ጥቂት ስለ ሕዝብ እና ቤት ቆጠራዉ !!!
ውብሸት ሙላት
*አንድ*
በሕዝብና ቤት ቆጠራ ወቅት የብሔሮችን ዝርዝር ለሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን አስቀድሞ የሚልከዉ የፌደሬሽን ምክር ቤት ነዉ፡፡ በ1987 ቱ ቆጠራ 84 ብሔሮች ተቆጥረዋል፡፡ በ1999ኙ ደግሞ 85 ተቆጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በ1987ቱ ከተቆጠሩት 5 ቀርተዉ ሌሎች 6 ተጨምረዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መረጃ ግጭት ቀስቃሽ መሁኑ አንድና ሁለት የለዉም፡፡ በተጨማሪም የፌዴሽን ምክር ቤት ለሕዝብና ቤት ቆጠራ ሲያሻዉ 84 በሌላ ጊዜ ቀንሶ እና ጨምሮ 85 ቢያደርግም በምክር ቤት ዉክልና (መቀመጫ) ያላቸዉ ግን በ1987 ዓ.ም. ሥራዉን በጀመረዉ ምክር ቤት 67 ሲሆኑ አሁን 77 ደርሰዋል፡፡
ለቆጠራ ሌላ መረጃ፣ለመቀመጫ ሌላ መሥፈርት ማቅረብ ኢፈትሐዊ፣የተዘበራረቀ፣ ግጭት ቀስቃሽ ስለሆነ የአሁኑ ቆጠራም ላይ እንዲህ ዓይነቱ የተዘበራረቀ መረጃ ለሕዝብና ቤት ቆጠራ እንዳይሰጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ቢቻል አስቀድሞ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ቢያንስ ያለፉትን የ1987ቱና የ1999ኙን  አጢኖ የሁለቱንም  ዝርዝር ከግምት በማስገባት የብሔሮችን ዝርዝር ማዘጋጀት አሰፈላጊ ነዉ፡፡
ሁለት:-
የሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን በቋሚነት እንዲኖር ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 ላይ ተደንግጓል፡፡ ሕዝብን የመቁጠር ሥልጣኑም የኮሚሽኑ ነው፡፡ አስፈላጊዉ የሆኑ ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞችም እንደሚኖሩት እንዲሁ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ቋንቋ አስቀምጦታል፡፡ በጀቱንም በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያስጸድቃል፡፡ በየጊዜዉም ስለ አፈጻጸሙ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀርባል፡፡
 የኮሚሽኑን አባላትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በዚሁ ምክር ቤት ይሾማሉ፡፡ ይህንን የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ተግባራዊ በማድረግ በ1985 የተቋቋመዉን ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጁን በ1989 ተስተካከለ፡፡ ድጋሜ በ1991 ተሻሻለ፡፡
ይሁን እንጂ፣በ1997 ዓ.ም. በሚያዚያ ወር የማእከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲን ማቋቋሚያ አዋጅ (ቁጥር 442/1997) በማሻሻል የሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽኑን ብዙዎቹን ሥልጣንና ተግባር ወደ ኤጀንሲዉ እንዲተላለፍ ተደረገ፡፡
በዚሁ  በ1997 ዓመት ግንቦት 18 ቀን አዋጅ ቁጥር 180/1991ን በመሻር የኮሚሽኑን ኃላፊነትም ተግባር መቀናነሱን እዉቅና በመስጠት ኮሚሽኑ ከእንደገና በአዋጅ ቁጥር 449/1997 ተቋቋመ፡፡ የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤትም ኤጀንሲዉ ሆነ፡፡ ባለሙያና ሠራተኞቹም የኤጀንሲዉን እንዲጠቀም ተወሰነ፡፡ ኤጀንሲዉ በሕዝብና ቤት ቆጠራ ወቅት ብቻ ተጠሪነቱ ለኮሚሽኑ እንዲሆን ይሄዉ አዋጅ ወሰነ፡፡
ቆጠራ የሚደረገዉ በዚህ ኤጀንሲ ነዉ፡፡ ኤጀንሲዉ በገንዝበና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ሥር ነበር፡፡ ይህ ኤጀንሲ የ1999ኙን ሕዝብና ቤት ቆጠራ አከናወነ፡፡ የአማራ ሕዝብ ምን ያህል እንዲቀንስ፣ ቅማንት ሳይቆጠር እንዲቀር ተደረገ፡፡
ኮሚሽኑ የነበሩትን ሥልጣን ተነጥቆ፣ ኤጀንሲዉ እንዲፈጽማቸዉ የተወሰነበትን ጊዜ ሁሉ ልብ አድርጉ፡፡ ምርጫ 1997 ዉይይትና ክርክር ጣራ በነካበት ወቀት ሚያዚያ 12 (የኤጀንሲዉ) እና ከምርጫ በኋላ ትርምስ ዉስጥ በነበርንበት ግንቦት 18 ቀን ነዉ፡፡ ያለ ነገር በዚህ ወቅት ይህ ተሠራ ማለት አዳጋች ነዉ፡፡ የታሰበዉን ሴራ በ1999ኙ ቆጠራ ግልጽ ሆኗል፡፡
ስለሆነም፣ ኮሚሽኑ ይህን ኤጀንሲ ተጨማሪ የባለሙያዎች ቡድን በመሠየም ለሕዝብና ቤት ቆጠራ ያደረጋቸዉንና የሚያደርጋቸዉን  ተግባራት መቆጣጥርና ማስገምገም አለበት፡፡ በ1997 ሥልጣን ተሰጥቶት በ2 ዓመቱ ያን ያህል በደልና ተንኮል የሠራ ኤጀንሲ 14 ዓመታት ሙሉ ምን ምን ተንኮል እንደቀመመ አይታወቅም፡፡
ኮሚሽኑ በአፋጣኝ ባለሙያዎችን ሰይሞ ሙያዊ ክትትል፣ቁጥጥርና ግምገማ ማድረግ ይጠበቅበታል
ሦስት:-
በሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጁ (ቁጥር 449/1997) መሠረት የኮሚሽኑ አባላት  ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ከምርጫ ቦርድና ከፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲሁም ከፌደራል ሚኒስትር ሚኒስቴሮች እንደሚሆን አንቀጽ 7 ይናገራል፡፡
በዚህ ዓመት ህዳር ወር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የኮሚሽኑ ብዛት 20 ሲሆን በሕጉ ላይ ከተገለጸዉ ባፈነገጠ መልኩ የባለሥልጣኑን ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምርጫ ቦርድ ኃላፊን፣ የአዲስ አበባና የአፋር ክልል ተወካዮችን አልያዘም፡፡
በተለይ የአፋር ክልልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮሚሽኑ ዉስጥ አለመካተት ሲጀመር አዋጁን ስለሚጥስ ሲቀጥልም የፍትሕ ጉዳይም ስለሆነ በኮሚሽኑ ዉስጥ ሊካተቱ ይገባል፡፡ ሌላ የግጭት ምንጭ እንዳይሁኑም አስቀድሞ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
አራት:- 
የተለያየ ብሔር ካለቸዉ የተወለዱ ሕጻናት ብሔር ጉዳይ…
በሕዝብና ቤት ቆጠራ ወቅት ቆጣሪዎቹ ሁለት ዓይነት ቅጾችን ይጠቀማሉ፡፡ አንዱ አጭር ቅጽ ሲሆን አድሜ፣ ጾታ፣ ብሔር፣የአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ ሃይማኖት የመሳሰሉትን የያዘ ነዉ፡፡ ይኼ ከሁሉም ሰዉ መረጃ የሚወሰድበት ቅጽ ነዉ፡፡
ሁለተኛዉ ረጅም ቅጽ ሲሆን ከቤተሰብ መካከል (ብዙ ጊዜ ከአምስት ሰዉ አንዱን በመምረጥ) በአንዱ የሚሞላ ነዉ፡፡ ከ15 እስከ 20 በመቶ ገደማ የሚሆነዉ ሰዉ በረጅሙ ቅጽ ላይ የሰፈሩትን ጥያቄዎች ይመልሳል፡፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ናቸዉ፡፡
በአጭሩ ቅጽ መሠረት የሚሰበሰቡ መረጃዎች አንዱ ብሔር ነዉ፡፡ ብሔር የሚወነሰዉ በመላሹ ሰዉ ነዉ፡፡ ብሔሩ ምን እንደሆነ የሚወስነዉ የሚቆጠረዉ ሰዉ ነዉ ማለት ነዉ፡፡ የሕጻናትን ብሔር በሚመለከት የሚመልሱት በወላጆች መሆኑ አይቀሬ ነዉ፡፡ ምክንያቱም የብሔርን ምንነት ስለማያዉቁ፡፡
በተለይ የተለያየ ብሔር ያላቸዉ ወላጆች በሚኖሩበት ጊዜ መረጃዉን የሚሰጠዉ ሰዉ ወገን የልጆቹን ብሔር ከራሱ/ሷ ብሔር ጋርማመሳሰሉ አይቀሬ ነዉ፡፡ ብሔራቸዉ የተለያዩ ባለትዳሮች መኖራቸዉ የታወቀ ነዉ፡፡ ስለሆነም ስለ ሕጻናት የሚሰጡ ምላሾችን ቆጣሪዎችም ወላጆችም ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የብሔር ብዛት ዉክልናን ይወስናል፡፡ የብሔር ብዛት የፌደራል ድጎማን ይወስናል፡፡  አሁን ላይ የብሔር ቁጥር ብዙ አንድምታ አለዉ፡፡ በመሆኑም ወላጆች ትኩረት ሊሰጡት ይገባል!!