>

አዲስ አበባ የእኛ አይደለችም (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

አዲስ አበባ የእኛ አይደለችም

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

 

ትላንትንና ዛሬን እያጣቀስን አዲስ አበባን በባለቤትነት ለመውረስ የምናደርገው ትርምስ ይገርማል።  አንዱ የኦሮሞ ናት ሲል፥ ሌላኛው የአዲስ አበቤዎች ናት ይላል፥ ደግሞ ሌላኛው የኢትዮጵያ ናት ይላል።  ዛሬ ላይ ቆመን ይህንን ማሰባችን አሁንም ነገን እያገናዘብን እንደማንራመድ ያሳያል። ነገ የሚሆነውን አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ከመነሳት ይልቅ፥ አሮጌ ታሪክ ወይም ዛሬው ያስረናል።  ታዲያ መድረሻችንን የማናውቅ ሆነን ሳለ፥ በለውጥ ጎዳና ላይ ነን ማለት ጥቅሙ ምንድነው?

አዲስ አበባ የኦሮሞ፥ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት መዲና ሆና ዛሬ እያገለገለች ነው።  ነገን ብናይ ደግሞ አዲስ አበባ የእኛ አይደለችም። ነገ የምስራቅ አፍሪካ አንድነት ብሎም የመላው አፍሪካ አንድነት ህልውና ከሕልምነት ወደ እውንነት ስለሚለወጥ፥ አዲስ አበባ ለዚያን ወቅት እየተሞሸረች ያለች የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ዋና ከተማ ልትሆን ያለች ናት። ነገን ዛሬ እንዳየ ሕዝብ፥ ሁላችንም አዲስ አበባን በዚህ መነፅር አይተን፥ አዲስ አበባን ለጥቁር ሕዝብ የምስራችና የድል ዜና አብሳሪና ተስፋ ሰጭ ማዕከል እንድትሆን እንፍቀድላት።

የራሳችን ጎሣ እንደ ትንሽ ደሴት በልፅጎና አድጎ ለብቻው በጨለማው ኢትዮጵያ ላይ እንዲገን እንፈልጋለን?  ኢትዮጵያ እንደ ትንሽ ደሴት በልፅጋና ተመንድጋ ለብቻዋ በጨለማው አፍሪካ ላይ ገና እንድትታይ እንመኛለን? ካለንበት አዘቅት አንዳችን በአንዳችን ላይ ተረማምደንና ሁሉንም ወደ ዋላ ጥለን፥ ራሳችንን ብቻ ይዘን ወደ ላይ መውጣት አንችልም።  የራስ ጎሣ ተኮር ሆኖ ሁሉንም በዚያ መነፅር ማቀንቀን ጠባብነት እንደሆነ ሁሉ፥ ኢትዮጵያ ተኮር ብቻ ሆኖ ሁሉንም በዚያ መነፅር ማቀንቀን መጥበብ ነው።

በኢትዮጵያዊነት ስም አብሮነትንና አንድነትን ስናስብ፥ ጥቁር ሕዝብ ሁሉ እንዲያሸንፍ እናልም።  እኛ በጎሣ ተከፋፍለን እርስ በርስ ስንነካከስ፥ ልዩነታችንን እናገናለን እንጂ በዓለም ዕይታ ሁላችንም አንድ ጥቁር ሕዝብ ነን።  የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ባስገባንበት ባሁኑ ወቅት፥ የአፍሪካን አንድነት ማሰብ ጅልነት ነው ይባል ይሆናል። ነገር ግን ነገራችንን ከአፍሪካ አንድነት ሳንጀምር ቀርተን፥ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ መነታረካችን፥ ለመራኮታችን ምክንያት ቢሆንስ?  የተጠራንለትን ታላቅ ጥሪ ችላ ብለን፥ በመንደር ህሳቤ እርስ በርስ ስንበላላ እንዳንጠፋፋ ፈጣሪ ይርዳን።

የነገው የምስራቅ አፍሪካ ብሎም የመላው አፍሪካ ዕምብርት ለመሆን ዕድል ያላት አዲስ አበባን ለዚህ ታላቅ ጥሪ እንድትመረጥ ታሪክ ስላደላት፥ ኦሮሞም ሆን፥ አዲስ አበቤዎችም ሆን፥ ኢትዮጵያውያንም ሆን፥ ሁላችንም በአዲስ አበባ ልዩ ታላቅ ጥሪ ልንኮራ ይገባል እንጂ፥ አሸናፊና ባለቤት ለመሆን እርስ በርስ አንጣላ።  አዲስ አበባ ከእኛ በላይ የሆነች ለጥቁር ሕዝብ ምልክት ናት። ይልቁንስ ለአፍሪካ መድሃኒት ሆነን ራሳችንን እንድንፈውስ፥ ለጥቁር ሕዝብ ልዕልና ፋና ወጊ እንሁን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ።

እግዚአብሔር አፍሪካን ይባርክ።

Email: Z@myEthiopia.com

Filed in: Amharic