>

‹‹ታሪኩን የማያውቅ ሰው.. ልክ ከብዙ ሴቶች መካከል እናቱን መለየት እንደሚሳነው ህፃን ነው!!!››  (አሰፋ ሀይሉ)

‹‹ታሪኩን የማያውቅ ሰው.. ልክ ከብዙ ሴቶች መካከል እናቱን መለየት እንደሚሳነው ህፃን ነው!!!›› 
አሰፋ ሀይሉ
መኮንን ወልደሚካኤል ጉዴሣ (ራስ መኮንን፤ ከ፲፰፻፵፬–፲፱፻፺፰ ዓ.ም.)
Makonnen Wolde Mikael Gudessa (Ras Makonnen, 1852 – 1906)
ይህ በአዲስ አበባ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፊት ለፊት ቆሞ የሚታየው የአፄ ምኒልክ ኃውልት አይደለም፡፡ ይህ ታላቅ ኃውልት በሐረር ከተማ መሐል አደባባይ የቆመው የተፈሪ መኮንን (የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ወላጅ አባት የመኮንን ወልደሚካኤል ጉዴሣ ኃውልት ነው፡፡ ሐረር ወደ ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ግዛት ተጠቃልሎ የገባው ቀደም ባለው የአፄ ዮሐንስ አራተኛ ዘመነ-መንግሥት ነበር፡፡* /*እዚህ ላይ በምኒልክ ዘመን በሐረር ስለሆነው ግን በተጨማሪ የአፈወርቅ ገብረየሱስን ‹አጤ ምኒልክ› ልብ ይሏል፡፡/ መኮንን በ14 ዓመታቸው ጀምረው አንኮበር በሚገኘው የንጉስ ምኒልክ ቤተመንግስት በአባታቸው ተወስደው ከምኒልክ ጋር ልዩ ወዳጅነትን አዳበሩ፡፡ በ1879 ዓ.ም. መኮንን የሐረር ሹም (አስተዳዳሪ) ሆኑ፡፡ በመጀመሪያው በታላቁ የአድዋ ጦርነት መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ የጣልያንን ጦር በመጠራረግ ቁልፍ ሚና የተወጡ ጀግና ነበሩ፡፡ በግላጭ ስያሜውን አይጠሩበት እንጂ በምኒልክ ዘመን የታወቀላቸው የዲፕሎማትነት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሚና ነበራቸው፡፡ በ1894 ዓ.ም. መኮንን እንግሊዝ ሃገር በመሄድ በንጉስ ኤድዋርድ ሰባተኛ የንግሥና ሥነሥርዓት ላይ ተገኝተዋል፡፡ መኮንን ኢጣልያን፣ ፈረንሣይን እና ጀርመንን ጎብኝተዋል፡፡ ከዓለም ኃያላን ሃገራት መሪዎች እጅ ከተሰጧቸው እጅግ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው የክብር ሜዳይ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ የየእንግሊዝን የቅዱስ ሚካኤልንና የቅዱስ ጊዮርጊስን የከፍተኛ ተዋጊ አዛዥነት የክብር ኮከብና ኒሻን ሜዳይ (Badge & Star of the Order of St. Michael and St. George (Knight Commander)) ተሸልመዋል ፡፡ የራሺያን የቅዱስ አንን ከፍተኛ የክብር ኮከብ ሜዳይ (Star of the Russian Order of St. Anne) ተሸልመዋል፡፡ የፈረንሣይን የሶስተኛው ሪፐብሊክ ወታደራዊ ሠልፈኞች ከፍተኛ የክብር ኮከብ ሜዳይ (Star of the French Legion d’Honneur (Third Republic)) ተሸልመዋል፡፡ የኢጣልያን ከፍተኛ የንጉሠነገሥት የክብር ዘውድ የኮከብ ሜዳይ (Star of the Order of the Crown of Italy) ተሸልመዋል፡፡ የኦቶማንን ከፍተኛውን የኦስማኒያ የክብር ኮከብ ሜዳይ (Star of the Ottoman Order of Osmania) ተሸልመዋል፡፡ በ1898 ዓ.ም መኮንን ሲያልፉ ልጃቸው ደጃች ይልማ መኮንን የሐረር ሹም ሆነው ተተኩ፡፡ በዓመት በኋላ ደግሞ ይልማ መኮንን የሐረር ሹምነቱን  ወደፊት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ለሚሆኑት ለታናሽ ወንድማቸው (ለአባታቸው ልጅ) ለተፈሪ መኮንን አስተላለፉ፡፡
እኚህን በዓለም አንድ ጥቁር ሰው እንኳንስ በኃያላን ያለም ነገሥታት በክብር እየተጠራ ሊሸለም ይቅርና ሙሉ መብት እንዳለው ሰው በማይቆጠርበት በዚያ ዘመን… በሥራቸው፣ በምግባራቸው፣ በሕዝባቸው የተባበረ ክንድ፣ በሥልጣኔያቸው የተነሣ… እነዚያን ለጥቂት ውድ ሰዎች ብቻ ተመርጠው የሚሰጡትን እጅግ የከበሩ ታላላቅ ዕውቅናዎችና የክብር ሽልማቶችን ያገኙት እኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሰው… መኮንንን ወልደሚካኤል ጉዴሣ… በእውነት በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ክብርና ፍቅር ሊለገሣቸው የሚገባ እጅግ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሣይሆን ለመላው አፍሪካና.. ለመላ የዓም ጥቁር ሕዝቦች የምንጊዜም ኩራት የሚሆኑ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ ቅድም እንዳልነው እዚህ አዲስ አበባ በቅ/ጊዮርጊስ የሚገኘው ኃውልት የመኮንን አይደለም፡፡ የእሳቸው ያለው ሐረር ከተማ ነው፡፡ አዲስ አበባ የሚገኘው.. በፒያሣ ኃብተጊዮርጊስ ድልድይ አቅራቢያ የሚገኘውን… እስካሁን ድረስ የሚፈስሰውንና ብዙዎችም የሚቀዱለትና የሚጎነጩለትን.. የብረት ቅጥር የተሰራለትን የምንጭ ውሃ ያየ ሰው ካለ ግን ያ ማለት፡- የልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሣ ምንጭ ነው፡፡ ‹‹ታሪኩን የማያውቅ ሰው.. ልክ ከብዙ ሴቶች መካከል እናቱን መለየት እንደሚሳነው ህፃን ነው፡፡›› ይል ነበር አንድ ታላቅ ወዳጄ፡፡ ራሳችንን እንፈልግ፡፡ ራሳችንን እናግኝ፡፡ ራሳችንን እናክብር፡፡ እና ራሳችንን እንሁን፡፡ መልካም ጊዜ ለሁላችን፡፡
Filed in: Amharic