>

እመኑኝ - ሕወሓት ኦህዴድን በነፍሰ ሥጋው እየተጫወተበት ነው (ነፃነት ዘለቀ)

እመኑኝ – ሕወሓት ኦህዴድን በነፍሰ ሥጋው እየተጫወተበት ነው

ነፃነት ዘለቀ 

ከሕወሓት የትሮይ ፈረሶች አንዱ የነበረው ኦህዴድ “አገር እየገዛሁ ነው፤ መንግሥት ነኝ” ብሎ ልቡ ውልቅ ብሏል፡፡ እየገዛን ያለው ግን አሁንምና ምናልባትም ላልተወሰነ ጊዜ ወደፊትም ሕወሓት ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም – ጥቂት ማስረጃዎችንም ከዚህ በታች ማቅረብ እችላለሁ፡፡

1. ትናንት መብራት ልከፍል ወደ አንዱ የክፍያ ጣቢያ ሄድኩ፡፡ መብራት እንደሚጨምር አውቃለሁ፡፡ ምክንያቱም ከሁለት ወራት በፊት ጀምሮ በሥነ ልቦና ሲያዘጋጁን ቆይተዋል – አንዳችም ርኅራኄ ለሌለው ቄራቸው ልክ እንደፊሪዳ ሲያዘጋጁን ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለ የለዬለት ዝርፊያ በመንግሥትነት ስም ይፈጸማል ብለን አልጠበቅንምና ጭማሬው ማጅራት መምታት እንጂ ለሀገርና ለወገን ዕድትና ብልፅና ታስቦ የተደረገ ጭማሪ እንዳሆነ በግሌ ተረዳሁ፡፡ ዱሮ በአማካይ ብር 400 በወር ስከፍል የነበረው የኮረንቲ ሂሳብ አሁን ብር 1150 ገደማ ሆኖ ጠበቀኝ፡፡ ማበድና ፀጉር መንጨት ዋጋ ቢኖራቸው ኖሮ ትናንት ከብሬ ነበር፡፡ ይህ ጭማሪ ሆን ተብሎ ሕዝቡ “ወያኔ ማረኝ!” እንዲል ተፈልጎ በወያኔዎች የተከናወነ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ጭማሪ ይደረግ – ያለ ነው፡፡ ግን ከ175% በላይ በአንድ ምሥኪን ደሞዝተኛ ላይ መጨመር የጤና አይደለም ብቻ ሣይሆን ወያኔዎች ከሥር ሆነው የዶ/ር አቢይን መንግሥት በግልጽ እየናዱት ስለመሆናቸው ዋና ማስረጃ ነው፡፡ ጭማሬው አሁን ለምን? ለምንስ ይህን ያህል? ምን ዓላማ አንግቧል? ደግሞም በዚያ መሥሪያ ቤት አንድ መጋዘን ጠባቂ የመጀመሪያ ዲግሪ ስላለው ብቻ 23 ሽህ ብር ገደማ እንደሚከፈለው እንሰማለን፡፡ የደሞዙ ነገር ከመንግሥት እስኬል ሲነጻጸር እጅግ ጣሪያ የነካ ነው፡፡ በመቶ ሽዎች የሚከፈላቸው ብዙ እንደሆኑ ይገራል፡፡ በሌላ በኩል አቶ አዝብጤና አቶ ዳባ በዘበኝነት የ987 ብር ደሞዝ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ይላሉ – ለመኖር ብለው አምፑል ሲሰርቁ ቢሊዮን የሰረቀው በሊሞዚን እየተንፈላሰሰ እነዚህ ምሥኪኖች በዚያች አምፑል ሳቢያ ዘብጥያ ይወርዳሉ፡፡ የዞረ ድምሩ ለሁላችንም እንዳይተርፍ ኧረ ይታሰብበት ግዴላችሁም? በምዝበራና በሙስና በተለወሰ የግዥ ሂደት የሚመዘበረው ገንዘብም የኛን ኪስ እያሟጠጠ መሆኑን እናውቃለን – ከነትራንስፖርት ወጪው ኢትዮጵያዊ የግል ድርጅት በሰማንያ ብር ላስገባ ያለውን አንድ ምርት በሙስናና በዘረኝነት ምክንያት ጥራቱ የተጓደለ ተመሳሳይ ምርት በ180 ብር ያውም ትራንስፖርትን ሳይጨምር በአድልዖ ከራሳቸው ወገን እንደሚገባ ሰምተናል፡፡ ኤልፓ እኮ አንዱ ደም መጣጭ ነው፡፡ (ወያኔዎች ነፍሳችሁ አይማር! ኢትዮጵያን እንዲህ መቅ አግብታችሁ ዘር ከወጣላችሁ ቱ! ከምላሴ ፀጉር ይነቀል፡፡…) ይህን ሁሉ የመብራት ኃይል ወጪ ምሥኪን ድሃ ሕዝብ ላይ መጫን ጡር አይሆንም ታዲያ? – ምክንያቱ ወጪ ነው ከተባለ፡፡ ሰው ባይፈራ ፈጣሪ አይፈራም? ለድንቁርናና ለደደብነት ድንበር ቢበጅላቸው አይሻልም? ግዴለም ሃምሣ ብር ይጨመር፤ መቶ ብር ይጨመር፤ በአንዴ 750 ብር ይጨመራል? የግፍ ግፍ ነው፡፡ ማንአለብኝነት የወለደው ጀብደኝነት ነው፡፡ እግዜር ይይላቸው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

2. የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም እየወረደ ባለበት ሁኔታ የኛ በየወሩ እየተሰቀለ መጥቶ አሁን ለምሣሌ ቤንዚን በሊትር 20 ብር ከ19 ሣንቲም ነው፡፡ በወያኔ ዘመን – ወጉ አይቀርም እንዳለፈ እንቁጠረውና – በወያኔ ዘመን ብር 17 ወይ 18 አካባቢ የነበረው ቤንዚን ምንም አዲስ ነገር ሳይፈጠር እንዲህ እንዲያሻቅብ የተደረገው ሩቅ የሚያዩ በሚመስሉት ግን እንደ አህያ ከሦስት ሜትር በላይ በማያዩት አዲሶቹ የመንግሥት መሪዎች ላይ የወያኔ ሥውር ታጋዮች ጢባጢቤ በሚጫወቱባቸው የውስጥ አርበኝነት ነው፡፡ ሀገር በሽግግር ላይ እያለች እንዲህ ያለ ጭማሪ ማድረግ ለአሻጥር (ሳቦታጅ) እንጂ ለጤና ሊሆን ከቶውንም አይችልም፡፡ ሕዝቡን ለማስቆጣትና በመንግሥት ላይ እንዲያምጽ ለማድረግ ሆን ተብሎ በወያኔ ቢሮክራቶች እየተከናወነ ያለው ይህ ዓይነቱ በሕዝብ ላይ የመከራ ዶፍ የማዝነብ ጉዳይ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

3. በነዳጅና በመብራት ላይ የሚደረገው ጭማሪ ብዙ የጎን ውጋቶች አሉት፡፡ ኑሮን ለማሟላት ሲባል የሚካሄድ ሌብነትንና ሙስናን ይበልጥ ያስፋፋል፡፡ የኑሮ ውድነትን ከአሁኑ በባሰ ሰማይ ይሰቅለዋል፡፡ ለደን መጨፍጨፍ ትልቅ አሉታዊ አስተዋፅዖ ያደርጋል፡፡ ትራንስፖርቱ፣ ህክምናው፣ የአገልግሎት ዋጋው፣ የቤት ኪራዩ፣ የወተት ኪራዩ፣ ምግቡና መጠጡ፣ ልብሱ፣ጫማው … ሁሉ ዋጋው ይበልጥ ይሰቀላል – ነጋዴዎቻችን ደግሞ “እንኳን ዘምቦብሽ…” ዓይነት ናቸው፡፡ የወያኔ ሥውር ተጋዳላዮች በየቢሮው እየሠሩት ያለው ተንኮል የመፈንቅለ መንግሥት ያህል ነው – ከዚያም በላይ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

4. በዋናነት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ የሚመራው የቢራ ጠመቃው ኢንዱስትሪ በዚሁ ድርጅት አማካይነት በሚቆሰቆስ የዋጋ ጭማሪ ቀደም ሲል በ8 እና በ9 ብር ይጠጣ የነበረው – በዚያ ዋጋ ራሱ ስንጥቅ ያተርፉበት ነበር – አንድ ጃምቦ ድራፍት አሁን በሸማቾች የቀበሌ መዝናኛዎች በአማካይ ብር 14 ሲሆን በሌሎች ብር 20 እና ከዚያም በላይ ደርሷል፡፡ ከሥራ መልስ በዚህ መጠጥ ራሳቸውን ይደብቁ የነበሩ ዜጎች አሁን ግራ ገብቷቸዋል፤ ዘመኑ “ያውጡብሽ እምቢ፣ ያግቡብሽ እምቢ” ዓይነት ሆኖባቸው ምርጫ በማጣታቸው ብቻ ወደ ሰማይ እያንጋጠጡ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ የ100 ሚሊዮን ዜጎች ሰፊ እሥር ቤት መሆኗ የሚነገረው እውነት ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

5. የሸቀጦችን ዋጋ ያየን እንደሆነ በነዚህ አሥር ወራት ውስጥ ብቻ በፊት ከነበራቸው ዋጋ ከዕጥፍ በማይተናነስ ጨምረዋል፡፡ ይህም የተደረገው ሆን ተብሎ የኦህዴድን መንግሥት በሕዝብ ዐመፅ ለመጣል ነው፡፡ እነ አቢይ ግን የነቁ አይመስልም ወይም በመሠሪ አማካሪዎች ተታለዋል፡፡ የምግብ ዘይት፣ ሣሙና፣ ጨው፣ ስኳር፣ … ዕጥረት ከመኖሩም በላይ ዋጋቸው የሚቀመስ አልሆነም፡፡ በየመደብሮች በአንጻራዊነት እንደአቅማችን መጠን እንገዛቸው የነበሩት የምሥርና የአተር ክክ አሁን አሁን ከሥጋ ሊበልጡ ምንም አልቀራቸው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

6. በየመሥሪያ ቤቱ የሚጠየቀው የአገልግሎትና የግብር ተመን ተራውን ዜጋ በተለይ መፈጠሩን እንዲጠላ እያደረገው ነው፡፡ የትም ቢሮ ግባ “ይችን እዚያች መስኮት ከፍለህ ና” ስትባልና ወደተባልከው መስኮት ሄደህ የክፍያውን መጠን ስትጠይቅ ጭንቅላትህን ያዞራል፡፡ ማንም ለማንም ደንታ የለውም፡፡ ሕዝብ ተንቋል፡፡ ቢሮክራሲው ማርጧል፡፡ ክፉኛ ባልጓል፡፡ ባንተ ግብር ደሞዝ እየተከፈለው አንተን ሊያገለግል በየቢሮው የተኮፈሰው ሁሉ አንተን የሚያይህ በዐይኑ ቂጥ ነው፡፡ ያንጓጥጥሃል፡፡ ያሾፍብሃል፡፡ ሲፈልግ ፋይልህን ያጠፋና ዞር በል ይልሃል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

7. የእህሉን ዋጋ ተመልከት፡፡ በወያኔ ጊዜ በ1500 ብር ገደማ ይሸጥ የነበረው ነጭ ጤፍ አሁን ሦስት ሽህ ብርን ሊነካ የቀረው ቁርጥራጭ ሣንቲም ብቻ ነው፡፡ ለጤፍ ብቻ ይህን ያህል ተከፍሎ ሌላው አስቤዛ እንዴትና በምን ሊሸፈን እንደሚችል አስቡት፡፡ በዚህ ላይ የ1000 ብርና ከዚያም በታች ደሞዝተኛ አለ፡፡ ትራንስፖርት፣ ልብስ፣ ቤት ኪራይ፣ ህክምና፣ ምግብ፣ … ወጪዎች በምን ይሸፈኑ? ብቻ የዚህች አገር ነገር ቁጭ ብላችሁ ስታስቡት በርግጥም ያሳብዳል፡፡ ደግነቱ ወያኔዎች አእምሯችንን አደንዝዘውት ስለሄዱ ማንም የማበድ ስሜት አይታይበትም፡፡ ዕብዶቹ “ጤነኞች ነን” የምንል እየሆን ነው፡፡ በአውሮፓ አንድ ሠራተኛ በአንድ ወር ደሞዙ አፍሪካን ጎብኝቶ መመለስ ሲችል በኢትዮጵያ እኔን መሰሉ ትልቅ ደሞዝ ተከፋይ ዕቁብ ካልገባ በስተቀር በአንድ ወር ደሞዙ ቆንጆ ሸሚዝ አይገዛም – እንኳንስ በሀገር ውስጥ ለአብነት መቀሌን – ጎብኝቶ ሊመለስ ይቅርና፡፡ የሀገራችን መንግሥት ቀልድ ማለቂያ የለውም፡፡ በዚህ ላይ አንድ መምህር ለምሣሌ ከሚሠራበት ት/ቤት በትርፍ ሰዓቱ ሌላ ቦታ ቢያስተምር ከመቶ ብር 30 ብር ይቆረጥበታል፤ – የግፍ ምድር – የደም መሬት – ኢትዮጵያ፡፡ የነተበ ሸሚዝ፣ የተሰነጣጠቀ ጫማ ካደረገ አንድ ምሥኪን መምህር ይህን ያህል ገንዘብ በግብር ስም የሚዘርፍ የገዛ መንግሥት ከኢትዮጵያ ውጪ በየትኛውም ዓለም የለም – ያደለው ስንትና ስንት ድጎማ ያደርጋል የኞች ደናቁርት ግን የተለፋበትን ገንዘብ በልበ ድፍንነት ይዘርፋሉ፡፡ አዙሮ የሚያስብ ከመካከላቸው አንድም የለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ ሥልቶች (tax evasion, tax avoidance, corruption, lying) የሚጠበቅባቸውን ግብርም ሆነ ቀረጥ ለመንግሥት የማያስገቡ ቁጥራቸው የትዬለሌ የሆነ ነጋዴዎችና የቢዝነስ ሰዎች አሉ – “ታላቅ ተቃርኖ”፡፡ ኢትዮጵያ – ላንዱ እናት ለሌላው እሳት፡፡ ግርምቲ አዲ!! ለማንኛውም እነዚህን “በፍትኅና በርተዕ የሚያስተዳድሩንን ምሁራንና የየዘር ባለሙያዎች” ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የሀገር መሪዎች ለአንድ ወር ያህል ብቻ በስማዊ ደሞዛቸው እንዲኖሩ ቢደረግ ችግራችን ይገባቸውና የደሞዝ መዋቅሮቻቸውን ሁሉ በአንዴ ለዋውጠው እኛም ወግ ይደርሰንና እንደ አውሮፓውያኑ መቀናጣቱ ቀርቶብን ቢያንስ በቅርባችን እንደሚገኙት የኬንያና ሰሜን ሶማሌ ሠራተኞች ያልፍልን ነበር፡፡ አሁን ግን እነሱን ምን ቸገራቸው? የኑሮ እሳቱ የት አግኝቶ ሲገርፋቸው? እንዴት እየተሰቃየን እንደምንኖር በምንና እንዴትስ አውቀውት? አሁን አሁን እኮ እኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት እኮ ራሱ እያሳፈረን ነው ወንድሞቼ – (ይሄ የመንጌ አማርኛ መቼ ይሆን የሚረሳኝ)፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

8. በቀበሌም ግባ፣ በከፍተኛም ግባ፣ በሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ሂድ ምንም የተለወጠ አሠራር አታይም፡፡ የነበረው እንዳለ ቀጥሏል፡፡ እነአቢይ የሚፍጨረጨሩት በባዶ መሬት ላይ ነው፡፡ “ኢኮኖሚውን የያዘ ፖለቲካውንም ይዘውራል” የሚባለው ነባር ብሂል ትክክል ነው፡፡ ወያኔዎች አልወደቁም፡፡ ሁሉንም ቢሮዎችና ጦሩን ጭምር ተቆጣጥረው ወጥረው ይዘውናል፡፡ የዚህ ሁሉ ዳፋ ግን የሚያመጣውን ማሰብ የሚፈልግ የለም፡፡ መንግሥቶቻችን በጉልበታቸው የመጡና በጉልበታቸውም የሚገዙ ይመስላቸዋል፡፡ የሀገራችንን ልዩ ጠባይ አልተረዱም፡፡ ደርግ ከአፄው፣ ወያኔ ከደርጉ፣ ኦህዴድም ከወያኔ ሊማሩ አልቻሉም፡፡ ሁሉም በጉልበቱ የሚገዛ ይመስለዋለፈ፤ ነገር ግን እነዚህን ጉዶች ሁሉ በየተራ የሚያመጣብን የኛው ክፉ ሥራ፣ የኛው ነውርና ኃጢኣት ነው – mia culpa mia culpa – mia grandissima culpa ይላሉ ላቲኖች በቅዳሴያቸው “የኔ ኃጢኣት፣ የኔ ኃጢኣት፣ የኔ ትልቅ ኃጢኣት” ለማለት፡፡ ሰባት ሰባራ ክላሽ የታጠቁ ጮርቃ ሕጻናት አፍሪካን የሚያስፈራ የደርግ (በአሁኑ ግንዛቤየ ደግሞ የኢትዮጵያ) ጦር እንደዋና ምክንያት ሆነው በረጂም ጊዜም ቢሆን እንዲፈረካከስ ሰበብ መሆን ከተዓምር የማይተናነስ የቅጣት ኹነት እንጂ እውነተኛና ተፈጥሯዊ አካሄድን የተከተለ እውነተኛ የድል ብሥራትን ሊፈጥር የሚችል አይደለም፡፡ መርምረው አንተም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

9. ሕዝቡ ከፍ ሲል በተጠቀሱትና በተጓዳኝ ችግሮች መሰቃየቱ ቀጥሏል፡፡ የሕዝቡ ብቸኛ መሣሪያ ደግሞ ዕንባው ነው፡፡ ዕንባችንን ቀን ከሌት ወደ ፈጣሪ እናፈሳለን፤ እናለቅሳለን፡፡ መልስም እንደምናገኝ እናምናለን፡፡ እምነታችን ከነዚህ የቀን ጅቦች ቀርቶ ከሌላም የውጭ ጠላት ሲያድነን ቆይቷል፡፡ ችግር ሲገጥመን ይህ የመጀመሪያችን አይደለም፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ወደፈጣሪ፣ ወደፍርድ አስታካካዩ የጌቶች ጌታ እናልቅስ፤ እንጸልይም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

10. በቅርቡ እግዚእብሔር ኢትዮጵያን በፀጋው ይጎበኛታል፡፡ በትግስት እንጠብቅ፡፡ እሾህ አሜከላዋንም ከላይዋ ላይ ያራግፍላታል፡፡ እኛ ፊታችንን ወደርሱ ካዞርንና ከልብ ከጸለይን በክፉ ሥራችን ምክንያት የተነጠቅናቸውን ፀጋዎች ይመልስልናል፡፡ አለመከባበር፣ መመቀኛኘት፣ አለመተዛዘን፣ በዘር ተቧድኖ በነገር ጦርና በመሣሪያ አፈሙዝ መጠዛጠዝ፣ እኛነትን ክዶ በኔነት ሰይጣናዊ መንፈስ በመማረክ ለግል ብልጽግና መራኮት፣ በቋንቋና በወንዝ በሸንተረር እየተከፋፈሉ ጊዜን፣ ገንዘብንና ጉልበትን አላግባብ ማባከን… በቅርብ ወደታሪክ መዝገብ ይገባሉ፡፡ በአጭሩ ሰው እንሆናለን – ይታየኛል፡፡ አሁን ሰው ነን ማለት አንችልም፡፡ አሁን ሀገር አለን ማለት አንችልም፡፡ አሁን መንግሥት አለን ማለት ይቸግረናል፡፡ አሁን … የብዙ ጉድለቶች ባለቤቶችና በነዚያም ጉድለቶች ሳቢያ ክፉኛ የምንሰቃይ ሕዝብና ሀገር ነን፡፡ ባልጨርስም ጨረስኩ፡፡

በቃኝ!!!!!

ነፃነት ዘለቀ (netsanetz28@gmail.com)

Filed in: Amharic