>

ተዋጽዖ!! (ዳንኤል ክብረት)


ተዋጽዖ!!!
ሙሃዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት
 ለብሔር ብሔረሰቦች በዓል የመጡ ሰዎች በጀልባ እንዲንሸራሸሩ ተባለ፡፡ ከየብሔረሰቡ ሰው ወደ ጀልባዋ ገባ፡፡ ጀልባዋም ቀስ እያለች መንሳፈፍ ጀመረች፡፡ ተንሸራሻሪዎቹም ብሔር ብሔረሰቦችን እያመሰገኑ በስማቸው መንሸራሸር ቀጠሉ፡፡ የሽርሽሩ ዳርቻ ደርሰው ሲመለሱ ግን ከባድ ማዕበል ተነሣ፡፡ ጀልባዋም የግልንቢጥ ትደንስ ጀመር፡፡ ግማሹ ይጸልያል፣ ግማሹ ይሳላል፣ ግማሹ ይዘላል፤ ሌላው ጥግ ይፈልጋል..
የጀልባዋ ነጅ ያሰማውን የድረሱልኝ ጩኸት ሰምተው የመጡት የከተማው ሰዎች ሐይቁ ዳር ቆመው ይጨቃጨቃሉ፡፡
‹እንዴት አድገን እንርዳቸው?› አለ አንዱ፡፡
‹ሁሉንም ብሔር በሚያመጣጥን መንገድ ነው መርዳት ያለብን› አለ ሌላው
‹ሞት ደግሞ ምን ተዋጽዖ አለው› አሉ አንድ አዛውንት
‹ኖ ኖ ስናወጣቸው ከአንድ ብሔረሰብ እንዳይበዛ፤ ከሁሉም እኩል እኩል ሰው ነው ማዳን ያለብን›
‹ቆይ ከየብሔረሰቡ ስንት ስንት ሰው ነው የገባው›
‹አናውቅም፤ ብቻ አወጣጣችን ፍታዊ መሆን አለበት›
‹አሁን እኛ ቶሎ ደረስን ተረባርበን ማውጣት እንጂ፣ ከየብሔረሰቡ ሁለት ሁለት ሰው ኑ፤ ልንል ነው? አሁን በነፍስ የተያዘ ሰው መዳኑን እንጂ ብሔረሰቡን ያስብልሃል? ለመሆኑ ሲሰጥሙ ከየብሔረሰቡ ተመጣጥነው ነው የሚሰጥሙት?› አሉ አዛውንቱ ገርሟቸው፡፡
‹አንድ ማስተካከያ አለ› አለ አንድ ጎልማሳ፡፡ ሁሉም ዞር ብለው አዩት፡፡
‹የእንትን ብሔረሰብ እኛን አያገባንም፡፡ ሲጨቁን፣ ሲመዘብር፣ ሲዘርፍ የኖረ ነው፤ ጦሱ ያውጣው፤ እነርሱን ማውጣት የለብንም›
‹እንደዚያማ ከሆነ፣ ቅድሚያ ማግኘት ያለበት የኛ ብሔረሰብ ነው፡፡ ታግለን፣ ለፍተን፣ ሞተን እንዲህ በጀልባ እንዲዝናኑ ያደረግናቸውኮ እኛ ነን›
‹እሱን እንኳን ተዉት፤ እኛ በወርዳችንና በቁመናችን ልክ ነው ማግኘት ያለብን፡፡ ከሞት ከሚተርፉት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የእኛ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡›
የሚሰጥሙትን ሰዎች ለማዳን የመጡት ሰዎች ይጨቃጨቃሉ፡፡
የጀልባዋ ሩብ ወደ ሐይቁ ገባ፡፡
‹ጎበዝ፤ እናንተ ስትጨቃጨቁ ሰዎቹኮ እየሰመጡ ነው፡፡ ለምን ተረባርበን ሁሉንም አናወጣቸውም› አለ አንድ ልጅ እግር፡፡
‹የብሔር ፖለቲካ ያልገባህ ጩጬ ነህ› አለው ጎልማሳው፡፡
‹መጀመሪያኮ ሰው ሲኖር ነው ብሔር የሚኖረው፤ ሰው እየሞተ ብሔር ምንድን ነው› አለው ልጅ እግሩ፡፡
‹አልገባህም ያልኩህኮ ይኼንን ነው፡፡ ሰው ይሞታል፤ ብሔር ይቀጥላል›
‹ቆይ አሁን እዚያ ጀልባ ውስጥ እየሰመጡ ያሉት ብሔሮች ናቸው ወይስ ሰዎች?›
‹ብሔር ብሔረሰቦችን ወክለው ነው የሚሰምጡት› አለ ጎልማሳው፡፡
‹የትኛው የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት ሄደው ነው ብሔረሰቦች እነዚህን ሰዎች የወከሉት›
‹እይውልህ ጅሉ፤ ሰዎቹ እስከሚሞቱ ብሔር ይወክላሉ፤ ሲሞቱ ግን – ሟቾቹ የትኛውንም ብሔር አይወክሉም- የሚል መግለጫ ይወጣል› አለው ጎልማሳው፡፡
‹ኧረ ሰዎቹ ከመስጠማቸው በፊት እናውጣቸው› አለ ልጅ እግሩ በጩኸት፡፡
‹አውጭዎቹም ብንሆን ከሁሉም ብሔረሰቦች የተውጣጣን መሆን አለብን› አለና ጎልማሳው ሰዎችን መምረጥ ጀመረ፡፡ አንድ ዐሥር ብሔረሰቦችን ‹የሚወክሉ› አውጭዎች አልተገኙም፡፡
‹ወደየ ብሔረሰቡ እንሂድና ከየብሔረሰቡ ሰው መርጠን እናምጣ› አለ ጎልማሳው፡፡
የጀልባዋ ግማሽ ሰመጠ፡፡
‹ሰዎቹኮ እየሰመጡ እንጂ እየተዝናኑ አይደሉም፤ ለምን እኛ ገብተን ሁሉን አናወጣቸውም› አለ ልጅ እግሩ፡፡
‹ኖ ኖ ይሄማ እኔ ዐውቅልሃለሁ ማለት ነው፡፡ ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን የማዳን መብት አላቸው፡፡ ማንም እኔ ዐውቅላችኋለሁ ብሎ የእነርሱን ሟች ሊያተርፍላቸው አይገባም፡፡›
‹ልክ ነው› አለ አንድ ፈርጣማ ጡንቻ ያለው ወጣት፡፡ ‹ሌላ ብሔረሰብ አተርፋለሁ ብለን ገብተን ሳይተርፍ ቢቀር በኋላ የብሔር ግጭት ያስነሣል፡፡ ማን ግቡ አላችሁ? ማን ፈቀደላችሁ? ማን ወከላችሁ? ስንት ጥያቄ ይነሣል›
‹አንዴ ጠጋ ጠጋ በሉልኝ፡ ለፌስ ቡክ የሚሆን ፎቶ ላንሳ› አለና አንዱ ገለል አደረጋቸው፡፡ ራቅ ብለው ጭቅጭቁን ቀጠሉ፡፡ ልጁ ጀልባዋ ስትሰምጥ የሚያሳይ ፎቶ አንሥቶ በፌስ ቡክ ለቀቀ፡፡ በአንድ ጊዜ ሺ ላይክ አገኘ፡፡
‹እኔ ሄድኩ› አለ አንድ ልጅ፡፡ ‹ዝም ብዬ ነው የደከምኩት፡፡ የኛ ብሔረሰብ ተወካይ ከሚሰምጡት መካከል የለም፡፡›
‹ሌሎቹን ለምን አታግዝም› አለው ልጅ እግሩ፡፡
‹የራስን ዕድል በራስ መወሰን ምን እንደሆነ አልገባህም›
አንድ ሁለት ሐሳቡን የተቀበሉ ወጣቶችን ይዞ ሄደ፡፡
‹እናንተ ስለ ብሔር ብቻ ነው የምታስቡት፡፡ የሴቶችስ ጉዳይ? የሃይማኖትስ ጉዳይ?› አለና አንዱ አፋጠጣቸው፡፡
‹ልክ ነው፤ የተረሳውን ነው ያስታወስከን፡፡ ጀልባዋ ውስጥ ልዩ ልዩ እምነቶችን የሚወክሉ ሰዎች አሉ፡፡ የሴቶችም ተዋጽዖ ሊታሰብ ይገባል›
‹አሁን ችግር ሊገጥመን ነው፡፡ ሴቶች በአካባቢያችን የሉም፡፡ ሴቶቹን ማን ሊያወጣቸው ነው?›
‹ለምን እኛ አናወጣቸውም፤ የሴቶች ጉዳይ የሴቶች ብቻ ነው እንዴ› አለ ያ ልጅ እግር
‹አንተ ልጅ ቀደም ቀደም አትበል? የሴቶችን ጉዳይ ወንዶች የሚወስኑበት ዘመን አልፏል፡፡ ሴቶች የራሳቸውን ጉዳይ እንዲወስኑ መፍቀድ አለብን፡፡
‹ቀላል ነው፡፡ ለሴቶች ሊግ ወይም ለሴቶች ማኅበር ወይም ለሴቶች ሚኒስቴር ለምን አናሳውቅም፡፡ ሴቶች እየሰመጡ ነውና አስፈላጊ ሁሉ ይደረግ ለምን አንልም›
አጨበጨቡ፡፡
‹እሺ ጀልባዋ ውስጥ ምን ምን ዓይነት እምነቶች አሉ› አለ ጎልማሳው
‹እምነቶች የሉም፤ አማኞች ናቸው ያሉት› አለ ልጅ እግሩ፡፡
‹የሚወክሉትን እምነት ነው የፈለግነው›
‹ማን ወከላቸው፤ ለራሳቸው አመኑ እንጂ›
‹ነገርንህኮ፤ ችግር እስኪፈጠር ይወክላሉ፡፡ ችግር ከተፈጠረ አይወክሉም›
‹መረጃው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው ያለው›
‹ጥሩ አንድ ኮሚቴ ይቋቋምና መረጃውን ይዞ ይምጣ› አለ ጎልማሳው፡፡ ብዙዎቹ ተስማምተው ኮሚቴ አዋቅረው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ላኩ፡፡
ሌሎች ደግሞ ስለ ሴቶች ጉዳይ ሊያስረዱ ሄዱ፡፡
ሌሎቹ ሰው ያልተገኘላቸው ብሔረሰቦች፣ ከመካከላቸው መርጠው ነፍስ አድን እንዲልኩ ለመንገር ሄዱ፡፡
ሌሎቹ ደግሞ የየሃይማኖቱ መሪዎች ሰው እንዲወክሉ ለመንገር ተሠማሩ፡፡
የቀሩት ሰዎች ዋኝተው በመሄድ የሚሰምጡትን እንዳያወጡ በፖሊስ ወደቡ ይጠበቅ ጀመር፡፡ በአወጣጣቸው ላይ አድልኦ ከተፈጸም የብሔር ግጭት እንዳይነሣ ተፈርቷል፡፡
በዚህ መካከል ጀልባዋ ሙሉ በሙሉ ሰመጠች
Filed in: Amharic