረግ በመሆኑ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉብኝቱን በመቃወምና እንዳይከናወን በማድረግ ብሔራዊ ክብሩንና ሉዓላዊነቱን ያስጠብቅ፣ የወገኖቻችንን ክብር ያስከብር፣ የሞቱለትን የተቀደሰ ዓላማ እንዳይረክስ ይከላከል!!!
————

• የካቲት 12

• ሕይወቴ (ግለ ታሪክ፤በተመስገን ገብሬ)
• የካቲት 12…. የካፋው ሚካኤል—የሰማዕታት ቀን
ወንደሰን ውቤ
 
…ከአንድ ካሚዮን ላይ አንድ የኢጣሊያ ኦፊሰር ወረደና ቀበቶውን ጠበቅ አድርጎ እየቆለፈ መጣ።… ስድስት ሰዎች ባለውኃውን መትረየስ ከካሚዮኑ አውርደው መጡ። እነሊቀ ጠበብት እውነቱ ከቆሙበት ከአቃቂ ወንዝ ፊት ለፊታቸው ላይ ወስደው… ጠመዱት።…
እጅ ለእጅ በሠንሠለት የተያያዙትን እስረኞች የአቃቂ ወንዝ ገንገን ላይ አቆሟቸው።…ሊቀ ጠበብት ተራራው፣ ወንዙ እንደ እንዝርት የሚዞር መሰላቸው። በሩቅ ደግሞ የአቃቂ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ጣራውን ዐዩ።… ከመትረየሱ የርሳስ ዝናም ዘነመ።…
የጫማ ዱካ ወደ ወደቁበት እየቀረበ እንደመጣ ሊቀ ጠበብት እውነቱ ሰሙ። …  ቆስለው ከነበሩት ሰዎች «እባክህን ጨርሰን» ብለው መግለፅ በማይቻል የስቃይ ድምፅ ሜጀሩን ለመኑት። ሳቀና ተዋቸው። ሊቀ ጠበብት እውነቱም ሲስቅ ሰሙት። …
ሊቀ ጠበብት አንዱን  ዐይናቸውን እንደገና ከፈቱት። ጫማ ብቻ አዩ። ሰው ከዚያ ጫማ ጋር አለ እንደሆን ለማስተዋል አልተቃኑም። የሞትን ሕግ ጠበቁ። በልባቸው «ሚካኤል በዕለተ ቀንህ በክንፍህ ጋርደኝ» ብለው ጸለዩ።
ኳኳታ ሰሙ፤ ጫማው እየራቀ መሔዱን ዐዩ።…
ቀኑ ሔደና ሌሊቱ መጣ። ሌሊቱ ደግሞ ሊሔድና ቀን ሊመጣ ነው። እርሳቸው ግን በህልም ውስጥ ወይም  በእውን እንደሆኑ እርግጠኛ ሁነው የሚያውቁት አልነበራቸውም። አዲስ አበባ ኢጣሊያኖች በለኮሱት እሳት ተቃጥላ ስትጨስ ዐይተው ነበር።ሌሊት ደግሞ በቃጠሎዋ ነበልባል እንደ ኮከብ ስታበራ ዐይተው አንድ ጊዜ አለቀሱ። ግን እንባቸው በቁስላቸው ወረደና ፈጃቸው፤ ለበለባቸው። «አምላከ ቦታውንና ሕዝቡን ትቶ ሔዷል» አሉ።…
አዲስ አበባም ኢትዮጵያዊያንን ኢጣልያኖች የሚያርዱበት ቄራ ሁና ነበር። … አናቱን ተቀጥቅጦ፣ ጫንቃውን ተሰብሮ፣ በሳንጃ ተወግቶ፣ በአካፋና በዶማ ተፈልጦ ብዙ ሕዝብ ሲቃዥና ሲያቃትት ሰሙት፤ እርሳቸውም ሳያውቁት አቃሰቱ።…
*ሕይወቴ (ግለ ታሪክ፤በተመስገን ገብሬ)
ክ ብ ር  ለ ሰ ማ ዕ ታ ት!!!
Filed in: Amharic