>
5:13 pm - Friday April 19, 1213

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት አባል አና ጎሜዝ አዲስ አበባ ገቡ!!! (ኢዜአ)


የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት አባል አና ጎሜዝ አዲስ አበባ ገቡ!!!
ኢዜአ
አዲስ አበባ የካቲት 9/2011አና ማሪያ ማርቲንስ ጎሜዝ በአጭሩ ‘አና ገሜዝ’ በመባል የሚታወቁት የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት አባልና የፖርቱጋል ሶሻሊስት ፓርቲ አባል ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል።
አና ጎሜዝ ቦሌ አለም ዓቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርሱ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ ሌሎች ወዳጆቻቸውና አድናቂዎቻቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በኢትዮጵያ በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ለመታዘብ የአውሮፓ ኅብረት ልዑክን የመሩት አና ጎሜዝ ምርጫውን ተከትሎ በተፈጠረው ውዝግብ ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲ እንዲመጣ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
አና ጎሜዝ በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ፤ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የአገራዊ ለውጥ አድንቀዋል።
ከኢትዮጵያ መንግስት የስራ ሃላፊዎችና ከሲቪክ ማህበራት ጋር ተገናኝተው የመምከር ሃሳብ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር የመጣውን ለውጥ ያደነቁት አና ጎሜዝ በፖለቲካና በተለያዩ ምክንያቶች የታሰሩ ሰዎች ነጻ በመውጣታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ጠቁመዋል።
ከአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት አባልነታቸው በዚህ ወር መጨረሻ እንደሚለቁ ያስታወቁት አና ጎሜዝ በቀጣይ በሚኖራቸው ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ያላቸውን ልምድ ለማካፈል ፍልጎት እንዳላቸውም ገልፀዋል።
አና ጎሜዝ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የሚወያዩ ሲሆን ዛሬ በሚሊንየም አዳራሽ በሚካሄደው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን (ኢሳት) ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ለህዝብ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፖርቹጋላዊቷ ፖለቲከኛ አና ጎሜዝ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ህብረት አባል በመሆን የተመረጡት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2004 ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የፓርላማው አባል በመሆን እየሰሩ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት አና ጎሜዝ በሲንትራ የከተማ ምክር ቤት አባልም ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
አና ጎሜዝ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ1980 ጀምሮ የፖርቱጋል ዲፕሎማት በመሆን በተለያዩ አገሮች ያገለገሉ ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፖርቱጋል ልዑክ በኒው ዮርክና በጄኔቫ፣ በቶክዮ በለንደን ኤምባሲዎች ሰርተዋል።
በጃካርታ ደግሞ ዋና መልዕክተኛ አምባሳደር በመሆን ለአገራቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጠናከር የሰሩ ናቸው።
በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባልነታቸው ዘመን በስደት፣ በሰብዓዊ መብት፣ በደህንነትና መከላከያ፣ በአለም ዓቀፍ ግንኙነት፣ በስርዓተ ጾታና በሌሎች የልማት ዘርፎች ዙሪያ በርካታ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ይነገርላቸዋል።
Filed in: Amharic