>

"የተክደናል እና ተታለናል ረጅም ሙሾ!!!" (ደረጄ ገረፋ ቱሉ)


“የተክደናል እና ተታለናል ረጅም ሙሾ!!!”
ደረጄ ገረፋ ቱሉ
ቴውድሮስ ፀጋዬ በሪዮት የሬዲዮ ፕሮግራሙ ጠቅላይ ሚንስትሩን በተመለከተ  አዲስ መረጃ ይዘናል በሚል የተክደናል እና ተታለናል ረጅም ሙሾ አውርዷል።
ቴወድሮስ ረጅም መንገድ የሄደው ነገሩን በሙሉ ምስቅልቅሉን በማውጣት እና መረጃዎችን በማዳቀል ነው።
ተገኘ የተባለውን መረጃ ጠቅላይ ሚንስትሩ ያደረጉት ንግግር  በይፋ በሚንስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለፓርላማ በቀረበ የሸገር ረቂቅ አዋጅን በማስመልከት ለጫፌ ኦሮሚያ  አባላት በማብራሪያ መልክ ነው።
ቴወድሮስ ደግሞ ጠቅላዩ ተናገሩት ብሎ አላግባብ በሆነ መልኩ እየተቻቸ ያለው ሾልኮ ወጥቷል ተብሎ ኦህዲድ የኔ አይደለም ብሎ በካደው መረጃ ላይ ነው።ቴወድሮስ ጠቅላዩን በብዛት እየተቸ ያለው በሰነዘሩት ሃሳብ ሳይሆን ሾልኮ የወጣውን ሰነድ ደገፉ በማለት ነው።እኔንም ያበሳጨኝ ከሃሳቡ በላይ ሄዶ በልተጨበጠ መረጃ እዬየ ማለቱ ነው።
እዚህ ላይ ስለ ቴውድሮስ ሁለት ነገር መታዘብ ይቻላል።
1 ቴዎድሮስ ይህንን ግልፅ መረጃ እንኳን ሳያጣራ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በዚህን ያህል ድፍረት መተቸቱ ሀገሩቷ የእብድ ገላጋይ የበዛባት መሆኑን ነው።
2 ጠቅላዩ የተናገሩት ቋንቋን በተመለከተ በግልፅ በሚንስትሮች ምክር ቤት ላይ የተናገሩትን ሃሳብ ከመተቸት ሾልኮ ወጥቷል በተበለው እና ድርጅቱ የኔ አይደለም ከላው ሰነድ ጋር ጠቅላዩን አያይዞ ከህዝቡ ለመነጠል የሄደበት ርቀት ቴድ እቅዱ የህዝብ እና የኢትዮጵያ ፍቅር ሳይሆን ሌላ መሆኑን ነው።
ነገሩን ለማጠቃለል ጠቅላይ ሚንስትሩ ያደረጉት ንግግር በሚንስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ የወጣውን ሰነድ ለማብራራት ነው።ይህ ደግሞ የኢህአዲግ ስራ አስፈፃሚ ያፀደቀው እና በሚንስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ በመፅደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ሰነድ ነው።የዚህ ሰነድ አስኳሉ ነጥብ ደግሞ አፋን ኦሮሞ በሸገር ተጨማሪ የስራ ቋንቋ ይሆናል ብሎ ይደነግጋል።
ስለዚህ ጠቅላይ ሚንስትሩ ያራመዱት አቋም ድርጅታቸውም ሆነ እሳቸው በግልፅ የሚያምኑበትን ፤
የሚንስትሮች ምክር ቤት ያፀደቀውን ሃሳብ ነው።
ቴድ ደግሞ  ሙሾ እያወረደ ያለው ስለ ሾለከው ሰነድ ነው።አልተገናኝቶም።
ይህንን ሃሳብ ( ለሚንስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ የፀደቀውን ) በጥብቅ የኮነኑት እና የተቃወሙት በአብዛኛው የኦሮሞ ፖለቲከኞች መሆኑ ይታወቃል ።
በነገራችሁ ላይ እኔ ጠቅላይ ሚንስትሩ መቼም ቢሆን ከማይነቃነቅ አቋማቸው ውስጥ በዋናነት እኔ የታዘብኩት
1ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ያላቸው ፅኑ አቋም እና ለሀገራቸው  ያላቸው ፍቅር
 2 ለገዳ ስርዓት ያላቸው አድናቆት ሌላኛ ነው። የገዳ ስርዓት እሴቶች ለሀገር ግንባታ እና ለህዝቦች ወንደማማችነት በጣም ጠቃሚ  እንደሆነ ደጋግመው ስናገሩ ነበር።
እነዚህ ሁለቱን ደግሞ በቃል ብቻ ሳይሆን ሆነው እያሳዩን ነው።
3 ስለ አፋን ኦሮሞ እና ሌሎች ቋንቋዎች በሀገራችን በተጨማሪነት  በሁሉም አከባቢ በስራ ላይ መዋል ለሀገር አንድነት ያለው ፋይዳ ነው።እሄንንም ስራ ላይ ያውላሉ ብለን እየጠበቅን ነው።
ለደረጀ ገረፋ ቱሉ:-
የሙሾ ፖለቲካ ከዋኞች እናንት ዘውገኞችና ኩርማናውያን እንጂ እኛ የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞች አይደለንም
ከቴዎድሮስ ጸጋዬ
 ጉዳዩ ኦሮሚያ በአዲስአበባ ላይ አላት የሚባለውን ግራ ልዩ ጥቅም አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላላቸው አቋም የሰራነውን ዝግጅት በተመለከተ የሰነዘሩትን አስተያየት ይመለከታል፡፡
 በዚህ እርስ በእርሱ በሚጣረስና ምን ለማለት እንደፈለጉ እንኳ ለመረዳት ግራ በሚገባ አስተያየትዎ፣ በርዕዮት ሬድዮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስአበባን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ስላንጸባረቁት አቋም በግልጽ የሚነግረንን ይህንን Video ተመርኩዘን ባቀረብነው ዝግጅት ሙሾ እንዳወረድንና አለአግባብ ማስረጃውን እንደለጠጥን ገልጠዋል፡፡ ምናልባት ያልነውን ከመረዳትዎ አቅም በላይ ያደረገው መርዘሙ ከሆነ፣ በዝርዝር ያልነውን እስኪ በተቻለ መጠን አሳጥሬው እንዲገባዎ ልሞክር፡፡
 የሙሾ ፖለቲካ
1 ትላንት ያልነበረ የብሶት ታሪክ እየፈጠራችሁ፣ አንዱን ጨቋኝ የተቀረውን ተጨቋኝ በማድረግ አገር ልታፈርሱ የምትዳክሩ፣ በዘውግ ተቧድናችሁና እንባ እየሸጣችሁ ወደስልጣንና ጥቅም የምትመነዝሩት የሙሾ ፖለቲካ ከዋኞች እናንት ዘውገኞችና ኩርማናውያን እንጂ እኛ የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞች አይደለንም፡፡ እርስዎና መሰሎችዎ፣ የህዝብ ጠብና ልዩነት ህይወታችሁ፣ የሰለባነት እንጉርጉሮ ዜማችሁ፣ የ “ተበደልኩ” ልቅሶ ንግዳችሁ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊ ብሄረተኞችና የዜግነት ፖለቲካ ደጋፊዎችማ ወደኋላ የምናየው የአባቶቻችንን በደም ጭምር የተገለጸ አንድነትና ፍቅር፤ ዛሬ ላይ የምናየው የሀገራችን ተዋስኦ በሚነጣጥል የዘውግ ፖለቲካ አረም መወረሱን፤ ነገ ላይ የምናልመው ደግሞ ተስፋና ብርሀን ነው፡፡
 የሚኒስትሮች ምክርቤት
 2 በዚህ አስተያየትዎ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ለመደገፍ የቀድሞውን የሚኒስትሮች ምክርቤት ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ደረጀ፣ አንድ ዜና ልንገርዎት፤ ያ በህወሀት የተዋቀረው የሚኒስትሮች ምክርቤት እኮ በህዝብ ትግልና ተቃውሞ ፈረሰ? እርስዎና መሰል ዘውጌ ፖለቲከኞች ከህወሀት ጋር ያላችሁ ልዩነት የርዕዮት ሳይሆን የስልጣን መሆኑ አይጠፋንም፡፡ የህወሀት የሚኒስትሮች ምክርቤት የልዩ ጥቅምን ጉዳይ የሚወስን ረቂቅ አዋጅ ማጽደቁን በዋቢነት መጥቀስዎ ምክንያቱ ይህ መሆኑንም እናውቃለን፡፡ በህወሃትና ኦነግ አስተሳሰብ ዙርያ  የሰፈናችሁ ብሄር የምትከለሉ ዘውጌ ፖለቲከኞች ርዕዮትና አካሄድ ግን ለእኛ ለዜጎች አገር የሚያፈርስ፣ ባእድና አደገኛ የህልውናችን ስጋት ነው፡፡ በሁለት ቢላ መብላት ለእርስዎ እሴት ሲሆን ለእኛ ግን ኢሞራላዊና የምንጠየፈው ነው፡፡
 ስለሆነም፣ ጥያቄዎቻችን ግልጽ ናቸው፡፡ (ጠቅላይ ሚኒስትሩ እዚህ Washington DC መጥተው በጎበኙን ጊዜ አዲስአበባን አስመልክቶ ጥያቄ አቅርቤላቸው እንደነበርም ልብ ይሉአል፡፡)
 በዚህ ሰሞኑን በተለቀቀው Video ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስአበባን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ያራመዱት አቋም ከፓርቲያቸው የማይለይና አዲስአበባን ለአንድ ክልል ባለቤትነት አሳልፎ የሚሰጠውን ከፋፋይ  ረቂቅ አዋጅ የሚደግፍ እንደነበር ተመልክተናል፡፡ ይሄ የያኔው አቋማቸው ነው ከተባለ፤ አሁን ኢትዮጵያንና ታላቅነቷን ባገኙት መድረክ ሁሉ መስበክ ጀምረዋልና፣ እኛ ዜጎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለዚህ ልዩ ጥቅምና የአንድ ዘውግ ብቸኛ ባለቤትነት  ስለሚሉት ጉዳይ እርግጠኛ አቋማቸውን ማወቅ እንሻለንና ይንገሩን፡፡ ዝም ካሉ ግን በዝያው አቋማቸው መቀጠላቸውን ተገንዝበን፤ እኛም ዜጎች፣ እኛም የአገር ባለቤቶች ነንና፣ አዲስአበባም ሆነች አገራችን ኢትዮጵያ በማያሻማ ሁኔታ ዘውግንና ማናቸውንም ሰበቦች የአድልዎ ምክንያት የማታደርግ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትሆንበት እውነታ ተፈጥሮ እስክናይ ሰላማዊ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
 ማስታወሻ
 አቶ ደረጀ አተያይዎን አሁንም በአደባባይ ሊሟገቱለት የሚፈቅዱ ከሆነ ወደርዕዮት መድረክ መጥተው ሀሳብ እንድናፋጭ ተጋብዘዋል፡፡
 አዲስአበቤነት ይለምልም፤
 ኢትዮጵያ ምን ጊዜም በክብር ትኑር፡፡
Filed in: Amharic