>

ኢሕአዴግን ማፍረስ የኢትዮጵያን ትንሣዔ ማረጋገጥ መሆኑ መታወቅ አለበት!!! (ሳምሶን ሚሀይሎቪች)

ኢሕአዴግን ማፍረስ የኢትዮጵያን ትንሣዔ ማረጋገጥ መሆኑ መታወቅ አለበት!!!
ሳምሶን ሚሀይሎቪች
ጠ/ሚ ዓብያችን እጅግ ቅን፣ ሀገርና ሕዝብ ወዳድ፣ ዴሞክራት እንዲሁም ባለተሰጥኦ መሪ እና ጨዋ ቆንጥጦ ያሳደጋቸው የጨዋ ልጅ መሆናቸው ለመመስከር ብዙ ምርምር አያስፈልግም። ግን ምን ዋጋ አለው፣ ኢሕአዴግ ናቸው።
*****
አቶ ለማ መገርሳ ሰው የሆኑ ሰው፣ ለሀገር እና ለሕዝብ የቆሙ፣ ቆፍጣና፣ ቀጥ ያሉ የአቋም ሰው የሆኑ መሪ ናቸው። ግን ምን ዋጋ አለው፣ ኢሕአዴግ ናቸው።
****
አቶ ገዱ፣ በሠላም ሰሞን የሚወደሱ፣ ሲወራረዱ በመጡ ክፉ ነገሮች ደግሞ በብቸኛ ተጠያቂነት የሚብጠለጠሉ ሰው አይደሉም። አቶ ገዱ ሀገር እና ሕዝባቸውን ወዳድ፣ በብዙ የመከራዎች መአት በመፈተን ላይ የሚገኙ ከብርታታቸው ንቅንቅ የማይሉ አቋመ ጠንካራ መሪ ናቸው። ግን ምን ዋጋ አለው፣ እሳቸውም ኢሕአዴግ ናቸው።
*****
እኔ በግሌ ሳስበው ሳስበው፣ ደብረፅዮን ገ/ሚካዔል (ዶ/ር) በህወሓቶች፣ በትግራይ ሕዝብ እና በቀሪው የሀገራችን ሕዝብ የፖለቲካ ፍላጎት አለመጣጣም ምክንያት፣ ያን ልዩነት ለማስታረቅ መሃል ቤት የሚጠበሱ ሰው ናቸው። ቢሆንም ያን ሁሉ መአት ችለው ቀጥ ያሉ፣ ነገሮችን ሁሉንም ለማጣጣም የሚጥሩ፣ በጣም ጎበዝ እና ጠንካራ መሪ ናቸው። ግን ምን ዋጋ አለው፣ እሳቸውም ኢሕአዴግ ናቸው።
******
ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ አርዓያ የሆኑ ሴት፣ ተስፋ የሚጣልባቸው፣ ድብልቅልቅ ያለን ክልል ተረክበው በጥሩ አመራር መልክ ለማስያዝ የተጉ፣ ስክነትና ርጋታ ያላቸው፣ ውድ ከሆኑት የዘመናችን ሴት ፖለቲከኞቻችን መካከል አንዷ ናቸው። ግን ምን ዋጋ አለው፣ እሳቸውም ኢሕአዴግ ናቸው።
*****
የፈለገ ቅን፣ ጎበዝ፣ ምሁር፣ ባለተሰጥኦ መሪ፣ ልበ ርኅሩህ ፖለቲከኛ ብናገኝ፤ ኢሕአዴግ እስከ ሆነ ድረስ፣ በአንድም ይሁን በሌላ ከሀገራችንና ሕዝቧ የጋራ ጥቅም አንፃር ተፃራሪ የሆነ ተግባር መፈፀሙ የማይቀር ነገር ነው። የቱንም ያህል ጥሩ ፖለቲከኛ ብናገኝ ሰውዬው ኢሕአዴግ እስከሆነ ድረስ ከጎሣ ማዕቀፉ እና ከመርዘኛው ሕገመንግሥቱ መስመር ወጥቶ ማሰብም ሆነ መንቀሳቀስ አይቻለውም። ኢሕአዴግ ማለት ተዋደን፣ ተፋቅረንና ተከባብረን የኖርን የኢትዮጵያ ልጆችን እንዲህ እንደ አሁኑ በመከፋፈልና በማባላት፣ ሕልውናውን እንዲመራ ተደርጎ የተመሠረተ ሸቃባ “የፖለቲካ ፓርቲ” ነው።
ትግሬን ጥሉ፣ ኦሮሞን አትመኑ፣ ከአማራ አትጋቡ፣ ከጉራጌ አትዛመዱ የሚል ነገር በኢትዮጵያ ምድር ከጥቂት አመታት በፊት ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። ዕድሜ ለኢሕአዴግ¡ ጎሰኝነት፣ በጎጥ መከፋፈልና መባላት የኢትዮጵያውያን የተፈጥሮ ባሕርያት መስለው እንዲገኙ አደረገ። ለማንኛውም የኢሕአዴግ ፓርቲ መፍረስ የኢትዮጵያን ትንሣዔ ማረጋገጥ መሆኑ መታወቅ አለበት። “ማን ያፍርስው?” ለሚለው፣ ቢቻል ይህን እውነት ልባቸው የሚያውቀው ራሳቸው ቅን አባላቱ፣ ካልሆነም ደግሞ ሌሎች ጎበዝ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች። አለበለዚያ ይሄ የጥፋት መዋቅር ሳይፈራርስ ቅኖቹን እና ባለተሰጥዎቹን ፖለቲከኞች እነ ጠ/ሚ ዓብያችንን፣ ኢትዮጵያ ሙሉ አቅማቸውን አግኝታ መጠቀም የመቻሏ ነገር ፉርሽ ነው።
Filed in: Amharic